በፓሪስ ኦሊምፒክ እንደሚደምቁ ከሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች መካከል አንዱ የ10ሺ ሜትር ኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ ነው። በዚህ ርቀት እጅግ ተፎካካሪ የሆኑትን የምስራቅ አፍሪካም ሆነ ሌሎች አትሌቶችን በመፈተን ሁሌም ለውጤታማነት የሚተጋው አትሌቱ በቅርቡ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ዳግም የክብር ባለቤት ለመሆን በዝግጅት ላይ ይገኛል።
የ24 ዓመቱ ወጣት አትሌት ምንም እንኳ በአካል ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ ቢሆንም፤ ለአሸናፊነት ይህ በቂ እንዳልሆነ እምነቱ ነው። ይልቁኑ ሩጫ የጭንቅላት ጨዋታም እንደመሆኑ በዚህ ረገድም ራሱን እያበቃ መሆኑን ነው ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበረው ቆይታ የጠቆመው። ሀገሩን በኦሊምፒክ ለመወከል የሚያስችለውን ዝግጅት በአራራት ጫካ ሲያከናውን የቆየው አትሌቱ በስፔን በተካሄደው የኦሊምፒክ ማጣሪያ ሩጫ ፓሪስ ላይ በ10ሺ ሜትር ውድድር ከሚሰለፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አንዱ መሆኑን አረጋግጧል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው በዚህ የሰዓት ማሟያ ውድድር ላይ ሰለሞን 26:34.93 በሆነ ሰዓት በመሮጥ፤ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሪሁ አረጋዊን በመከተል 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁም ነው የብሄራዊ ቡድኑ አካል ያደረገው።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ግላስኮ ላይ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በ3 ሺ ሜትር የወርቅ ባለቤት የነበረው አትሌቱ፤ አብዛኛውን ትኩረቱን ከውድድር ይልቅ በልምምድ ላይ አድርጎ ነበር የቆየው። ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎበታል በተባለው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 4 ሜዳሊያዎችን (1 የወርቅ፣1 የብር እና 2 የነሃስ) ሲያስመዘግብ የሀገሩን ባንዲራ በብቸኛነት በድል ያውለበለበው አትሌት ሰለሞን ባረጋ መሆኑ አይዘነጋም። ባለፈው ዓመት በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ቢያገኝም በታላቁ የውድድር መድረክ ግን እንደ ቶኪዮው ሁሉ ሌላኛውን ስኬት ማስመዝገብ የዚህ ዓመት ዕቅዱ መሆኑን የአሶሼትድ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል።
በዚህ ርቀት ነግሳ የቆየችው ኢትዮጵያ ከውጤታማነት ርቃ ሳለች በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ያልተጠበቀው ድል መመዝገቡ የስፖርት ቤተሰቡን ጮቤ ያስረገጠ እንደነበር ይታወሳል። ከሁሉ በላይ አስደናቂ የነበረው ግን በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች የዓለምን ክብረወሰን ጠቅልሎ ከእጁ ያስገባው ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቺፕቴጊን መርታቱ ነበር። አትሌቱ በ5ሺ ሜትር አሸናፊ የነበረ ሲሆን፤ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ ቢያቅድም በኢትዮጵያዊው ወጣት ሊመክንበት ችሏል። ይህም የአትሌቲክስ ቤተሰቡን ከሚስቡ ጉዳዮች መካከል የሚመደብ ሲያደርገው ፓሪስ ላይ የኡጋንዳዊያኑን ጨምሮ እሱን ከመሰሉ ወጣት የሀገሩ ልጆች ጋር ለአሸናፊነት የሚደረገው ትንቅንቅ እጅግ አጓጊ ነው።
በወጣትነት እድሜው በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ የሚገኘው ሰለሞን አሁን ላይ ተስፋ ከሚጣልባቸው ጠንካራና ተፎካካሪ አትሌቶች መካከል አንዱ በመሆኑ ለሌሎች ወጣት አትሌቶች አርዓያ ነው። በ1992 ዓ.ም በጉራጌ ዞን የተወለደው አትሌቱ በልጅነቱ ሩጫ ላይ ሳይሆን ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩር በቤተሰብ ግፊት ቢደረግበትም በግል ጥረቱ አሁን ካለበት ደረጃ መድረሱን ይናገራል። እሱንና ሌሎች ስኬታማ አትሌቶችን መመልከታቸው አሁን ላይ አመለካከት ላይ ለውጥ በማምጣቱ ተተኪ አትሌቶች በተሻለ ሁኔታ ወደ ስፖርቱ በመግባት ላይ ይገኛሉ።
ይሁንና የአትሌቲክስ ፍላጎት ብቻውን ውጤታማ ሊያደርግ እንደማይችልም ነው የሚያወሳው ‹‹በርካቶች የኦሊምፒክ ሜዳሊያ አጥልቀዋል፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ እኔ ነኝ። ነገር ግን አሸናፊ የሚኮነው ጥሩ የአየር ሁኔታ፣ በሥነልቦና የተገነባ መሆን አሊያም በተመቻቸ ሁኔታ ስላለ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ወርቅ ማግኘት የሚቻለው የአእምሮ ዝግጅት ሲኖር ነው። ለምሳሌ ለኦሊምፒክ የማደርገው ዝግጅት ጠንክሮ ከመስራት ባለፈ አእምሮዬ የሚያስበውን ወደ እውነታ ለመቀየር የሚያስችል መሆን ይኖርበታል›› ሲልም ያስረዳል። ይህንን ተከትሎም በአካልና በሥነልቦና ዝግጅት ማድረጉን የሚጠቅሰው ሰለሞን ለዚህ ኦሊምፒክ ሲል የሌሎች ውድድሮች ተሳትፎን አስወግዶ እንደቆየም ነው የሚገልጸው።
ዝግጅቱ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ስኬትን በመመዘን ላይ የተመሠረተም ሲሆን፤ የወርቅ ሜዳሊያው የተገኘበትን የዝግጅት ሁኔታ መለስ ብሎ ከአሠልጣኞቹ ጋር በመተንተን ላይ ይገኛል። ይኸውም በፓሪሱ ኦሊምፒክ እንደ ቶኪዮ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን የሚቻልበትን አካሄድ የሚያመለክትም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም