በራስ ወርቅ መድመቅ  

ወይዘሮ ፋጤ ሰሞኑን የጤና ችግር አጋጥሟቸው ተኝተዋል። በጤናቸው ምክንያትም ጎረቤታቸው ወይዘሮ ይመናሹም ቤት ቡና ከጠጡ ቀናቶች ተቆጥረዋል። ቡና መጠራራቱ ቀረ እንጂ ጎረቤታቸው ወይዘሮ ይመናሹ ከወይዘሮ ፋጤ ቤት አልጠፉም። አጥሚቱንም ገፎውንም እያደረጉ ጠዋት ማታ ይጠይቋቸዋል። እያስታመሟቸው ነው።

ቡናም እዛው ቤታቸው አፍልተው አብረው ይጠጣሉ። ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ማታ በመኝታ ሰአት ብቻ ነው የሚለያዩት። በጉርብትና ረጅም ዓመት አብረው በመኖራቸው አብሮነታቸው በጣም የጠነከረ ነው። እንደታላቅና ታናሽ እህት ነው የሚተያዩት። አንዳቸው የጤና ችግር ሲያጋጥማቸው ሌላዋ ያስታምማሉ። ይረዳዳሉ።

የሁለቱን ጎረቤታሞች መተሳሰብና መዋደድ የሚያዩ የአካባቢያቸው ነዋሪዎችም ‹‹ጉርብትና እንደነሱ ነው›› ይላሉ። አንዳንዶችም መንፈሳዊ ቅናት ያድርባቸዋል። የወይዘሮ ፋጤና የወይዘሮ ይመናሹ መተሳሰብ ‹‹ከዓይን ያውጣችሁ›› የሚባለው አይነት ነው።

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ከግማሽ በላይ እድሜያቸውን አብረው ነው ያሳለፉት። በመካከላቸው አለመግባባት ሳይፈጠር ቀርቶ አይደለም። ግን የከረረ ነገር አልገጠማቸውም። ተጣልተው ለማስታረቅ ሽማግሌ በመካከላቸው ገብቶ አያውቅም። ነገሮችን ቀለል አድርጎ በማየትና ሆደ ሰፊም ሆኖ በማሳለፍ ጭምር ነው አብሮነታቸውን ያጠናከሩት።

በጉርብትና፣ በጓደኝነት፣ በትዳር አጋሮች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በሀገራችን ባህልና ወግ የችግሮች መፍቻ መንገዱ ሽምግልና ነው። በአካባቢ ማህበረሰብ ከበሬታ ያላቸው፣ በሥነምግባራቸው ጥሩ የሚባሉና ሀቀኛ ተብለው የሚታወቁ ሰዎች ተመርጠው ያልተግባቡ ወይንም የተጣሉ ሰዎችን እንዲሸመግሉ ይደረጋል። በዳይና ተበዳይም ቢሆኑ ሽማግሌዎችን ያከብራሉ። በፊታቸው ቀርበው ችግሮቻቸውን ያስረዳሉ። ሽማግሌዎቹም ከወገኝተኝነት ነፃ ሆነው በሁለቱም ወገን ያለውን ችግር ጠይቀው ጉዳዩን መርምረው ችግሩ በእርቅ እንዲፈታ ያደርጋሉ። በዳይ ተበዳይን እንዲክስም ይወስናሉ።

በዚህ መልኩ አለመግባባቱ ከተፈታ በኋላም ተጣልተው የነበሩ ሰዎች ወደቀደመው ችግር አይመለሱም። ተስማምተው ሰላማዊ ኑሮአቸውን ይመራሉ። በዚህ ወቅት ወይንም በዚያኛው ጊዜ ለማለት ቢያስቸግርም አሁን ላይ በሰዎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ነገሩን አክርሮ አላስፈላጊ ወደሆነ ፀብና መጎዳዳት ላይ ሲደርሱ ይስተዋላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ከቀጠለ ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል።

ሰዎች በመነጋገር አለያም በሽማግሌ ችግሮቻቸውን ፈተው ተስማምተው አብረው መኖር እየቻሉ ቂምና ቁርሾ ይዘው የከረረ ነገር ውስጥ ይገባሉ። ይህ በመሆኑ የተጠቀመ ሰው የለም። ይልቁንም ለጤና እና ለተለያየ ችግር ነው የሚጋለጡት።

እንደው ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ በጉርብትና ሲኖሩ ከግጭት ይልቅ አብሮነትን ማስቀደማቸው ለሌሎች ምሳሌ ይሆናል ብለን ጉዳዩን እንዲህ አነሳን እንጂ ወይዘሮ ይመናሹና ፋጤ አብረው ሲውሉ የሚያወጉት ወግም ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ አይደለም። ሌሎችንም ያስተምራል።

በተለይ ደግሞ የሚያነሷቸው ነጥቦች ይሄንንም ይታዘባሉ ማለት ነው? ብለው እጅዎን በአፍዎ ላይ አድርገው እንዲገረሙ የሚያደርጉ ናቸው። ጎረቤታሞቹ የተማሩ አይደሉም። የቢሮ ሠራተኛም አይደሉም። በአነስተኛ ንግድ ሥራ ነው ኑሮአቸውን ሲመሩ ነው የኖሩት። ግን በተፈጥሮ አስተዋይ ናቸው። በነገሮች ላይም መወያየትን መጠያየቅን የሚወዱ ናቸው። አንዳቸው የሰሙትን ነገር ለሌላኛቸው የመንገር ባህልን አዳብረዋል። ንቁ እንዲሆኑ ያደረጋቸውም ይኸው ተሞክሮአቸው ነው።

ምንም እንኳን ወይዘሮ ፋጤ ታመው አልጋ ላይ ቢሆኑም ወይዘሮ ይመናሹ ከቤታቸው ስለማይጠፉ በየቤታቸው ቡና እየተጠራሩ እንደሚጫወቱት ሁሉ ወይዘሮ ይመናሹ ወይዘሮ ፋጤ ቤት በመሄድ ይጫወታሉ። ደግሞ ጨዋታ በሽታ ያስረሳል ይባል የለ? ወይዘሮ ይመናሹም የተለያዩ ርእሰጉዳዮችን እያነሱ ለማጫወት ሙከራ ያደርጋሉ። ወይዘሮ ፋጤም ቢሆኑ ለጎረቤታቸው ምላሽ ለመስጠት አልቦዘኑም። የሚሰማቸውን ሃሳብ ይሰነዝራሉ።

በጨዋታቸው ጊዜ ወስደው ያነሱት ጉዳይ የባህልና ወግ መበረዝና እየተሸረሸረ መሄድ ነው። የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ አንዳንድ ባህልና ወግ እሴቶች እየተሸረሸረ ሄዷል ብለው ያምናሉ። ባህሉ ተሸርሽራል ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የሽምግልና ሥርዓት ጉዳይና የወፍ አጥር አትይሽ ተብሎ ለመውለድ ቀኗ ለተቃረበ ሴት እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ነው።

ያነሱት ርእሰጉዳይ ብዙ ሲያከራክራቸው ነበር። እነርሱ ያለፉበትና አሁን ላይ የሚያስተውሉት ፈጽሞ ስለተራራቀባቸው የትኛው ዘመን ይሻላል የሚለው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እንኳን አልቻሉም። ግን ደግሞ የራስ የሆነ የባህል፣ የታሪክ፣ የሥነምግባር፣ ሌሎችም መገለጫዎች፣ እሴቶች ሊኖሩ ይገባል ብለው ያምናሉ።

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ባይጠቀሙም ከልጆቻቸው፣ ከጎረቤት ልጆችም የማየቱን ዕድል ስለሚያገኙ እየሆነ ያለውን ታዝበዋል። ዛሬ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካችን እየተለቀቀ የምናየውን ልጅህን ለልጄ ተብሎ ለሚላከው ሽምግልና እና ለመውለድ ለተቃረበች ሴት የወፍ አጥር አትይሽ ተብሎ የሚዘጋጀውን ድል ያለ ድግስና ጭፈራ ነው ጎረቤታሞቹን አግራሞት የጫረባቸውና በጉዳዩ ላይም ለመነጋገር ያነሳሳቸው።

በርእሰ ጉዳዩ ላይ ጨዋታውን የጀመሩት ወይዘሮ ይመናሹ ነበሩ። እርሳቸው ሲዳሩ የነበረውን ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለው ዘመኑን እንዲህ አስታወሱ፤ የልጆቻቸውን አባት ሲያገቡ የሚያውቋቸው ሰው ሊሆኑ ቀርቶ የሚያስቧቸው እንኳን አልነበሩም። እርሳቸው ባገቡበት ዘመን ልጅህን ለልጄ ብለው ለልጆቻቸው የትዳር አጋር የሚመርጡት ወላጆች ናቸው የነበሩት።

ሽማግሌም ሲላክ ሙሽሪትና ሙሽራው አያውቁም። ወላጆች በሚያደርጉት ስምምነት የሰርጋቸው ቀን ተቆርጦ ለሰርግ ዝግጅት ሲደርግ ነው ተጋቢዎቹ እንዲያውቁ የሚደረገው። አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ልጆች ጋብቻውን አይቃወሙም። የቤተሰብ ትእዛዝ ይከበራል። ከወላጆቻቸው ፈቃድ አይወጡም።

ወይዘሮ ይመናሹ እንዳሉት፤ ሽምግልና በጣም ከባድ ነው። ወላጆች በቀላሉ ስለማይቀበሏቸው ሽማግሌዎች ከብዙ መመላለስ በኋላ ነው መልስ የሚያገኙት። ሽማግሌዎቹ ተመላልሰው፣ ደክመው እንኳን መልሱ አይሆንም የሚልም ሊሆን ይችላል። ከቻሉ ያሳምናሉ። ካልተሳካላቸውም በፀጋ ከመቀበል ውጭ አማራጭ የላቸውም። ወይዘሮ ይመናሹም በወቅቱ በነበረው ባህልና ወግ ነው የአሁኑን የልጆቻቸውን አባት በሰርግ ያገቡት።

ወይዘሮ ይመናሹ በእሳቸው ጊዜ የነበረውን የሽምግልና ሥርዓት ትክክል እንደሆነ አድርገው ይቀበላሉ። ለታይታ ሳይሆን፣ ለሚጋቡትም የሚጠቅም ነው ብለው ያምናሉ። ተጋቢዎቹ ችግር እንኳን ቢያጋጥማቸው ችግራቸውን በቤተሰብ ዙርያ ለመፍታት ዕድል ያገኛሉ የሚል እምነት አላቸው።

ስለዚህም መጀመርያውኑ ዘሎ ከመጋባት ሽማግሌ መላኩ ለሚጋቡትም ሆነ ለቤተሰብ ክብርም ጭምር እንደሆነ ይገልጻሉ። ተጋቢዎች በትዳር ዘመናቸው ችግር ቢያጋጥማቸው ወይንም በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር የሚጠሩት ሲጋቡ ሽምግልና የተላኩትን ወይንም ሽማግሌ ሆነው እንዲጋቡ ያደረጓቸውን ነው። ‹‹አንተም ተው፤ አንቺም ተይ፤ ብለው በትዳራቸው ፀንተው እንዲኖሩ መክረውና ዘክረው ያስሟሟቸዋል›› በማለት ነበር መልካም ጎኑን ለወይዘሮ ፋጤ ሲነግሯቸው የነበረው።

አሁንም ወንዱ ወደ ሴቷ ቤት ሽማግሌ መላኩ የቀረ ባይሆንም፤ ሥርዓቱ ግን ተለውጧል፤ ኢትዮጵያዊ ባህልም አይደለም ብለው ነበር የተከራከሩት። እርሳቸው ትዳር ከያዙበት ዘመን ጋር አሁን ያለው ሥርዓት የተገላቢጦሽ ነው የሆነባቸው። እርሳቸው እንዳሉት በእርሳቸው ጊዜ በልጆች የትዳር ሁኔታ ላይ ወላጆች ሚና ነበራቸው። አሁን ላይ ደግሞ ወላጆች እንግዶች ናቸው። ተጋቢዎቹ ሁሉንም ነገር ከጨረሱ በኋላ ነው ወላጆች የሚያውቁት።

ሽማግሌ የሚላክበት ቀን ተነግሯቸው ደግሰው እንዲጠብቁ ነው የሚደረገው። በሽምግልና ወቅትም ሽማግሌዎችን መጠየቅ ያለባቸውን ነገሮች እንኳን አይጠይቁም። ቢጠይቁም የሚለወጥ ነገር የለም። ሙሽሪትና ሙሽራውም ሽምግልና በተላከበት ቀን ይገናኛሉ። ይህ ሁኔታ እየተለመደ በመምጣቱም ልክ እንደ ባህል ተወስዷል።

ወይዘሮ ይመናሹ ነገሩ ውድድር ውስጥ ገብቷል ይላሉ። በድግሱና በሚላኩ ሽማግሌዎች አንዱ ከሌላው በልጦ ለመታየት የሚደረገውን ጥረት ማለታቸው ነው። እነእከሌ የላኳቸው ሽማግሌዎች መባልም እንደ አንድ መስፈርት የመወሰዱ ጉዳይና የኃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ለሰርግ ሽምግልና የመላካቸው ሁኔታ ጥያቄ እየፈጠረባቸው ነው።

እንደ ወይዘሮ ይመናሹ እምነት የኔ ከሌላው ይበልጣል ካልሆነ በስተቀር በወዳጅ ዘመድ፣ በጎረቤት ሽማግሌ የሚሆን ሰው ጠፍቶ የኃይማኖት አባቶችን መላክ የሚያደርስ ነገር አይደለም። ተጋቢዎቹ ቀድመው የጨረሱትን ጉዳይ ለምን ማግዘፍ አስፈለገ? የሚለው ነው ያልገባቸው። ድግሱና የሚላኩት ሽማግሌዎች ቅንጦት እንጂ ባህልና ወግን ለማክበር ነው ብለው አያምኑም።

‹‹የሽምግልና ሥርዓቱን እንዲያደምቁ ነው መሰለኝ ቤተሰብ ወዳጅም ይጋበዛል። የተለመነችውም በእለቱም አምራና ደምቃ ነው የምትውለው። ሰርግ ነው ወይንስ ሽምግልና ነገሩ ግራ ያጋባል›› ሲሉ የገለጹት ወይዘሮ ይመናሹ ለጨዋታ ያነሱት ነገር ያበሳጫቸው ይመስላል። እየተደረገ ያለው ነገር ኢትዮጵያዊ ባህል እንዳልሆነ ነው ቆጣ ብለው ሲናገሩ የነበረው።

ወይዘሮ ፋጤም በሃሳባቸው ይስማማሉ። ምንም እንኳን በእርሳቸው እምነት በእስልምናው ሥርዓቱ የተለየ ቢሆንም፣ ዘመኑ መቀያየሩና ከባህል ውጭ የመሆኑን ጉዳይ እርሳቸውም ቢሆኑ ታዝበዋል። የሚፈጠረው አዲስ ነገር ባህልን ማንነትን የሚዘነጋ መሆን የለበትም በሚለውም ወይዘሮ ፋጤ ይስማማሉ።

ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ሌላው በጨዋታቸው ያነሱት የአጥር ወፍ አትይሽ ጉዳይ ነበር። አሁንም ወይዘሮ ይመናሹ ናቸው ሃሳቡን የጀመሩት፤ እርሳቸው እንዳሉት የአጥር ወፍ አትይሽ የቆየ የኢትዮጵያ ባህል ነው። ጥሩ ባህልም ነው። አንዲት ለመውለድ ቀኗ የደረሰ ሴት ያዘጋጀችውን የገንፎ እህል ለማስቀመስ ጎረቤቶችዋን፣ ወዳጅ ዘመዶችዋን ሰብስባ ገንፎ ታቀምሳለች።

የዚህ ሥርኣት ዋናው ዓላማ ምጧ ቀላል እንዲሆንላት፣ በጤና በሰላም እንድትገላገል፣ ጤነኛ የሆነ ልጅ እንድትወልድ፣ ልጇን ለማቀፍ እንዲያበቃት፣ በአጠቃላይ መልካም ምኞታቸውን እንዲገልጹላት ነው። በተለይም በእድሜ የገፉ ሰዎች ምርቃት ጥሩ ነው ተብሎ በባህሉ ስለሚታመን ምርቃታቸውን ለማግኘት በጣም ስለምትፈልግ ለመውለድ ቀኗ የደረሰ ሴት ገንፎ ታዘጋጃለች። ጎረቤትም ቢሆን ገንፎ የሚቀምስበትን ቀን በጉጉት ነው የሚጠብቀው።

ይሄ መልካም የሆነ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደሆነ የሚገልጹት ወይዘሮ ይመናሹ፤ አሁን ላይ ‹‹ቤቢ ሻወር›› ተብሎ ስሙም ተቀይሮ በሆቴል ቤት ውስጥ ሁሉ ሳይቀር መዘጋጀቱን አልወደዱትም። አንዳንዶችም ነፍሰጡሯ ሳታውቅ የተለያዩ ነገሮችን አዘጋጅተው በመጥራት ለማስደነቅ የሚሞክሩትንም አግባብ ነው ብለው አያምኑም። ዓላማውን የሳተ ነው ይላሉ።

አንዳንዶቹም ለሰርግ የሚደረግ ዝግጅት ያህል ነው የሚዘጋጁት። ይሄም ቢሆን ሽምግልና ሲላክ ከሚደረግ ዝግጅት ያልተናነሰ መሆኑ ጉረቤታሞቹ እንግዳ ሆኖባቸዋል። ጎረቤታሞቹ እንዲህ ያለው ነገር ቅጥ ያጣና ኢትዮጵያዊ ባህል እንዳልሆነ ነው የተነጋገሩበት። የራስ የሆነን የባህል እሴት ትቶ የሌላውን መከተል ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ ነው ሲሉም ነው የገለጹት።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You