የሐረሪ ክልል ሁነኛ መታወቂያ እና ትልቁ ሀብት ቱሪዝም ነው። የክልሉ መንግስት እንዲሁም የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮም ይህን በውል በመረዳት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እና ለማዘመን የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛል።
ይህም ሐረርን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም ዘርፉ ቀዳሚ እና ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችል ከመሆኑ ባለፈ ቀርሶችን ለትውልድ ጠብቆ ከማስተላለፍ አኳያ የሚኖረው ሚና የማይተካ ነው ።
በክልሉ እየተከናወነ ያለው ቅርሶችን መልሶ የማልማት ስራ የቱሪዝም ዘርፉን ከማሳደጉም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የቻለ ነው። ይህ የሐረሪ ክልል ተግባር ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮ መሆን ስለሚችል በቱሪዝም ዘርፉ እየተከናወነ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ስንል ከሐረሪ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን ፡- የሐረሪን የቱሪዝም ጸጋ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ተወለዳ፡– ሐረር የዓለም ስልጣኔ ማሳያ ጥንታዊት ከተማ ነች። የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ በርካታ ቅርሶችን በጉያዋ አቅፋም ይዛለች። ጀጎል እና ሸዋልኢድን የመሰሉ ቅርሶቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ በመሆናቸው የሰው ልጅ ሃብት ሆነው ተመዝግበዋል።
እነዚህን ቅርሶች ደህንነታቸውን ጠብቆ ለትውልድ ከማስተላለፍ አንጻር እንደ ክልል እና እንደ ቢሮ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ስንሰራ ቆይተናል። እየሰራንም ነው። የሰው ልጅ ቅርስ የሆነውን ጀጎልን እንዲሁም በውስጡ ያሉ ትውፊቶችን እና ባህሎችን ከትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራን ነው።
እንደ ቢሮ ጀጎልን ብቻ ሳይሆን ከጀጎል ውጭ የሚገኙ በገጠር እና በከተማ ያሉ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችን ደህንነታቸውን አስጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ ልዩ ትረኩረት ሰጥተን ስንሰራ ነበር። እየሰራንም እንገኛለን።
በተለይ ከጀጎል ጋር ተያይዞ በርካታ ስራዎችን አከናውነናል። ለረጅም ጊዜ በሚባል ሁኔታ ጀጎል እና ዙሪያዋ በሕገወጦች የተወረረበት፤ ቅርሱ እየተበላሸ የነበረበት እንደዚሁም አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የጀጎል መልሶ ማልማት ስራ በክልሉ ፕሬዚዳንት አነሳሽነት ከተጀመሩ ስራዎች አንዱ ነው።
የጀጎል ውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባጣም ያረጁ፣ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ እና ቆሻሻ የበዛባቸው ነበሩ። በነገራችን ላይ የጀጎል መንገዶች ሁሉ ቅርስ ናቸው። ነገር ግን ከእንክብካቤ ጉድልት ከ40 ዓመታት በላይ የተዘጉ መንገዶችም ነበሩ። እነዚህ መንገዶች ከመዘጋታቸውም ባለፈ ሁሉም ሰው ቆሻሻ ይጥልባቸው ስለነበር የአካባቢውን ውበት ከማሳጣታቸውም በላይ የማኅበረሰቡን ጤና በከፍተኛ ሁኔታ ሲጎዱት ነበር።
ይህን ችግር ለመፍታት እንደክልል ቀን ከሌት ሰርተናል። በዚህም ቅርሱን ለትውልድ መሸጋገር በሚችልበት ደረጃ ማድረስ ችለናል። አሁን ላይ የጀጎል ግንብ ውስጥ እና ዙሪያው በአረንጓዴ ተሸፍኖ ለቱሪስቱ ሳቢ እና ማራኪ እንዲሆን፤ ለነዋሪው ደግሞ ምቹ የኑሮ ቦታ ማድረግ ተችሏል።
ቅርሱን ስናድስ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም እና አሰራሮችን በመዘርጋት የመልሶ መልማት ስራ ሕዝባዊ የማድረግ እና የአመለካከት ለውጥም ማምጣት ተችሏል። ቀደም ብሎ ይህ ቅርስ ይታሰብ የነበረው የአንድ አካል እንደሆነ ነው። የጥበቃ እና የእንክብካቤ ስራውም ለመንግስት ብቻ የተተወ ነበር። ከዚህ እሳቤ ጋር ተያይዞ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣና ቅርሱ የሁላችንም ቅርስ ነው፤ ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል፤ እኔም ድርሻ አለኝ የሚል አስተሳሰብ እንዲኖር የተሰራበት እና ሁሉም በባለቤትነት እንዲሳተፍ ለማድረግ ተሞክሯል።
በዚህም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የንግዱ ማኀበረሰብ፣ ዲያስፖራው እና የከተማው ነዋሪዎች በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸው እና በጉልበታቸው በመልሶ ማለቱ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ ተሳትፈዋል። በመንግስት ደረጃም ከባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በባለቤትነት ተሳትፈዋል። ይህ ሲሆን ልዩ ካፒታል በጀት አልተመደበም። የመልሶ ማልማቱ ተግባር በሴክተሮች መደበኛ ወጭ እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ብቻ የተከናወነ ነው።
ከመልሶ ማልማቱ ወይም እድሳቱ በፊት ጀጎል እና ዙሪያው ላይ እንኳንስ ለመኖር ለማለፍ የሚከብዱ ቦታዎች ነበሩ። በአሁኑ ግን የአረጋውያን መቀመጫ፤ የህጻናት መጫዎቻ እንዲሆኑ እና ህብረተሰቡም ደስ ብሎት የሚኖርበት ስፍራ እንዲሆን የማድረግ ስራ ተሰርቷል። እድሳቱን በምናከናውንበት ወቅት ቅርሱ ሳይጎዳ፤ ቅድመ ይዞታውን ሳይለቅ ውብ እና ማራኪ እንዲሁም ምቹ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል። በእድሳቱ ወቅት የቅርሱ መግለጫ የሆኑ ስዕሎችን ተጠቅመናል።
አዲስ ዘመን ፡- ሐረር ጥንታዊ ከተማ እንደመሆኗ ከጀጎል በተጨማሪ ሌሎች ቅርሶችን በውስጧ ይዛለች። እነዚህን ቅርሶች በማደስ ለትውልድ ከማስተላፍ አኳያ ምን ሰርታችኋል?
አቶ ተወለዳ፡- ከጀጎል ውጭ ያሉ ቅርሶች ተጠብቀው እና በተገቢው መልኩ ተሰነድው ለትውልድ ለማስተላለፍ አኳያ በርካታ ተግባራትን ስናከናውን ቆይተናል። ጀጎልን ከማደስ በተጨማሪ በክልሉ ‹‹የማንስክሪፕት›› ሙዚዬም እንዲከፈት ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ ሐረር ‹‹በአለላ ስፌትም›› የምትታወቅ ሲሆን በኢትዮጵያ የአዕምሮ ፈጠራ ባለስልጣን እውቅና አግኝተናል። ይህ እውቅናም ‹‹በአለላ ስፌት›› ሐረር በዓለም ገበያ ላይ ተሳታፊ መሆን እንድትችል አድርጓል። ይህን የሐረር መታወቂያ የምናሳይበት የአለላ ስፌት ሙዚዬም ከፍተናል።
ከዚህ ባሻገር በክልሉ ያሉንን ቀደምት ሙዚዬሞች የመንከባከብ፣ የማደስ እና ለቱሪስት ምቹ የማድረግ ስራዎችም በሰፊው ሰርተናል። በዚህም ‹‹የሸሪፍ ሙዚዬምን›› በማደስ ብሔራዊ ሙዚዬም እንዲኖረን ተደርጓል። በፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ደረጃ በሚሰጥበት ጊዜ አራት ሙዚየሞቻችን እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል።
ከሐረር ከተማ በተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ላይ የሚገኙ ቅርሶችን ለማደስ ችለናል። በዚህም ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ የሆነው ‹‹የአውብርኸሌ›› አድባር ወይም ‹‹አዎቻ›› ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን በተገኘ ድጋፍ እንዲታደስ ተደርጓል። በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያ ምዕራፍ እድሳቱ እየተጠናቀቀ ነው። ‹‹አውጀላን›› የሚባል አካባቢ የሚገኙ ቅርሶችን የማደስ ስራ ተከናውኗል።
በተጨማሪም በሐረር ታዋቂ ግለሰቦች ይኖሩባቸው የነበሩ ቤቶችን በማደስ ሙዚዬም አድርገናል። ከዚህ አንጻር የቀዳማቂ ኃለስላሴ ባለቤት እቴጌ መነን የጫጉላ ቤት እና የቃዲዎኒስ ቤት ተጠቃሽ ናቸው ።
ከዚህም በተጨማሪ ሐረር በሰላም፣ በመቻቻል፣ በአብሮነትና በአንድነት እንዲሁም በመፈቃቀርና በመፈቃቀድ የመኖር እሴት መታወቂያዋ ነው። የተለያዩ ኃይማኖቶች ተከባብረውና ተቻችለው በጋራ የሚኖሩበት ከተማ ናት። ይህንን እሴት ይዞ ለማስቀጠል በየጊዜው የሚፈጠሩ ሳንካዎችን በመቀልበስ አላስፈላጊ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርቷል። በተለይም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱና ወንድማማችነቱ ጸንቶ እንዲቆይ ለማድረግ ቀድሞ የነበረንን እሴት ለማጎልብት በተለይም በጳጉሜ ወር ላይ የሚከበሩ በዓሎችን በሚገባ ተጠቅመንባቸዋል። የአንድነት፤ የአብሮነት ቀን ስናከብር አንዱ የሌላውን እሴት አውቆ፣ አክብሮና ወዶ እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎችን ሰርተናል።
አዲስ ዘመን ፡- ከሕዝቡ የዘመናዊነት እሳቤ አንጻር የጀጎል ቤቶችን እንዴት አጣጥሞ ማደስ ተቻለ?
አቶ ተወለዳ፡- የሐረር ጀጎል ሲባል ግንቧ ብቻ ሳይሆን በግንቡ ውስጥ የሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን ይጨምራል። እነዚህ ቤቶች በቅርስነት የተመዘገቡ ናቸው። ይህም ቅርሱን ለማደስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ያከብደዋል። በጀጎል ውስጥ በየቀኑ ማህኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ይከናወኑበታል። ይህ ማለት ጀጎልን እየኖርንበት የምንጠብቀው ቅርስ ነው። ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የነበረው እና አሁን ያለው የሰው ልጅ ፍላጎት አንድ አይደለም። የሰው ልጅ እንደየዘመኑ መሰልጠን እና መዘመን ይፈልጋል። ስለሆነም አሁን ላይ ቅርሱን በምናደስበት ወቅት የነዋሪዎችን የመሰልጠን ፍላጎት እና ቅርሱን ይዘት የመጠበቅ ፍላጎትን ሚዛናዊ አድርጎ መሄድ ያስፈልግ ስለነበር ይህን ፍላጎት ለማጣጣም ክፍተኛ ስራዎች ተከናውነዋል።
እውነት ለመናገር ቅርሱን የመጠበቅ እና የሕዝቡን የመዘመን ፍላጎት አጣጥሞ ይዞ መሄድ ትልቅ ፈተና ነው። ከዚህ አንጻር ልምድ እንውሰድ ቢባል በቅርብ ሄደን ልምድ የምንወስድበት ቦታ እንኳን የለም። ኢትዮጵያ ብዙ ቅርሶች አሏት። ነገር ግን እንደ ሐረር ሕዝብ የሚኖርባቸው አይደሉም። በመሆኑም የእድሳት ስራ ሲያከናውኑ እንደ ጀጎል አይቸገሩም። የሐረር ቅርስ ግን ሕዝብ የሚኖርበት በመሆኑ ከአባቶች የተረከብነውን ቅርስ ለማደስ እና አሁን ላይ ሕብረተሰቡ ያለውን የመዘመን ፍላጎት አጣጥሞ ለመሄድ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውን ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር አጣጥመን በጥበብ ማለፍ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- በጥበብ ተወጣነው ሲሉ በምን መልኩ ነው?
አቶ ተወለዳ፡– ጀጎል ቅርስ የሆነ ከተማ ስለሆነ ለትውልድ ለማስተላለፍ በምናደርገው ጥረት አንዱ ፈታኝ ነጥብ የግንባታ ቁሳቁስ ማግኘት ነው። የግንባታ ቁሳቁሱን ማግኘት በራሱ ትልቅ ፈተና ነው። ለምሳሌ አንድ የሐረሪ ባህላዊ ቤት ለማደስ ከ500 እስከ 700 ሺ ብር ይፈልጋል። አንደኛ ጣራው የሚሰራው ከወፍራም ጥድ እንጨት ነው። የጥድ እንጨቱ በከተማው ላይ ስለማይገኝ ከሌላ ቦታ ነው የሚመጣው።
የአንዱ ጥድ ዋጋም ከአንድ ሺ ብር በላይ ነው። ቤቱ የተሰራበት ድንጋይም ይለያል። ለምሳሌ የብሎኬት ቤት በብርድ ጊዜ ይበርዳል በሙቀት ጊዜ ይሞቃል። የሐረሪ ቤት ግን ከተሰራበት ድንጋይ ተፈጥሮ የተነሳ እንደ ብሎኬት ቤት አይደለም። በብርድ ጊዜም ሆነ በሙቀት ጊዜ የቤቱን ሙቀት ይጠብቃል። ቤቶቹ የተገነቡበት ድንጋይ የተለየ ነው። ድንጋዮቹ ኩሮን ከሚባል ቦታ ላይ የሚወጡ ናቸው። ጥንታዊ ቤቶች በአይነታቸው በተለዩ ድንጋዮች የተሰራ በመሆኑ እድሳት ስናከናውንም በራሱ ድንጋይ ነው የምናድሰው። ይህም እድሳቱን ፈታኝ ያደርገዋል። ሆኖም የግንባታ እቃዎቹ ያሉበትን ቦታ በመለየት እና በማምጣት የሐረሪ ሕዝብን ፍላጎት በሚመጥን መልኩ ለመገንባት ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- እድሳቱ ከተከናወነ በኋላ ያለው የቱሪዝም ፍሰት ምን ይመስላል?
አቶ ተወለዳ፡- ከእድሳቱ በፊት የቱሪዝም ፍሰቱ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆል ታይቶበት ነበር። በተጨማሪም ኮቪድ በፈጠረው ስጋት እና ከሰላም ሁኔታዎች አንጻር የቱሪስቱ ፍሰቱን በተለይም የውጭ ቱሪስት ፍሰቱ ቀንሶ ነበር። ነገር ግን እንደሌላው አካባቢ ዜሮ አልሆነም። ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም 700 አካባቢ የውጭ ቱሪስት ወደ ክልላችን መጥቷል። አሁን ግን እስከ ከ4000 በላይ ቱሪስቶች ወደ ክልላችን መጥተዋል።
ከሀገር ውስጥ ቱሪስት አንጻር አሁን ላይ 127ሺ በላይ ቱሪስቶች ወደ ክልላችን መጥተዋል። በአንጻራዊነት ክልሉ ሰላም በመሆኑ የቱሪስት ፍሰቱ ጨምሯል። የክልሉ ሰላም ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጓል።
ባሳለፍነው የሸዋል ኢድ በዓል ላይም እጅግ ሰፊ በሚባል ሁኔታ ብዙ ሰው ታድሟል። እድገቱም ከመቶ ፐርሰንት በላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ‹‹ማንስክሪፕቶችን›› በማዘመን ‹‹ዲጅታላይዝ›› የማድረግ ለጥናት እና ምርምር እንዲውሉ በሌሎች ቋንቋዎች ከመተርጎም አንጻር ምን ሰራችሁ?
አቶ ተወለዳ፡- አሁን ላይ ያሉንን ማንስክሪፕቶች ዲጅታላይዝ የማድረግ ተግባራት አከናውነናል። ዲጅታላይዝ ያደረግናቸውን ማንስክሪብቶች ለጥናት እና ምርምር የሚውሉበትን መንገድ ለማመቻቸት የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል። ነገር ግን በተለያዩ ቋንቋዎች ከመተርጎም አንጻር ገና ስራዎችን አልጀመርንም።
ማንስክሪፕቶች በተለያዩ ግለሰቦች እጅ ይገኙ ስለነበር መጀመሪያ እንደቢሮ የሰራነው ከተለያዩ ቦታዎች ማንስክሪፕቶችን መሰብሰብ ነበር። ቅርሶች በተለያዩ ሰዎች እና ቦታዎች ተበታትነው ስለነበር እነሱን የማሰባሰቡን ስራው ገና አልጨረስንም። ሰብስበን ከጨረስን በኋላ የመጠገን፣ የመጠረዝ እና የማስተካከል ስራዎች እንሰራለን። ከዚያ በኋላ ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ ይሰራል። አሁን ላይ ማንስክሪቢቶች በመሰብሰብ እየጠገን እና ዲጅታላይዝ የማድረግ ስራዎችን እየሰራን ነው። በቀጣይነት ለጥናት እና ምርምር እንዲውሉ ለማስቻል የትርጉም ስራ ልናከናውን እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የጅብ ትርኢት ማሳያ ፕሮጀክት ግንባታ ምን ላይ ደረሰ ?
አቶ ተወለዳ፡- በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ የተጀመረው የጅብ ትርኢት ማሳያ ፕሮጀክት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። ለቱሪስቱ ምቹ እንዲሆን በሰጡት አደራ መሰረት የክልላችን ፕሬዚዳንትም አደራውን ተቀብለው የገቢ ማሰባሰቢያ ተደርጓል። በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ 70 ሚሊዮን ብር ከሕዝብ መሰብሰብ ተችሏል። በገንዘቡ ዲዛይኑ ተሰርቶ ተጠናቆ ግንባታ ላይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ ፕሮጀክቱ ተጠናቋል። በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ሸዋል ኢድን ለሕብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት ከመጠቀም አንጻር ምን ተሰርቷል?
አቶ ተወለዳ፡– ሸዋል ኢድን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት ሲደረግ ነበር። ይህንንም ከፌዴራል ቅርስ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ቦትስዋና ላይ በተደረገው የማይዳሰሱ ቅርሶች ስብሰባ ላይ ተቀባይነት አግኝቶ ተመዝግቧል።
ሀገራችን የማይዳሰሱ ቅርሶችን በማስመዝገብ ቁጥር በመጨመር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንድትሆን አድርጓል። በዚህም ሐረር የሚዳሰስና የማይዳሰስ ቅርስ በማስመዝገብ ቀዳሚ ከተማ ያደርጋታል። በእነዚህ ስራዎች በቂ ስራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል።
የሸዋል ኢድ በዓልን “ሕብረ ብሄራዊነታችን ለቱሪዝም እድገታችን” በሚል መሪ ቃል ስናከበር ቆይተናል። ወደፊትም በዚህ ልክ ይከበራል። ይህም ወንድማማችነትን እና አብሮነትን አጠናክሮ ለትውልድ እንዲሸጋገር ከማድረግ አኳያ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን:- በሐረሪ ክልል የተለያዩ ብሔር ብሔር ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ ሙዚየሞች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡ ያሉም አሉ። እነኝህ ሙዚየሞች የሐረርን የሰላም ከተማነት እሴት ከማጉላት አንጻር የሚኖራቸውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል ?
አቶ ተወለዳ:- ሙዚዬሞችን እየሰራን ያለው በክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ግቢ ውስጥ ነው። መጀመሪያ የሐረሪ ባህላዊ ቤቶች ተሰርተዋል፣ ቀጥሎም የኦሮሞ ባህላዊ ቤቶች እና የአባገዳ እልፍኝ ተሰርቷል። የአባገዳ እልፍኝ ሲሰራ እያንዳንዱን ኦሮሞ ባህልና እሴቶች እንዲሁም ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ነው። ከኦሮሞ የባህል ማዕከል በተጨማሪ የሶማሌና የአፋር ክልሎችም የባህል ሙዚዬሞቻቸውን ለመገንባት በሂደት ላይ ናቸው ።
ይህም የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሕዝቦችን ቀደም ብሎ የነበራቸውን በሰላም፣ በአብሮነት የመኖር እሴቶቻቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ሐረርንም ቀድሞ የነበራትን እሴት ይመልሳል።
አዲስ ዘመን:- ሐረር የሰላም ከተማ ተብላ በዩኒስኮ ሽልማት እንድታገኝ ያስቻላት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ተወለዳ:– ሐረር የሰላም ከተማ በመባል በዩኒስኮ ሽልማት አግኝታለች። ሐረር ላይ የሚገኙ ኃይማኖቶችን ብንወስድ በአንድ ቦታ ላይ ያለምንም ችግር ከ110 ዓመታት በላይ የቆዩ ሶስት ኃይማኖቶች አሉ። እነዚህ ኃይማኖቶች በአንድ ስፍራ ያለምንም ችግር የአምልኮ ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። አንዱ ለአንዱም ጌጥ ነው።
በሌላ መልኩም የሕብረተሰቡን አኗኗር ማየት እንችላለን። በአንድ ግቢ ውስጥ የተለያዩ ብሄሮችና ኃይማኖቶች በመቻቻል አንዱ የሌላውን ወዶና አክብሮ የሚኖርባት ከተማ ናት። ሐረር ላይ አጽንተው ያቆዩንም እነዚህ እሴቶቻችን ናቸው።
አዲስ ዘመን:- ሐረር ላይ ያለው መቻቻልና አብሮነት ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ምን አስተዋጽኦ አለው?
አቶ ተወለዳ:– ጀጎል ውስጥ በቀደመው ጊዜ የተገነቡ ከ99 በላይ መስጊዶች አሉ። እነዚህ መስጊዶች ግማሾቹ ከ500 ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ከ1000 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ናቸው። እነዚህ መስጊዶች ባሉበት አካባቢ የኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አብረው አሉ። በአንድ ግቢ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መኖር ብዙ ሰው ሊከብደው ይችላል። ነገር ግን ሐረር ላይ ምንም አይነት ልዩነት ሳይፈጠር ልዩ ውበት ነው ብለው እየኖሩ ነው።
የሐረርን አብሮነት ሚስጥር አንዳንድ አካላት እንጠቀምበት ካሉ ለግጭት መንስኤ ሊያደርጉት ይችላሉ። እኛ ግን ይህን ለአብሮነታችን ተምሳሌት አድርገን ይዘን እየቀጠልን ነው። ይህም የሆነው አንዱ የሌላውን ባህልና የሚከተለውን እምነት እያከበረ ስለሚኖር ነው።
በመድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን ያሉ አባቶች የመስጊዱን አዛን ይሰማሉ። በዚህም የሚሰሙት የድምጽ ማን እንደሆነ ስለሚያውቁ ድምጹ ብዙ ጊዜ ከጠፋ አዛን የሚያደርገው ሰው የት ሄደ? ብለው ይጠይቃሉ። ይህ በተግባር የሆነ ነው። አንድ የኦርቶዶክስ አባት ለረጅም ግዜ ሲሰሙት የነበረው አዛን የሚያደርጉ አባት ድምጽ ሲጠፋባቸው ምን ሆነው ነው? ታመው ነው ወይስ አርፈው? ብለው መስጅድ ድረስ ሄደው ጠይቀዋል። ይህ ለማኅበራዊ ትስስሩ ጠንካራ መሆን ትልቅ ማሳያ ነው። ስለሆነም ሐረር ላይ አንዱ ለአንዱ ሸክም ሳይሆን ጌጥ ሆኖ እየኖረ ነው። ይህ ለሌላው የሀገሪቱ ክፍል ምሳሌና ተሞክሮ የሚሆን ነው። ይህም ለቱሪዝም ፍሰቱ ከፍተኛ አስተዋጾ ያለው ነው ።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የሜዲካል ቱሪዝምን ከማስፋፋት አኳያ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ተወለዳ:– በሐረር የሚገኘው ጀጉላ ሆስፒታል በእድሜ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ነው። አሁን ላይ የጀጉላ ሆስፒታልን ጨምሮ በርካታ ሆስፒታሎች ይገኛሉ። በመሆኑም በሐረር ከአጐራባች ክልሎች የሚመጡ ታካሚዎች በብዛት አገልግሎት ያገኛሉ። ይህም ለሜዲካል ቱሪዝም እድገት የራሱ የሆነ አስተዋጾ አለው። የሜዲካል ቱሪዝም ለማሳደግ እንደክልል የተጀመሩ ስራዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የጤና ኮርደር ልማቱ ተጠቃሽ ነው። ይህ የኮሊደር ልማት ሲጠናቀቅ የሜዲካል ቱሪዝም ፍሰቱን እንደሚጨምር ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- ለቱሪዝም ፍሰቱ ሆቴሎች ትልቅ ሚና አላቸው ፤ሐረር ላይ ያንን መሸከም የሚችል የሆቴሎች ጥራት እና ቁጥር አለ? በዚህ ዘርፍስ ኢንቨስተሮች እንዲሳተፉ ምን አይነት ጥረት እያደረጋችሁ ነው?
አቶ ተወለዳ፡– ሐረር ላይ ትልቁ ጉድለታችን ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አለመኖር ነው። የቱሪስቶች የመቆያን ጊዜ እያሳጠረው ያለው ይሄው ችግር ነው። ይሄንን ችግርም ለመቅረፍ በሁለት መንገድ እየተሰራ ነው። የመጀመሪያው ያሉት ሆቴሎች ብቃትና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያ ሆቴሎች ያሉባቸውን ክፍተቶች በማጥናት በስልጠና፣ በክትትልና በቁጥጥር እንዲስተካከሉ የማድረግ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን።
ሁለተኛ የሆቴል ክፍተቱን ለመሙላት ለኢንቨስትመንት ቦታ ያዘጋጀንበት ሁኔታ አለ። ትልልቅና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲገነቡ ቦታ ተዘጋጅቷል። በቅርቡ ክልሉ ጥሪ በማድረግ ኢንቨስተሮችን ይጋብዛል።
በዚህ አጋጣሚ በሐረር ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ለመገንባት ፍላጎት ያላቸውን ኢንቨስተሮች ሐረር ለማስተናገድ ዝግጁ ናት። በኢኮ ፓርኩ እና በከተማው የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተዘጋጁ ቦታዎች አሉ። አሁን ላይ እየተገነቡ ያሉ ሆቴሎችም አሉ። የእነዚያን ግንባታዎች እያበረታታን እንገኛለን። የቱሪስቶች የቆይታ ግዜ ለመጨመርም እየሰራን እገኛለን።
ኢኮ ፓርኩ ሲጠናቀቅም የቱሪስቶችን ቆይታ ያራዝማል። በቀን እና በምሽት አገልግሎት ይሰጣል፤ የጅብ ትርኢቱን ማሳየት ይችላል። ከዚህም ቱሪስቱን በመሳብ ሐረር ላይ እንዲቆይ የሚያስችሉ ስራዎችን በስፋት እየተከናወኑ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- አስጎብኚዎችን በማስተማርና በማሰልጠን ረገድ ምን እየሰራችሁ ነው?የቱሪዝም ዘርፉ ስራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ ምን እያበረከተ ነው ?
አቶ ተወለዳ፡- ከኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማህበር ጋር ትስስር ፈጥረን እየሰራን ነው። ከ35 በላይ ለሚሆኑ አስጎቢኚዎቻችን ስልጠና እንዲወስዱ አድርገናል። ሰልጣኞቹ እራሳቸው አምባሳደር እንደሆኑ አውቀው የገጽታ ግንባታ ስራ እንዲያከናውኑ ተደርጓል።
በቀጣይ ከሌላ አካባቢ ካሉ አስጎብኚዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩና አካባቢያቸው ላይ ያለውን ቱሪስት ወደዚህ እንዲልኩ፤ እዚህ ያለውንም ወደዛ እንዲጋብዙ ለማድረግ እየሰራን ነው። ከድሬደዋ፤ ከሱማሌ ጋር አብረን መስራት የምንችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው። በዋናነት ግን በዚህ ዓመት የሰራነው ስልጠና መስጠትና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር እንዲተዋወቁ የማድረግ ስራዎችን ነው። በዚህም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ያሉትን የቱሪስት ሀብቶች ለማስተዋወቅ ደረጃቸውን የጠበቁ ማስተዋወቂያዎችን ከመስራትና ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ምን ሰርታችኋል?
አቶ ተወለዳ፡- በቅርቡ ወደ ትግበራ የገባ ‹‹ቪዚት ሐረር›› የሚል የዌብሳይ ፔጅ አለን። ቪዚት ሐረር ፌስቡክ እና በሌሎች የማህኅበራዊ ድረገጾች የማስገባት ስራዎችን እሰራን ነው ። በዚህም አንድ ቱሪስት መነሻ ቦታው ላይ ሆኖ ሐረርን ማየት የሚችልበትና ከሆቴሎች ጋርም ትስስር መፍጠር የሚችል መተግበሪያ ነው። በዚህ መተግበሪያ ማንኛውም ሰው በስልኩ ስለ ሐረር ማወቅ ይችላል። ይሄ ግን በቂ አይደለም።
የማስታወቂያዎች ወጪ ውድ ነው። ጥራታቸው ሲጨምር እና ትልልቅ ሚዲያዎች ላይ እናስተዋውቅ ሲባል ዋጋቸው ይጨምራል። ነገር ግን በራሳችን አቅምና ባለሙያ የሚሰሩት ላይ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወንን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች ክልሎች ጋር ያላችሁ የልምድ ልውውጥ ምን ይመስላል?
አቶ ተወለዳ፡- የልምድ ልውውጥ ለማድረግ አንድ መድረክ አዘጋጅተን ነበር። ይህም በአምስቱ አጎራባች ክልሎች ካሉ የቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በመተባበር የሚሰራ ነበር። ዋና ሃሳቡም ድሬደዋን፣ ኦሮሚያን፣ አፋር እና ሱማሊያን ለመጎብኘት የመጣ ቱሪስት ሐረርን ሳይጎበኝ መሄድ የለበትም የሚል ነው። ሐረርን ሊጎበኝ የመጣ ጎብኝም በተመሳሳይ ሌሎችን ቦታዎች እንዲጎበኝ ለማድረግ የተዘጋጀ ክላስተር ነበር። ተባብረን ተሳስረን መሄድ አለብን የሚል ተነሳሽት ነው። ያንን አጠናክረን እንሄዳለን። ከሁሉም ክልሎች ጋር የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርመናል። ግን ያንን ወደ ስራ ማስገባት ይቀረናል፤ በሰፊው መስራት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ተወለዳ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም