አዲስ መንገድ

ጥበብን ለምትፈልጓትና ፈልጋችሁም ላጣችኋት፤ ጥበብ ወዲህ ናት… ሰሞኑን ከአንድ አዲስ መንገድ ላይ ጉዞ ጀምራለች። ከሰሜን እስከ ምሥራቅ፣ ከደቡብ እስከ ምዕራብ ጓዛቸውን ሸክፈው ሁሉም አዲስ አበባ ላይ ይከትማሉ። ቱባ ቱባ ባህሎች ፍሪዳ ፍሪዳ ጥበባት ጥለው፣ ሙዳውን ከጮማው እየቆረጡ ሊያበሉን ሳይሆን አይቀርም። እኛ ካልቀረን በስተቀር ጥበብማ ቀድማን ደርሳለች። አራቱንም ማዕዘናት በአንድ መድረክ ላይ ያገናኘ የኪነ ጥበብና የሥነ ጥበብ ውድድር አሐዱ የተባለበትን የባህል ሸማ ተለብሶ በትእይንቱ እሽቅርቅር ሊባልበትም ታስቧል። ማነውስ አሳቢው? ከተባለ፤ የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሲሆን ለዚህ ደግሞ እኔ አለሁኝ ይላል።

በታሪኩ የመጀመሪያው የሆነውን ሰፊ የጥበብ ገበታ አዘጋጅቶ ሽርጉድ ማለቱን ተያይዞታል። ከብዙ የሽርጉድ ሌትና መአልት በኋላ ቀኑ ደርሶ ጠሪ አክባሪውን በመቀበል የአዳራሹን በር፣ የመድረኩን መጋረጃ ገልጦ እንደቆመ ነው። ጥበብም መቀነቷን አጥብቃ ሰንዳ ትላለች። እኛም እሷኑ ተከትለን እብስ ማለታችን አይቀሬ ነው። በዛሬው ዕለተ ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን፤ ከኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ደጃፍ ተነስታ በጊዮን ሆቴል አዳራሽ ውስጥ ሽብርቅ ትላለች። በባህል ቀሚሷ አምራና ደምቃ ገና በጠዋቱ ከማለዳው የብርሃን ጮራ ጋር ስታንጸባርቅ ለማየት እኛም እንቸኩላለን።

“የባህል ጥበባት ለማኅበረሰብ ትስስር እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ” ይላል የዓላማው አትሮኖስ ከተራራው ላይ ሽቅብ እያበራ። ኪነ ጥበቡን ለመዝናናት ብቻ የምንፈልገው ከእንግዲህ ወዲያ አንፈልገው። ከዚህም ያለፈና የገዘፈ ምንነት እንዲኖረው በተረሳበት ደጅ ሁሉ አሁን ታውሷል። አሁን ላይ አንድም ከባህል ጉብታ ላይ ወጥቶ፣ ሁለትም ከሀገር ግንባታ ላይ ተሰማርቶ ታላቅነቱን ለማሳየት የሚችልበትን ዕድል ወደማግኘቱ ላይ ነው። ዕድሉን ካገኘማ ሁለቱንም ባላዎችን አንድ አድርጎ ያማረ ትርኢት ያሳየናል። ከሰሞኑ የተሰማው አዲስ መንገድ ደግሞ ወደ ሀዲዱ መግቢያው ነው። “መቼ ነው ግን መንግሥት ዞር ብሎ ኪነ ጥበቡን የሚመለከተው?” ብለን ስንጠይቅ ለነበርንም ቢያንስ የአፍታ እፎይታን የሚሰጠን ይሆናል። ኪነ ጥበባትና ሥነ ጥበባት ከሁሉም የውብ ባህል ህብረ ብሔሮች ጋር እንደ ሀገር በአንድ መድረክ የታዩበትን ጊዜ ለማስታወስ ያዳግታል። ያሉን ነገሮች የማይነጥፉ የባህል እሴቶች ብቻም ሳይሆኑ፤ የማይነጥፉ ህብረ ጥበባትም ጭምር ናቸው። እናም ባህሎቻችንን ከኪነ ጥበባትና ሥነ ጥበባት ጋር ሲነሰነሱ ልንመለከታቸው ነው። ከእያንዳንዱ የሀገራችን ክፍል የተወከሉ ተወዳዳሪዎች ደርሰዋል። በተለያዩ ዘርፎች ለማወዳደር የተመረጡ ቁንጮ ዳኞችም ዝግጁ ሆነው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ዛሬ ሰኔ 13 ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ 15 ቀን ድረስ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ይዘልቃል። ከውድድሩ በተጨማሪም ትርኢታዊ ትእይንቶች የሚቀርቡ ይሆናል።

2016፤ ወርሀ ሰኔ፣ የመጀመሪያውን ዙር ለማዘጋጀት የተመረጠች ዕድለ ጥበብ ሆናለች። ቀጣዩን ለሚቀጥለው ዓመት ከሰጠን በኋላ ቀጥሎስ? ስንል…ወዲሁ ይመልሰንና ታዲያ እንዴትና በምንስ ይሆን ውድድርና ትእይንቱ? ማለት አይቀርም። የዝግጅቱ ዋና አጋፋሪ የሆነው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፤ ከሳምንት በፊት ከሚዲያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ቢጤ ምክረ ሃሳብ አድርጎ ነበርና ከነገሩን እናጋራችሁ…በዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር አራት ያህል ጥበባት የተመረጡ ሲሆን አንደኛው ግን ለኤግዚቢሽን ትርኢት የሚውል ይሆናል። እያንዳንዱ የክልልና የከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪዎቻቸውን ይዘው ይቀርቡባቸዋል የተባሉት ዘርፎችም ሙዚቃ፣ ስዕልና ፋሽን ናቸው። በሙዚቃው ዘርፍ በድምጽና በሙዚቃ መሣሪያዎች ሲሆን እያንዳንዱ የሚቀርብበት መንገድ የራሱን የባህል ሙዚቃ በሚያንጸባርቅ መልኩ ይሆናል። በስዕል ዘርፍ ወጣትና ልምድ ያላቸው ሰዓሊያን በሁለት ጎራ ይሳተፋሉ። በፋሽኑ ደግሞ በወንድና በሴት ሞዴሎች ተለይቶ ይደረጋል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ውድድሩ በምን ልኬትና ሚዛን ነው አሸናፊውን ለመለየት የሚቻለው? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፤ ምክንያቱም ውድድሩ በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን ባህላቸውን ይዘው በቀረቡ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ነውና። “እኛ ሥራውን እንጂ ባህልን ከባህል አናወዳድርም” ሲሉ ተናግረው ነበር፤ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ዘርፍ ኃላፊዋ ክብርት ነፊዛ አልማህዲ ከሚዲያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ። ዶሮ ወጥ አሊያም ሽሮ ወጥ ሠርቶ ማቅረብ ማንም የማይጋፋው መብት ነው። የዳኛው የምግብ ምርጫ ዶሮ ወጥ ስለሆነ አሸናፊ እንዲሆን አያደርገውም። ሽሮ የሚወደውንም እንዲሁ… ዶሮ ወጥ አቅራቢው የሚወዳደረው ከሽሮው ጋር ሳይሆን ከሚታወቀው የዶሮ ወጥ አሠራርና ጣዕም ጋር ነው። ማንኛውም ተወዳዳሪ ይገልጸኛል የሚለውን ምንም ነገር ይዞ መቅረብ ይችላል። ነጥብ የሚያስገኝለት ይዞ የመጣው ነገር ሳይሆን ይዞ የመጣውን ነገር የሚያቀርብበት መንገድ ነው። ስለዚህ ከተወዳዳሪው ፊት የተቀመጡት ዳኞች ሚዛኖቻቸውን የሚያስቀምጡት ከራሱ ከብሔረሰቡ ትውፊታዊ መስፈርቶች ላይ ይሆናል። የሚቀርቡት ተወዳዳሪዎችም እዚህ የደረሱበት መንገድ ቀደም ሲል በየክልልና ከተሞቻቸው ከታች ከወረዳ ጀምሮ እየተወዳደሩ እንጂ በዘፈቀደ ተመርጠው የመጡ አለመሆናቸውንም ክብርት ነፊሳ አውስተውታል። በእያንዳንዱ ዘርፍ አሸናፊ ለሚሆኑትም የማበረታቻ ሽልማቶች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።

ኪነ ጥበብ ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት ምሰሶና ዋርካ መሆኑን አሁን አሁን መንግሥትም እያመነና ለመሥራት እያሰበበት ያለ ይመስላል። ከዚህ ቀደም እንደምናውቀው ለሀገር ግንባታው ቀርቶ ከመዝናኛነትና ከጊዜያዊ የስሜት ቋጥኝ ያለፈ መቀመጫ አነበረውም። በመሪ ቃሉ ላይ ከተቀመጠው አንጻር ብቻ አንድ ርምጃ ወደፊት ልንለው እንችላለንና ይህም አንድ አዲስ መንገድ ነው። ኪነ ጥበብ ከተጠቀሙበት ሀገርን እንደ ባቢሎን የመሥራት አቅም አለው። እንደ ሀገርም እንደ ዓለምም ፖለቲካን በፖለቲካ ከመፍታት ይልቅ፤ ፖለቲካን በኪነ ጥበብ መፍታት ጊዜ፣ ገንዘብና ነብስንም ቆጣቢ ነው።

በባህል እሴት ለታጨቅን እኛ እንዲህ ዓይነቱ ባህል ወለድ ኪነ ጥበባዊ መንገድ ፍቱን መድሃኀኒታችን ነበር። ነገሩ ግን ለመረዳት እጅግ የዘገየን ይመስላል። ልንጠለልበት የምንችልበትን ትልቁን ዋርካ እንደ ጉቶ ስንቀመጥበት ብቻ ኖረናል። ከሰው ልጆች አፈጣጠር ጀምሮ እድሜ ጠገብ የሆነውን ኪነ ጥበብ እስካሁንም ድረስ “አቡሽና ሚጣ” ብለን በምንጠራው ደረጃ ላይ መሆኑ ያሳዝናል። ሌላው ቀርቶ ከያሬድ ጀምሮ ያለው ሙዚቃ፣ ዋሻና አለቱን እየፈለፈሉ ስዕልና ቅርጻ ቅርጽን የጀመሩበት፣ ቆዳውን ድጠውና አልፍተው በብራና ላይ የከተቡበት ዘመን ብናስብ እንኳ አንቱ የሚያንሰው ነበር። አዲስ ነገር ልንሠራባቸው ባንችል እንኳን ተገቢውን ክብርና ዕውቅና ሰጥተን ልንከባከባቸው ይገባን ነበር። በየጓዳው ተሰግስገው ሳንጠቀምባቸውና ሳንጠቅማቸው ከገሚሱ ተፋጠን ከገሚሱም ተጠፋፍተን ኖረናል። አሁን ግን እንደ አንድ ሀገር መንግሥት ጠቀለል አድርጎ ለመሥራት መታሰቡ ይበል የሚያሰኝ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በነበረው አሠራር የኪነ ጥበብ ዘርፍ ይመራ የነበረው እንደ አንድ ክፍል ነበር። ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን እራሱን ችሎ በሚኒስትር ደረጃ እየተመራ የተሻለ ትኩረት ለማግኘት ችሏል። በሀገር ደረጃ የጥበብ ባለ እዳ ነን። ጥበብ ካሳ ይገባታል ቢባል፤ በምንም መልኩ እዳዋን ከፍለን የምንጨርሰው አይደለም። የአሁኑ አዲስ መንገድም የእስከዛሬውን ስብራት ለመጠገን በማሰብ ይመስላል።

ግን ደግሞ አንድ ነገር ያሰጋናል…በኛ ሀገር ውስጥ የሚጀመሩ ብዙ ነገሮች፤ ጊዜ ሁኔታውን ግራና ቀኙን እየተመለከቱ መሀል ላይ ደብዛቸው የሚጠፋው ነገር አለ። ከመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚለዋወጡ ጉዳዮች ቀላል አይደሉም። አሁን የተጀመረው በመንግሥት እንደመሆኑ፤ ታዲያ ለወደፊቱስ ምን ታስቧል? የሚል ጥያቄ እንድንጠይቅ ያስገድደናል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንደጀመረው በነካ እጁ የወደፊቱንም ህልውናውን ቢቀይሰው መልካም ነው። የጥበባት ኢንዱስትሪዎች እና የግሉን ባለሀብቶች በማካተት፤ ቀስ በቀስ እራሱን የቻለ አንድ ግዙፍ ተቋም አድርጎ የማይሻር የማይለወጥ ማድረግ ይኖርበታል። አሊያማ የሚሰበር እስካለ ድረስ ሰባሪው ብዙ ነው። በሚገባው ልክ ተይዞ ከተኬደበት መንገዱ ወደ ታላቅነት ነው። እራሱን እያንበሸበሸ በሀገር ኢኮኖሚው ላይ ብትን አበባ ይነሰንስበታል።

ውድድሩን ፊት ለፊት በደመነብስ ብቻ ከተመለከትነው ባህልን ከባህል ጋር የማወዳደር ብዥታ ይደነቀርብን ይሆናል፤ ያ ግን እውነት አይደለም። ከውድድሩ በፊትም ሆነ በኋላ ሁሉም አንደኛ ናቸው። ተወዳዳሪዎቹ ወደ መድረኩ ሲወጡና ይዘው የመጡትን በዳኞች ፊት ሲያቀርቡ በኪነ ጥበባዊና በውበት ሚዛን ይለካሉ። ስለዚህ አዲስ ፈጠራ አዲስ እይታን መፍጠር ይኖርባቸዋል። ፈጠራው ግን ያነበረውን መፍጠር ላይ ሳይሆን የነበረውንና ያለውን ማራኪ በሆነ መንገድ የማቅረብ ነው። ሁሉም ተወዳዳሪ ዶሮ ወጥ ይዞ እንደሚያቀርብ ዳኞች ቀድሞም ያውቁታል፤ ስለዚህ ነጥብ የሚያሰጠው ያቀረቡት ዶሮ ወጥ ሳይሆን ጥፍጥናው ላይ ነው። ያ ደግሞ በተወዳዳሪው የግል ችሎታ ላይ እንጂ በባህሉ ላይ የተመረኮዘ አይደለም። ከዳኞች ፊት በጋሞ ብሔረሰብ ጭፈራ የቆመ አንድ ሰው የሚለካው ከሚጨፍርበት ሙዚቃ ጋር በተዋሃደበት መጠንና ጋሞኛ ጭፈራ ከሚጠይቀው እንቅስቃሴያዊ ችሎታ አንጻር ብቻ ነው። ከዳኞቹ ይልቅ ብሔረሰቡ ባስቀመጠውና በሚያውቀው መስፈርት ላይ የተደገፈ ይሆናል።

ውድድሩ እንደ ውድድር ብቻ ተካሂዶ እጅ የሚጣፋበት አይደለም። ከዚህ በስተጀርባ ሌሎች ግዙፍ ዓላማዎች እንዳሉት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚዲያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በነበረው የውይይት ወቅት ገልጾ ነበር። ከሃሳቡ ውስጥ ሦስት አንኳር ነጥቦችንም ለመጥቀስ እንችላለን። የመጀመሪያው ነገር የጅምሩን ቀጭን መንገድ ይዞ እስከ ክልልና ዞን፤ አልፎም እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ መዘርጋት ነው። ከላይ ቢጀምርም የሚያስፈልገው ግን ከታች መጀመርን ነው። ሰፊ ጊዜና ዝግጅት ቢሻም እንደ ወርቅ እየተፈተነ በስተመጨረሻ በሀገር ደረጃ የምናገኘው የነጠረውን ንጽሁ ወርቅ ይሆናል። ሁሉንም የኢትዮጵያን ባህልና ጥበብ የምናውቀው ይመስለናል እንጂ ገና ምኑም አልተነካም። ካለው አንጻር ምንም የምናውቀው የለም። በእንዲህ ዓይነቱ ከባህል ተራራ ስር ከሚቀዳ የጥበብ ምንጭ፤ ከእያንዳንዱ ገጠርና ከተማ እስከዛሬ ድረስ ካልታዩና ካልተሰሙ አዳዲስ ነገሮች ጋር ፊት ለፊት እንገናኛለን። የዚያን ጊዜ ታዲያ፤ ጥበብስ ቢሆን በሀገር ምድሩ ተምነሸነሸችበት ማለት አይደል… ሌላኛውና ሁለተኛው ጉዳይ እስከዛሬ ሲደረግ የምንመለከተውን በተናጠልና የሚደረገውን እንደ አይድልና የተሰጥኦ ውድድሮች የመሳሰሉት ናቸው። በአንድ አሊያም በጥቂት ግለሰቦች ጫንቃ ላይ ያረፉ በመሆናቸው ተጀምረው ሁለትና ሦስት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሲቋረጡና እንደ ጠዋት ጤዛ ሲረግፉ ተመልክተናል። በተደራጀ መንገድ የሚደግፋቸውም ሆነ የሚያንቀሳቅሳቸው ተቋም ባለመኖሩም ዝብርቅርቅ ወለፈንዲ ናቸው።

ችግሩን ለመቅረፍ እንዲህ በተቋም ደረጃ መያዙ አንደኛው የመፍትሄ መርፌው ነው። ይህቺን ዘለል ለማለት ስንችል ደግሞ ሦስተኛው ይመጣል። መንግሥት የዘርፉን ጠቀሜታ ተረድቶ ይበልጥ እንዲጠጋና እንዲደግፈው ያደርጋል። መንግሥትን ከኪነ ጥበብ፣ ኪነ ጥበብን ከሕዝብ ጋር በሦስት ማዕዘናት አቆራኝቶ ሁሉንም በእኩል ያስጠቅማል። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ኪነ ጥበባዊ ጉዳዮቻችን ሰከን ደልደል እንዲሉ ያስችላቸዋል። በሚመጣው ትውልድም እንደ ሀገር ምን ሠሩ ብንባል፤ ይኸው…ተብሎ የሚጠቀስልን ይሆናል። በዚህ መንገድ አጠንክረን ለመሄድ ከቻልን ለውጥ የማንፈጥርበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ወደኋላኛው ዘመን መለስ ብንል እንኳን በሕዝብ ለሕዝብ ሀገራችን የማያልቅ ኪነ ጥበባዊ በረከትን አግኝታበታለች። ከዚሁ አልፎ ወደ ውጭ ሀገራት ሁሉ በርካታ ኪነ ጥበባዊ ጉዞዎች ይካሄዱም ነበር። ፖለቲካው ሊከፍታቸው ያልቻላቸውን በሮችንም ጭምር ኪነ ጥበቡ ይከፍተዋል። ምን ያህል ጠቅሞናል አሊያም ይጠቅመናል የሚለውን የሚያውቀው ያውቀዋል።

ኪነ ጥበብ ያለ ሚዲያው በጎ ፈቃድ የማይታሰብ ነው። ምክንያቱም አብዛኛው የኪነ ጥበብ ማዕድ የሚቀርበው ከሚዲያና በሚዲያ በመሆኑ ነው። ይህንንም በመረዳት ይመስላል አዘጋጅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስቀድሞ ከሚዲያዎች ጋር የግንዛቤ ፈጠራና የውይይት ምክረ ሃሳብ መድረክ ማዘጋጀቱ። እያንዳንዱ ሚዲያስ? ኪነ ጥበቡን በእጁ እንደያዘ ተረድቶ በምን ያህል ደረጃ እየሠራበት ይሆን? የሚለውም ምላሹ የሚዲያው የራሱ ነው። በርከት ያሉ ኪነ ጥበባዊ የመዝናኛ ሚዲያዎች ቢኖሩም ባህልና እሴቶቻችን ከነባለቤቶቻቸው የሚንጸባረቁበት ሜዳ ጠባብ መሆኑ ነው። ለመቦረቅም ለማስፈንደቅም አይሆንም።

ይህ ሁሉ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም። ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል፤ በትንሽዬዋ ጅምር ውስጥ ከዛሬ ይልቅ የነገው ኪነ ጥበብ ቆሞ በእግር ሲሄድ ለመመልከት ያጓጓናል። ለዚህ ዓመት የተመረጡት የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ዘርፎች ካሉት አንጻር በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። በቀጣይ እየጎመራ ሲሄድ ፊልምና ቲያትሮችንም ለመመልከት እንደምንችል ተስፋ እናደርጋለን። እርግጥ ነው ገና ከጅምሩ በአንድ ጀንበር ሁሉን ለማካተት አይቻልም፤ ቢሆንም ግን ሥነ ጽሁፉ ሊዘለል አይገባውም ነበር። ከሁሉም አንጻር ለዳኝነቱም ሆነ ለዝግጅቱ እምብዛም የሚከብድ አይደለም። ሥነ ጽሁፍ ያልተካተተበት የኪነ ጥበብ ጉባኤ ፀበል ጸዲቅ የጎደለው ማህበር ይሆናል። አብዛኛዎቹ የጥበብ ዘርፎችም ከሥነ ጽሁፉ ጋር የተሳሰሩም ጭምር ናቸው። ኮሜዲውም ድሮ ድሮ በየትኛውም የጥበብ ድግስ ድንኳን ሰባሪ ነበር። አሁን አሁን በብዙ ቦታዎች ላይ የመረሳት አደጋ ይጋረጥበታል። ለቀጣዩ ዕድል አግኝተው ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ነገሮች አንደኛው የኮሜዲው ዘርፍ ነው።

እንግዲህ አዲሱ መንገድ ብዙ ካፈጠጡበት እሩቅ ያስኬዳል። ከውድድሩ አስቀድመን በረዥም መንገድ ውስጥ እንዳንጠፋና እንዳንጠፋፋም፤ አቅጣጫ ጠቋሚ ግብዣችንን ወደ ጊዮን ሆቴል በመቀሰት፣ ጋባዦቹ ግን ከወዲሁ መመለሳችን ነው። ጥበብን ለምትፈልጓት ከዚያው ትጠብቃችኋላች።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You