ዓለም በነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ጥገኝነት በመውጣት በኤሌክትሪክ ወደሚሰሩ ተሽከርካሪዎች መጠቀም እያደረገ ያለውን ግስጋሴ ቀጥሏል። በዚህም ዋጋው በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው እንዲሁም በአካባቢ ብክለት ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል አንዱ ከሆነው ነዳጅ እየተላቀቀ ነው።
በሀገራዊ ዕድገት ላይ ትልቅ አቅም እንዳላቸው የሚነገርላቸው እነዚህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተለይ ለአፍሪካ ሀገራት ሰፊ ዕድል ይዘው መምጣታቸው ይገለጻል። አፍሪካ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ገበያዎች አንዷ መሆኗ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪው መስፋፋት ከፍተኛ እድሎችን የሚፈጥር ይሆናል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተለይም ብክለትን የሚቀንሱ እና ኃይል ቆጣቢ መጓጓዣ በመሆናቸው ወደፊት እጅግና ተፈላጊ እንደሚሆኑም ይታመናል።
በአሁኑ ወቅትም ብዙ የአፍሪካ መንግሥታት ማበረታቻዎችን በማቅረብና የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ተጠቃሚዎችንና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪዎችን እየደገፉ ይገኛሉ። የኤሌክትሪክ ተከርካሪዎች ብዙ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ቢሆንም፣ የአፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ኢንዱስትሪ በመጪዎቹ ዓመታት ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በ2030 በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ገበያ 100 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል አንዳንድ ግምቶች ያመለክታሉ።
እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ የኤሌክትሪክ መኪኖች በዓለም አቀፍ ደረጃም እንዲሁ ቁጥራቸው በከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል። መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በአሁኑ ወቅት በመላ ዓለም ከ25 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ የሚገኙት በቻይና ነው። ከዓለም የኤሌክትሪክ መኪኖች 60 በመቶ ያህሉም የተመረቱት በቻይና ነው።
ኢትዮጵያም ይህንኑ ጉዞ በመቀላቀል አያሌ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በአውራ ጎዳናዎቿ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ላይ ትገኛለች። ሀገሪቱ በከፍተኛ መጠን እያለማች የምትገኘውን እምቅ ታዳሽ ኃይል ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹም በማዋል ለነዳጅ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን እየቻለችም ነው።
ተሽከርካሪዎቹ በተለያዩ አማራጮች ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ሲሆን፤ የግል ባለሀብቶችም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም ጀምረዋል። ከአንድ መቶ ሺ በላይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ መገኘታቸውም ይህንኑ ያመለክታል።
ዘርፉ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ላሉ ሀገራት ማስፈንጠሪያ እንደሚሆን ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት የኤሌክትሪክ መኪና በብዙ መልኩ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ቴክኖሎጂ መሆኑን ሲገልጹ፤ “ይህቺ ሀገር ኤሌክትሪክ የማምረት አቅም አላት። ከወዲሁ ይህንን መኪና (የኤሌክትሪክ) መገጣጠም እና ማምረት ከጀመርን የዛሬ አምስት እና አስር ዓመት የምንመኛትን፣ የበለጸገች ሀገር ለማየት ይቻላል” እንዳሉትም ተሽከርካሪዎቹ በስፋት በመጠቀም እድገቱን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል።
የዓለም ጉዞ ወደ ኤሌክትሪክ መኪኖች ባጋደለበት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም የሚያስችል ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆን ባለፈ በማህበረሰቡ ዘንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ፍላጎት ከፍ ማለቱ እንደ ሀገርም እንደ ማህበረሰብም ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
የእነዚህ መኪኖች በሀገሪቱ ሥራ ላይ መዋል የነዳጅ ወጪን ከመቀነሱ በተጨማሪ ሀገሪቱ በአየር ንብረት ላይ ሊከሰት የሚችለውን ብክለት በተወሰነ መልኩም እንድትቀንስ ያስችላታል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ድምጽ አልባ መሆናቸውም በድምጽ ብክለት በኩል ሊመጣ የሚችል ችግር እንዳይኖር ያደርጋል።
በእነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች በሀገሪቱ ተሽከርካሪዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በኤሌክትሪክ መኪና ፍላጎት ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ መሰለፏም እየተገለጸ ነው።
የአየር ንብረትን በከፍተኛ ደረጃ የሚበክል ካርበን የሚለቁ አሮጌ መኪኖች በብዛት የሚነዱባት ሀገር፣ የታዳሽ ኃይል ልማት ሥራን አጠናክራ በመቀጠል የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለመጠቀም የጀመረችው ጉዞ ፈጣን የሚባልም ነው።
እነዚህ ሁሉ መልካም አጋጣሚዎች ተሽከርካሪዎቹን ከውጭ ለሚያስመጡ ድርጅቶችና ግለሰቦች መልካም አጋጣሚ እየፈጠረላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የግሉ ዘርፍ እነዚህን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም ውስጥ እንዲገባም አስችሎታል። ይህም ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍና ከዘርፉ ለሚገኘው ቱሩፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ነው።
መንግሥትም በዘርፉ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። ለእዚህም በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ በ10 ዓመት ዕቅድ ውስጥ ለታዳሽ ኃይል ቅድሚያ መሰጠቱ አንድ ማሳያ ነው። በዚሁ መነሻና ዕቅድም በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የሕዝብ ማመላለሻ እና አነስተኛ ተሽከርካሪዎች በብዙ ቁጥር ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ታቅዷል። በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚጣለው ግብርም እንዲሁ ዝቅ መደረጉ ተሽከርካሪዎቹ በስፋት ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ የሚያበረታታ እንደሆነ ይታመናል።
እንደሚታወቀው የኤሌክትሪክ መኪኖቹ በዋናነት የሚፈልጉት የኤሌክትሪክ ኃይል ነው። ይህን ኃይል ለማግኘት ደግሞ መኪኖቹ ቻርጅ መደረግ ይኖርባቸዋል። ቻርጅ የሚደረጉባቸው መንገዶች ሁለት አይነት ናቸው። ፈጣን/ፋስት/ እና ፈጣን ያልሆነ በሚል ይታወቃሉ። ፈጣን የሚባለው በ30 ደቂቃ ውስጥ ቻርጅ የሚያደርገው ነው። ሌላኛው ዘለግ ያለ ጊዜን የሚፈልገው ነው።
የኤሌክትሪክ መኪኖቹ በስፋት ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ መደረጉ ትልቅ ነገር ሆኖ የቻርጅ ጉዳይ ግን ስጋት እየሆነ ይገኛል። ኃይል መሙያ መሠረተ ልማቶች/ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች/ እንደልብ አለመኖራቸው ለቴክኖሎጂው መስፋፋት ስጋት ሆኗል። ቻርጅ ማድረጊያዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች እንደልብ አይገኙም፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ደግሞ ፈጽሞ የሚታሰቡ አልሆኑም።
መኪኖቹ እንደ አፍሪካም ስጋቶች አሉባቸው። ከነዳጅ ወይም ከናፍጣ ተሽከርካሪዎች የበለጠ ውድ መሆናቸውና አፍሪካ ውስጥ ብዙዎች ሊገዟቸው የማይችሉ መሆኑ ተሽከርካሪዎቹን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል በኩል አንድ ችግር ሆኗል።
ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመሠረተ ልማት አውታር አለመሟላትም እንዲሁ አንዱና ዋነኛው እንቅፋት እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎቹ አንዱ ፈተናም ይሄው ነው። የቻርጅ ማድረጊያ ስፍራ እንደ ልብ አለመኖር ፈተና ሆኗል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱባቸው የኃይል መሙያ መሠረተ ልማቶች ልክ እንደ ነዳጅ ማደያ ሁሉ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። እነዚህን የኃይል መሙያ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ በማድረግ በኩል ትልቅ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ስለመሆኑ ይገለጻል። ድርጅቱ በእዚህ ጉዳይ ላይ ረቂቅ ሕግና መመሪያ በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉ ተጠቁሟል፤ ይሁንና እስካሁን መመሪያውን አዘጋጅቶ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንዲገባ አላደረገም።
ባለስልጣኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ መሠረተ ልማትና ታሪፍ ቀደም ተብሎ መሟላት ያለበትና የዘገየ ስለመሆኑ በማመን በአጭር ጊዜ ውስጥ የኃይል መሙያ መሠረተ ልማቱ እንደሚሟላና ታሪፍም የሚወጣለት መሆኑንም ከሰሞኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ጠቁሟል።
ተሽከርካሪዎቹ ወደ ሀገሪቱ ከመግባታቸው አስቀድሞ መሠራት ያለበት ሥራ ያልተሠራ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፤ ተሽከርካሪዎቹ በግለሰብ ደረጃ እንዲሁም በተለያዩ አማራጮች ኃይል እያገኙ መሆናቸው ተገልጿል። ለመንቀሳቀስ የሚያስፈልጋቸውን ኃይል ሕጋዊ በሆነ አሠራርና መመሪያን መሠረት ባደረገ መልኩ በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች ጭምር ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው አጠያያቂ ባይሆንም፣ ይህ ሲሆን ግን አልታየም።
በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ እያጋጠማቸው ከሚገኘው የኃይል መሙያ መሠረተ ልማት ችግር በተጨማሪ ሌሎች ስጋቶች እንዳሉባቸው ቢገለጽም፣ ዘርፉ ብዙ እድሎችን ይዞ የመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሽከርካሪዎቹ ብዛት መጨመሩን ቀጥሏል። በችግሮች ውስጥም በመሆን የተሽከርካሪዎቹ ብዛት መጨመሩንም እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል።
ይህ በራሱ አንድ እድል ነው፤ ይህን በሚገባ ለመጠቀም መሠራት የሚገባቸው የቤት ሥራዎችን በፍጥነት መሥራት ይገባል። በተለይ የኃይል መሙያ መሠረተ ልማት ለማሟላት የግል ባለሀብቶችና የተሽከርካሪ ባለቤቶች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ሲሆን፤ መንግሥትም የጉዳዩ ባለቤት በመሆን ይህን ጥረት በሚችለው ሁሉ መደገፍ ይኖርበታል።
ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች መኪኖቹን በስፋት በሚጠቀሙ እንደ ቻይና ባሉ ሀገሮች የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ሥራ ላይ የዋሉ መንገዶችን በማጥናት እንዲተገበሩ ማድረግ ላይም መሥራት ይኖርበታል። አሁን የሚታዩትን ችግሮች መፍታት ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን በቀጣይ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮች የሚፈቱ ሥራዎች ከወዲሁ መሠራት ይኖርባቸዋል እንላለን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም