በጀት ለአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አጠቃላይ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ከማድረግ አኳያ የሚኖረው ሚና ተኪ የሌለው ነው፡፡ የሀገራት የእድገት መንገድ የሚለካውም የኢኮኖሚ አቅማቸው በሚፈቅድላቸው ልክ በሚመድቡት በጀት እና በጀቱን በተገቢው መልኩ ተጠቅመው በሚያሳዩት ውጤት ነው፡፡
በዚህ ረገድ በጀታቸውን በአግባቡ የተጠቀሙ ሀገራት የእድገታቸውን ምጣኔ ሲያፋጥኑ የመታየታቸውን ያህል፤ የሚመደበውን በጀት ላልተገባ ዓላማና ጥቅም የማዋል አዝማሚያ የሚታይባቸው ሀገራት በሙስናና ብልሹ አሠራራቸው ምክንያት ኢኮኖሚያቸው በሚታሰበው ልክ ሳይሆን የመቅረቱ ጉዳይ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ባልተቆራረጠው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷ ውስጥ ኢኮኖሚዋ የሚያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ፣ እንዲሁም ብድርና ርዳታን ማዕከል በማድረግ በየዓመቱ ለምታከናውነው ሀገራዊ ሥራ በጀት እየመደበች እዚህ ደርሳለች፡፡ ይሁን እንጂ ይሄንን በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ አውሎ የሚፈለገውን ውጤት ከማምጣት አኳያ ችግሮች መታየታቸው አልቀረም፡፡
ምክንያቱም አይነትና መጠኑ ይለያይ እንጂ በጀትን በአግባቡ እና በቁጠባ ተጠቅሞ የተሰጠን ተልዕኮ ከማሳካት አኳያ በተቋማት የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ይሄም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ በሪፖርት የሚገልጸው ሀቅ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ (ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም) የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትም ይሄንኑ እውነት ያመላከተ ሆኗል፡፡
በዚህ ሪፖርት እንደተመላከተው፤ እንደ ሀገር የታለሙ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ለ2014 የተመደበው በጀት ላይ የኦዲት ተግባር የተከናወነ ሲሆን፤ በዚህም በጀቱን ለታለመለት ዓላማ ከማዋል ባሻገር ክፍተቶች ታይተዋል፡፡ በዚህም ከገቢ አሰባሰብ ጀምሮ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ያለአግባብ ክፍያ፣ መመሪያን ያልተከተለ ግዢ፣ እና ያልተወራረደ ውዝፍ ሂሳብን አለማስመለስን የመሳሰሉ ችግሮች ተስተውለዋል፡፡
ለአብነትም፣ ከትናንት በስቲያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት እንዳመለከተው፤ በ2014 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት በተከናወኑ የኦዲት ሪፖርቶች መሠረት እርምጃ የተወሰደ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ተደርጓል፡፡
በዚህም በ92 መሥሪያ ቤቶች ተመላሽ እንዲደረግ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊዮን 23 ሺህ 846 ብር እና 23ሺህ 230 ዶላር ውስጥ ተመላሽ የተደረገው 11 በመቶው ብቻ ነው፡፡ በተመሳሳይ በ2014 በጀት ዓመት የተሟላ ማስረጃ ሰነድ ካልቀረበበት ብር አምስት ቢሊዮን 61 ሚሊዮን 185 ሺህ 100 ብር ውስጥ 10 በመቶው ብቻ ነው ማስረጃ የቀረበለት፡፡
በሌላ በኩል፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለትን ለመመልከት በተደረገ የኢዲት ሥራ በ2 መሥሪያ ቤቶች 383ሺህ 238 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል፡፡ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተም በ124 መሥሪያ ቤቶች በጠቅላላው ከ14 ቢሊዮን 119 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ተሰብሳቢ ሂሳብ ተገኝቷል፡፡
ከወጪ አሠራር አኳያም፣ በወጪ የተመዘገቡ ክፍያዎች ሕጋዊ ማስረጃ የቀረበላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ11 መሥሪያ ቤቶች ከ43 ሚሊዮን 545 ሺህ ብር በላይ ምንም አይነት ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገበ ገንዘብ ተገኝቷል፡፡ በተመሳሳይ በ30 መሥሪያ ቤቶች 16 ሚሊዮን 407 ሺህ 985 ብር ከደንብና መመሪያ ውጪ ያለአግባብ ተከፍሏል፡፡
በ32 መሥሪያ ቤቶች እና በ9 ቅ/ጽ/ቤቶች ለተለያዩ ግንባታና ግዢዎች፣ እንዲሁም ለውሎ አበልና ለሌሎች ወጪዎች በሚል 62 ሚሊዮን 683 ሺህ 793 ብር ያለአግባብ በብልጫ ተከፍሏል፡፡ በ73 መሥሪያ ቤቶችና በ15 ቅ/ጽ/ቤቶች በድምሩ ከሁለት ቢሊዮን 199 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥትን የግዢ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዥ ተፈጽሟል፡፡
እነዚህን እና መሰል የዚህ ኦዲት ግኝት ደግሞ፣ ወደ አንድ ትሪሊዮን የሚጠጋ ሀብት ለተበጀተለት የ2017 በጀት ዓመት የበጀት አጠቃቀም ሂደት ትልቅ ግብዓት ሊሆን የሚገባው ሲሆን፤ በዚህም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ሕግና አሠራርን ተከትለው ሥራ ላይ ለማዋል የሚችሉበትን ተቋማዊ ኃላፊነት ለመወጣት እንዲዘጋጁ የሚያደርግ፤ ምክር ቤቱም ይሄንኑ ማዕከል አድርጎ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱን እንዲከውን ግንዛቤን የሚያሳድግለት ነው፡፡
ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት ከምክር ቤቱ “በሕገ-መንግሥቱ እና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ላይ እንደተመላከተው፤ ምክር ቤቱ በጀት ማፅደቅ ብቻ ሳይሆን፤ የፀደቀው በጀት በተገቢው አሠራር፣ ቁጠባን መሠረት ባደረገ መልኩ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉና ውጤታማ ስለመሆኑ የመከታተል መብትና ግዴታውን መወጣት አለበት፤ ተቋማትን የሚከታተሉ ቋሚ ኮሚቴዎችም በዚሁ መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤” በሚል የተነሳው ሃሳብም ይሄንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም