በክልሉ በጸጥታ ምክንያት የተቋረጠውን የሌሊት የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ለማስጀመር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጸጥታ ምክንያት የተቋረጠውን ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ የሌሊት የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስጀመር እየተሠራ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱና ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ በሚያስገቡ መንገዶች ላይ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት መኪናዎች በቀን የጊዜ ሰሌዳ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፤ ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ፤ ከክልሉም ወደ አዲስ አበባ የተቋረጠውን በማታ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን ለማስጀመር ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው።

ከአዲስ አበባ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚያስገቡ መንገዶች ማለት በወሊሶ፣ በቡታጅራ፣ በቀለበት መንገድ በዝዋይ ወደ ክልሉ በሚያስገቡና እና ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ በሚያስወጡ መስመሮች ላይ ሸኔ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው ችግሮች ነበሩ ብለዋል።

ክልሉ ከተዋቀረ በኋላ የጥፋት ቡድኑ በተሽከርካሪዎችና በተጓዦች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር የቅንጅት ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ እንዳሻው፤ በተሠራውም ሥራ ተሽከርካሪዎች በቀን ያለምንም የጸጥታ ስጋት መንቀሳቀስ ችለዋል ብለዋል።

አልፎ አልፎ የሚሸሸግ የጥፋት ኃይል ሰዓት እየጠበቀ መኪና የማቃጠል ድርጊት ይፈፅማል፤ በተለይ በቡታጅራ በኩል ከሌመን ወደ ክልሉ በሚያስገባው መስመር ላይ ድርጊቱ በቅርብ ጊዜ ተፈፅሟል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ አልፎ አልፎ የጥፋት ኃይል ሲሸሽ የሚያደርሳቸውን ችግሮች ለመፍታት ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ክልሉ ወደ አዲስ አበባ የሚያስወጡና የሚያስገቡ መንገዶችን ከስጋት ቀጣና ነፃ በማድረግ መኪናዎች በማታ የጊዜ ሰሌዳ እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አቶ እንዳሻው አያይዘውም፤ “በክልሉ ውስጥ በምሥራቅ ጉራጌ ምሥራቅ መስቃንና በማረቆ አካባቢዎች፣ በወልቂጤ አካባቢ በቀቤናና በጉራጌ ወንድማማቾች የተፈጠሩ ግጭቶች ነበሩ፤ የተፈጠሩት ግጭቶች ሕዝብ ለሕዝብ አልነበሩም፤ የጥቂት ግለሰቦች ፍላጎቶች ናቸው። የተፈጠሩ ችግሮችን በአካባቢ ሽማግሌዎች በእርቅ ከስር ከመሠረታቸው እንዲፈቱ ተደርጓል፤ አሁን ክልሉ ሙሉ ለሙሉ ሰላም ነው፤ ሰዎች በሰላም አምሽተው የሚሰሩበት፣ በሰላም ወጥተው የሚገቡበት ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

በክልሉ ያለውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት የማደራጀት፣ ማህበረሰቡን የማስተማር፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከባለሀብቶች ፣ ከወጣቶች፣ ከእናቶችና በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ከተደራጁ ዜጎች ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግና ወደ ወንጀል የተቀየሩ ጉዳዮችን በሕግና በሥርዓት እንዲዳኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉም አመላክተዋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You