በአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሚሳተፈው ቡድን ዛሬ ወደ ዱዋላ ይጓዛል

በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ የሚያደርገውን ዝግጅት አጠናቆ ዛሬ ወደ ካሜሮን ያቀናል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለቡድኑ ሽኝት ያደረጉ ሲሆን፤ የስራ መመሪያና የባንዲራ ርክክብ ሥነሥርዓትም ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ 14 እስከ 19/2016 ዓ.ም በካሜሩን ዱዋላ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ሥፍራው የሚያቀና ይሆናል። ብሔራዊ ቡድኑ ለ15 ቀናት ተሰባስቦ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። ቡድኑ በሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ ከሚካሄዱት 45 የውድድር ተግባራቶች መካከል በ41ዱ ይሳተፋል። ከነገ በስቲያ በሚጀመረው ትልቁ የአህጉሪቱ የአትሌቲክስ የውድድር መድረክ 34 ሴት እና 43 ወንድ በአጠቃላይ 77 አትሌቶች፣ በ15 አሰልጣኞች እየተመሩ በውድድሩ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ፉክክርን እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

ለሁለት ሳምንታት በዝግጅት ላይ የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከትናንት በስቲያ ይፋዊ ሽኝትም ተደርጎለታል። በሽንት መረሃግብሩ ላይም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን የማበረታታትና የባንዲራ ማስረከብ ሥነሥርዓትም ተከናውኗል። የዝግጅት ጊዜው አጭር ቢሆንም ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሄዱ የጠቆሙት የቡድኑ አትሌቶችና አሠልጣኞች፤ ለቡድኑ ጥሪ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ለውድድሩ የሚያበቃ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። የዘንድሮውን ውድድር ለየት የሚያደርገው ኢትዮጵያ በሁሉም የውድድር ተግባራት የምትሳተፍ በመሆኑ በማትታወቅባቸው ውድድሮች ልምድን በመቅሰም በዓለም ቻምፒዮና የመሳተፍ እድል ሊፈጠር ስለሚችልም ነው። ፌዴሬሽኑም አስፈላጊውን እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል።

እአአ የ2022ቱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና አዘጋጅ የነበረችው የሞሪሺየሷ ሴንት ፒሬ ስትሆን፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 14 ሜዳሊያዎችን ሰብስቦ 5ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው። ዱዋላ ላይም ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተሳትፎውን ያደርጋል። በነበረው የአጭር ጊዜ ዝግጅት ሁሉም አሠልጣኞችና አትሌቶች ዝግጁና ብቁ በመሆናቸው የተሻለ ውጤትን አስመዝግበው ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። አትሌት ዘገየ ሞጋ እና አትሌት ውብእርስት አስቻለው፤ ለሀገራቸው ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከሁለት ዓመት በፊት ሞሪሺየስ በተካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና አጥጋቢ ውጤት መመዝገቡን አስታውሳ፤ በዚህ ውድድር የመዘጋጃ ጊዜው በቂ ባይሆንም የመተዋወቅና ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጻለች። ውድድሩ ኢትዮጵያ ለኦሊምፒክ እየተዘጋጀች በምትገኝበት ወቅት መሆኑ ታሪካዊና ልዩ የሚያደርገው ሲሆን፤ አሠልጣኞችና አትሌቶች በመተባበርና በመተጋገዝ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚተጉ እምነቷ መሆኑንም ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ዓመቱ በውድድሮች መብዛት ለኦሊምፒክ ኮሚቴና ለአትሌቲክስ ፌዴረሽን እጅግ ከባድና ፈታኝ እንደነበር ገልጸዋል። ይህንን በብቃት በመወጣት ብቁ አትሌቶችን እና አሠልጣኞችን መመልመል ትልቅ ጥንካሬን ይጠይቃል፤ በመሆኑም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላሳየው ብቃትና ጥንካሬ ምስጋና አቅርበዋል። ሁሉም አትሌት ህልሙ በውድድሮች ውጤትን ማምጣት እና በኦሊምፒክ መሳተፍ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ውድድሮች መነሻ ናቸው። ውድድሩ ትልቅ ጥንካሬን የሚጠይቅና ፈታኝ እንደመሆኑ፣ አትሌቶች የተለመደውን የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን በመላበስ በድል እንደሚመለሱ እምነታቸው እንደሆነም አንስተዋል። ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ተመርጦ ሀገርን መወከል ትልቅ እድል መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ መደጋገፍ እንደሚያስፈልግና ኦሊምፒክ ኮሚቴም ከጎናቸው መሆኑን ገልፀዋል። ልዩነት እንደማያስፈልግ እና ጠንክሮና ተባብሮ አንዱ የአንዱን ቀዳዳ በመሸፈን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡

ከተመሠረተ ቅርብ ጊዜ የሆነውና አትሌቶችን ለማበረታታት እንዲሁም ጥሩ ውጤት እንዲመጣ የማይናቅ ሚናን በመጫወት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ደጋፊዎች ማህበርም እንዲሁ ወደ ሥፍራው በማቅናት ቡድኑን እንደሚያበረታታ ተገልጿል። ከቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ጀምሮ ድጋፉን ሲያደርግ የቆየው ማህበሩ 20 የሚደርሱ ልዑካንን ወደ ሥፍራው ለመውሰድ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You