ለፅኑ ሀገረ መንግስት ግንባታ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም ያስፈልጋል

ውሉን መለየት በሚያስቸግር፣ እርስ በርስ በተሳሰረ እና ውስብስብ በሆነ ዓለም ውስጥ የግለሰብ እና የቡድን መብቶችን ከብሔራዊ ጥቅም ጋር አስታርቆ ለመሄድ የሚደረገው እንቅስቃሴ የፖለቲከኞችን የመምራት ችሎታ ከመፈታተኑም በላይ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት በመፍጠር የክርክር እና የንትርክ ምንጭ ከሆነ ሰነባብቷል።

የዚህ ጽሁፍ ጥቅል ሃሳብ ከግል ጥቅም ይልቅ ብሄራዊ ጥቅም መቅደም አለበት የሚለውን ለማመላከት እንጂ ለበርካታ ጊዜያት ፖለቲከኞቻችን ጋግረው ያነኮሩትን እና አኝከው የተፉትን የግል እና የቡድን መብት ላይ ማብራራያ ለመስጠት አይደለም። በእርግጥ ከግል ጥቅም ይልቅ ብሄራዊ ጥቅም መቅደም አለበት የሚለውም ሃሳብ አዲስ አይደለም፤ ለፖለቲካዊ ቲዎሪ እና ለመንግስት ስራ ምሶሶ ሆኖ የቆየ አመለካከት ነው።

እንደ ፕላቶ እና አርስቶትል እስከ ሆብስ እና ሩሶ ያሉ ዘመናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ አመንጪ ፈላስፋዎች “የሃገር ጥቅም ከግለሰብ ወይም ከቡድን ጥቅም በላይ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ የአንድ ሀገረ መንግስት ምሰሶ ወይም ማዕከላዊ መርህ መሆኑን አስቀምጠዋል። ከዚህ አመለካከት በስተጀርባ ያለው ምክንያት ግልጽና ቀጥተኛ ነው።

ብሔሮች የግለሰቦች ድምር ብቻ ሳይሆኑ የራሳቸው ግዴታዎች፣ የደህንነት መስፈርቶች እና የረጅም ጊዜ የእድገት ፍላጎቶች ያሏቸው ውስብስብ የማኅበረ ሰብ ስብስቦች መሆናቸውን ያመላክታል። በመሆኑም በየጊዜው ዓለምን እየፈተኑ ባሉት እንደ አየር ንብረት ለውጥ፣ ዓለም አቀፍ የጤና ቀውሶች እና መሰል ችግሮችን ለመቀልበስ በሚደረግ ትግል ውስጥ ሀገራት ከጠባብ ግለሰባዊ ጉዳዮች ይልቅ የጋራ ጥቅምን የማስቀደም አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተገለጠላቸው ይመስላል።

አንድ ሀገር የውጭ ወታደራዊ ወረራ፣ የሽብርተኝነት ችግር ወይም ሌሎች የሀገርን ሉአላዊነት የሚጋፉ ችግሮች ሲፈጠሩ ሀገርን ማዳን ተግባር የቅድሚያ ቅድሚያ ይሰጠዋል። በዚህ ጊዜ ከግለሰብ እና ከቡድን መብቶች ይልቅ ብሄራዊ ጥቅምን ማስከበር የግድ ነው። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩም መንግስታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃሉ። የአደጋ ጊዜ ኃይሎችን እስከመጥራት ይደርሳሉ።

ለምሳሌም እ.አ.አ 2020-2022 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት በርካታ የዓለም ሀገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን በማወጅ የግለሰቦችን እና ቡድን መብቶችን በእጅጉ የሚገፉ ጥብቅ ትዛዞችን ሲያስተላልፉ አይተናል። የእንቅስቃሴ ገደብ፤ ጭንብል የማጥለቅ እና ሌሎችም በርካታ ትዛዛት ተላልፈዋል። እነዚህ ትዛዞች “የሕዝቡን መብት የሚጥሱ” ቢሆንም እንኳን የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅ የተደረጉ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በተመሳሳይም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ወይም የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ መንግስታት ከግለሰባዊ ፍላጎቶች ይልቅ ብሄራዊ መረጋጋትን እና ማገገምን የሚያስቀድሙ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሊገደዱ ይችላሉ።

የብሔራዊ ጥቅም ቀዳሚነት በውጭ ፖሊሲያችን እና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መስኩም በግልጽ ተመላክቷል። የአንድ አገር ስትራቴጂካዊ አቋም ወይም ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ አደጋ ላይ ሲወድቅ መሪዎች ለብሔራዊ ጥቅም ሲሉ የግለሰብ ምርጫዎችን የሚሰዋ ከባድ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ሊጠየቁ ይችላሉ።

ይህ ሲባል የብሔራዊ ጥቅሞች የግለሰብ እና የቡድን መብቶችን መድፈቅ አለባቸው፤ የግለሰብ ፍላጎቶች አስፈላጊ አይደሉም ወይም መንግስታት የግለሰብ ነጻነቶችን እንደፈለጉ መሻር እና መደፍጠጥ ይችላሉ ለማለት አይደለም። ይልቁንም ቀጣይነት ያለው እድገትና ለማምጣት አጠቃላይ የሀገር ደህንነት ለማረጋገጥ የብሔራዊ ጥቅሞች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ለማስገንዘብ እና የብሔራዊ ጥቅሞች ከግለሰብ እና ከቡድን መብቶች ጋር ተጣጥመው፤ ሚዛኑን ጠብቀው መሄድ እንዳለባቸው ለማመላከት ነው።

ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም ከግለሰብ ደኅንነት ጋር የሚቃረን ሳይሆን፣ የሀገርን ደህንንት እና እድገት ዕውን ለማድረግ የሚከናወን ተግባር መሆን ይኖርበታል። የሀገሪቱን የረዥም ጊዜ የዕድገትና የልማት እቅዶች ለማሳካት ለግለሰቦች እድገት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት፣ ጤና አጠባበቅ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች እና ምኞቶቻቸውን የሚያራምዱበት ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን ለመፍጠር የብሔራዊ ጥቅሞችን ከግለሰብ እና ከቡድን መብቶች ጋር ተጣጥመው ሚዛኑን ጠብቀው መሄድ አለባቸው።

በእርግጥ በግለሰብ እና በብሔራዊ ጥቅም መካከል ያለው ትክክለኛ ሚዛን እንደየሀገሩ ልዩ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ይለያያል። ለሁሉም የሚስማማ መፍትሄ የለም። የፖሊሲ አውጪዎችም ተግዳሮት ይህንን ስስ ኩነት ሚዛናዊነት ያለማቋረጥ በመዳሰስ ለሚከሰቱ አደጋዎች እና እድሎች የግለሰብን መብትና ነፃነት በሚያስጠብቅ መልኩ ምላሽ በመስጠት የጋራ ጥቅሙንም ማስጠበቅ ነው።

ብሄራዊ ጥቅም ከግል ጥቅም ለጽኑ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሚኖረውን ፋይዳ በታሪክ መነጽር ማየት ይቻላል። የጋራ ጥቅም ለጠባብ የግልም ሆነ የቡድን አጀንዳዎች ሲታዘዝ ሊያደርሱ የሚችሉ አስከፊ መዘዞችን ከታሪክ ማየት ይቻላል። ለብሄራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሳይሰጥ ሲቀር ወይም የግለሰብና የቡድኖች ጥቅምን እና ፍላጎት ሲቀድም በመንግስታት ላይ የተከሰቱ ታሪኮችን ማንሳት እንችላለን፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሶቪየት ህብረት መበተን ምክንያቶቹን ማየት ተገቢ ነው። በታሪክ ውስጥ በርካታ የተበተኑ አገሮች ተመሳሳይ ዳይናሚክሶች የታዩባቸው ናቸው። ብሔራዊ ጥቅምን ለግለሰብ፣ ለቡድን ወይም ለርዕዮተ ዓለማዊ አጀንዳዎች መተው (ማመቻመች) የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች እንዲወድቁ አድርጓል።

በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውን የዌይማር ጀርመንን ሁኔታ እንመልከት። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት፣ አዲስ የተመሰረተችው የዌይማር ሪፐብሊክ ከጦርነት እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት እስከ ጥልቅ የፖለቲካ ክፍፍል እና የሀገር ቂም ስሜት የጎለበተበት ፈተናዎች አጋጥመዋታል። የዌይማር መንግስት ሀገሪቱን በአንድ የጋራ ሀገራዊ የመታደስ ራዕይ ላይ ከማስተሳሰር ይልቅ በእርስበርስ ሽኩቻ፣ የአስተሳሰብ ጦርነት እና ጠባብ ወገናዊ ጥቅምን በማሳደድ ሽባ አድርገዋታል።

ይህ ከግለሰብ ወይም ከቡድን አጀንዳ ይልቅ ብሔራዊ ጥቅምንና ፍላጎትን ማስቀደም አለመቻል ለአዶልፍ ሂትለር እና ለናዚ ፓርቲ መነሳት መንገዱን ጠርጓል። የዚህ ብሔራዊ ውህደት መፈራረስ ያስከተለው መዘዝ አስከፊ ነበር፣ ሃገራትን ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መርቷል፣ እልቂት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል በተጨማሪም ጀርመን ራሷ ለአደጋ ዳርጓታል።

በቅርቡ፣ እ.አ.አ በ2010ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተነሳው የአረብ ሕዝባዊ አመጽ ሌላኛው ማሳያ ነው። በበርካታ የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ህዝባዊ ተቃውሞው መጀመሪያ ላይ የተቀሰቀሰው በኢኮኖሚ እኩልነት፣ በፖለቲካ ጭቆና እና መንግስት ለሕዝቡ ፍላጎት ምላሽ አለመስጠቱ እንደ ምክንያትነት የሚነሳ ነው። ይሁን እንጂ ሁከቱ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር ትኩረቱ በስርዓት አገራዊ ችግሮችን ከመፍታት ወደ ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ ጥቅም ማስከበር፣ የአክራሪነት እንቅስቃሴዎችን ማባባስና ቀጠናውን ረዘም ላለ ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነቶች መክተት መጨረሻው ሆነ።

እንደ ሶሪያ፣ ሊቢያና የመን ባሉ አገሮች የግለሰብና ብሔራዊ ጥቅምን ማስታረቅ ባለመቻሉ ሥራ ላይ ያሉ የመንግሥት ተቋማት መውደቅ፣ የማኅበራዊ ትስስር መሸርሸር፣ በአማፂ ቡድኖች፣ በጦር አበጋዞች የተሞሉ የሥልጣን ክፍፍሎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ይሄውም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት እንዲፈናቀሉ፣ ለቁጥር የሚታክቱት ሕይወታቸው እንዲጠፋ፤ የመረጋጋት እና የማደግ ዕድሎችም በእጅጉ እንዲወድቁ አድርጓል።

እነዚህ የታሪክ ምሳሌዎች ከግለሰብ ወይም ከቡድን አጀንዳዎች ይልቅ ብሄራዊ ጥቅም ካልቀደመ ሊከተል የሚችለውን አስከፊ መዘዝ ያሳያሉ። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የጋራ ጥቅምን ለጠባብ የግል ፍላጎት ወይም ለርዕዮተ ዓለም መተው፤ የአገሪቱን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ፈታኝ አድርጎ፤ በሕዝብና በሰፊው ጂኦፖለቲካዊ ገጽታ ላይ አስከፊ መዘዝ አስከትሏል።

ከታሪክ አንደሚያስረዳን የብሔራዊ ጥቅም ቀዳሚነት ረቂቅ መርህ ብቻ ሳይሆን፤ ለማንኛውም ማህበረሰብ የረዥም ጊዜ መረጋጋት፣ ደህንነት እና ብልጽግና ሊያመጣ የሚችል ቅድመ ሁኔታ ነው። በግለሰባዊ እና በጋራ ደህንነት መካከል ያለውን ውስጣዊ ጥገኝነት በመገንዘብ እና ከግለሰብ ወይም ከጥቅማጥቅሞች ይልቅ የጋራ ጥቅም በማስቀደም የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራና ፍትሃዊ ማህበረሰብን መገንባት ያስፈልጋል፡፡

ሃሳቤንም ስጠቀልል ለማናችንም የሚበጀን ለብሔራዊ ጥቅም መስራትና በዛ ውስጥ የሚገቡንን ጥቅሞችና መብቶች ለማግኘት መጣር ነው። “እኔ እና ለእኔ” የሚሉ አመለካከቶች ሌሎችን ለበቀል እና ለጥላቻ የሚዳርግ ነው። ከተቻለ ከእኔ ይልቅ ለወንድሜ ይገባዋል! በሚል መተሳሰብ መኖር አስፈላጊ ነው። ፍትሃዊነት እና እኩልነትን (equity and equality) አስታርቆ መኖር የግድ ነው፡፡

ያንን ማድረግ ካልተቻለ እና “እኔ ብቻ ልክ ነኝ”፤ “ለኔ ብቻ ይገባል”፤ “እኔ ብቻ አውቅላችኋለሁ”፤ እጅ አውጥቶ ላልመረጣቸው ብሔር “ነጻ አወጣዋለሁ” ወይም ለምንና ለማን እንደሚታገል ሳያውቅ የሰው መብት እየነጠቀ “መብቱን አስከብርለታለሁ” የሚሉ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ እሳቤዎች ሀገርን ሊበትኑ ይችላል። ስለዚህ ወገኔ! የሰውን መብትና ጥቅምን በማክበር የራስን መብትና ጥቅም ማስከበር ይቻላል መልእክቴ ነው።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You