ከቡናው ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን !

መንግሥት ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ያላትን አቅም አሟጦ ለመጠቀም ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ግብርናው አጠቃላይ በሆነው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ካለው እና ሊኖረው ከሚችለው አስተዋጽኦ አንጻር የመንግሥት አሁናዊ ጥረቶች እንደሀገር ለጀመርነው ድህነትን በልማት የማሸነፍ ትግል እንደ ዋንኛ አቅም ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።

የግብርናው ዘርፍ ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ጉዞ ካለው ስትራቴጂክ አስተዋጽኦ አንጻር ፤ መንግሥት አሁን ላይ ግብርናውን ከማዘመን ጀምሮ ተጨማሪ ለእርሻ የሚሆን መሬት በማስፋት ምርት እና ምርታማነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት በብዙ መልኩ ውጤታማ እየሆነ ነው።

በግብርናው ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ ሀገር ያስመዘገብናቸው ስኬቶች ፤ ሀገሪቱ ከነበረችበት ፈተና አንጻር ፤ ፈተናው ሊያስከትል ይችል የነበረውን የከፋ አደጋ መሻገር የቻልንበትን ዕድል ፈጥሯል፤ ከዚህም ባለፈ ዘርፉ የቱን ያህል ሀገርን ከደህነት ወደ ብልጽግና በማሻገር ሂደት ውስጥ ትልቅ አቅም እንዳለው በተጨባጭ አመላክቷል።

ለዚህም የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማትን ጨምሮ በምግብ እህል ፤ በአትክልት እና ፍራፍሪ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ሀገርን ከፍተኛ ከሆነ የውጭ ምንዛሬ ወጪ መታደግ አስችለዋል ፤ ሀገሪቱ አጋጥሟት ከነበረው የሰላም ችግር አኳያ ከምግብ እህል አቅርቦት ጋር ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለመቀልበስ አቅም ሆነዋል።

ከዚህም ባለፈ መንግሥት የፖሊሲ ትኩረት በመስጠት ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሆነችባቸው የቡና እና የሻይ ቅጠል ልማት እየተመዘገበ ያለው ተስፋ ሰጪ ውጤት በግብርናው ዘርፍ ከሚካሄዱ ልማቶች ተጠቃሽ ነው።

በአንድ በኩል በመደበኛ የግብርና ሥራው ውስጥ በቡና እና የሻይ ቅጠል ልማት ትኩረት በመስጠት በልማቱ ተሳተፊ አርሶ አደሮች ጥራቱ የተጠበቀ ምርት በስፋት ለገበያ የሚያቀርቡበትን እድል እየፈጠረ ነው። የገበያ ትስስር እና የግብዓት አቅርቦቶችን በጊዜ የሚደርስበትን ሁኔታ እያመቻቸ ይገኛል።

በሌላ በኩል በተለይም በቡናው ዘርፍ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ ከመደበኛ የቡና ችግኝ ተከላ ባለፈ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በሚሊዮን የሚቆጠር የቡና ችግኞችን በቡና አብቃይ አካባቢዎች በመትከል ፤ ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

ቡና አምራች ገበሬዎች የልፋታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ጠንካራ ሥራም ፤ አርሶ አደሩ በተናጠልም ሆነ በማኅበራቱ አማካኝነት ምርቱን ለዓለም ገበያ የሚያቀርብበት እድል በስፋት ተፈጥሯል ። በዚህም ማኅበራትን ጨምሮ ግለሰብ አርሶ አደሮች የገበያው የተሻለ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

በዚህም እንደ ሀገር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ኤክስፖርት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ይህ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ውጤት በራሱ አበረታች ቢሆንም ፤ ሀገሪቱ ለቡና ምርት ካላት ተስማሚ አየር ፤ ተፈላጊ የቡና አይነቶች እና የቡና መገኛ ሀገር ከመሆኗ አኳያ ገና ብዙ በመሥራት ብዙ ተጠቃሚ መሆን ይገባል።

በተለይም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ በጥራት እና ብዛት አሸንፋ እንድትወጣ ፤አምራች የኅብረተሰብ ክፍል ለቡና ጥራት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚያስችል ሰፊ የግንዛቤ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ። ችግኞችን ከመትከል ጀምሮ ምርቱን በመሰብሰብ እና በማከማቸት ፤ ወደ ውጪ በመላክ ሂደት ውስጥ በምርቱ ጥራት ላይ ሊፈጠሩ ለሚችሉ ችግሮች ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

በምርቱን ወደ ውጪ በመላክ ሂደት የሚያጋጥሙ የሎጂስቲክ እና ቢሮክራቲክ ችግሮችን ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ በመቅረፍ ፤ ምርቱ በፍጥነት ወደ ገበያ የሚቀርብበትን አሠራር ከፍ ባካለ የተጠያቂነት ሥርዓት ጋር ማስፈን ያስፈልጋል።

የቡና ምርት ላይ አሴት በመጨመር ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረጉ ጥረቶችን አግባብ ባለው መንገድ ማበረታታት ፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይልን በስፋት ለማፍራት የሚደረጉ ጥረቶችም ሆኑ በቡና ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መደገፍ ፤ ለዚህ የሚሆን ሥርዓት ማበጀት ይገባል።

በተለይም ቡና አምራች በሆኑ አካባቢዎች ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለጉዳዩ ትልቁን ኃላፊነት ወስደው መንቀሳቀስ፤ ምርቱ በዓለም አቀፍ ገበያ የተሻለ ተወዳዳሪ የሚሆንበትን ጥራት ከማስጠበቅ አንስቶ፤ የተለያዩ ሀገራዊ የቡና ምርቶችን በሁለንተናዊ መልኩ በማስተዋወቅ ረገድ የሚጠበቅባቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህም ባለፈ በዘርፉ የሚከሄዱ የምርምር ውጤቶች፤ ፈጥነው ወደ ተግባር የሚሸጋገሩበትን የአሠራር ሥርዓት መፍጠር ፤ በዘርፉ ጥናት ለማካሄድ የሚፈልጉ ተመራማሪዎችን በማበረታታት እና በመደገፍ ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ሀብት ወደ ተጨባጭ ልማት መለወጥ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You