የማህጸን ጫፍ ካንሰርን የመከላከል ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

አዲስ አበባ:- የማህጸን ጫፍ ካንሰር የህብረተሰቡ የጤና ችግር እንዳይሆን የሚከናወኑ የመከላከል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ መርሃ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት ሰለሞን (ዶ/ር)፤ በ2022 ዓ.ም የማህጸን ጫፍ ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ የህብረተሰቡ የጤና ችግር እንዳይሆን እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ የሚፈጠረውን የማህጸን ጫፍ ካንሰር በሽታን ለመከላከል የልጃገረዶች ክትባት በስፋት እየተሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ሴቶች ላይ የሚከሰተውን የማህጸን ጫፍ ካንሰር ለመከላከል በተለያዩ አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አንስተዋል።

የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ስምንት ዓመታት የካንሰር ሕክምናን ከማስፋፋት አንጻር ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል። ከትልልቅ ሆስፒታሎች ጀምሮ እስከ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ድረስ ሕብረተሰቡን ያማከሉ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፕሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረውን የጨረር ህክምና በማሳደግ በአራት ማዕከላት ሕክምናው እየተሰጠ መሆኑን አስታውሰው፤ በቅርቡም አገልግሎቱ ወደሰባት ማዕከላት ከፍ እንደሚል አስታውቀዋል። የካንሰር ህክምና ባለሙያዎች ቁጥርም እያደገ መምጣቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

በመንግሥትና በጤና ተቋማት ብቻ የካንሰር ሕክምናን ማከናወን ከባድ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ሕይወት፤ እንደ ማቲዎስ ወንዱ አይነት ግብረሰናይ ማኅበራት ሊበራከቱና ሥራውን ሊያግዙ ይገባል ብለዋል።

የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ማኅበር የካንሰር ታማሚ ህፃናትና ወላጆችን በማገዝ ለሚሰራው ስኬታማ ሥራም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንዱ በቀለ በበኩላቸው፤ ልጃቸው በህጻን ማቲዎስ በካንሰር በመሞቱ ምክንያት በገጠማቸው ኀዘን የጀመሩት በጎ ሥራ መሆኑን አስታውሰው፤ በ20 ዓመት ውስጥ በርካታ የካንሰር ታማሚ ህፃናት ወላጆችን የመድኃኒት፣ የትራንስፖርትና ልዩ ልዩ ወጪዎችን በመሸፈን እንዲሁም የማረፊያ ቤት በማዘጋጀት እገዛ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ማህበር እያደረገ ያለውን መልካም ሥራ በመደገፍ ከማህበሩ ጎን የነበሩትን አመስግነው ፤ በቀጣይም ሁሉም ዜጋ የካንሰር ታማሚ ህጻናትና እና ወላጆቻቸውን እንዲደግፍ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማህበሩን በ20 ዓመታት ቆይታው ላገዙ ለጤና ሚኒስቴር፣ ለምግብ መድኃኒት ባለሥልጣን እና ሌሎች መሰል ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You