ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ከአባታቸው ከቀኝ አዝማች አበራ ደስታ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሙሉ አብርሃ በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ዞን በአክሱም ከተማ ጥር 1953 ዓ.ም ተወለዱ።
እድሜአቸው ለትምህርት እንደደረሰ አክሱም አብረሃ ወአፅብሃ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ በነበሩበት ወቅት ከነበረው አስከፊ የደርግ ስርዓት በትጥቅ ትግል በ1969 ዓ.ም ጥር ወር በህወሓት ወደ ሚመራው የትጥቅ ትግል ተቀላቀሉ።
ሜ/ጄኔራል ገዛኢ አበራ ወታደራዊ ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከ1969ዓ.ም እስከ ግንቦት 1970ዓ.ም በህወሓት 30ኛ ሻምበል በተዋጊነት፣ግንቦት ከ1970 እስከ 1971 መጨረሻ በማዕከላዊ ግንባር የኢኮኖሚ ክፍል ኃላፊ፣ ከ1972 እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ የሪጅን ሁለት የስንቅና ንብረት/ሎጅስቲክ/ ኃላፊ በመሆን ግዳጃቸውን ፈፅመዋል።
ከ1976 እስከ 1978 ዓ.ም የሰራዊት ግልጋሎት አደረጃጀት ሲፈጠር የህወሓት ሰራዊት ከተለመደው በደጀን ከመገልገል ወጥቶ ሰራዊቱ የራሱን ሎጂስቲክ ድጋፍ ሰጪ አካል ኖሮት እራሱን ችሎ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማስቻል ታስቦ ሲደራጅ በዚህ ሥራ በተመደቡበት የቅድመ ግንባር አገልግሎት ሰጪ አመራሮች አንዱ ጄኔራል ገዛኢ አበራ ነበሩ። ይህንን አዲስ አስተሳሰብና አመለካከትን መልክ በማስያዝና በመምራት ቀዳሚ ከነበሩና ድላቸውን በብቃት ከተወጡ አመራሮች አንዱ ነበሩ። ይህ አካሄድና አሰራር የሰራዊቱን የውጊያ ብቃት በመጨመር ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው።
ከ1987 እስከ 1979 ዓ.ም በተደረገው አዲስ የሰራዊት የክንፍ አደረጃጀት የክንፍ አንድ ወይም የምዕራባዊ ትግራይ ቀጣና የወታደራዊ ሎጀስቲክ ኃላፊ በመሆን እንዲሁም በ1980 ዓ.ም በማዕከል ወታደራዊ ቢሮ በተፈጠረው አዲስ አደረጃጀት የወታደራዊ ሎጂስቲክ ኃላፊ በመሆን በቅድመ ግንባር በሚደረጉ የሰራዊት ወታደራዊ ስምሪቶች ለተዋጊ ኃይልና በደጀን በሚያስፈልገው የተሟላ ማቴሪያል በማቅረብ በተለይም ሰራዊቱ በ1980 ዓ.ም ባካሄዳቸው ተከታታይ ውጊያዎች በብቃት እንዲወጡ፣ በዝግጅት ምዕራፍ ብቁ የሎጀስቲክ አቅም ዝግጅት በማድረግ፣ በውጊያ ምዕራፍ የሰራዊቱን ብቃት ድጋፍ በመስጠት፣ከውጊያም በኋላ በውጊያም የጎደሉ ማቴሪያሎችን አሟልቶ ዳግም ወደ ውጊያ በማቅረብ፣ ለቀጣይ ግዳጅ የተሟላ የትራንስፖርት አቅም ባልነበረበት ፋታ በማይሰጡ ተከታታይ የውጊያ ጫናዎችን ተቋቁመው ሰራዊቱን ደግፈው ለድል ለማብቃት በሚጠይቀው ግዳጅ የአመራር ብቃታቸውን ተወጥተዋል።
ከ1977 እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ የህወሓት ሰራዊት ይመራበት የነበረው የሰራዊት ግንባታና የውጊያዎች አቅጣጫዎች ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በሚቀመርበት ወቅት ሜ/ጄኔራል ገዛኢ ከሌሎች የክፍሉ አባላት ጋር በመሆን ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
ይህ ወታደራዊና የሳይንስ ቀመር የትጥቅ ትግሉን ለድል ያበቃ የአስተሳሰብ ቀመር ነው። እነዚህ ድምር የሎጀስቲክ ድጋፍ አሰጣጥ አካሄዶች ከየካቲት 1980 እስከ የካቲት 1981 ዓ.ም ድረስ በተደረጉ ተከታታይ ውጊያዎች በትግራይ የነበረውን የደርግ ሰራዊት ጠራርጎ በማውጣት ትግራይን ነፃ እንዲወጣ ያስቻለ ነበር።
ከግንቦት 1981 እስከ 1983 ዓ.ም የውጊያ ቀጣናዎች ሰፍተዋል በማለት የኢህአዴግ ሰራዊት ከሀይቅ ጀምሮ እስከ ሰሜን ሸዋ ፣ከደቡብ ወሎ እስከ ደቡብ ጎንደር የተዘረጋበትና የተሟላ ድጋፍ ያገኘበት ከነበረው ነባር ደጀን የራቀበት፣አዲስ አካባቢ የገባበት፣የውጊያ ድጋፍ ፍላጎት በአይነትና በመጠን የጨመረበት፣ በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ በቂ የሎጀስቲክ ድጋፍ በመስጠት ሰራዊቱ ተልዕኮውን በድል እንዲወጣ ያስቻለ ብቁ አመራር በመስጠት ሜ/ጄኔራል ገዛኢ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
ከ1983 እስከ 1985ዓ.ም ድረስ ከደርግ ስርዓት ውድቀት በኋላ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአዲስ መልክ በተደራጀበት ወቅት በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በሎጀስቲክ ዋና መምሪያ የስንቅና ንብረት መምሪያ ዋና ኃላፊ በመሆን በሙያው የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት በአዲስ መልክ በማደራጀትና በመምራት የአመራር ሚናቸው ከፍተኛ ነበር።
ከ1985 እስከ 2005 ዓ.ም የሀገር መከላከያ የሎጂስቲክ መምሪያ ዋና ኃላፊ በመሆን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሎጂስቲክ በአዲስ በተደራጀበት ጊዜ ዘመናዊ ሎጂስቲክ የሚጠይቀውን ሳይንስ የሚመራበት የፖሊሲ ሀሳቦች፣ማንዋሎች ፣ደንቦችና መመሪያዎች አዳዲስ አሰራሮችን በማውጣት ወቅቱ የሚጠይቀውን አዲስ አደረጃጀት በመፍጠርና በየደረጃው የነበሩ የሎጀስቲክ አመራሮችን በስልጠና አዳዲስ ሀሳቦችን እንዲይዙ በማብቃት ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ የሎጀስቲክ በመከላከያ እንዲገነባ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል።
ሰራዊታችን ተልእኮውን በብቃት እንዲወጣ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን የሎጀስቲክ እቅዶች በማቀድ በማዘጋጀትና በአግባቡ እንዲፈፀሙ በማድረግ ሰራዊቱ እንዳይቸገር ራሳቸውን ከሰራዊት ህይወት ኑሮ ውስጥ በማስቀመጥ ያሳዩት የነበረው እንክብካቤና ትኩረት ከፍተኛ ነው።
ሜ/ ጄኔራል ገዛኢ እምቅ የሎጀስቲክ የአመራር ብቃት ያሳዩበት ወቅት ግንቦት 1990 ዓ.ም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በተደረገው ጦርነትና በሌሎችም ውጊያዎች የሎጀስቲክ ድጋፍ አሰጣጥ የሚጠይቀውንና ከዚህ በተጨማሪ የሎጅስቲክ ድጋፍ አሰጣጥ ስልጠና ማቴሪያል በማዘጋጀት ሎጀስቲክስ አባላትን በማሰልጠንና በማብቃት አዲስ የሎጀስቲክ አስተሳሰብ ለውጥና እመርታን በማምጣት ጄኔራሉ የማይተካ የመሪነት ሚና ተጫውተዋል።
የትራንስፖርት አቅም ብቃት በመጨመር የተሰራ ሀይልን የማባዛት ጥበብ የሚሰጥ የሎጀስቲክ አመራር ብቃት እንዲሁም ሰራዊታችን የሀገራችንን ሰላም በማረጋገጥ ድንበር ተሻግሮ በአሸባሪ ኃይሎች ላይ ያካሄደውን ስኬታማ ወታደራዊ ስምሪት ብቁ የሎጀስቲክ ድጋፍ በመስጠትና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ሰራዊታችን ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጅ በብቃት እንዲወጣ ይሰጡት የነበረው የሎጀስቲክ ድጋፎች አመራር ጄኔራል መኮንኑ በሎጀስቲክ ስራ አመራር ጎልቶ የሚታይ ልዩ መለያቸው ነበር።
ሜ/ጄኔራል ገዛኢ አበራ በነበራቸው ከፍተኛ የአመራር ብቃት የኢፌዴሪ መደበኛ ሰራዊት ሲቋቋም በ1988 ዓ.ም የሙሉ ኮሎኔልነት ጀምሮ 1996 ዓ.ም የሜጀር ጄኔራልነት ማዕረግ የደረሱ ሲሆን፣ የትጥቅ ትግል ተሳትፎ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳልያ ጨምሮ የአገልግሎት ሜዳልያና ኒሻኖች ከኢፌዴሪ መንግስት ተበርክቶላቸዋል።
ሜ/ጄኔራል ገዛኢ በነበራቸው የመማርና ራስን በትምህርት የማሳደግ ፍላጎት ትምህርታቸውን በመቀጠል በ1986 ዓ.ም የሎጀስቲክስ ማኔጅመንት ከአሜሪካ ሀገር፣ 1998 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከለንደን ኦፕን ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የሎጀስቲክስ ማኔጅመንት ሁለተኛ ማስተርስ ዲግሪያቸውን በአንፊልድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ሜ/ጄኔራል ገዛኢ በሎጀስቲክስ አመራራቸው ብቻ ሳይሆን በሀገር መከላከያ ካውንስል አባል በመሆን በመከላከያ የሚፈፀሙ ሁለገብ ሥራዎችን መልክ ለማስያዝ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸው ጀነራል መኮንን ናቸው።
ጀኔራል ገዛኢ በ2005ዓ.ም በመከላከያ የመተካካት ሂደት በክብር በጡረታ ከተሰናበቱበት እስከ እለተ ህልፈታቸው ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት የተለያዩ መመሪያዎችን አዘጋጅተው በማደራጀትና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትን ዘመናዊ በማድረግ፣ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በልዩ አማካሪነት ህዝባቸውንና መንግሥታቸውን በማገልገል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ በነበረበት በአንድ የጠላት ቅጥረኛ ጥበቃ አባል በተተኮሰባቸው ጥይት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተወለዱ በ58 አመታቸው ተሰውተዋል።
ሜ/ጀኔራል ገዛኢ አበራ በህይወት ዘመናቸው ከስራ አመራራቸው፣ ከበላይ አለቆቻቸውና ከሚመሯቸው ጋር በመተሳሰብና በመደጋገፍ የተሞላ ጓዳዊ ዝምድና ነበራቸው። በአላማ ፅናታቸው፣ በጀግንነታቸው በአመራር ብቃታቸው አርአያ የሆኑ በአካባቢያቸው በስራ ባልደረቦቻቸው በትግል ጓዶቻቸው በጣም ተወዳጅና ምስጉን ነበሩ። ሜ/ጄኔራል ገዛኢ አቅማቸው በፈቀደ በችግር የሚገኙ የሰማእታትን ቤተሰቦች በአግባቡ በማገዝ ላይ ነበሩ።
ሜ/ ጄኔራል ገዛኢ ለቤተሰቦቻቸው አርአያ ፣አርቆ አሳቢ ሰው ወዳጅ ምግባረ ጨዋነትን የሚያስተምሩ በተለይም ልጆቻቸው በትምህርት በስነምግባር በሀገር ወዳድነት እንዲታነፁ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ነበሩ። ከባለቤታቸው ከታጋይ አበባ ዘሚካኤል አራት ወንድ ልጆችና አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011