ተስፋ ሰጪ ውጤት የታየበት የተማሪዎች የፈጠራ አውደርዕይ

በምርምርና በፈጠራ ሥራቸው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች የፈጠራ ሀሳባቸው መነሻ ትምህርት ቤት ስለመሆናቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ትምህርት ቤቶችም ለእነዚህ የፈጠራ ሀሳቦች ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። የእውቀት መገኛ ስፋራዎች እንደመሆናቸው መጠን ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የቀሰሙትን ትምህርት ወደ ተግባር እንዲለውጡ በማድረግ በኩልም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ተማሪዎቹ ሀሳቦቻቸው አድጎ እንዲጎለብት በማበረታታት በሳይንስና በፈጠራ የዳበረ ትውልድ መፍጠር ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያም የፈጠራና የምርምር ሥራዎችን የሚያካሂዱ ግለሰቦችን፣ ተቋማትን፣ ወዘተ. ለማበረታታቱ ተግባር በትኩረት እየተሰራ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል፡፡

በሀገሪቱ ተማሪዎች የሚሰሯቸውን የፈጠራ ሥራዎች ለማበረታታትና በመካከላቸው ጤናማ ውድድርን ለመፍጠር የሚያስችሉ አውደ ርዕዮች ይካሄዳሉ። ከእነዚህ ውድድሮች አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሚያዘጋጀው ነው። ይህ ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ስራ ውድድር አውደ ርዕይ ዘንድሮም በቅርቡ ለዘጠነኛ ጊዜ ‹‹በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ተካሂዷል።

በአውደ ርዕዩ ከከተማዋ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ በርካታ ተማሪዎች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ተማሪ በረከት በለጠ አንዱ ነው፡፡ የማርያም ጽዮን ካቶሊክ ትምህርት የ12 ክፍል ተማሪው በረከት ‹‹ሳይለንት ኤንድ ሱፐርሶኒክ ሮኬት ላውንቸር›› የተሰኘ የጦር መሳሪያ የፈጠራ ስራውን ይዞ ቀርቧል፡፡

የተማሪ በረከት የፈጠራ ሥራ አሁን ካሉት የጦር መሳሪያዎች ለየት ይላል፤ በአንድ ጊዜ ብዙ አይነት አገልግሎቶች የሚሰጥ እንደሆነ ተማሪ በረከት ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያሉት የጦር መሳሪያዎች በጦርነት ወቅት መሠረተ ልማት የሚያወዱሙ፣ የሰው ሕይወት የሚቀጥፉ እና ራሳቸውንም ለጥቃት ያጋለጡ መሆናቸውም ይገልጻል፡፡ የእሱ የፈጠራ ሥራ ግን ለየት ባለ መልኩ እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንዲቀርፍ ተደርጎ እንደተሰራ አመልክቷል፡፡

እሱ እንዳብራረው፤ መሳሪያው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተገጥሞለታል፤ የሚቆጣጠረው ሰው ሳይሆን ሰውሠራሽ አስተውሎት ነው፡፡ በተሰጠው ቅደም ተከተል መሠረት የተሰጠውን ግዳጅ መወጣት ይችላል፡፡ ይህ የሆነበት ዋንኛው ምክንያት በአንድ ጊዜ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዲሰጥ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡

ከእነዚህ ጠቀሜታዎች ውስጥ አንደኛው መሳሪያው ጦርነት ባለበት አካባቢ እንዲቀመጥ በማድረግ እኛ የፈለገንበት ቦታ ሆነን መዋጋት የምንችልበት ነው ሲልም ያብራራል፡፡ ሁለተኛው አሁን በስራ ላይ ያሉ ሁሉም የጦር መሳሪያዎች የአየር መቋወሚያ/ራዳር ሲሰተም/ ውስጥ ስለሚገቡ በቀላሉ ይመታሉ ሲልም ጠቅሶ፣ አዲሱ የፈጠራ ሥራ ግን የአየር መቋወሚያ/ራዳር ሲሰተም/ ውስጥ እንዳይገባ ተደርጎ መሰራቱን ያስረዳል፡፡

ተማሪ በረከት መሳሪያ እንዴት እንደሚሰራ ሲያብራራም ጦርነት ላይ ወታደሩ የሚወጣው የአንድ ሰው ተግባር ብቻ ነው፤ እሱም ከተመታ ይህ ተግባር ያበቃለታል ማለት ነው፡፡ ይህ ሮኬት ላውንቸር ግን ሳይታይ ተሰውሮ ፣ ድምጽ ሳይኖረው ስድስት ሰዎች ሊከውኑት የሚችሉትን ተግባር በአንድ ጊዜ መከወን ይችላል ሲል ገልጸል፡፡ በሰዎች እስከ 50 ኪሎሜትር ድረስ ያለውን ወታደራዊ ቦታን ለመቆጣጣር ከወራት በላይ የሚፈጀውን ጊዜ፣ አዲሱ መሳሪያ በአምስት ደቂቃዎች ብቻ መቆጣጠር የሚችልበት ስርአት የተገጠመለት ነው ይላል፡፡ ይህ ሮኬት ላውንቸር የተገጠመለት ሲስተም ምንም አይነት ፍንዳት አይፈጥርም ሲል አብራርቶ፣ ይህ በመሆኑም በመሠረተ ልማት ምንም አይነት አያደርስም ይላል፡፡

መሳሪያው አሁን ባለበት ሁኔታ በጦርነት ግዳጅ ላይ መሳተፍ እንደሚቻልም ተማሪ በረከት ተናግሯል። ከሚመለከተው አካል ፈቃድ በመውሰድ ለአንድ ጊዜ ሙከራ ተደርጎበት የተረጋገጠ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ይህን የፈጠራ ሥራ ለመስራት ያነሳሳው ብዙ የሕዝብ ሀብት ወጥቶባቸው እና ረጅም ጊዜ ወሰደው የተገነቡ መሠረተ ልማቶች እና ከተሞች እንደቀልድ በአንድ ጀምበር በጦርነት መጥፋት እና በጦርነቱም ብዙ ሰዎች መሞታቸው ለምን የሚል ሀሳብ በውስጡ በመጸነሱ ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን መፍትሔ ለማምጣት በሚል ወደዚህ ፈጠራ ስራ መግባቱን ይናገራል። ‹‹ጦርነት በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገር ላይ ሊከሰት ይችላል፤ ይህንንም ቀደም ብለን መከላከል የምንችልበት መንገድ ቢኖር ብዬ አስብ ስለነበር ይህን የፈጠራ ውጤት ለመስራት ችያለሁ›› ይላል፡፡

ተማሪ በረከት ‹‹ከባድ አድርገን የምንመለከታቸው ሳይንሶች እኛ ለመቅረብና ለመረዳት ከሞከርን ለማድረግ ያስችሉናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በሌሎች ሀገሮች በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ከኛ በላይ እውቀቱ ኖራቸው ሳይሆን የማወቅና የመመራመር ፍላጎታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ነው ውጤታማ የሆኑት ሲል ጠቅሶ፣ እንደ ሀገር ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች መስራት እንችላለን›› ሲል ተናግሯል፡፡

ይህ የፈጠራ ስራ በአካባቢው ከሚገኙ ቁሳቁስ በፕሮቶታይፕ ደረጃ የተሰራ መሆኑን ገልጾ፤ መሳሪያውን ለመስራት 30ሺብር ወጪ እንዳደረገበት ይናገራል። ‹‹በፕሮቶታይፕ ደረጃ የተሰራው የፈጠራ ሥራ ሙሉ አካሉን በብረት ቢቀየር አቅሙን መጨመርም እንደሚቻል አመልከቶ፣ አሁን ግን ሳይንሱን በመጠቀም ሀሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ፈጠራ መስራቱን ጠቁሟል፡፡

የፈጠራ ሥራዎች በአውደርዕይ በዚህ መልኩ እንዲቀርቡ መደረጉም ለተማሪዎች የመነሳሳት ስሜትን ይፈጥርላቸዋል ፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ሳይንሱ በሌላ አገራት ብቻ ያለ ሳይሆን ማንበብና መተርጎም ከቻልን ወደ አገራችን በማምጣት የተለያዩ ፈጠራዎች መስራት እንደምንችል የሚያሳያ ነው፡፡

ቀደም ሲል የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች በመስራቱ የማበረታቻ ሽልማት መቀበሉን የሚናገረው ተማሪ በረከት፤ በቀጣይም ለአገር ችግር መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት አላማ እንዳለው ተናግሯል፡፡

ሌሎቹ የአውደርዕዩ ተሳታፊዎች ተማሪ ዮሐንስ ሰለሞንና ሁለት ጓደኞቹ ናቸው፡፡ እነ ተማሪ ዮሀንስ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስኩል ኦፍ ኢንዲያን የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ የውሃ ብክነትን የሚከላከል ፈጠራ ነው ይዘው የቀረቡት፡፡ የፈጠራ ስራቸው በራሱ ውሃ ለክቶ የሚለቅ መሆኑን ተማሪ ዮሀንስ ይገልጻል፡፡

እነ ተማሪ ዩሐንስ እንዳብራራው፣ ይህን የፈጠራ ሥራ ስድስት ጓደኛሞች ሆነው ሀሳብ አመንጭተው የጀመሩት ቢሆንም፣ ሀሳቡን ወደ ተግባር በመለወጡ ሂደት እስከመጨረሻው የተጓዙት ግን ሦስቱ ብቻ ናቸው። ለፈጠራ ሥራቸው መነሻ የሆናቸው በየቤታቸው እና በየአካባቢያቸው ውሃ ሲቀዳ ያላግባብ እየፈሰሰና እየባከነ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡

ይህ ማሽን እየባከነ ላለው ውሃ መፍትሔ ያመጣ ነው፡፡ ማሽኑ በብዙ ቦታዎች ላይ ሊጠቅም የሚችል ሲሆን፤ በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሩ ማሽኑን ቢጠቀም ለመስኖ ልማት የሚፈልገውን ውሃ ለክቶ እንዲጠቀም ያስችላል፡፡ አርሶ አደሩ ለመስኖ ልማቱ የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ማሽኑ እንዲጠቀም ትዕዛዝ ሰጥቶ እሱ ወደ ሌላ ሥራው መሄድ ይችላል፡፡

የፈጠራ ስራው አትክልት ውሃ ለማጠጣትም ይውላል፤ ውሃውን መጥኖ በመቅዳት አትክልቱ በሚፈልገው ልክ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ ያስችላል። በጤናው ዘርፍም እንዲሁ ማሽኑ በፈሳሽ መልኩ የሚቀዱ መድሃኒቶችን በሚታዘዘው መጠን ለመያዝ፣ በላብራቶሪዎች ኬሚካሎችን ለክቶ ለመቅዳት ፣ በነዳጅ ማደያም እንዲሁ ነዳጅን በመቅዳት ሊያገለግል ይችላል ሲል ተማሪ ዩሐንስ ያስረዳል፡፡

ማሽኑ የሚያስፈልገውን ሀይልም ከባትሪ ወይም ከኤሌክትሪክ መጠቀም ይችላል፡፡ መስራቱ በፍተሻ የተረጋገጠ ሲሆን፤ አሁን አገልግሎት ላይ ማዋል ይቻላል፡፡ ከዚህ በላቀ ሁኔታ ማሻሻል ከተፈለገም ማሻሻያ ሊሰራለት ይችላል ያለው ዮሀንስ፣ ውሃን ሊያጣራ የሚችል ማሽን ለመስራት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸል፡፡

‹‹ማሽኑ በአካባቢያችን ላይ ከሚገኙ የተለያዩ ቁሳቁስ የተሰራ ነው፡፡ ለቁሶቹ መግዣም 3ሺ ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ይህ ማሽን ከጠቀሜታው አንጻር ሲታይ የወጣበት ወጪ በጣም ትንሽ ነው›› ብሏል፡፡

እነተማሪ ዩሐንስ በአውደርዕዩ ላይ ሲሳተፉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው፤ እንደዚህ አይነት አውደርዕይ መኖሩ ከሌሎች ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር የእርስበርስ ግንኙነት በመፍጠር ተሞክሮን ለመውሰድ ያስችላል፡፡

ከባህር ዛፍ የተሰራ ለመጽኃኒት የሚያገለግል ዘይት የምርምርና ፈጠራ ሥራ ይዘው የቀረቡት ተማሪ ሩቂያ ካሊድና ሁለት ጓደኞቿ ሌላኛዎቹ የአውደርዕዩ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ እነሩቂያ የፓሽን አካዳሚ የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ የፈጠራ ሥራቸውም ‹‹ከባህር ዛፍ የተሰራ ለመጽኃኒት የሚያገለግል ዘይት ሲሆን፤ ይህ የፈጠራ ሥራ በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት ወደ ተግባር በመቀየር የሰሩት ነው፡፡

ተማሪ ሩቂያ በተለምዶ የአረቄ ማውጣት (ዲስትሌሽን ፕሮስስ) ሂደት በመከተል ፈጠራውን እንደሰሩት ትናገራለች፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ ለመድኃኒትም በሚውል መልኩ በቀላል ውጪ መሰራቱንም ትገልጻለች። መጀመሪያ የነጭ ባህርዛፍ ቅጠልን ከውሃ ጋር በማፍላት ዘይቱ በተለመዶ የአረቄ አወጣጥ ሂደትን በመጠቀም እንደሚዘጋጅ ጠቁማለች፡፡

ይህን ከባህር ዛፍ የሚገኝ ዘይት በሀገር ውስጥ በቀላሉ መስራት እየተቻለ እስካሁን ከውጭ ይመጣ እንደነበር የምትገልጸው ተማሪ ሩቂያ፤ የእነሱ የፈጠራ ሥራ ዘይቱን በሀገር ውስጥ በቀላሉ መስራት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ትናገራለች፡፡ የፈጠራ ሥራው በሀገራችን እንደ ጉንፋን፣ የመገጣጠሚያ ህመም እና ቁርጥማትን የመሳሳሉ ህመሞች ሲያጋጥሙ መዳህነቱ መውሰድ በህኪሞች እንደሚመከር ጠቅሳ፤ መጽኃኒቱን ለመግዛት ደግሞ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ትናገራለች፡፡ በሀገር ውስጥ ማምረት ከተቻለ ግን በቀላሉ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ መጠቀም እንደሚቻል ጠቁማለች፡፡

‹‹ከእኛ የፈጠራ ሥራ የተማርነው ትምህርትን ወደተግባር በመለወጥ ችግር መፍታት የሚችል መሆኑን ነው፤ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ያሉ ችግሮችን በትንሽ ነገር በቀላሉ መፍታት የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ሥራዎች መስራት እንደሚቻል ነው›› ብላለች፡፡

በቀጣይ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው አካላት ካገኙ የፈጠራ ሥራውን ወደ ተግባር በመለወጥ ከባህር ዛፍ የሚሰራውን መጽኃኒት በሀገር ውስጥ በማምረት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርጉ አመላክታለች፡፡

በአውደ ርዕዩ ሦስት አይነት የፈጠራ ሥራዎች ይዞ የቀረበው ሌላኛው ተሳታፊ ተማሪ አሕመድ ጀማል ነው፡፡ ተማሪ አሕመድ የአልሁዳ ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በሦስቱ የፈጠራ ሥራዎቹ የሀገርን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ የመፍትሔ ሀሳቦች ያላቸው ቴክኖሎጂዎን ይዞ ቀርቧል፡፡

ተማሪ አሕመድ ዘመናዊ የአይነ ሥውራን ኮፊያ/ስማርት ኬፕ/፣ የልጆች ሒሳብ መማሪያ /calculator/ እና ተንጠልጣይ ባቡር የተሰኙ የፈጠራ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡

የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው ዘመናዊ የአይነሥውራን ኮፊያ /smart cape/ ነው፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ ለአይነ ሥውራን አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ፤ ከ20 እስከ25 ሜትር ርቀት ድረስ ያሉ አይነ ሥውራንን ሊጋጩ የሚችሉ ነገሮች ሲኖሩ ማስጠንቀቂያ በመደወል እንዲጠነቀቁ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ በእዚህም እንደልባቸው ያለስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ሲል አብራርቷል።

ሁለተኛው የፈጠራ ሥራ የልጆች ሒሳብ መማሪያ /calculator/ ነው፤ ይህ የፈጠራ ሥራ ልጆችና መስማት የተሳናቸው ወገኖች የሒሳብ ትምህርትን በቀላሉ እንዲማሩ ያስችላል፡፡ መስማት የተሳናቸው ወገኖችም ሂሳብን በቀላሉ እንዲማሩ ይረዳቸዋል።የፈጠራ ሥራው ጥያቄና መልስ እንዳለው ጠቅሶ፣ ለሚቀርበው ጥያቄ መልሱ ትክክል ከሆነ ትክክል መሆኑን መብራት በማብራት ያሳያል ይላል፤ መልሱ ትክክል ካልሆነ ደግሞ መብራቱ እንደማይበራ ተናግሮ፣ ተጨማሪ ሙከራዎች እንዲያደርጉ ያደርጋል ብሏል፡፡ ለልጆችም እንዲሁ ሒሳብን በራሳቸው እንዲማሩ የሚያስችል ቀላል ያለ የሂሳብ መማሪያ ዘዴ ነው ሲል አብራርቷል።

ሦስተኛው የፈጠራ ሥራ ተንጠልጣይ ባቡር ነው፡፡ የአስፓልቱን መንገድ ለተሸከርካሪዎች በመተው፣ ባቡሩ በሚሰራለት ተንጠልጣይ ሃዲድ ላይ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ የሚያስችል ፈጠራ ነው ይዞ የቀረበው፡፡

እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች በአካባቢው ከሚገኙ የወዳደቁ ነገሮች እንደሰራቸው የሚናገረው ተማሪ አሕመድ፤ ከተንጠልጣይ ባቡሩ በስተቀር ሌሎቹን የፈጠራ ሥራዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ሠርቶ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻልም ይገልጻል፡፡ በቀጣይ የተሻሻሉ እንደ ሀገር ችግር የሆኑና መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በመለየት የፈጠራ ሥራዎችን የመስራት ሀሳቡ እንዳለው ጠቁሟል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You