የኤሌክትሪክ ኃይል ልማትና ተጠቃሚነት ውጤታማነቱን ከነግለቱ

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በተለይ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል በማልማትና በመጠቀም መጠነ ሰፊ ተግባሮችን ስታከናውን ቆይታለች፤ እያከናወነችም ትገኛለች። በዚህም ውጤታማ መሆን ችላለች የሚያስኙ ስራዎችን ሰርታለች ብሎ መናገርም ይቻላል፡፡

ውጤታማነቷም አካባቢን የማይጎዱ ይልቁኑም የሚታደጉ ስራዎችን በመስራቷ ይገለጻል፡፡ አረንጓዴ ልማት ከሚጠይቃቸው መካከል የካርቦን ልቀትን የሚቀነሱ ወይም የሚያስቀሩ ስራዎችን መስራት አንዱ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን መገንባትንና ጥቅም ላይ ማዋልን ይጠይቃል፡፡

ሀገሪቱ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማትና በእዚህም ተጠቃሚ ለመሆን ስትል ያከናወነቻቸው ተግባሮች ከዚህ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎቷን የሚመልስ የኤሌክትሪክ ኃይል በተለይ ከውሃ ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ እያመነጨች ትገኛለች፡፡ በዚህ ብቻ ብዙ ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭታለች፡፡ በአባይ ግድብ፣ በጊቤ ሶስት፣ በኮይሻ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ የውሃ ኃይል ልማት ግዙፍ ስራዎች ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ልማቱ ማሳያዎች እጅግ ብዙ ቢሆኑም፣ የኃይል ማመንጫዎቹ አይነት እያመነጩት የሚገኘው የኃይል መጠን አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ከገባ ዓመታት የተቆጠሩት የጊቤ ሶስት ኤሌክትሪክ ኃይል ከአንድ ሺ 700 በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚችል ይታወቃል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብቻ ከአምስት ሺ አንድ መቶ በላይ ሜጋ ዋት ለማመንጨት እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም ወደ ስራ በገቡ ጥቂት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ብቻ ከሰባት መቶ በላይ ሜጋ ዋት ማመንጨት ተችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት ተገንብተው ወደ ስራ በገቡ ሌሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችም እንዲሁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል፡፡ ግንባታ እየተካሄደ የሚገኘው የኮይሻ ግድብም ከአባይ ግድብ ቀጥሎ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

የኃይል ልማቱ በውሃ ኃይል ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም፡፡ የንፋስ፣ የሶላርና የጂኦተርማል የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮችም ሌሎች አማራጮች ተደርገው እየተሰራባቸው ይገኛል፡፡ በተለይ በንፋስና በሶላር የኃይል አማራጮች ላይ በሰፊው እየተሰራ ነው፡፡

በአዳማ አንድና ሁለት፣ በአይሻ በንፋስ ኃይል ልማት የተሰሩ ስራዎች ሀገሪቱ ምን ያህል ለታዳሽ ኃይል ልማት ቁርጠኛ አቋም ይዛ እየሰራች መሆኗን በሚገባ ያመላክታሉ፡፡ ሌላ ትልቅ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ግንባታ መግባቱም ይታወቃል፡፡

በጸሀይ ኃይል ልማት የገጠሩን አካባቢ ሕዝብ ለመድረስ እየተከናወኑ ያሉ በርካታ ስራዎችም ሌሎች የዚህ ልማት ማሳያዎች ናቸው፡፡ በዚህ የኃይል አማራጭ በርካታ የገጠር ቀበሌዎችን መድረስ እየተቻለ ነው፡፡ ከዋናው ኃይል ማስተላለፊያ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙትን ከዋናው ግሪድ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከዚህ ብዙ ርቀት ላይ መንደሮችን ደግሞ ሚኒግሪዶችን በየአካባቢው በመገንባት ከጸሀይ ኃሀይል የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፣ በቀጣይም ከ200 በላይ ሚኒ ግሪዶች እንደሚሰሩ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡

የሶላር ኃይል ልማቱ ብርሃን እና ሌሎች አገልግሎቶችን ከመስጠት ባለፈ ለመስኖ ልማት ጭምር እንዲውል ለማድረግም እየተሰራ ነው፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ለመስኖ ውሃ ማሳቢያ አገልግሎት ላይ የዋሉ በነዳጅ የሚነሱ ጀነሬተሮችን በጸሀይ ኃይል በሚሰሩ ጀኔረተሮች መተካት ያስችላል፡፡

ከእነዚህ ለአካባቢ ተስማሚ ከሆኑ የኃይል አማራጮች የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል እያደገ የመጣውን የሕዝቡን ወይም የሀገሪቱን፣ የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል ባያገኙም የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ስራ የማያስቆም ደረጃ ወይም ኢንዱስትሪ መክፈት የማያስችል ደረጃ ሲያደርስ የማይሰማው ልማቱ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ ነው፡፡

በሀገሪቱ አንድ ወቅት ላይ በስፋት ይስተዋል የነበረው የኤሌክትሪክ ፈረቃ መቅረት በራሱ ሌላው የልማቱ ውጤታማነት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። የፈረቃ መቅረት ምርታማነትን ጨምሮታል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሕዝቡ ኑሮውን፣ አገልግሎት ሰጪዎች ስራቸውን ያለችግር እንዲያከናወኑም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለመኖር የተነሳ ማምረት የተቸገረ ወይም ከማምረት ስራው ፈጽሞ የወጣ ኢንዱስትሪ አለ ስለመባሉ አለመስማቱ በራሱ ልማቱ ምንም እንኳ ልማቱ የሚፈልገውን ያህል የአሌሌክትሪከ ኃይል ማመንጨት ወይም ማድረስ ባይቻልም፣ የኢንዱስትሪዎቹን ፍላገት በተወሰነ መልኩ እየመሰለ ስለመሆኑ ያመልክታል፡፡

ለመኖሪያ ቤቶችም ሆነ ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ በኩልም የሚታዩ እጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ግን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት በመኖሩ ሳይሆን መሰረተ ልማቱን ለመዘርጋት የሚያስፈልጉ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችና የመሳሰሉት ላይ ካለ እጥረት የመነጨ ሊሆን ይችላል ብሎ መውሰድ የሚያስችል ሁኔታ ነው በሀገሪቱ የሚስተዋለው፡፡ የማሰራጫና ማስተላለፊያ መስመሮችና ጣቢያዎች አቅም ውስንነት የሚያስከትለው ችግር ለእነዚህ ችግሮች መንስኤ ስለመሆኑ ሲገለጽም ከመቆየቱም መገንዘብ የሚቻለው ይህንኑ ነው፡፡

ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት በግድቦች፣ በንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ወይም በሶላር ኃይል ማመንጫዎች ብዛት ወይም የኃይል ማመንጫዎቹ በሚያመርቱት የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን/ ሜጋ ዋት/ ብዛት ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ በፈታው ችግር ፣ ለሀገራዊ ልማት አልፎም ተርፎ ዓለምን ከአየር ንብረት ለውጥ ለመታደግ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ጭምር መታየት ይኖርበታል፡፡

ሀገሪቱ በዚህ ልማት ተጠቃሚ መሆን በመቻል በኩል ብዙ ርቀት እየተጓዘች ትገኛለች፡፡ አያሌ በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ከማገዶ ጭስ መታደግ እየተቻለ ነው፤ ኢንዱስትሪዎች የወጪ ምርቶችን እንዲተኩ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በስፋት እንዲያመርቱ ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው፡፡

ሀገሪቱ በኢኮኖሚ እያደገች መምጣቷን ተከትሎ በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት መመለስ መቻል በራሱ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በከተሞች ሕይወት እጅግ ቀላል ማድረግ እያስቻለ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በሀገሪቱ ከተሞች ኤሌክትሪክ ለመብራት አገልግሎት ብቻ አይፈለግም፤ ፍላጎቱ ከብርሃን በላይ መሆን ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ምድጃው፣ ልብስ ማጠቢያው፣ ውሃ ማሞቂያው፣ ወዘተ ኤሌክትሪክን የግድ ይፈልጋሉ፡፡ ሕይወት ያለኤሌክትሪክ ኃይል ከባድ ሆኗል፡፡

የኤሌከትሪክን ፋይዳ የምናውቀው የጠፋ፣ የተቋረጠ እለት ነው፡፡ ቴሌቪዥን፣ ዋይፋይ፣ ወዘተ. ጭጭ ይላሉ፡፡ ሁሉም ነገር ዝም ሲል ቤቱ ሊባለን ይደርሳል፤ ሕጸናት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ይመስል እንቅስቃሴያቸው ክፉኛ ይገደባል፤ በተለይ ማታ ከሆነ ደግሞ በጊዜ ይተኛሉ፡፡ ልጆች አስቀድመው ሲተኙ ምን ያህል ቤቱ እንደሚቀዘቅዝ ማንም ሊገምተው ቢችልም ቤተሰብ ደግሞ በሚገባ ያውቀዋል፡፡

ውሃው አገልግሎት ሊያቆም ይችላል፤ የንግድ ቤቶች በብዛት ያሉበት ሰፈር ከሆነ ደግሞ አካባቢው በጀነሬተር ድምጽ ይናወጣል፤ በጭሱም ይታፈናል፡፡ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ወጪ ያለው የኃይል ምንች ምን ያህል የብክለት ምንጭ እንደሆነም ያስገነዝባል፡፡

የመንግስትም ይሁን የግል ድርጅቶች የቢሮ አገልግሎት በአጠቃላይ ኤሌክትሪክን የግድ የሚል መሆኑ ይታወቃል፤ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ ሁሉም ነገር ስንክልክል የሚልበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። ጉዳዩን ቶሎ ሊፈጸም የወጣ እንዳሰበው ሳይሆንለት ይቀራል፤ የተቋማት የእለት ተእለት ተግባር ይጓተታል፡፡ መንገዶች በጨለማ ይዋጣሉ፤ ይህ ደግሞ ለወንጀል ምቹ ሁኔታ አንዲፈጠር ያደርጋል። የመብራት መጥፋቱ ሁኔታ ሲራዘም በማቀዝቀዣ አስቀመጥኩት ያሉት ሳይቀር ለብልሽት ይዳረጋል፤ ሊጋገገሩ ያሰቡት ይበላሻል፤ እንደ ዳቦ ያለው ደግሞ ተጥዶ ከሆነና መብራቱ ለረጅም ጊዜ ከጠፋ እጣ ፈንታው መጣል ይሆናል፡፡ እናም የኤሌክትሪክ ፋይዳ የጠፋ እለት ይበልጥ ይታወቃል ማለቴ ለእዚህ ነው፡፡

ሀገሪቱ ከምታመርተው የኤሌክትሪክ የተወሰነው ለውጭ ገበያ እያቀረበች ያለችበት ሁኔታም ሌላው የልማቱ ከፍታ ማሳያ ሆኖ መጠቀስ ይኖርበታል። በእዚህ አገልግሎት የሚገኘው የውጪ ምንዛሬ እንደመሆኑ የልማቱ ከፍታ ላቅ ይላል፡፡ ለቀጣናዊ ትስስር ያለው ፋይዳም ሌላው የልማቱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ እስከ አሁን ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ተችሏል፡፡ በቀጣይ ታንዛንያ ደቡብ አፍሪካም ጭምር ታስበዋል፡፡

ሀገሪቱ ለእነዚህ ሀገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ስታቀርብ ታዳሽ ኃይል የመጠቀም አቅጣጫ እንደመከተሏ እንደ ሀገር ብቻም ሳይሆን እንደ አህጉርም አንድ ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦ እንደምታደርግ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በርካታ የኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ወደ ጎዳና በማስገባት ላይ ትገኛለች፡፡ ቆየት ያሉ መረጃዎች ያመለከቱትን ብቻ ብንጠቀስ በሀገሪቱ ከ100 ሺ በላይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ከቤት አውቶሞቢል ጀምሮ እስከ አውቶብስ ድረስ ወደ ስራ የገቡ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ የሚሰሩ ቢሆን ሀገሪቱ ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ ለእዚህ እንደሚያስፈልጋት ሲታሰብ የኤሌክትሪክ ልማቱ ፋይዳ ከፍተኛነት ነጋሪም አያሻም፡፡

በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ወደ ስራ መግባት የሚገኘው ፋይዳ ለነዳጅ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ እርግጥ ነው ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ነዳጅ ቢጠቀሙ ኖሮ በአካባቢ ላይ ሊደርስ ይችል የነበረው ብክለት ሲታሰብ ደግሞ ፋይዳው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡

የሀገሪቱ የባቡር ትራንስፖርትም የሚሰራው በኤሌክትሪክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የሚሰጠው የባቡር አገልግሎት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ መሆኑ አሁንም ለባቡር አገልግሎት የሚውል ታዳሽ ያልሆነ ኃይል ለማቅረብ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቅ እንደነበር መገመት አይከብደም፤ ባቡሮቹ ከታዳሽ ኃይል ውጪ የሚጠቀሙ ቢሆኑ ኖሮ በአካባቢ ላይ ሊደርስ ይችል የነበረው ብክለት ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ማንም ይገነዘበዋል፡፡

የኤሌክትሪከ ኃይል በተሽከርካሪም ሆነ በባቡር ትራንስፖርቱ በኩል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ልማቱ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሌላ ማሳያ ነው፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ ነዳጅ መጠቀም አካባቢን ሊበከል የሚችልበትን እድል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በታዳሽ ኃይል መተካት የተቻለበት ሁኔታ ሀገሪቱ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ካሳየችባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑም መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የኃይል ልማቱ እና ተጠቃሚነት ስኬታማነት ቱሩፋት ለዓለምም ተርፏል፡፡ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ እየተቸገረ ባለበት በዚህ ዘመን የኃይል አማራጭን ታዳሽ ለማድረግ ይህን ያህል ረጅም ርቀት መጓዝ መቻል ዓለም ይህን ችግር ለመፍታት እያከናወነ ለሚገኘው ተግባር ተጨባጭ አስተዋጽኦ ማድረግ መቻልም ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ልማቱና ተጠቃሚነቱ ስኬት የሀገሪቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላት ፍላጎት ከፍተኛ አንደሆነ ይታወቃል፤ ፍላጎቱ በቀጣይም እየጨመረ እንደሚሄድም ይጠበቃል፡፡ ፍላጎቱ አህጉራዊም ዓለም አቀፋዊም ጭምር እንደመሆኑ የኃይል ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ከእነ ግለቱ ለማስቀጠል መስራት ያስፈልጋል፤ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ፍላጎቱም ይህን የግድ ይላሉና፡፡

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You