በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮች ሀገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ከሚገኙ ተግዳሮቶች አንዱ ነው። ችግሩን ለመፍታት በየወቅቱ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ፤ እየተባባሰ ከመሄድ ሊያቆመው የሚችል የመፍትሄ እርምጃ አስካሁን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። በዚህም ዜጎች ላልተገባ መጉላላት እየተዳረጉ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው።
ችግሩ በከተሞች አካባቢ አጠቃላይ በሆነው የከተማ ነዋሪ የእለት ተእለት የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ መሠረታው የሚባል ፈተና መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል። ለተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ከቤት ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በተግዳሮት የተሞሉ አድርጓቸዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ ያለው የችግሩ አሳሳቢነት ፈጣን ስትራቴጂክ መፍትሄ ካልተገኘለት ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ የሚችልበት አጋጣሚ ሠፊ ነው። ለዚህ ደግሞ በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰአት የሚታየው የትራንስፖርት ፈላጊዎች መጉላላት የችግሩ ደረጃ ምን ያህል እንደደረሰ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በከተማዋ በየጊዜው እያሻቀበ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥር ፤ ከከተማዋ መስፋት ፤ በከተማዋ ካለው የመንገድ መሠረተልማት ውስንነት ጋር ተያይዞ ከተፈጠረው ፍላጎት ጋር የማይጣጣመው የትራንስፖርት አቅርቦት ለችግሩ በዋንኛነት እንደ ምክንያት የሚጠቀስ ነው ።
ከዚህ ጎን ለጎን በትራንስፖርት ዘርፉ ያለው ሥርዓተ አልበኝነት ሀይባይ ማጣቱ ፤ ራሱ የትራንስፖርት ሥርዓቱ ችግሩን መሻገር የሚያስችል አቅም ማጣቱ በዘርፉ ለሚታየው ችግር መባባስ ተጨማሪ ምክንያት ስለመሆኑም ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህ ደግሞ በጠራራ ጸሀይ በማን አለብንነት በዘርፉ የሚከናወኑ ሕገወጥነቶች ማሳያ ናቸው።
ከተፈቀደ የሰው ቁጥር በላይ መጫን ፤ ከተተመነ የጉዞ ሂሳብ በላይ ማስከፈል ፤ የስምሪት መስመርን አክብሮ አለመሥራት ፤ በሥራ ሰአት መኪና አቁሞ ሥራ መግቢያና መውጪያ ሰአታትን መጠበቅ ፤ ለሕዝብ አገልግሎት በማይመጥኑ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት .. ወዘተ በዘርፉ የሚስተዋሉ ዛሬ ድረስ መፍትሄ ያጡ ችግሮች ናቸው።
ችግሩን ለመፍታት ዘርፉን በከተማ ሆነ በፌዴራል ደረጃ የሚመሩ አካላት አውቶቡሶችን ከመግዛት ጀምሮ ብዙ ሰው የመጫን አቅም ያላቸውን ተሽከርካሪዎች ፤ ከስምሪት ውጪ የሆኑ የሀገር አቋራጭ ተሽከርካሬዎችን ወደ ስምሪት በማስገባት ፣ የትራንስፖርት ሥርዓቱን በጠንካራ ቁጥጥር መስመር ለማስያዝ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ይህም ሆኖ ግን ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት አልተቻለም ።
ችግሩ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ከፈጠረው መልከ ብዙ ፈተና የተነሳ ፤ ለሠራተኛው በሥራ መግቢያና መውጪ ሰአታት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በመመደብ ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት ተሞክሯል፡፡
ከችግሩ ግዝፈት አኳያ በተለመደ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት የአንድ ወቅት የዘመቻ ሥራ ከመሆን ባለፈ የተለየ ነገር ያመጣል ተብሎ አይታሰብም። ለችግሩ ካለው ሀገራዊ እይታ አንጻርም ያልተሞከረ የመፍትሄ አማራጭ አለብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም።
አሁን ላይ ለችግሩ ተጨባጭ መፍትሄ ለማፈላለግ ከአዲስ እይታ የሚመነጭ አዲስ ስትራቴጂክ የመፍትሄ ሃሳብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከመጣንበት የችግር አፈታት እሳቤ ወጥተን ማሰብ ያስፈልገናል። ከተለመደው መንገድ ወጥተን ለመሄድ መድፈርን ይጠይቀናል።
ለዚህ ደግሞ የዘርፉ ተዋንያንን እና ባለሙያዎችንና ከፍተኛ የምርምር ተቋማትን ያሳተፈ ሰፊ የመፍትሄ ማፈላላጊያ መድረኮችን ማዘጋጀት ፣ የውጭ ሀገር የተሳኩ ተሞክሮዎችን በመቀመር የሀገርን አቅም ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ በጠንካራ ዲሲፕሊን ተግባራዊ የሚሆንበትን አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል።
ወቅቱ እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግና ለማስፈን መሠረት የምንጥልበት ከመሆኑ አንጻር ፣ ለችግሩ የምናስቀምጣቸው የመፍትሄ ሃሳቦች በቀጣይ ለዘርፉ ዕድገት ዘላቂ መሠረት መሆን የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል። በችግሩ ዙሪያ ቆም ብለን ብዙ አስበን እና አሰላስለን ፣ተመራምረን ተግባራዊ የምናደርጋቸውም ሊሆኑ ይገባል ።
ከለውጥ መሠረታዊ አስተሳሰብ ተነስተን ችግሩን በመመርመር ፣ ከትናንት እስከ ዛሬ ለችግሩ የተሰጡ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማጤን፣ አሁን ባለበትን ግዝፈት ፣ ነገ ሊኖረው የሚችለውን ተጨማሪ አቅም በአግባቡ በመረዳት ለችግሩ አዲስ ስትራቴጂክ የመፍትሄ እይታ ልናበጅለት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም