ዲዛይነር ገባይል አሰግድ ትባላለች:: የ‹‹ ገባይል ፎር ኦል›› ብራንድ መስራች ናት:: ‹‹ገባይል›› ማለት ሕዝባዊት፤ ለብዙ የሆነች የሚል ትርጓሜ እንዳለው ጠቅሳ፣ ‹‹ገባይል ለሁሉም›› የሚል ስያሜን ሰጥታ የባህል አልባሳትን ዲዛይን በማድረግ ታመርታለች:: በዚህም አልባሳቱን ለሁሉም አልያም ለብዙዎች ማድረስ የሚል እሳቤን ይዛ እየሠራች ትገኛለች::
ዲዛይነር ገባይል ሥራዎቿን ‹‹ቀለል ያለ ነገር ግን ውብ እና ግርማ ሞገስ የሚያላብስ ›› በማለት ትገልጸዋለች :: በሥራዎቿ የሀበሻ ልብስን እንደ ዋና ግብዓት ትጠቀማለች:: ‹‹ ለሀገር ባህል ልብስ በጣም ቅርብ ነኝ፤ ነገር ግን የሀበሻ ልብስ በበዓላት ብቻ ይለበሳል በሚለው ሃሳብ አልስማማም›› ትላለች::
በተለምዶ እነዚህ የባህል ልብሶች ሲሠሩ አንድን በዓል አልያም ሁነት ተመርኩዘው ነው:: ‹‹ገባይል ለሁሉም›› ግን የሀበሻ ልብስን ማንኛውም ሰው በፈለገው ቀን፣ የሥራ ቦታ ፣ መዝናኛ ላይ በነጻነት እንዲለብሰው አድርጋ በማዘጋጀት ለገበያ ታቀርባለች ::
ገባይል ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በሜካኒካል ምህንድስና ቢሆንም፣ ከልጅነቷ አንስቶም ዲዛይነር የመሆን ፍላጎቷ እንደነበራት ትናገራለች:: የመጣሁበት ቤተሰብ ለፋሽን ቅርብ ነው የምትለው ዲዛይነሯ፣ እናቷ በቤት ውስጥ ሹራቦችን በመሥራት ፣ አያቷ እንዲሁ በቤታቸው ውስጥ ባላቸው መስፊያ ማሽን ለልጆቻቸው ልብሶችን ይሠሩ እንደነበር ትገልጻለች::
‹‹እናቴ ትምህርቴን እንዳልተው በማሰብ ፋሽን ትምህርት ቤት ገብቼ እንድማር አትፈቅድልኝም ነበር›› የምትለው ገባይል፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችበት የናዝሬት ትምህርት ቤት የእጅ ሥራ ክፍለጊዜ የነበረው መሆኑ ገባይልን ይበልጥ ወደ ፋሽኑ እንድትሳብ እና ፋሽን ትምህርት ቤት ገብታ ለመማር ፍላጎት እንዲያድርባት አድርጓል::
ለፋሽን ያላት ፍላጎት ልጅ ሆና የሚገዙላትን አሻንጉሊቶች ልብስ እንድትቀይር፣ እያደገች ስትመጣ ደግሞ የራሷን ልብሶች እንደሚመቻቸት አድርጋ ዲዛይን እንድታደርግ ይገፋፋት እንደነበር ታስታውሳለች:: የአራተኛ ዓመት የሜካኒካል ምህንድስና ተማሪ ሳለች በታላቅ ወንድሟ አማካኝነት የመማር እድሉን አግኝታ ለአንድ ዓመት የፋሽን ዲዛይን ትምህርትን ተከታትላለች :: ይሄው ወንድሟ የልብስ መስፊያ ማሽን ገዝቶላት በቅርቧ ላሉ ሰዎች ልብሶችን መሥራት መጀመሯን ታብራራለች::
ገባይል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው ሙሉ በሙሉ ትኩረቷን አደረገች :: በዚህም በሥራዎቿ ራሷን የምትገልጽበትን መንገድ ለመፈለግ ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም :: ሥራዎቿን ለማሳደግ በራሷ መንገድ እየተንቀሳቀሰች ባለችበት አፍሪካን ሞዛይክ የተሰኘ በየዓመቱ ለዲዛይነሮች የሚዘጋጅ ሥልጠና ላይ የመሳተፍ እድል አገኘች ::
ለአንድ ዓመት በቆየው ሥልጠና ማብቂያ ዲዛይነሮች የራሳቸውን ሃሳብና እይታ የሚገልጹበት ስብስብ ይዘው መቅረብ ይገባቸው ነበር:: ሥራዎቿ ለብዙዎች እንዲደርሱ ያደረገው ሁነት የተፈጠረውም በዚህ ሰዓት ነው ::
በዚህ ስብስብ ማስተላለፍ የፈለገችው ስለ አዕምሮ ጤና ነበር :: ‹‹ከዚህ ቀደም ስለ አዕምሮ ጤና ያለኝ አመለካከት ከመንፈሳዊ ነገር ጋር የተገናኘ ነበር፣ ነገር ግን በዙሪያዬ ድባቴ ውስጥ የገቡ ፣ በተለያየ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚሉትን በጣም መስማት ጀመርኩ›› የምትለው ገባይል፣ በዚህ ሥራዋ አዕምሮም ልክ እንደሌላው የሰውነት ክፍላችን ይታመማል፤ ይታከማል በሚል ‹‹ከድባቴ ጀርባ ያሉ ውብ ልቦች›› በሚል የዲዛይን ሥራዎቿን ይዛ መቅረቧን ትናገራለች::
ይህ ስብስብ ገባይል አባቷን በሕይወት በማጣቷ ምክንያት በአንድ ወቅት የተፈጠረባት ድባቴ በሌሎች ላይ እንዳለ በማሰብ የአዕምሮ ጤና እክል ያጋጠመው ሰው አይድንም ወደ ቀድሞው አይመለስም ማለት ትክክል እንዳልሆነ እና ሰዎች በአዕምሮ ጤናቸው ምክንያት መፈረጅ የለባቸውም የሚል መልዕክትን ያስተላለፈ ነበር ስትልም ታብራራለች::
ሥራዎቿን በጀርመን በተዘጋጀ የበርሊን የፋሽን ሳምንት ‹‹ ኒዮ የፋሽን መድረክ ›› ላይ አቀረበች:: መድረኩ በስፋት እውቅና እንድታገኝ አደረጋት፤ የአዕምሮ ጤናን በአልባሳት በኩል የገለጸችበት መንገድ በዓለምአቀፍ ደረጃ በሚታወቁት የበርሊንና እንግሊዝ ሀገር ጋዜጦች ላይም ለመውጣት ችላለች ::
ገባይል ሥራዎቿን ለማስተዋወቅ ማህበራዊ ገጾችን ትጠቀማለች:: የምትሠራውም በቤቷ ሆና ነው :: የፋሽን ዲዛይን መነሻዋ ከቤተሰብ እንደሆነ የምትገልጸው ገባይል፣ ‹‹እማዬ የወረደች ቀሚስ›› በሚል በአያቷ ስም የሠራችውን ስብስብ ለደንበኞቿ ማስተዋወቋንም ትናገራለች::
‹‹አያቴ በድሮው ጊዜ በተለያዩ ጌጣጌጦች የምታስጌጠው ልብስ ነበራት :: በጊዜው ጥሩ ኢኮኖሚ ላይ ያሉ ሴቶች በወርቅም ጭምር የተጌጡ ልብሶች ነበሯቸው::›› ስትል ጠቅሳ፣ ከዚህ በመነሳት በሸማኔ በተሠራው የፈትል ጨርቅ ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ እንስቶች በአንገታቸው፣ በእጃቸው ላይ የሚያደርጓቸውን ማጌጫዎች በማከል ልብሱ የተለየ ውበት እንዲሰጥ አድርጋ እንደምትሠራው ታብራራለች:: ጌጣጌጦቹን ከአክሱም ፣ ከላሊበላ እንደምታገኛቸው ተናግራ፣ ራሷ በምትፈልገው መንገድ ዲዛይን በማድረግ ጌጣጌጦቹን በልብሶቹ ላይ እንደምትጠቀምባቸው አመልክታለች::
የምትሠራው ልብስ በአብዛኛው የሰውነት ቅርጽን አይከተልም:: ወገብ ላይ እንደመቀነት የሚታሰሩ ጌጦች ስላሉት፣ እንስቶች ሲያሻቸው ለቀቅ ባለ መልኩ ቀለል ላለ ፕሮግራም እንዲሁም መቀነቱን አድርገው ደግሞ ለትልቅ ሁነት መጠቀም የሚችሉት ነው ::
እነዚህን አይነት ልብሶችን ገባይል ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ ለገበያ ታቀርባቸዋለች:: ‹‹በአብዛኛው የምንሠራው ለሴቶች ነው:: የወንዶች ግን በትእዛዝ ካልሆነ ገጥሞን አያውቅም›› ትላለች::
ልብሶቹን አይቶ የሚወዳቸው፣ ቀለል ያለ ልብስ መልበስ የሚፈልግ ሰው እንዳለ ሁሉ የሀበሻ ልብስ መሆኑን የሚጠራጠርም እንዳለ ትገለጻለች:: እኔ ግን ሥሰራው ራሴ የምወደውን ስለሆነ እንደኔ አይነት የልብስ ዲዛይን አማራጭ ላላቸው ሰዎች እሠራለሁ::›› በማለት ሥራዎቿን ትገልጻቸዋለች ::
ገባይል ምርቶቿን በተለያዩ ሰዎች መጠን ሰርታ በማዘጋጀት ሰዎች መጥተው የሚበቃቸውን ልብስ ለክተው ይዘው የሚሄዱበትን መንገድ መፍጠር ፣ ቅርንጫፎችን መክፈት እና ሥሯዎቿ ከኢትዮጵያ ውጪ እንዲገኙ ማድረግ የወደፊት ህልሟ ነው :: በአሁኑ ወቅትም ሶስት ሠራተኞችን ይዛ እየሠራች ትገኛለች ::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም