‹‹ጆርናል ለችግር ፈቺ ጥናታዊ ሥራዎች ፋይዳው የጎላ ነው›› -ዶ/ር ሠራዊት ሀንዲሶ

ጆርናል የህትመት ውጤት ነው። እንደማንኛውም መረጃ ማቀበያ መሣሪያዎች ጆርናልም መረጃ አቀባይ፤ ሰጪ መሣሪያ ነው። እንደማንኛውም ሰው ሰራሽ ምርት ጆርናልና ኮንቴንቱ (ይዘቱ)ም ሰው ሰራሽ፣ በሰው ልጅ የሚመረቱ ናቸው። ይሁን እንጂ፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤ ከሰው መርጦ ለሹመት እንደሚባለው፣ ጆርናልም ስክሪፕቶ ያለው ሁሉ ጣቱን የሚቀስርበት የሰነፎች መናኸሪያ ሳይሆን ለበቃ አእምሮ፣ ለላቁ ባለሙያዎች፣ ሊቃውንት የተመደበ የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ሥፍራ ነው።

ጆርናል፣ እንደ ዛሬው እንግዳችን ዶ/ር ሠራዊት አተያይ ችግር ፈቺ፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚቀርብ፣ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች፣ ስለ ሕይወት፣ ስለ ትምህርት ጥያቄዎች የሚነሱበትና ለሰው ልጅ ጥያቄ ተገቢው መልስ የሚሰጥበት፤ “ሳይንሳዊ የምርምር ጆርናል” ብለን የምንጠራው ሲሆን፤ ለሌላው ዓለም ሁሉ የሚተርፉ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት የምርምር መጽሔት ወይም ሰነድ ነው።

ጆርናል ከተለያዩና አዳዲስ አተያዮች፣ ንድፈ-ሃሳቦችና ሥነ-ዘዴዎች፣ አኳያ ለተቃኙ የፈጠራ ሃሳቦች እና/ወይም የምርምር ሥራዎች (innovative researches) ቅድሚያና ልዩ ትኩረትን የሚሰጥ ሲሆን፤ ተመራማሪዎቹም ከመጽሔቱ ባልተናነሰ ለእነዚህ ጉዳዮች ልዩ ትኩረትን መስጠት ይጠበቅባቸዋል የሚለው ሚዛን የደፋ አስተያየት ነው።

ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ጆርናሎች የተመለከትን እንደ ሆነ የእስካሁኖቹ በተቃራኒው ሆነው ነው የምናገኛቸው።

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ስርፀት ዴስክ ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሠራዊት ሀንዲሶ እንደሚሉት ምንም እንኳን ከ1962 ዓ•ም ጀምሮ በሀገራችን “የምርምር መጽሔት” በሚል ስያሜ የሚታወቁ ጆርናሎች ይዘጋጁ የነበሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ሰነዶች ቢኖሩም፤ በተለይ ባለፉት 20 ዓመታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስፋፋት ቢታይም ከተደራሽነትና ተሳትፎ አኳያ ጥሩ ሲሆን፤ ጥራት ላይ ግን ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል። ያ የጥራት ችግርም እስከ ጆርናሎቹ ጥራት መጉደል ድረስ መጥቷል። በመሆኑም ጆርናሎቹ ከጥራት፣ ሳይንሳዊነት (ከይዘትም ሆነ አቀራረብ) የጎደላቸው፣ የማህበረሰቡን ችግሮች ከመፍታት፣ ከተወዳዳሪነት አንፃር ሲታዩ ከፍተኛ ችግር ያለባቸው ሆነው ነው የሚገኙት። ያ ማለት ደግሞ ለእውቀት የምናደርገውን አስተዋፅኦ አናሳ ያደርገዋል። እውቀት የማምረት አቅማችንን ያወርደዋል ማለት ነው። የተመረተውንም ካየነው ጥራት ያለው አይደለም። ከመደርደሪያ ላይ ወርዶ ሊነበብ የሚችል አይደለም።

ሃላፊው እንደሚሉት በእንጭጭ ደረጃ ላይ የሚገኙት ጆርናሎቻችን በተለይ ዓለም አቀፍ አተያይ ላይ ከፍተኛ ችግር ነው ያለባቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ጥናት ይዘው የሚቀርቡ አይደሉም። በመሆኑም፣ ተቀባይነታቸው እስከዚህም ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደረጃ ያወጣል፤ ያን ጊዜ የኛዎቹ ከተወዳዳሪነት ውጪ ነው የሚሆኑት። በመሆኑም በዓለም አቀፍ የፈጠራ ሥራዎች መጠቆሚያ (Global Innovation Index) ላይ ስር ሆነን እንገኛለን ማለት ነው።

ትምህርት ሚኒስቴር ጥራትን ለማስበቅ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መመሪያ አውጥቶ በመሥራቱ በተወሰነ ደረጃ ለውጥ እየታየ፤ መሻሻል እየመጣ ይገኛል ያሉት ዶክተሩ፣ በአሁኑ ሰዓትም 8 ጆርናሎች ዓለም አቀፍ ደረጃን ተቀላቅለው በ “Inter­national Scientific Indexing (ISI)” ዳታ ቤዝ ውስጥ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ይህ ማለት ግን እነዚህ ጆርናሎች ጥራት፣ ተከታታይነት፣ ወቅታዊነታቸውን እየጠበቁ ካልሄዱ ከዛ ደረጃ እንደሚወጡም መታወቅ ያለበት መሆኑን አስረድተዋል።

መመዘናቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ሠራዊት አንድ እውቅና ለሶስት ዓመት እንደሚቆይና በአራተኛው ለዳግም እውቅና እንደገና እንደሚወዳደር፤ ለዚህም መረጃዎቹን ሁሉ ይዞ እንደሚቀርብ ይናገራሉ። እውቅናው ሶስት ዓመት እንዲሆን የተደረገበትን ምክንያትም “ለማበረታታት” መሆኑንና ሌላው ዓለም ግን በወራት ሁሉ እንደ ሆነ ያስረዳሉ።

ትምህርት ሚኒስቴር በጆርናሎች ብዛት (አንድ ተቋም 10 እና 15 ጆርናሎች ስላሳተመ፤ ወይም በተለያዩ የትምህርት አይነቶች የተበጣጠሰና የተዋቀረ ጆርናል) ችግር ይፈታል ብሎ አያምንም። ትምህርት ሚኒስቴር ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ዓለም አቀፍ እይታ ያላቸው፤ ሳይንሳዊ የሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን ሊመረጡ የሚችሉ ጆርናሎችን ነው የሚያበረታታው። በመሆኑም፣ ከማብዛት ይልቅ ባሉትና በተወሰኑት ላይ በሚገባ መሥራትን ያበረታታልም ነው የሚሉት ሃላፊው።

ጆርናሎች የተለያዩ አካላትን ሊያስተናግዱ እንደሚችሉና ሊሆንም እንደሚገባ መመሪያው “ዳይቨርሲቲ” ብሎ ያስቀመጠ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ሠራዊት ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያለ ተመራማሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጆርናል ላይ ሊያሳትም እንደሚችል፤ የግድ እሱ በሚያጠናው መስክ እዛ ጆርናል መኖር እንደሌለበት ይናገራሉ።

ወጣት ምሁራንን በተመለከተም ጆርናል በከፍተኛ ደረጃ ጠቃሚ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሠራዊት ወጣት ምሁራን፣ እጩ ዶክተሮች ጥናቶቻቸውን ታዋቂ ጆርናሎች (ከጥራት፣ ተወዳዳሪነት፣ ተደራሽነት አኳያ) ላይ ቢያሳትሙ እነሱም፣ ሀገርም፣ ዓለምም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይናገራሉ። ተቋማቸውም ይህንን እንደሚያበረታታ አስታውቀዋል።

ይህንን መሠረት ባደረገ መልኩ በሀገራችን እውቅናን አግኝተው ለህትመት እየበቁ ያሉና በቅተው የነበሩ በርካቶች ሲሆኑ፤ በ2016 እውቅና ከተሰጣቸው 17 የምርምር ጆርናሎች መካከል በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የሚታተመው፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲው EJBME (Ethiopian Journal of Business Management and Economics) ይገኝበታል፤ በአጠቃላይም ዩኒቨርሲቲው አራት ጆርናሎች አሉት።

“ከእነዚህ ጆርናሎች በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ Disability, CBR and Inclusive Development Journal (DCIDJ) እና Ethiopian Journal of Natural and Computation­al Sciences (EJNCS) የሚባሉ የምርምር ጆርናሎችን በማሳተም ለእውቀት ሽግግር፣ ለሳይንሳዊ ምርምሮች ስርጭት እና ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።” የሚለውንና ስለዩኒቨርሲቲው የተነገረን እውነት እዚሁ ላይ ጠቅሶ ማለፍ ተገቢ ይሆናል።

ይኸው ዩኒቨርሲቲ ለምርምር ጆርናል ለየት ያለ ትኩረትን የሚሰጥ ሲሆን፣ የዚህ ማሳያው ደግሞ በየአመቱ የምርምር ሳምንትን ማክበሩና በዩኒቨርሲቲው ጆርናል ህትመቶች ላይ ውይይት ማድረጉ፤ እንዲሁም፣ “ናይል የኢትዮጵያ ህዳሴ ጆርናል’’ ን በመሳሰሉት ላይ መነጋገሩ ነው። ይህ አይነቱ የምርምር ባህል በሌሎች የትምህርት ተቋማት ይኑር ወይም አይኑር ለጊዜው ማወቅ ባይቻልም፣ ይኖራል ብለን በማሰብ ልናልፈው እንችላለን።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲዎቹ “Hawassa Journal of Law”፣ Ethiopian Journal of Education Stud­ies እና “Journal of Science and Development” ጆርናሎች የሚጠበቅባቸውን ዝቅተኛ የግምገማ መስፈርት በማሟላት እውቅናውን ያገኙ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቆ የነበረ መሆኑም የሚታወስ ነው።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚያሳትመውና ትኩረቱን በፋይናንስ፣ ቢዝነስ፣ ኢኮኖሚክስ እና ልማት መስኮች ላይ ያደረገው፣ የፖሊሲ እና ችግር ፈቺ ምርምሮች የሚቀርቡበት ነው የተባለው African Journal of Eco­nomics and Business Research ጆርናል በአፍሪካ ጆርናሎች ኦንላይን (AJOL) ድረ-ገጽ (https://www.ajol.info/index.php/ajebr) ላይ መካተቱን ዩኒቨርሲቲው ከለቀቃቸው መረጃዎች ማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የጆርናሉን ተደራሽነትንና ተነባቢነትን የበለጠ እንዲጨምር እንዳደረገው ከዩኒቨርሲቲው የወጡ መረጃዎች ይገልፃሉ።

በሦስተኛ ዙር ለሶስት ዓመት የሚቆይ ዕውቅና ከተሰጣቸው 15 የሀገር ውስጥ የምርምር ጆርናሎች አንዱ የሆነውና በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚዘጋጀው East Afri­can Journal of Veterinary and Animal Sciences ጆርናልም አንዱና ተጠቃሽ የሀገራችን ጆርናል ሲሆን፤ የጅማ ዩኒቨርሲቲው፣ በእንግሊዝኛ እና በአፋን ኦሮሞ የሚታተመው Gadaa ጆርናልም ተመሳሳይ ነው።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ “በትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ ምርምር ለሚሠሩ ተመራማሪዎች እንዲሁም ለትምህርት ዘርፍ ማህበረሰብ ትልቅ ፋይዳ” ይኖረዋል በሚል እሳቤ መነሻነት “ኮተቤ የትምህርት ጆርናል” (KOTEBE JOURNAL OF EDUCATION, KJE) ያዘጋጀውን የመጀመሪያ ህትመት ማስመረቁን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) መግለፃቸው፤ በዚሁ ህትመት “ተቀባይነት ያገኙ ስድስት ጥናታዊ ፅሑፎች መካታቸውን” የጆርናሉ ዋና አርታኢ ሩቂያ ሀሰን (ዶ/ር) መግለፃቸው ይታወቃል።

በሦስተኛው ዙር ዕውቅና ከተሰጣቸው 15 የሀገር ውስጥ የምርምር ጆርናሎች አንዱ የሆነው፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲው Ethiopian Journal of Environment and Development EJED፤ ለሦስት ዓመት የሚቆይ ዕውቅናን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘው፣ የሰመራ ዩኒቨርሲቲው Daagu International Journal of Basic and Applied Research ወዘተ ጆርናሎችም እንዲሁ ተገቢውን ፈተና አልፈው እዚህ የደረሱ፤ ወደ ፊትም እየተሻሻሉ፣ ጥራትና ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ እያደረጉ ለታሪካዊነት ይበቃሉ ተብለው የሚታሰቡ ናቸው። እንደ ዶክተር ሠራዊት አስተያየትም ይህ ይሆን ዘንድ ነው ምዘናና እውቅናው በየሶስት ዓመቱ ያስፈለገው።

ለማሳያ ያህል እነዚህን እንጥቀስ እንጂ እንደ ሀገር ካየነው ጉዳዩ ደረት የሚያስነፋ አይደለም።

በአፍሪካ ደረጃ 7ኛ መሆናችእንን የገለፁት ዶክተር ሠራዊት እንዳጫወቱን ከሆነ የሀገራችን ጆርናሎች ከጥራትና ተወዳዳሪነት አኳያ ይቀራቸዋል። ትምህርት ሚኒስቴርም ጆርናልን በተመለከተ በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ጥራትን ማስጠበቅ እንደ መሆኑ መጠን በጥራት ላይ ምንም አይነት ድርድር የለም።

ዶክተር ሠራዊት እንደሚሉት ከሆነ በእውቅናውም ሆነ የምርምር ሥራዎች ሲገመገሙ የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል። ማንም ገምጋሚ ወይም ፈታሽ እሱ የተመረቀበትን ተቋም አያይም። ለጆርናሉ ጥራት ትኩረቱ እዛ ድረስ ሁሉ ይሄዳል።

በፍተሻና እውቅና አሰጣጥ መመሪያ (Amended Guideline for Evaluation of Journals Published in Ethiopia No.: Research 01/2019) መሠረት ለሀገር ውስጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ለምርምር ተቋማት እና ሙያ ማህበራት ጆርናል የማሳተምና ማስተዳደር ፍቃድ የሚሰጠው፣ በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምር እና ስርጸት ዴስክ ኃላፊ ዶ/ር ሠራዊት ሀንዲሶ እንዳሉት ጆርናል ከተመራማሪው በርካታ ቁም ነገሮችን የሚሻ ሲሆን፤ ከሙያና ሥነምግባር አኳያም ኢዲቶሪያል ፖሊሲ፣ ዋና አዘጋጅ፣ መምሪያ (Guideline)፤ አማካሪ ቦርድ፣ እና ሌሎችም በሃላፊነት ይመሩታል። ፈቃድና እውቅና ሲሰጥም እነዚህ ግዴታዎች ናቸው።

ሚኒስቴሩ በሀገር ውስጥ የሚታተሙ የምርምር ጆርናሎችን ጥራት ለማሳደግ በማሰብ በዘረጋው የምዘና እና እውቅና አሠራር ሥርዓት መሠረት የሀገር ውስጥ የምርምር ጆርናል አርታኢዎች እና አሳታሚዎች የምንተፋና ዘረፋ (Plagiarism) ችግር እንዳይከሰትና “ጆርናል” የተባለውን ከጨዋታ ውጪ እንዳያደርገው ልዩ ትኩረት በመስጠትና ቅድመ ፍተሻ በማድረግ የምርምር ጆርናል ጥራትን እንዲያስጠብቁ እንደሚያሳስብ ማስታወቁ ይታወቃል። ይህም ለጆርናሎቹ ጥራት የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለውና ባለ ጆርናል ተቋማትም በዚሁ መሠረት ይሠራሉ ተብሎ ይታሰባል።

ዶ/ር ሠራዊት በዴስክ ሃላፊነትና በየምርምር ማበልፀግ ጉድኝት ሥራ አስፈፃሚ ተወካይነት የሚሠሩበት ዘርፍ “በርካታ በሀገር ውስጥ የሚታተሙ የምርምር ጆርናሎች ጽሑፎች (Manuscripts) የምንተፋና ዘረፋ (Plagiarism) መጠናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ከሚሰጠው ነጥብ በላይ መሆኑን በዚህ ዓመት ባደረገው የፍተሻ ሥራ” ማረጋገጡን አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል። ይህ ዳግም እንዳይከሰት ምን እየተሠራ እንደሆነ ጠይቀናቸው እያንዳንዱ ጆርናል በየሶስት ዓመቱ ለፍተሻና ምዘና እንደሚቀርብ፤ ስታንዳርዱን ካላሟላና ወርዶ ከተገኘ እንደሚነጠቅ ነግረውናል።

“ከመጋቢት 30/2016 ጀምሮ የ Plagiarism መጠኑ ከ30% በላይ የሆነ የምርምር ጆርናል ለፍተሻ ብቁ የማይሆንና ዕውቅና የማይሰጠው መሆኑ” ንም በቅርቡ ተቋሙ ይፋ ካደረጋቸው ማስታወቂያዎች ተገንዝበናል።

እንደ ምርምርና ስርፀት ዴስክ ሃላፊው ዶ/ር ሠራዊት ሀንዲሶ ገለፃ እኛ ሀገር ያሉ ጆርናሎች የተወሰኑ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን የያዙና የታወቁ የመኖራቸውን ያህል ተከታታያይነት የሌላቸው፣ የሚቆራረጡ፣ ሳይንሳዊነት የሚጎድላቸው ብዙ አሉ። እነዚህና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ለአቅመ ጆርናልነት የማያበቁ ሲሆኑ፤ እውቅናን ያገኘ እንኳን ቢሆን የተሰጠውን እውቅና የሚያስነጥቁ ናቸው።

በመጨረሻ የሚሉት ካለ ያልናቸው ዶ/ር ሠራዊት፣ እውቀት የዓለም ነው። የሰው ልጅ ሁሉ ነው። በአንድ ቦታ የተወሰነ አይደለም። ቅብብሎሽ ነው። ሳይንስ ደግሞ አንዱ ለሰው ልጅ የተሰጠ ትልቁ እድል ነው። በመሆኑም ይህንን እድል ተጠቅመን እውቀትን ተደራሽ ማድረግ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ስፍራ ጆርናል ነው። በእነ ስኮፐስ ዳታ ውስጥ ከ40 እስከ 50ሺህ ጆርናሎች አሉ። እዛ ውስጥ መግባት ይገባናል። እዛ ከገባን እንነበባለን። ለዓለም ሁሉ እንተርፋለን። በተለይ ወጣት ምሁራኖቻችን ከደከሙ አይቀር በሚገባ ሠርተው፣ በተዘጋጀ ሥርዓት ውስጥ አልፈውና ተወዳዳሪ ሆነው ሊታዩ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ተገቢው መንገድ ታዋቂ ጆርናል ላይ ሥራዎችን ማሳተም ነው። ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያበረታታል። ሀገራችንን፣ እራሳችንንም፤ እንዲሁም ሌላውን ዓለም ጭምር እንድንጠቅምና የምርምር ሥራችንን እንድናዘምን በጋራ እንሥራ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You