የኢድ አል አድሃ በዓልና ኢትዮጵያዊ እሴቶች

የአረፋ በዓል ታላቅ በዓል ነው። የእስልምና እምነት እንደሚያስተምረው አረፋ የሚለው ቃል በአረብኛ “አወቀ” እንደማለት ነው። ይህም ታሪክ አለው። አዳምና ሔዋን ወይንም አደምና ሃዋ ከጀንነት ወደ ምድር ከወረዱ በኋላ ለብዙ ዘመናት ተጠፋፍተው ነበር። ለረጅም ጊዜ ሲፈላለጉ ከቆዩ በኋላ በዚህ ዕለት በሳዑዲ አረቢያ ባለው የአረፋ ተራራ ላይ ተገናኙ። እዚያም “ዐረፍቱከ… ዐረፍቱኪ” ተባባሉ። “አወቅኩህ! አወቅኩሽ” ማለታቸው ነው። ይህንን ታሪክ ለመዘከር ሲባል ነው የአረፋን በዓል ማክበር የተጀመረው፤ ይህ በዙልሂጃ ዘጠነኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዋዕት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም ይከበራል።

ኢድ አል አድሃ የመተሳሰብና የመረዳዳት በዓል ከመሆኑም ባሻገር ሙስሊሞች የመስዋዕትነት በዓሉን እርድ በመፈጸም፣ በጋራ በመጸለይ እና ከፈጣሪ ምህረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን ያሳልፉታል።ይህም ያጡ ወገኖች የሚደገፉበትና መረዳዳትና መደጋገፍ የሚታይበት በመሆኑ በዓሉ የተለየ ገጽታ ይዞ ይከበራል።

ኢድ አል አድሃ የነብዩ ኢብራሂምና ልጃቸውን የእስማኤልን ታሪክ መነሻ በማድረግ ኢድ ይከበራል። በዓሉ የመስዋዕት፣ የእርድ በዓል ነው። በተለይም የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ቀን ከብት የማረድ ግዴታ አለበት። የተቀረውም ሙስሊም ዕለቱን አቅሙ በፈቀደ ከብት በማረድ ከቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ጋር ያሳልፈዋል። ለኢድ አልአድሃ አንድ ሰው ከሚያርደው ከብት ሲሶውን ብቻ ለራሱ እንዲወስድ ነው ደንቡ። የተቀረው ሲሶው ለዘመድ አዝማድ፣ ሲሶው ደግሞ አቅም ለሌለው ድሃ እንዲከፋፈል እስልምና ያዛል።

ይህንንም መሠረት በማድረግ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች በበዓሉ ዕለት ሰዎች ድሃ ጎረቤቶቻቸውን ይዘይራሉ፤ ያላቸውን ያቋድሳሉ፤ የታረዙትን ያለብሳሉ፤የተጠሙትን ያጠጣሉ።በተለይም ወላጅ አልባ ሕፃናት ከፍተኛ ትኩረትና እንክብካቤ ያገኛሉ። ስለዚህም በዓሉን ተደስተው ያሳልፋሉ።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በበዓሉ ዕለት ሙስሊሞች ክርስቲያን ጎረቤቶቻቸውን በመጥራት እና ማዕድ በመቋረስ በዓሉን በድምቀት ያሳልፋሉ።ስለሀገራቸው ሰላምና አንድነት ይጸልያሉ፤ አብሮነታቸውንም ያጠናክራሉ።

አረፋ የአብሮነት በዓል ነው። በአረፋ በዓል ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በዓሉን በጋራ ያሳልፋል፤ አብሮነት ይደምቃል። ከዚህ ባሻገር ግን ከጥንት በኢትዮጵያ ያለው የአረፋ በዓል አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት።ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በፀጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ነች። አረፋን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት ደግሞ በክርስትና በዓላት እንደሚደረገው ሁሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሲሆን፤ ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው።

ነብዩ ኢብራሂም በእስልምና ሃይማኖት በነበራቸው አስተምህሮት የሰው ልጆች ያለ ዘርና ሃይማኖት ልዩነት የምድር ፍጡራን ሁሉ እኩል መሆናቸውን ሲያስተምሩ የቆዩ በመሆኑ ዛሬ በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖት ልዩነት እየተናጠች ለምትገኘው ሀገራችን አስተምህሮቱ ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል። ሕዝበ ሙስሊሙም ልዩነትን፣ መገፋፋትና መወቃቀስን በማስወገድ ለሀገሩ አንድነትና ሰላም የሚሰራበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚገኝ መረዳት አለበት።

በተለይም ነብዩ ኢብራሂምና ልጃቸው እስማኤል ያሳዩት ታዛዥነት ለዛሬው ትውልድ ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል።ታናሽ ለታላቁ ታዛዥ መሆን አለበት፤ ሕዝብ ለመሪዎች ታዛዥ መሆን አለበት፤ ምዕምናን ለሃይማኖት አባቶች ታዛዥ መሆን አለባቸው።ይህ ሲሆን ፉክክር ይጠፋል፤ በምትኩም መተዛዘንና መረዳዳት ይነግሳል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው። የእስልምና እምነት ድሆችን ማብላትና ማጠጣት እንዲሁም በዓላትን እኩል በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ጥሎባቸዋል።ከእነዚህ ትዕዛዞች አንዱ ያጡና የተቸገሩ ወገኖች መርዳትና መደገፍ አንዱና ዋነኛው ነው።

የእምነቱ ተከታዮች በዓላትን እራሳቸው ብቻ ተደስተው እንዲያሳልፉ አይፈቀድላቸውም።ይልቁንም በዓላት ድምቀት የሚኖራቸውና በፈጣሪም ዘንድ ተቀባይነትን የሚያጎናጽፉት ከተቸገሩ ወገኖች ጋር አብሮ ማሳለፍ ሲቻል ነው።ስለዚህም ሙስሊሞች የመውሊድ በዓልን ሲያከብሩ ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ ከማጋራት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሊሆን ይገባል።

በአጠቃላይ መውሊድ የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ከዚህ በሻገር እንደሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል ነው።በተለይም በአሁኑ ወቅት በጸጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተሰደዱ በርካታ ወገኖች አሉ። ከዚሁ ባሻገር በድርቅ የተጎዱና በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጦርነት ካሳደረባቸው ጠባሳ ያላገገሙ ወገኖች በችግር ውስጥ ስለሚገኙ እነዚህን ወገኖች መደገፍና ተባብሮ ወደ ቀድሞ ህይወታቸው መመለስ አንዱ በመውሊድ ወቅት የሚከወን ተግባር ሊሆን ይገባል።

በአረፋ መረዳዳትና መደጋገፍ ቢስተዋልም በዚህ ወቅት የሚስተዋለው መደጋገፍ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚከናወን ተግባር ሊሆን ይገባል። የደካሞችን ቤት በማደስ፣ ለጦም አዳሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን ማቅረብ ፣ የታረዙትን ማልበስና ወላጅ አልባዎችን መጎብኘት በኢድ አልአድሃ የሚወደድ ተግባር ቢሆንም በሌሎችም ቀናት እነዚህ በጎ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ናቸው።

ማኅበረሰቡ በበዓል ወቅት ከመረዳዳት ባሻገር ሀገራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በጋራ መቆምም ይጠበቅበታል።ሰዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ከአካባቢያቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲራቡና ሲጠሙ ዝም ብሎ መመልከት ከእስልምና አስተምሮ አንጻር የሚያስጠይቅ ነው። በተለይም ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህም የኢድ አልአድሃ በዓልን ስናከብር እነዚህን ወገኖች በመጎበኘትና ወገናዊ ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል።

አሁን አሁን የድሆችን ቤት በማደስ፣ማዕድ በማጋራትና የተጀመሩ ሥራዎች የሚያስደስቱ ናቸው።እስልምና በጣም የሚደግፋቸውና አብዝቶም የሚሠራባቸው ናቸው። ወቅቱ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ መረዳዳት የሚያስፈልግበት በመሆኑ የተለያዩ ድጋፎች ለተፈናቃዮችና ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ማድረስ የግድ ይላል።

በእርግጥ በአሁኑ የመተሳሰብ ፣የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል።በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና ድሃ ድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።ይህ አኩሪ በዓልም በኢድ አልአድሃ አረፋ በዓልļ

የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።መጪው ጊዜም የክረምት ወቅት እንደመሆኑ መጠን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የሚበራከቱበት ነውና አኩሪ የሆኑ እሴቶቻችን ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

መልካም የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል!

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You