
– 1445ኛው የአረፋ በዓል በድምቀት ተከብሯል
አዲስ አበባ:- 1445ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ በዓል) የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የትብብር በዓል መሆኑን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ። በዓሉ ትናንት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት ተከብሯል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሕዝብ ጉዳዮች ተጠሪ ሀሰን አሊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአረፋ በዓል ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህልን በእጅጉ የሚያጎለብት ነው። በእስልምና ከተደነገጉ ሁለት ትልልቅ አስተምህሮቶች ውስጥ አንዱ ነው ያሉት ሀሰን አሊ፤ አረፋ የእርድ በዓል በመባል ይታወቃል ብለዋል።
አቅሙ የቻለ በዓመት አንድ ጊዜ ሀጅ ሥነ ሥርዓት ለማክበር ወደ ሳውዲ አረቢያ አረፋ መካ ተራራ በመሄድ በዓሉን እንደሚያከብር
ገልጸው፤ አቅሙ ያልፈቀደ በኢስላማዊ አስተምህሮው መሠረት በሶላትና በጸሎት በዓሉን እንደሚያከብር ተናግረዋል።
ምዕመኑ ከበዓሉ ሶላት መልስ አቅሙ በፈቀደው መጠን የእርድ ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድ ጠቅሰው፤ የእርዱን አንድ ሶስተኛ ለቤተሰቡ የቀረውን በአካባቢው ከሚገኙ ችግረኞችና ከጎረቤቶች ጋር በመቋደስ እንደሚከበር ገልጸዋል።
በዓሉን አቅም ያጠራቸውን ወገኖች በማሰብ ማክበር እንደሚገባ ገልጸው፤ እንደ ኢትዮጵያዊያን የመረዳዳት ባህልን የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመዋል።
እስልምና ጉርብትና መጠናከር እንዳለበት አጥብቆ ያዛል ያሉት ሀሰን አሊ፤ ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን ማጎልበት ትልቁ የእስልምና እሴት ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚና የሕግ ዘርፍ ተጠሪ ሳቢር ይርጉ በበኩላቸው፤ አረፋ ተካፍሎ በአብሮነት የሚበላበት የመተሳሰብና የትብብር በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢድ አል አድሃ (አረፋ) የእርድ በዓል በመሆኑ የነቢይ ኢብራሂምና ኢስማኤል ታሪክ ያለበት ነው ያሉት ሳቢር ይርጉ፤ ኢስላማዊ አስተምህሮቱን ተከትሎ የእርድ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል ብለዋል።
ለበዓሉ የታረደው ከብት ለሦስት ተከፍሎ ከፊሉን ቤተሰብ ጎረቤትና ሚስኪኖች እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ አረፋ ተካፍሎ በአብሮነት የሚበላበት የመተሳሰብና የትብብር በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያውያን ተካፍሎ መብላት ባህል መሆኑን አንስተው፤ የአረፋ በዓል መተባበርና መደጋገፍን የሚያጎለብት እና የኢትዮጵያዊነት ማሳያ መሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
የአረፋ ሶላት እስኪሰገድ ድረስ ጾም መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሶላት በኋላ ወደየቤቱ በመሄድ የእርድ ሥርዓት እንደሚፈጸምና ተካፍሎ የሚመገብ መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከበረው በዓል ላይ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባን ጨምሮ ኡስታዞች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም