የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የባንክ ሥራ አስኪያጅ

የኢትዮጵያን የባንክ ዘርፍ የመሩት የመጀመሪያዎቹ የባንክ ስራ አስኪያጆች የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። ‹‹ኢትዮጵያውያን ለባንክ ስራ አመራር ብቁ አይደሉም›› የሚለውን አስተሳሰብ በመስበር አመራሩን ከእነዚህ ዜጎች ተረክቦ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ ቀላል አልነበረም። በዚህ ከፍተኛ ጥረትና ጥበብ በሚጠይቅ መንገድ ተጉዘው ዘርፉን ውጤታማ ካደረጉት ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያውያን መካከል ተፈራ ደግፌ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ባለሙያ ናቸው። በስማቸው የባንክ ቅርንጫፎች ሁሉ የተሰየሙላቸው እኝህ ጀግና የዚህ ሳምንት ክስተት ስለሆኑ ታሪካቸውን ዘርዘር አድርገን እናያለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን አጠር አጠር አድርገን እናስታውስ።

ከ96 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 7 ቀን 1920 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ጁን 14 ቀን 1928) ዓለም አቀፉ አብዮተኛ፣ አርጀንቲናዊው የማርክሲስት አቀንቃኝ፣ የነፃነት ታጋይ፣ ሐኪም፣ ደራሲ፣ መምህር፣ ዲፕሎማት፣ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያ እና የጦር መሪ … ኧርኔስቶ ‹‹ቼ›› ጉቬራ ተወለደ። ይህ ዘርፈ ብዙ ባለሙያ በዋነነት በማርክሲስት አብዮተኛነቱ ይታወቃል። ለሌሎች ዓለም አቀፍ አብዮቶችም አርዓያ ተደርጓል። በኢትዮጵያም በተለምዶ ‹‹ያ ትውልድ›› እየተባለ የሚጠራው የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ

ፋኖ ተሰማራ

ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆቺ ሚኒ

እንደ ቼ ጉቬራ

የሚል መሪ ቃል ነበረው። ይህ መፈክር ዛሬ ድረስ ያንን ትውልድ ለማስታወስ ጥቅም ላይ ሲውል ይሰማል።

ከ86 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 7 ቀን 1930 ዓ.ም ጀግናው ዘርዓይ ደረስ በሮም አደባባይ የጣሊያንን ሕዝብ አፍ ያስያዘ የጀግንነት ታሪክ ፈጸመ። የኢጣሊያ መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባታቸው በዶጋሊ ጦርነት ዶግ አመድ ለሆኑት ጣሊያናውያን ሰኔ 7 ቀን 1930 ዓ.ም የመታሰቢያ መርሃ ግብር በሮም ከተማ በአንድ የመንግሥት አደባባይ ላይ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ ነበር ጀግናው ዘርዓይ ድረስ ጣሊያኖችን በጎራዴ የጨፈጨፋቸው። የዚህን ጀግና ሙሉ ታሪክ ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም የታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ማግኘት ይቻላል።

ከ42 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 6 ቀን 1974 ዓ.ም ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተወለደ።

አሁን በዝርዝር ወደምናየው የባንክ ባለሙያው ተፈራ ደግፌ ታሪክ እንሂድ።

ተፈራ የተወለደው ሰኔ 8 ቀን 1918 ዓ.ም በቀድሞው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ አንኮበር አውራጃ፣ አንበሴ በሚባል ቀበሌ ነው። አባቱ አቶ ደግፌ በላይነህ፤ እናቱ ወይዘሮ እርገጫቸው ገብረማርያም ይባላሉ። እድሜው ሰባት ዓመት ሲሆን ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአክስቱ ወይዘሮ ጌጤ ገብረማርያም ዘንድ መኖር ጀመረ። ከአንድ ቄስ ዘንድ ፊደል ከቆጠረ በኋላ አሊያንስ ፍራንሲስ በሚባለው የፈረንሳይኛ ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርት መማር ጀመረ።

ለሁለት ዓመታት ያህል እንደተማረ በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ ትምህርት ቤቱ ተዘጋ፤ ተፈራም ትምህርቱን አቋረጠ። ተፈራ በአምስት ዓመቱ የፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዘመን የኖረው ሌቭድሮዝደቭስኪ ከተባሉ የሩስያ ዜጋ ጋር ነበር። በጊዜውም ታዳጊው ተፈራ የሰውየው ረዳት ሆኖ አገልግሏል። ከሰውየው ልጅ ጋር በመማርም የሩስያና የጣሊያንኛ ቋንቋዎችን አወቀ። በእነዚህ ቋንቋዎችም ብዙ መጽሐፍትን ማንበብ ቻለ።

በ1933 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ሲባረር የተፈራ ረዳት የነበሩት የውጭ አገር ዜጎች ከኢትዮጵያ ስለወጡ ታዳጊው ተፈራ ከባድ የሕይወት ፈተና አጋጠመው። የትምህርት ዕድል ባለማግኘቱ በአንድ የስፌት መኪና ኩባንያ ውስጥ በአስተርጓሚነት ተቀጠረ። በኩባንያው ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ከሰራ በኋላ የመማር ጉጉት ስለነበረው ሥራውን ለመተው ወሰነ።

እንዳጋጣሚ ሆኖ አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ቋንቋ የሚያውቁ ሠራተኞች እየፈለገ ይቀጥራል መባሉን ሰምቶ ማመልከቻውን በፈረንሳይኛ ቋንቋ አቀረበ። የባንኩ ስራ አስኪያጅም ተፈራ እንዲቀጠር ፈቀዱ። በ1936 ዓ.ም በ18 ዓመቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በጸሐፊነት ተቀጠረ። ስራውን ለማከናወን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ አስፈላጊ ስለነበር ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ‹‹ብሪቲሽ ኢንስቲትዩት›› በተባለው ተቋም እንግሊዝኛ ለመማር ተመዘገቡ። በባንኩ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ከሠራ በኋላ ከሌሎች ወጣት ሠራተኞች ጋር ተመርጦ ትምህርቱን ለማሻሻል ኮተቤ ወደሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተላከ። ለአንድ ዓመት ተምሮ በ1938 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ካናዳ ተላከ። ይህም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ካናዳ ከተላኩት የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መካከል አንዱ ያደርገዋል።

ካናዳ እንደደረሰም መጀመሪያ ያመራው ካልጋሪ፣ አልበርታ ወደሚገኘው የንግድ ኮሌጅ ነበር። በአንድ ዓመት ውስጥ ትምህርቱን ጨርሶ በዲፕሎማ ተመረቀ። ወዲያውኑም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመቀጠል ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ገባ። ኮሜርስ ፋኩሊቲ በየዓመቱ የበጋ ትምህርት ጭምር እየወሰደ በ1942 ዓ.ም በዲግሪ ተመረቀ። ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት የሕግ ትምህርት ተከታትሎ በ1945 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የባንክ አገልግሎቱን ቀጠለ።

እነ ተፈራ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ባንኩ አድጎ፤ የሰራተኛው ቁጥርም ጨምሮ ነበር። ሌሎች ሰራተኞችም ትምህርትና የባንክ ስራ ስልጠና እንዲያገኙ እነ ተፈራ ማሳሰብ ጀመሩ። ሠራተኛው በየደረጃው የማታ ትምህርት እንዲከታተል ታስቦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በባንኩ እርዳታ የማታ ትምህርት የሚያስተምሩ ምሁራን ተቀጠሩ። የባንክ ሠራተኞች ትምህርት ከጀመሩ በኋላ ከሌሎችም መንግሥታዊ ድርጅቶች ብዙ የማታ ተማሪዎች ተመዘገቡ። የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ሊደራጅ የቻለው በባንክ ድጋፍ የተጀመረው ትምህርት ተስፋፍቶ ነው።

የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ተወግዶ ነጻነት ከተመለሰ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደገና በመቋቋም ላይ ሳለ ኢትዮጵያ የራሷን ባንክ ለማቋቋም ስትነሳ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋት ነበር። እንግሊዝ በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረውን የባንክና የገንዘብ ስርጭት ከምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛቶቿ ጋር አቀላቅላ የማስተዳደር ፍላጎት ነበራት። ሆኖም ችግሩን በውስጥ ምክርና ድፍረት በማለፍ በ1934 ዓ.ም ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ›› በአዋጅ እንዲቋቋም ተደረገ።

በጦርነቱ ጊዜ የታላቋ ብሪታኒያን የጦር ሠራዊት ተከትሎ መጥቶ የኢጣሊያ ባንኮችን አስወግዶ የባንኩን ሥራ ተረክቦ የሚያስተዳድረው ባርክሌይስ ባንክ ነበር። ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ›› ይህንን የእንግሊዝ ባንክ ተክቶ ነው ሥራውን የጀመረው። ባንኩ የተዋቀረው የጠቅላይ (ማዕከላዊ) ባንክንና የንግድ ባንክን ሥራ አጣምሮ እንዲሠራ ነው። ባንኩ ሥራውን ሲጀምር የነበሩት አብዛኞቹ ሠራተኞች የውጪ አገራት ዜጎች ነበሩ። ብዙዎቹ ከኢጣሊያ ወረራ በፊት የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ ሲያገልግሉ የነበሩ ናቸው።

ሰራተኛው እርስ በእርስ እየተረዳዳ ይማማር ነበር፤ የባንኩ ስራ እየተስፋፋ ሲሄድ የገጠር ቅርንጫፎች መከፈት ጀመሩ። የእነዚህ ቅርንጫፎች ኃላፊዎችም የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። በ1937 ዓ.ም አዲስ የኢትዮጵያ ገንዘብ በአሜሪካ በምስጢር ተዘጋጅቶ ታውጆ ወጣ። በዚህም የኢጣሊያ ሊሬ እና የምስራቅ አፍሪካ ሺሊንግ በአዲሱ የኢትዮጵያ ብር ተለወጠ። የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክም የባንክ ሥራው ቀስ በቀስ እየሰመረለት ሄደ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ እንደ ንግድ ባንክ ሆኖ ሲሠራ መጀመሪያ የሚሰጠው አገልግሎት የተንቀሳቃሽ ሂሳብና የገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ ነበር። ሥራው እየደረጀ ሲሄድ ተደራቢ ሥልጣን ተሰጠው። በ1938 ዓ.ም የቁጠባ ሂሳብ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። የባንኩን ሥራ ለሕዝቡ ለማለማመድና በባንኩ እምነትን ለመፍጠር ብዙ ዓመታትን ፈጅቷል። ባንኩ በሰራተኞቹ ትጋትና በመንግሥት ድጋፍ ሁለገብ ድርጅት ሆኖ ጠቅላላ የባንክ አገልግሎትን ማስፋፋቱን ቀጠለ። ዘመናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲጀመርና ትምህርትም እየተስፋፋ ሲሄድ ኢትዮጵያውያን ሥራውን እየተላመዱ፣ የባንኩን የአመራር ሥራም እስከመያዝ በቁ። በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ የነ ተፈራ ጥረትና አበርክቶ ከፍተኛ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በውጭ አገራት የሚሠሩ ሁለት ቅርንጫፎች ነበሩት። የመጀመሪያው የትራንዚት ሥራ የሚሠራ የጂቡቲ ቅርንጫፍ ነበር። ሁለተኛው ለባንክ አገልግሎት ሱዳን ውስጥ የተቋቋመው የካርቱም ቅርንጫፍ ነበር። እ.አ.አ በ1957 የወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚንስትር በነበሩት አቶ ጌታሁን ተሰማ የሚመራ የንግድ ልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን ሲሄድ ተፈራ የቡድኑ አባል ሆኖ ሄደ። የቡድኑ ጉዞ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የነበረው ንግድ የሚዳብርበትን እቅድ ለማጥናትና የንግድ ውል ለመደራደር ነበር። ለዚህ ዓላማ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ቅርንጫፍ በካርቱም ቢከፈት ለሁለቱ አገሮች የጋራ ንግድ እንደሚረዳ ታምኖበት ጥያቄው ቀረበ። የሱዳን መንግሥትም የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ቅርንጫፍ በካርቱም እንዲቋቋም ፈቀደ።

የንግድ ልዑካኑ ሪፖርት ቀርቦ ከተፈቀደ በኋላ ለታቀደው የባንክ ቅርንጫፍ ብቁ የሆነ ሥራ አስኪያጅ በአስቸኳይ ተመርጦ እንዲቀጠር ባንኩ ታዘዘ። በወቅቱ የባንኩ ገዥ የነበሩት አሜሪካዊ ጆርጅ ሬይ ‹‹በሥራው የሰለጠነ ኢትዮጵያዊ የለም›› በማለት የአንድ እንግሊዛዊ ዜጋ ስም አቀረቡ። ይሁን እንጂ ‹‹ለታቀደው ዓላማ የውጭ ዜጋ አይበጅም›› ተብሎ የባንኩ ምርጫ ውድቅ ሆነ።

በዚያን ጊዜ አቶ ተፈራ ደግፌ የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ይሰራ ነበር። አቶ ተፈራ የባንኩን የካርቱም ቅርንጫፍ እንዲመሩ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በጽሕፈት ሚኒስቴር ማዘዣ ተሾሙ። ከምክትል ሥራ አስኪያጁ ከአቶ ከበደ ሠረቀብርሃን ጋር ሆነው ቅርንጫፉን ለማቋቋም ወደ ሱዳን ሄዱ። ከዋናው መሥሪያ ቤት አራት ኢትዮጵያውያን ኃላፊዎች ተመርጠው ተልከው በ1950 ዓ.ም የባንኩ የካርቱም ቅርንጫፍ ተከፈተ። ለቅርንጫፉ የሚስማሙ ሱዳናውያን እየተመለመሉ እንዲሰለጥኑና እንዲቀጠሩ ተደረገ። በተቻለ መጠን የባንኩ ገጽታ አፍሪካዊ እንዲሆንም ጥረት ተደርጓል። ቅርንጫፉ በአጭር ጊዜ ብዙ ደንበኞችን አፍርቶ ተወዳጅ ሆነ። የባንኩ ሙሉ ስም ለአረብኛ ተናጋሪዎች ስለሚያስቸግር የባንኩ ደንበኞች ቅርንጫፉን በወዳጃዊ አጠራር ‹‹ባንክ ኤል ሐበሺ›› ብለው ሰየሙት።

በወቅቱ ሱዳን ውስጥ ስድስት የውጭ አገራት ባንኮች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ብቸኛው አፍሪካዊ ባንክ ደግሞ የኢትዮጵያው (የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የካርቱም ቅርንጫፍ) ነበር። በአቶ ተፈራ ደግፌ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የካርቱም ቅርንጫፍ ከደረጁ የምዕራባውያንና የአረብ አገራት ባንኮች ጋር ተወዳድሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ደንበኞች ማፍራትና አትራፊ ለመሆን በቃ። ይህም ቅርንጫፉ ለኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት አስችሎታል።

የካርቱሙ ቅርንጫፍ ለአስር ዓመታት ያህል ካገለገለ በኋላ በጄኔራል ኒሜሪ ዘመነ መንግሥት እ.አ.አ በ1969 የግል ባንኮች ሁሉ በሱዳን መንግሥት ሲወረሱ አብሮ ተወረሰ። በ1960 እና በ1970ዎቹ በአገር ውስጥ ለባንክ አመራር ብቁ ሆነው ያገለገሉት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የባንክ ባለሞያዎችና ኃላፊዎች ካርቱም ቅርንጫፍ እየሠሩ በቂ ልምድ ያገኙ ናቸው። ለአብነት ያህልም አቶ ከበደ ሠረቀብርሃን፣ አቶ መስፍን በለጠ፣ አቶ ታደሰ አበበ፣ አቶ ስሜ ታከለ፣ አቶ ቸርነት በየነ፣ አቶ ተሳለ ወርቁ፣ አቶ ጌታቸው ደስታ እና ወይዘሮ በላይነሽ ማንደፍሮ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች ታዋቂ የባንክ ባለሙያዎች ሆነው እያንዳንዳቸው በብሔራዊ ባንክና በንግድ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል።

እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ገዢዎች የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። ኢትዮጵያውያን በከፊል ስልጣን መጋራት የጀመሩት አቶ የወንድ ወሰን መንገሻ እ.አ.አ በ1959 ዓ.ም የባንኩ ምክትል ገዥ ሆነው ሲሾሙ ነው። በ1953 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ደግሞ አቶ ተፈራ ደግፌ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ። ይህ የአቶ ተፈራ ሹመት ‹‹ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን ለመምራት ብቁ አይደሉም፤›› የሚለውን አስተሳሰብ ውድቅ ያደረገና ከ1937 እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ በስድስት የውጭ አገራት ዜጐች ሲተዳደር የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን በኢትዮጵያዊ ስራ አስኪያጅ መመራት መጀመሩን ያበሰረ የለውጥ እርምጃ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

ከዚያ በኋላ ከዚያ ቀደም ያልታየና ከፍተኛ የሆነ የብድር እድገት፣ የቅርንጫፎች መስፋፋትና የገቢ መጨመር ተመዘገበ።

የተሟላ የባንክ አገልግሎት በአዲስ መልክ ለማቋቋም እቅድ ወጣ። ይህ የባንክን አቋም የማሻሻል እቅድ ሰፊ ጥናት እንደሚያስፈልገው ታውቆ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አንድ ባለሙያ በመቅጠርና ጥናት በማስጠናት አዲስ የባንክ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለፓርላማ ቀረበ። በአዋጁ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ለሁለት ተከፍሎ አንዱ ማዕከላዊ (ብሔራዊ) ባንክ፤ ሌላው ደግሞ የንግድ ባንክ ሆነው እንዲቋቋሙ ተወሰነ።

በታህሳሥ 1956 ዓ.ም ሁለቱ ባንኮች (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ተደራጅተው ስራቸውን ጀመሩ። አቶ ምናሴ ለማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ አቶ ተፈራ ደግፌ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ1960ዎቹ ከፍተኛ እድገት ሲያስመዘግብ አቶ ተፈራ በዋና ስራ አስኪያጅነት ይመሩት የነበረውና በ20 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተዋፅዖው ከፍተኛ ነበር።

ባንኩ በአዲስ መልክ ሥራውን እንደጀመረ ዋና እቅዱ ሠራተኞቹን ማሰልጠንና የባንክ ቅርንጫፎቹን ማስፋፋት ነበር። የባንክ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ማዕከል በመክፈት የሰራተኞቹን አቅም ለማሳደግ ሰፊ ጥረት አድርጓል። በዚህም ባንኩ ጥሩ አፈፃፀም እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል። ሌሎች የገንዘብና የመድን ተቋማት ያለባቸውን የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለልም ሚናው የጎላ ነበር። ለዚህ ሁሉ የአቶ ተፈራ ደግሜ ሚና ከፍተኛ ነበር።

በእርሳቸው ፋና ወጊነት የተጀመረው የኢትዮጵያውያን የባንክ መሪነትም እስካሁን ድረስ ተጠናክሮ ዘልቋል። ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ በመሆን አገልግለዋል።

ወታደራዊው መንግሥት ስልጣን በያዘ ማግሥት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወርሶ በብሔራዊ ባንክ ስር ሆነ። አቶ ተፈራም ‹‹ለአብዮቱ እንቅፋት እንዳትሆን›› ተብለው ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ያህል ለእስራት ተዳረጉ። ከእስራት ከተፈቱ በኋላም ኑሯቸውን በተማሩባት ካናዳ አድርገው ቆይተዋል። በዚምባብዌና በስዋዚላንድ የባንክ አማካሪ ሆነውም ሰርተዋል። የተማሩበት ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲም የሕግ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል። በአዲስ አበባ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸውን ለአዲስ አበባ የፌስቱላ ሆስፒታል በስጦታ ያበረከቱት አቶ ተፈራ፤ ከካናዳዊት ባለቤታቸው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። አንጋፋው ባለሙያ በስራቸው ላበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል። የምርምር መጻሕፍትንም ጽፈዋል።

የኢትዮጵያን የባንክ ስርዓት እንዲዘምን ካደረጉት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አቶ ተፈራ ደግፌ የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በቫንኩቨር ካናዳ ተፈፅሟል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You