«የምሰራው ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ነው» ሃጂ ከማል አብዱላኪም የቲም ሕጻናት እንክብካቤ ማዕከል መስራችና ስራ አስኪያጅ

“ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ “ ይባላል የመረዳዳትን አይተኬ ሚና ለመግለጽ፤ አዎ የትኛውም ችግር ቢሆን ከተረዳዱበት አይጎዳም ቢጎዳም መልሶ ለማንሰራራት እድልን ይሰጣል። ይህ መረዳዳት ደግሞ እንደ ኢትዮጵያዊ ዘመናትን አብሮን የተገሻገረ የኖርነውና እየኖርነው ያለ መሰረታችን ነው።

ክርስትናውም ይሁን እስልምናው ሃይማኖቶች ሁሉም የሚያዙት እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፣ተረዳዱ የተራበን አብሉ፣የታረዘውን አልብሱ፣አባት እናት የሌላቸውን ልጆች ጎብኙ ለቁም ነገርም አድርሱ ነው። ይህንን ሃይማኖታዊ አስተምሮ ስንቶቻችን እንተገብረዋለን የሚለውን ለራሳችን ትተን ነገር ግን ባመኑበት እምነት ብሎም በኖሩበት ቤተሰብና ኅብረተሰብ ይዘውት የመጡትን የመረዳዳት አንዱ ለአንዱ የመኖርን አስፈላጊነትና ጥቅም በተግባር ያሳዩ ለብዙዎች ተስፋ ከተስፋም አልፈው እንጀራ የሆኑ ብዙዎች ናቸው።

ልጆች ወላጅ አሳዳጊ በማጣታቸው እንዳይራቡ፤ እንዳይጠሙ፤ እንዳይታረዙ አልፎ ተርፎም ከሕልማቸው እንዳይቀሩ ብዙ የለፉም እየለፉ ያሉም አሉ ። ይህ ስራቸው ደግሞ ባመኑበት እምነት ከፍ ያለ ዋጋን የሚያሳጣቸው ከመሆኑም ባሻገር እንደ ዜጋ የሚያስመሰገን፤ ብሎም ሽልማት የሚያሰጥ መልካም ተግባር መሆኑንም መዘንጋት የለበትም።

የዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን ለኔ የሚሉት ነገር የሌላቸው ይልቁንም ከልጅነታቸው ጀምሮ ይዘውት በመጡት የመረዳዳትና የደግነት ባህል እየተመሩ ለብዙዎች የመኖር ምክንያት የሆኑ ናቸው። እሳቸው ከተወለዱበት የትውልድ ቀያቸው አንስተው አሁን እስከሚኖሩበት አዲስ አበባ ከተማ ድረስ በርካታ ሕጻናትን ለወግ ማእረግ አብቅተዋል፤ ብቸኛ እናቶችንም ራሳቸውን አስችለው ከጥገኝነት አውጥተዋል።

“የቲም” በእስልምና ሃይማኖታዊ ትርጉሙ አባት የሌለው ልጅ ማለት ነው። እዚህ ላይ ግን አባትም ኖሮ ሰርቶ ወጥቶ ወርዶ ቤተሰቡን መመገብ ማልበስ በጠቅላላው ማስተዳደር ካልቻለ የወለዳቸው ልጆች የቲም ይባላሉ። ሃጂ ከማል አብዱላኪም ደግሞ “የቲም ሕጻናት እንክብካቤ ማዕከል” መስራችና ስራ አስኪያጅ ናቸው።

ሀጂ ከማል ከፈጣሪ በተሰጣቸው የደግነትና ለሌሎች የመኖር ጸጋን ተጠቅመው የሀይማኖትና የዘር ልዩነት ሳያሳስባቸው ብዙ የቲም ሕጻናትን ብሎም እናቶችን ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ ከችግር እያወጡ ራሳቸውን እያስቻሉ፤ እያስተማሩ፤ እያስመረቁ ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ አገር ድረስ በትልልቅ ስራዎች ላይ እንዲገኙ ድልድይ የሆኑ ታላቅ አባት ናቸው።

ሀጂ ከማል ተወልደው ያደጉት አርሲ ሮቤ ሰዲቃ በሚባል አካባቢ ነው። ከሁለት ታላላቅ እህቶቻቸው ቀጥለው በሶስተኝነት የተወለዱት ሀጂ ከማል እጅግ በጣም ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ስለማደጋቸው ይናገራሉ።

“…….ቤተሰባችን የሼህ ቤተሰብ ነው፤ እናትና አባቴ ዘጠኝ ልጆችን የወለዱ ቢሆንም ቤተሰባችንን ተቀላቅሎ የሚኖረው ግን ስፍር ቁጥር የሌለው ሰው ከመሆኑ የተነሳ በጣም ሰፊ ቤተሰብ ያለን ነን” ይላሉ ።

አባታቸው ሼህ ፈቂ በከተማው በጣም የታወቁ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥም እጅግ ተሰሚነት ያላቸው፤ ከሌሎች ሼህ ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን በአንድ አካባቢ ላይ ተወስነው መኖር የማይችሉ በየአካባቢው እየዞሩ በርካቶችን ሀይማኖታዊ ትምህርት የሚያስተምሩ ለእምነታቸው የቀኑ ነበሩ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደ ልጆቻቸውም ተጋብቶ እነ ሀጂ ከማልም ሀይማኖታቸውን አጥብቀው የሚወዱ ብሎም እንደ አባት አጎቶቻቸው በሁለም ነገር ለብዙዎች የመትረፍ ልምድን ያካበቱ ሆነዋል።

“……..እኔ በቤተሰቦቼ ቤት ስኖር የተቸገረን ማብላት፤ የታረዘን ማልበስ ግዴታ እንደሆነ እየተነገረኝና በተግባርም እያየሁ ነው ያደኩት። ለምሳሌ አያቴ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ አርደው ምስኪኖች እንዲበሉ፤ መንገዶኞች አረፍ ብለው በልተው እንዲሄዱ ያደርጉ ነበር” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

ሀጂ ከማል እንደ ማንኛውም የአካባቢያቸው ልጆች ከብት በመጠበቅ ከእኩዮቻቸው ጋር በመቦረቅ ያሳለፉ ናቸው፤ ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ እሳቸውን ለየት ያደርጋቸው የነበረው ነገር በጨዋታቸውም ሆነ በእረኝነታቸው ወቅት የተቸገሩ ሰዎችን ሲያዩ ለመርዳት ያላቸው ጉጉት ነው።

“…..እኔ እረኛ ሆኜ ከብት ስጠበቅ የቤተሰቦቼን ከብቶች ብቻ አልነበረም የምጠብቀው ጓደኞቼን በማስተባበር የአካባቢውን ነዋሪዎች ከብቶች ሁሉ ጠብቀን ማታ በየቤታቸው አስገብተን ነበር የራሳችንን ይዘን የምንሄደው፤ ሌላው ደግሞ በእኛ ቤት ንብ የማነብ ስራ ይሰራ ስለነበር ማር በሚቆረጥበት ጊዜ ለሙስሊም ክርስቲያን ጎረቤቶቻችን ማር ለማድረስ በጉጉት ነበር የምንጠብቀው፤ ከዛም መንደሩን ሙሉ ስናድል ነበር የምንውለው “ በማለት ከቤተሰቦቻቸው ያዩት ደግነት ዛሬ ላይ ለሚሰሩት ስራ ትልቅ መደላደልን እንደፈጠረላቸው ያብራራሉ።

ሀጂ ከማል በሀይማኖት ትምህርት በቋንቋ በሼሪያ ሕግ ዙሪያ ሳውዲ አረቢያና ግብጽ በመሄድ የተለያዩ ኮርሶችን ወስደዋል። አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ ቅዱስ ቁርአን ከሚባል ድርጅት ጋር ይሰሩ እንደነበር የሚያስታውሱት ሀጂ ከማል ነገር ግን የራሳቸው የሆነ ነገር ኖሯቸው ችግረኞችን የመርዳት ምኞታቸው ላቅ ያለ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሀጂ ከማል ከልጅነታቸው ጀምሮ ሰውን መርዳት መደገፍ የሚያስደስታቸው ናቸው። በዚህም የእሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸው ተሰሚነትና ተቀባይነት በመጠቀምም የትውልድ ቀያቸው ላይ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አከናውነዋል።

በትውልድ መንደራቸው ከተማ ላይ ሰፊ ቦታን የያዘ ትምህርት ቤት ሕብረተሰቡን በማስተባበር ያሰሩ ሲሆን ከአዲስ አበባ ደግሞ አልባሳት የቁርአንና ሌሎች ዓለማዊ እውቀትን የሚያስጨብጡ መጽሀፍትን በማሰባሰብና ይዞ በመሄድ ትምህርት ቤቱ አገልግሎት እንዲሰጥ ስለማድረጋቸው ይናገራሉ። በሌላ በኩልም በዛው በአካባቢያቸው ላይ ላሉ መስኪዶች በወረዳ ደረጃ እንዲደራጁ በማድረግና ሀይማኖታዊ አገልግሎትን ለመስጠት ያስፈልጓቸዋል የሚሉትን ግብዓት በማሰባሰብ እንዲከፋፈሉ የማድረግ ተግብርንም ከውነዋል።

“…….እኔ ለስራው የተፈጠርኩ ይመስለኛል፤ ከበፊትም ጀምሮ የአካባቢዬ ነዋሪዎች ለእኔ ትልቅ እምነትና ፍቅር አላቸው፤ እኔም እነሱን አስተባብሬ ይህንን አምጡ ከማለት ባሻገር መስኪዱንም ትምህርት ቤቱንም እየሰራሁ አሳያቸዋለሁ፤ ይህ ደግሞ በጣም ስለሚያስደስታቸው በቀጣይ ይህንን እንስራ ስላቸው እምቢ የሚል አይኖርም። ይህ ነገር ደግሞ እያደገ ሲሄድ አገልግልቱም እየሰፋና ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መጣ “ይላሉ።

ሀጂ ከማል በትውልድ አገራቸው ላይ ያለውን የወፍጮ ቤት ችግር ለመቅረፍ አዲስ አበባ ካሉ ባለጸጋ 27 ወፍጮዎችን በመጠየቅና በየመስኪዱ እንዲተከሉ በማድረግ እናቶች የወፍጮ ችግራቸው እንዲቀረፍ ከፍ ያለ ስራንም የሰሩ ታላቅ ሰው ናቸው።

ሀጂ ከማል “ መስጠት መሰጠት ሆኖላቸዋል” አምላክ የሰጣቸውን የመስጠት በረከት እሳቸውም መንዝረው ስለተጠቀሙበት ዛሬ ላይ ለብዙዎች ተስፋ ከመሆናቸውም በላይ እሳቸውም በሰሩት ስራ ላቅ ያለ ክብር አግኝተው የሚኖሩ ናቸው ።

ይህ ደግነታቸው በጣም በሕዝቡ ውስጥ የገባ ከመሆኑ የተነሳ በእንግድነት እንኳን አገራቸው ሲሄዱ ነዋሪው የሚሰጣቸው ፍቅር ያስገርማቸዋል። ”…….እኔ የቲምን ከማቋቋሜም በፊት ቢሆን ለበዓል ከአዲስ አበባ አርሲ ስሄድ ለአሮጊት ሽማግሌው ዣንጥላ ካፖርት ለሴቶች የሚያስፈልጋቸውን ብቻ አቅሜ የቻለውን ሁሉ በሻንጣዬ ሞልቼ ነበር የምሄደው። ስመለስ ሻንጣዬ ባዶውን ነው የሚመጣው። ከለበስኩት ልብስ ውጪ የሚተርፈኝም ነገር አይኖርም “ በማለት ሁኔታውን ይገልጻሉ።

የቲም የሕጻናት እንክብካቤ ማዕከል

ማዕከሉ በ1993 ዓ.ም ልበ መልካምና የድሆች አባት በሆኑት ሀጂ ከማል ሀሳብ አመንጪነት በሁለት ሰራተኛና በ50 የቲም ሕጻናት የተመሰረተ ነው። ስራውን ሲጀምሩም እኔ ራሴን ልስጥ ግን ደግሞ የቲም ሕጻናትና የተጎዱ እናቶች ቀን ይውጣላቸው በችግር ኖረው አይሙቱ ብለው ነበርና ከዛ በኋላ ድርጅቱን በሁለት እግሩ አቁመው አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል።

“…….አንዳንድ ሰዎች የሕጻናትም ይሁን የሴቶች መርጃ ድርጅቶችን ሲመሰርቱ መጀመሪያ የሚሉት ራሴንና ቤተሰቤን ላቋቁም ነው። ይህ በጣም የተሳሳተ ብሎም የማይሆን አካሄድ ነው። ለምሳሌ አንድ ተክል ተተክሎ ተገቢውን እንክብካቤ ሳይደረግለትና አስፈላጊውን ትኩረት ሳይሰጠው እደግ ቢባል ውሎ አድሮ ደራቂ፤ ከሳሚ ነው የሚሆነው፤ ይህ ስራም እንደዛው ነው። አንድ ሰው ወደስራው ገብቶ ቆይ ለራሴ ቤት ልስራ፤ መኪና ልግዛ ዘመዴን ቤተሰቤን ላቋቁም ካለ ነገሮች እዛው ላይ ከስመው ነው የሚቀሩት” በማለት ተሞክሯቸውን ይናገራሉ።

እኛ ስራውን ለመስራት ልጆችን ከችግር አላቀን ተምረው ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ ለማድረግ የብዙዎችን ደጅ መጥናት ይጠበቅብናል፤ እነዛ ረጂ አካላት ደግሞ የሰጡት ገንዘብ ቁምነገር ላይ ውሎ ሲያዩ ነገም ለመስጠት ይበረታታሉ፤ የቲም ሕጻናት መንከባከቢያ ማዕከልም ያገኘውን ሁሉ ልጆቹ ለእናቶቹ ላይ በማዋል ከፍ ያለ ውጤትን ያስመዘገበ ተቋም በመሆኑ ዛሬ ላይ በአንድ የስልክ ጥሪ ብቻ ብዙ እርዳታን ማግኘት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ።

ሀጂ ከማል ስለ ስራው ሲናገሩ የበጎ አድራጎት ስራ በጣም ከባድ ሚስጥር ጠባቂነት የሚጠይቅ ታማኝነት፤ ሀቀኝነትን የሚፈልግ ነው ። አንዳንድ ጊዜ ረጂ አካላት ጥሬ ገንዘብን በማታ በፌስታል ሰጥተው ሊሄዱ ይችላሉ፤ ይህንን ገንዘብ እስከሚነጋ ድረስ በታማኝነት ጠብቆ ማስቀመጥ ትልቅ እድለኝነትንም ይጠይቃል እኔ በዚህ ውስጥ ያለፍኩ ነኝ ይላሉ።

“…….እኔ የቲምን ስመሰርት አብረን ፍቃድ ያወጣነው 13 ነበርን። ነገር ግን የታማኘነቱን ኬላ ማለፍ ተስኗቸው ብዙዎቹ በያሉበት ተንጠባጥበዋል። ግማሾቹ ከስመዋል ግማሹም ለራሱ ማረፊያ ቢሮ እንኳን ሳይኖረው በየሜዳው ይዞራሉ፤ እኔ ግን አባት አያቶቼ ባስተማሩኝ ሀቀኝነትና ታማኝነት እዚህ ደርሻለሁ። ዛሬ ከአገር አልፈን አለማቀፍ እውቅናና ተቀባይነት ያለን ብዙ የሚያግዙን ሰዎችን ማፍራት የቻልን ሆነናል “በማለት ይናገራሉ።

አሁን ላይ ድርጅቱ ባሳየው ውጤት ከጀርመኖች፣ከእንግሊዞች፣ከቱርኮች፣ከአረብ ኤምሬት፣ከዴንማርኮች ጋር ጠንካራ ግንኙነትን መስርቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ሃጂ ከማል ያስረዳሉ።

“……..ሰው ለሚሰራው ስራ ታማኝ ከሆነ ከሰጪ፤ ከመንግስት እንዲሁም ከራሱም ጋር አይጣላም። ነገር ግን በደሃ ስም ራሴን አበለጽጋለሁ ብሎ ከተነሳ ከሁሉም ጋር ከመጣላቱም በላይ ስራውም ዘላቂነት አይኖረውም “ይላሉ።

ሀጂ ከማል በ23 ዓመት የስራ ዘመናቸው በርካታ አስደሳች፤ አሳዛኝ አንዳንድ ጊዜም ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ያውቃሉ፤ ነገር ግን የተፈጥሮ ለጋስነታቸው ሩሁሩህነታቸው ብሎም ለሚሰሩት ስራ ከፍ ያለ ታማኝነት ያላቸው በመሆኑ ሁሉንም ተሻግረው ዛሬ የቆሙበት ደረጃ ላይ ለመድረስ አላቃታቸውም።

ከብዙ ስራዎቻቸው መካከል የማይረሷት አንድ እናት አለቻቸው፤ “……. ባሌ አካባቢ ናት፤ ሴትየዋ 6 ሄክታር መሬት አላት፤ ስምንት ልጆችንም የማስተዳደር ኃላፊነቱ እሷ ላይ የወደቀ ነው፤ ነገር ግን አንድ ኪሎ እህል በቤቷ የለም፤ ሄደን ጠየቅናት ምንድነው ችግርሽ አልናት በሬ፣ዘር፣ማዳበሪያ እያለች ችግሯን አስረዳች፤ በዚህ ወቅት ሁለት በሬዎች፣ሶስት ኩንታል፣ማዳበሪያ ሶስት ኩንታል ዘር ገዛን፤ አራት ኩንታል የዓመት ቀለብ የሚሆናትን እህል ገዛሁና በይ ስራ ስሪ አልኩ፤ በተሰጣት ስጦታ ሰርታ በዓመቱ 47 ኩንታል ስንዴና 7 ኩንታል ባቄላን ማምረት ቻለች። አሁን ሶስት ዓመት ሊሆናት ነው። ምርቷም በዛው ልክ በእጥፍ እያደገ ሴትየዋና ልጆቿም በከፍተኛ ሁኔታ ዘካዋን እያወጣች ትኖራለች” በማለት የስራቸውን ውጤት ይናገራሉ።

ከገጠር ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ 670 ልጆችን በአራዳ፣ጉለሌና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ያግዛሉ። “……ከተማው ላይ ልጆቹ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ከፍ ያለ ትኩረትን እንሰጣለን፤ እስከ አሁንም 360 ልጆች ትምህርታቸውን በአግባቡ ተምረው ከድርጅቱ ወጥተዋል፤ አሁንም ከመቶ በላይ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። ነገር ግን ከተለያዩ ክልሎች ምንም ሰብሳቢ አጋዥ በማጣታቸው ምክንያት በድርጅቱ ውስጥ ማደሪያና መሰረታዊ ነገሮች ተሟልቶላቸው የሚማሩ ልጆች አሉን” ይላሉ።

አዲስ አበባ ከተማ ላይ 284 እናቶችን በመመዝገብ ኮንደምንየም ቤት ምዝገባቸውን በመክፈል መጠለያ እንዲያገኙ ተደርጓል። ቤት ቦታ ኖሯቸው የሚሰሩት ነገር ላጡ እናቶች ደግሞ ከጉሊት ጀምሮ ሱቆችና የተለያዩ በቤት ውስጥ ተሰርተው ገቢ ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎችን እንዲሰሩ እየተደረገ ሲሆን በቀጣይም ከመንግስት ስራ አስፈጻሚዎች ጋር በመነጋገር ችግረኛ የሆኑ ሴቶች በአንድ ላይ ሼድ እንዲያገኙና እኛም እንድናግዛቸው እየሞከርን ነው።

አንድ እንዲታወቅ የምፈልገው ነገር ይላሉ ሀጂ ከማል በገጠርም ሆነ በከተማ የሚሰሩ ስራዎች ሰጥቶ መሄድ ብቻ ሳይሆን ሰዎቹ በተሰጣቸው ነገር ምን ያህል ፍሬ አፈሩ ተማሪዎች በምን መልኩ ነው ለትምህርታቸው ትኩረት እየሰጡ ያለው የሚለው ጥብቅ ክትልል ይደረግበታል፤ እናቶችም የባንክ ደብተር ከፍተው ገንዘብ እንዲቆጥቡ ይደረጋል ።

በሌላ በኩልም በገጠር አካባቢ ያሉ ሴቶች የወር አበባቸው በሚመጣበት ጊዜ አስፈላጊው የንጽህና መጠበቂያ ስለማይኖራቸው ከትምህርት የመቅረት የመሳቀቅ ሁኔታ አለና ድርጅቱ ይህንን ችግር ለመፍታት 8 ሚሊየን ብር ገደማ በመመደብና ከቱርክ በጎ አድራጊዎች ጋር በመተባበር የሚታጠብ ሞዴስ ማምረቻ ፋብሪካን በግቢው ውስጥ አቋቁሞ ምርቱን እያመረተ ለብዙዎችም የስራ እድል ፈጥሮ እየሰራ ነው።

አብሮ የመኖር ባህላችን

ኢትዮጵያ የእስላምም የክርስቲያንም አገር ናት። ከሁሉ በላይ ደግሞ መካና ሳውዲ አረቢያ እንኳን እስልምናን ሳይቀበሉ የተቀበለች አገር ናት። ሕዝቧም ድንቅ ሕዝብ ነው። እኔም በስራዬ እስላም ክርስቲያን ይሉት ክፍፍል አድርጌ አላውቅም፤ ወደፊትም አላደርግም፤ ፈጣሪም ያለው ነብያችንም ያስተማሩን የተራበን አብሉ አጠጡ የታረዘን አልብሱ እንጂ በዘር በሃይማኖት እየከፋፈላችሁ እርዱ አላሉም። እኔ ማነኝና ነው ክፍፍል ውስጥ የምገባው። የምሰራው በሙስሊምነቴ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቴ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ነው ይላሉ ።

በመሰረቱ የእርዳታ ድርጅት ተሁኖ ፖለቲካውም ሀይማኖቱም አይቅርብኝ ከተባለ መስራት አይቻልም። እኔ ከዚህ ነጻ ሆኜ የተቸገሩ የገጠር ልጆቸንና እናቶችን በከተማም ሁኔታዎች ያልተመቿቸውን የቲም የሆኑ ሕጻናትን ከመንግስት እየተቀበልኩ የሀይማኖት ልዩነት ሳላደርግ መስራት ነው የምፈልገው፤ እሱንም እያደረኩ ነው። እውነት ለመናገር ሌሎች ራሳቸው መጥተው እኛ ቤት የሚሰራውን ቢያዩ ትምህርት ይሆናቸዋል።

“…….በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ተካፍሎ የመብላት ተባብሮ የመኖር በችግር በደስታችን የመገናኘት ባህላችን ሕዝቡ ጋር እንዳለ ነው፤ ፖለቲከኞቹ ጋር ግን ጠፍቷል፤ ተበላሽቷል።የሀይማኖት አባቶች ጋርም ይህ ችግር ገባ ወጣ እያለ ነው። ከከተማም ወጣ ብለሽ ብታየ ሕዝቡ የቀደመ ፍቅርና መተባበሩ ላይ ነው፤ አብሮ ያርሳል እህል ሲደርስ ለእስላም ለክርስቲያን ብሎ አርዶ ተደስቶ በጋራ ይበላል፤ ይጠጣል፤ ልጆቹን ይድራል፤ ሀዘኑን በጋራ ይወጣል፤ እናም ፍቅሩ እንዳለ ነው። ነገር ግን ፖለቲከኞች ስራቸው ስለሆነ ፕሮፖጋንዳ ይሰራሉ። ሚዲያውም እነሱን ተቀብሎ የማይገናኝ ወሬን ያወራል፤ ይህ ቢታረም ደስ ይለኛል” ይላሉ።

ከከተማ ወጣ ተብሎ ትንሽ ኪሎ ሜትሮች መሄድ ቢቻል ሕዝቡ የድሮ እንግዳ አቀባበሉ ላይ ነው ያለው፤ ብሉ ጠጡ ማለት ያውቅበታል። እንዳልኩሽ እኛ እዚህ ቁጭ ብለን የምንሰማውና መሬት ላይ ያለው ነገር አይገናኝም የሚሉት ሀጂ ከማል አሁን እንኳን በቅርቡ ወደ ጫንጮ ሄጄ አንድ ተማሪ ጠራሁና “……አንተ ልጅ ቤተሰቦችህ አሉ እኛ ከሩቅ ነው የመጣነው፤ ተርበናል፤ የሚበላ የሚጠጣ ስጠን፤ ስንለው በጣም በሚገርም ደስታና ፈገግታ ግቡ ጠላ አለ እንጀራም በሚጥሚጣ ትበላላችሁ ወተት ብቻ ነው የሌለው ነው ያለን አንጂ አንተ እንደዚህ ነህ እንደዚያ የሚል ሀሳቡ ላይም አልመጣም። እንግዲህ ኢትዮጵያውያን ይህ ነን” በማለት የቆየው እኛነታችን አብሮን መዝለቁን ያስረዳሉ።

ስኬት

ሀጂ ብዙዎች ቢያልሙና ቢመኙም ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠን መልካም ስራ በመስራት ላለፉት 23 ዓመታት ቆይተዋል።በሰሯቸው ስራዎች ከገጠር እስከ ከተማ ብዙ ስኬቶችን ለማየት የቻሉ ናቸው። እሳቸው ጋር የሁለት የሶስት የአምስት ዓመት ሕጻናት ሆነው መጥተው አድገው ተምረው ዛሬ ላይ ዳኛ የሆኑ፣ ቢቢሲ የዜና ማዕከል የገቡ፣ቱርክ፣ባህሬን፣ዱባይ፣ካናዳ እንዲሁም በሌሎች የዓለም አገራት ላይ በመሄድ የራሳቸውን ስራና ኑሮ እየኖሩ ለሌሎችም እየተረፉ ያሉ ብዙዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። በያዝነው ዓመት እንኳን ስድስት ልጆች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተው ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል።

በዓልና ሀጂ ከማል

“……እንደ በዓል ረመዳንን እወደዋለሁ፤ ምክንያቱ ደግሞ ድሮም አባቴ ቤት ሆኜ ወደዚህ ስራ ከገባሁም በኋላ ረመዳን ሲሆን ብዙ ችግረኞችን እናግዛለን፤ እናስፈጥራለን በተለይም 18 ዓመት ሙሉ ሰላሳውንም ቀን በግቢያችን ከ 650 እስከ 700 ሰው በየቀኑ እናስፈጥራለን ያ ልዩ ስሜትን የሚፈጥር ነው” ይላሉ።

በሌላ በኩልም ረመዳን ንፉግ የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ራሱ እጃቸው የሚፈታበት ካላቸው ለማካፈል የሚፈቅዱበት ወር በመሆኑ ለእኔ ልዩ ነው በማለት ይናገራሉ።

በነገራችን ላይ ግን አረፋ ታላቅ በዓል ነው። ሙስሊሞችም የሚደሰቱበት ነው በእስልምናም አምስተኛ ደረጃ ላይ ያለ ትልቅ እለት ነው፤ ከዚህ ከዚህ አንጻር ደስ ይለኛል። እኔም ከወገኖቼ ጋር በመሆን በዓሉን በደስታ አሳልፋለሁ ።

የቤተሰብ ሁኔታ

ሀጂ የቤተሰብ ሁኔታቸውን ለመግለጽ በጣም ነው የሚከብዳቸው፤ የሚከብዳቸውም ብቻ ሳይሆን እንባ ይቀድማቸዋል፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ከወለዷቸው በላይ እሳቸውን አምነው ተማምነው አባዬ እያሉ አስር እስራቸው የሚሉት የቲም ልጆች ውስጣቸውን ስለሚያንሰፈስፉት ነው፤ አዎ እኔም ያየሁት ይህንኑ ነው፤ ሀጂ ቢሯቸው ባለበት ሰባራ ባቡር አካባቢ ያለው የቲም ሕጻናት እንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ያሉት ልጆች ሲያዯቸው ፊታቸው ይበራል። አባት አለን የሚለው ስሜታቸው ከፊታቸው ይነበባል፤ አባ እያሉ ይጠሯቸዋል፤ የሚፈልጉትን ነገር ይጠይቋቸዋል የከፋቸውን ያማክሯቸዋል። ሀጂም በምላሹ ሊሟላላቸው የሚገባው አሟልተው፤ አማክረው የትምህርት ውጤታቸውን ተከታትለው የደከመውን አበረታተው የጎበዘውን ሸልመው የአባት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ ።

“……..እኔ የወለድኳቸው ሶስት ልጆች አሉኝ። ነገር ግን የቲም ሕጻናት እንከብካቤ ማዕከል ውስጥ ከ 30 በላይ ሕጻናት በቋሚነት ይኖራሉ፤ እነዚህ ልጆች አላህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው “ባባ” ብለው ከትምህርት ቤት ሲመጡ አቅፈው ስመውኝ ውሏቸውን ሲነግሩኝ ልቤ ይነካል፤ እውነት ለመናገር ቤቴን አላውቀውም፤ እዚሁ ከእነሱ ጋር ነው የምውለው፤ ይህ ደግሞ በጣም ደስተኛ አድርጎኛል፤ እነዚህን ልጆች ከወለድኳቸው ልጆቼ ማበላለጥም ይህንን ያህል ልጆች አሉኝ ብሎ ማለትም በጣም ይከብደኛል “ በማለት ከእንባ ጋር ይናገራሉ።

ሀጂ የወለዷቸውን ልጆች እንደሚያሳድጓቸው ልጆች ትኩረት አይሰጧቸውም። ምክንያቱም እነሱ እናታቸው የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ሊያሟሉላቸው ይችላሉ ብለው ስለሚያምኑ ነው፤ እየሆነም ያለው እንደዛው ነው።

“……. እኔ ስለ አረፋ በዓል አከባበር ሳስብ ስለ ሶስት የአብራኬ ክፋይ ልጆቼ ብቻ ሳይሆን ስለ ሺዎች የቲም ሕጻናት ነው የማስበው፤ በምን መልኩ ነው እነሱን አስደስቼ በዓል የማከብረው የሚለው ነው የሚያስጨንቀኝ “ ይላሉ።

መጀመሪያ አካባቢ ስራው በጣም ይከብዳቸው እንደነበር የሚናገሩት ሃጂ ከማል ምክንያታቸው ደግሞ ሀጂ የብዙዎች መሆናቸውና ጊዜና ገንዘባቸውን ለቤቴ የማይሉ ለጋስ አባወራ መሆናቸው ነበር። ይህ ደግሞ በተለይም መጀመርያዎቹ አካባቢ ለባለቤታቸው በጣም ፈታኝ ነበር።

“……ባለቤቴ መጀመሪያ አካባቢ እንግዳ ሲበዛበኝ ከድርጅቱም አልፎ ስራው ቤቴ ድረስ እየሄደ ብዙዎች ቤት ማደር መዋል ሲጀምሩ በጣም ይከብዳት ነበር፤ ነገር ግን እኔ ፈጣሪዬንም ለምኜ ለእሷም እኔ ከሰፊ ቤተሰብ ነው የወጣሁት ብቻዬን መብላትም መኖርም አልችለም እንደውም ቀን 16 ሰው ምሳ ቤት እንዲበላ ማታም በተመሳሳይ 14 ሰው እራት እንዲበላ እፈልጋለሁ በማለት ቁርጡን ነግሬ ሙሉ ትኩረቴን ስራዬ ላይ ነው ያደረኩት።አሁን ፈጣሪ ይመስገን ከእኔ ይበልጥ ለስራዬ የምትጨነቅ ልጆቹንም ከእኔ በላይ የምትወድና የምትንከባከብ ሆናለች” በማለት ያስረዳሉ።

ዛሬ ላይ ባለቤታቸው ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን አስቤዛ በማድረግ ልብስ ጫማቸውን በመግዛት የትምህርት ቤት ክፍያ በመክፈልና ውጤታቸውን በመከታተል ብቻ ለድርጅቱ ቀኝ እጅ ሆነው የባለቤታቸውን የበጎ ስራ እየደገፉ አብረው እየኖሩ ነው።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You