ከለውጡ በፊት በነበሩት 27 ዓመታት አጋር በሚል አግላይ ስም ተፈርጀው በሀገራቸው ጉዳይ እኩል የመወሰን፣ የመጠየቅና የመጠቀም መብት ከተነፈጉ ክልሎች አንዱ የሶማሌ ክልል ነው። በኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ከጀመረ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ የሶማሌ ክልል ሕዝብ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ችሏል።
ለዘመናት በልማት ወደ ኋላ ተጎትቶ የኖረው የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ ሰላማቸውን አስጠብቀው በልማትና እድገት አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ከሚገኙት ክልሎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እስከመሆን መድረሱ እየተገለጸ ነው። ሕዝቡ ለበርካታ ዓመታት ሲያነሳቸው የነበሩ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የትምህርት፣ የጤና እና የሌሎችም መሰረተ ልማት ጥያቄዎች መልስ እያገኙ መጥተዋል። አንዳንዶቹም መሰረተ ልማቶች ከለውጡ በፊት ከነበረው ቁመናቸው በእጥፍ እስከማደግ ደርሰዋል።
በቅርቡ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባደረግነው የመስክ ምልከታ ከመሰረተ ልማት አውታሮች አንዱ በሆነው የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ አበረታች ተግባሮች መከናወናቸውን መመልከት ችለናል። ከለውጡ በፊት፤ የሶማሌ ክልል እንዳለው የቆዳ ስፋት እና ከሌሎች ክልሎች እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር እንዳለው ሰፊ ወሰን የመንገድ መሰረተ ልማት የተስፋፋበት እንዳልነበር የክልሉ ነዋሪዎችና አመራሮች ገልጸውልናል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ክልሉ ሰላሙን አስፍኖ ፊቱን ወደ ልማት በማዞሩ በተለይም በመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ውጤታማ ሥራዎች መስራት ችሏል። በዚሁ መሰረት ገጠርን ከከተማ፤ ከተማን ከከተማ ያስተሳሰሩ የአስፋልትና የጠጠር መንገዶች ተሠርተው ለሕዝቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ክልሉ በሚያስተዳድራቸው አስራ አንዱም ዞኖች የሚቀርቡ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንደ ቅደም ተከተላቸውና እንደ አስፈላጊነታቸው መጠን እየታዩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። ለአብነት በመስክ ጉብኝታችን ከተመለከትናቸው የመንገድ ግንባታዎች አለፍ አለፍ እያልን የተወሰኑትን እንመልከት።
በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ከተስፋፋባቸው ዞኖች አንዱ የኤረር ዞን ነው። ከለውጡ በፊት በዞኑ ምንም አይነት አስፋልት መንገድ አልነበረም። ከለውጡ ወዲህ ግን ሶስት ትልልቅ የአስፋልት መንገዶች ተገንብተዋል።
የመጀመሪያው የኤረር ዞን ዋና ከተማ ፊቅን እና የኦሮሚያ ክልል ባቢሌ ከተማን የሚያገናኘው የአስፋልት መንገድ ሲሆን አስፋልቱ እስከ 170 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። ሁለተኛው ከፊቅ – ያሆር- ገርቦ እስከ ጎዴ ድረስ የሚዘልቀው የአስፋልት መንገድ ነው፤ ይህም መንገድ ከጂግጂጋ በስተምዕራብ በኩል መዳረሻውን ጎዴ አድርጎ በርካታ ወረዳዎችን እያካለለና እያስተሳሰረ ይዘልቃል። ሶስተኛው ከፊቅ- ሀመሮ- ኢሜ ድረስ የሚዘልቀው ረዥም የአስፋልት መንገድ ነው።
እነዚህ መንገዶች በፌደራል መንግሥት በጀት የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ናቸው። ከእነዚህ አስፋልት መንገዶች በተጨማሪም ክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ያሠራቸው የጠጠር መንገዶች በርካታ ናቸው።
የፊቅ ከተማን ከባቢሌ ከተማ የሚያገናኘው መንገድ የኦሮሚያን እና የሶማሌ ክልሎችን ያስተሳስራል፤ መንገዶቹ በአጠቃላይ የአካባቢውን የትራንስፖርት ችግር የፈቱ ከመሆኑም ባሻገር የንግድ ልውውጥና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በማቀላጠፍ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የአካባቢው የመስተዳዳር አካላትና ነዋሪዎች ገልጸዋል።
መንገዱ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ከገበያ ጋር ለማገናኘት እንደጠቀመና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ያስረዳሉ። ከአሁን በፊት በአካባቢው ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ማከናወን አስቸጋሪ እንደነበር የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፣ ከለውጡ ወዲህ የአካባቢው ሰላም በመጠበቁ መንገድን ጨምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች በመሰራታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ያመለክታሉ።
በዶሎ ዞን ዋርዴር ከተማ ያገኘናቸው ነዋሪዎች ግን ከተጀመረ ስድስት ዓመታትን የፈጀው የዋርዴር ቀብሪደሃር አስፋልት መንገድ በመዘግየቱ ቅሬታ እንደተሰማቸው ገልጸውልናል።
ዋርዴር በሶማሌ ክልል የዶሎ ዞን ዋና ከተማ ነች። ከቀብሪደሃር ከተማ በስተምስራቅ 125 ኪሎ ሜትር ገባ ብላ የምትገኝ የጠረፍ ከተማ ስትሆን፣ ዶሎ ዞንን ከሌሎች ዞኖች ጋር ታስተሳስራለች። ከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ይስተዋልባታል።
ከቀብሪደሃር – ዋርዴር የሚሠራው የአስፋልት መንገድ ለከተማዋ እድገት ተስፋ የሰነቀና ለነዋሪዎች ደስታን የፈጠረ ቢሆንም፣ መንገዱ ዛሬም ድረስ ባለመጠናቀቁ የአካባቢውን ነዋሪዎችን ቅር አሰኝቷል።
ወይዘሮ ሀምዱ ሁሴን የዋርዴር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ዋርዴር ለዘመናት የመንገድ፣ የመብራት፣ የንጽህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ የነበረባት ከተማ ስለመሆኗ ያስታውሳሉ። የውሃና የመብራት ጥያቄዎቿ ከለውጡ ወዲህ ባሉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት መመለሳቸውን ገልጸው፣ እየተሠራ ያለው አስፋልት መንገድ ተጠናቆ አገልግሎት የሚሰጥበትንም ቀን በናፍቆት እየጠበቁ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
የመንገድ ሥራው የዛሬ ስድስት ዓመት እንደተጀመረ የተናገሩት ወይዘሮ ሀምዱ እስከ አሁን የመዘግየቱ ጉዳይ እርሳቸውን ጨምሮ የከተማዋን ነዋሪዎች ቅር እንዳሰኘ ጠቁመዋል። ‹‹እናት ልጆቿን ከረሜላ አመጣላችኋለሁ እያለች እንደምታባብል ሁሉ አመራሮቻችን ሁሉም ታገሱ ይሉናል›› ያሉ ወይዘሮ ሀምዱ፣ የከተማው ሕዝብ እስከ አሁን ድረስ በትዕግስት እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል። ሰሞኑን ግን መንገዱ በበጀት ምክንያት ሥራው ተቋርጧል መባሉን መስማታቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹የሚመለከተው አካል መንገዱን በፍጥነት አጠናቆልን አፎይ እንድንል ሊያደርገን ይገባል›› ብለዋል።
ወይዘሮ አብሽሮ ሁሩ ሌላዋ አስተያየት የሰጡን የዋርዴር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከለውጡ በኋላ ከተማችሁ ምን ለውጥ አገኘች? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ‹‹ወላሂ በአካባቢው ሰላምና ጸጥታ ከሰፈነ በኋላ በርካታ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ውሃ ገብቷል፤ ሆሰፒታል ተሠርቷል፤ በተለይ ከቀብሪደሃር ዋርዴር እየተሠራ ያለው የአስፋልት መንገድ አላለቀም እንጂ ቢያልቅ ኖሮ ከተማችን በደንብ ትቀየር ነበር፤ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በአስቸኳይ መንገዱን እንዲጨርስልን እንፈልጋለን›› ሲሉ ምላሻቸውን ገልጸዋል።
እኛም የነዋሪዎችን አስተያየት ለሚመለከተው አካል ለማድረስ በገባነው ቃል መሰረት በአጠቃላይ በመሰረተ ልማት ግንባታውና በተለይ ነዋሪዎቹ ባነሱት ቅሬታ ላይ ያነጋገርናቸው የዋርዴር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መውሊድ ቱርሃ ‹‹ክልሉ ሰላሙን ካረጋገጠ በኋላ የዶሎ ዞን በተለይም በመንገድ ዘርፍ የሚያነሳው የዘመናት ጥያቄ ሊመለስ ጫፍ ደርሷል›› ሲሉ ይገልጻል።
ሕዝቡ በግንባታው መጓተት ቅር የተሰኘበት መንገድ የሚሠራው በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለቤትነት መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታው በተለያየ ጊዜ በመቋረጡ ምክንያት በፍጥነት መጠናቀቅ አለመቻሉን በጋራ መድረክ ገምግመናል ይላሉ። ሥራው 58 በመቶ ደርሶ በበጀት እጥረት ምክንያት ለጊዜው እንደተቋረጠ በግምገማው መድረክ ተገልጾልናል ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በቅርብ ጊዜ ተጠናቆ ለማኅበረሰባችን አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር እምነታችን ነው።›› ሲሉ ተናግረዋል።
ዋርዴር ከፑንትላንድ በቅርብ ርቀት የምትገኝ የጠረፍ ከተማ እንደመሆኗ እየተሰራ ያለው መንገድ ዋረዴር ላይ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ድንበር ድረስ ዘልቆ ለቀጠናዊ የንግድ ትስስር እንዲሁም በክልሉና በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እንፈልጋለንም ብለዋል።
ዋርዴር በፑንት ላንድ ከምትገኘው ገርአብ ወደብ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደምትገኝ ተናግረው፣ በዚህ አካባቢ የመንገድ መሰረተ ልማት መስፋፋቱ ወደፊት በሀገራቱ መካከል በሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ትስስር አካባቢያዊ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊና ቀጠናዊ ፋይዳ ይዞ እንደሚመጣም ተናግረዋል።
በጉብኝታችን በሸበሌ ዞን ጎዴ ከተማ፣ በኮሬይ ዞን ቀበሪደሃር ከተማ፣ በጀረር ዞን ደጋሃቡር ከተማ፣ በሲቲ ዞን ሺኒሌ ከተማና በክልሉ ዋና ከተማ ጅግጂጋ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶች መሰራታቸውንም ተመልክተናል። በዚህም ነዋሪዎች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል።
ከመስክ ምልከታችን በኋላ የመንገድ መሰረተ ልማትን በተመለከተ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ እንዳብራሩልን፤ ክልሉ ከሰላም እጦት ባሻገር ለረዥም ጊዜ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ብዙም ስላልነበሩት ከፍተኛ የሕዝብ ሮሮ ይሰማበት ነበር።
ከለውጡ በኋላ በተገኘው ሰላም፤ የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት ከበጀት አቅርቦት ጀምሮ በሰጡት ትኩረት በተለያዩ ሴክተሮች በርካታ የልማት ሥራዎች መሥራታቸውን ገልጸው፤ በተለይም ከመንገድ መሰረተ ልማት አንጻር ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰዋል።
ከለውጡ በፊት በአንዳንድ ክልሎች በወረዳ ደረጃ የአስፋልት መንገድ ተደራሽነት ጥሩ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ሲገለጽ እንደነበር አስታውሰው፣ በሶማሌ ክልል በዞን ደረጃ ሆነው አስፋልት ያልደረሰባቸው ቦታዎች እንደነበሩም አመልክተዋል። ከለውጡ ወዲህ ክልሉ በተለይም በፌደራል መንግሥት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተከትሎ ከሁለት ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆኑ ከ17 በላይ የአስፋልት መንገዶች መገንባታቸውን አቶ ሙስጠፌ ገልጸዋል።
በበጀት እጥረት እና በኮንትራክተሮች ድክመት ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች መጓተት የታየባቸው የመንገዶች ግንባታዎች ስለመኖራቸውም እሳቸውም ጠቅሰዋል። ከቀብሪደሃር ዋርዴር ያለው የመንገድ ፕሮጀክት የዚህ አንዱ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል።
በፕሮጀክት ደረጃ ያሉት ጥቂት መንገዶች ሙሉ ለሙሉ አልቀው አገልግሎት ሲሰጡ የንግድ እንቅስቃሴዎችንና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድጉት አስታውቀው፣ የሕዝቡ እርካታም ከእስከ አሁኑም በላይ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
አቶ ሙስጠፌ እንዳሉት፤ በክልሉ አጠቃላይ ከነበረው አንድ ሺ 200 ኪሎ ሜትር የሚገመት የገጠር መንገድ ላይ ሌላ አንድ ሺ ኪሎ ሜትር በመጨመር እስከ ሁለት ሺ 200 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተሰርቷል። አንዳንድ ቦታ ላይ መጠናቀቅ የሚጎድላቸው ውስን መንገዶች እንዳሉም አንስተው በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሠራም ነው ብለዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የክልሉን ዋና ከተማ ጅግጅጋን ጨምሮ በከተሞች አካባቢ በጣም ከፍተኛ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ነበር። ከከተማ ልማት አንጻር መንገዶች ወሳኝ መሆናቸው ስለታመነበት በአጠቃላይ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ አስፋልት ያስፈልጋቸዋል በተባሉ አራት ትላልቅ ከተሞች ማለትም በጂግጂጋ፣ በደጋሃቡር፣ በቀብሪደሃርና በጎዴ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገዶች ተሰርተዋል።
የጂግጂጋ ከተማ ከለውጡ በፊት የነበረው መንገድ ከስምንትና ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ያልበለጠ እንደነበር እና በአሁኑ ጊዜ ወደ አርባ ኪሎ ሜትር እንደተሠራ አብራርተው፣ ጎዴ እስከ 16 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ተሠርቶ ግምሹ ለአግልግሎት ክፍት እንደተደረገ አስታውቀዋል። በቀብሪደሃርና ደጋሃቡርም ከ5 እስከ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶች እንደተሠሩ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ ክልሉ ካለው የቆዳ ስፋት አንጻር የተገነቡት መንገዶች በቂ ናቸው ማለት እንደማይቻል የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ፣ ከነበረው ችግር አንጻር ግን በጣም ጥሩ ጅምር ሥራዎች እንደተሠሩ አስታውቀዋል። እነዚህም ሕዝብና መንግሥትን በከፍተኛ ደረጃ ያቀራረቡ እንዲሁም የክልሉን ገጽታ የቀየሩ ስለመሆናቸው አቶ ሙስጠፌ አስታውቀዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም