ለለውጥ ጉዟችን ስኬት ማኅበረሰባዊ ስክነት ወሳኝ ነው!

ለውጥ ሰብዓዊ መሻት ነው። በለት ተለት ህይወታችን የሚያጋጥመን / የሚሰማን ከየትኛውም አሮጌ ነገር ጋር አብሮ ያለመቆየት መነቃቃት ነው። ማኅበረሰባዊ ለውጥም ከዚህ ተጨባጭ እውነት የሚቀዳ፤ የማኅበረሰብ መሻት ነው። አግባብ ባለው መንገድ በጠንካራ ዲሲፕሊን ከተመራ ማኅበረሰብን ወደ ተሻለ ቀጣይ የሕይወት ምዕራፍ ማሻገር የሚያስችል ትልቅ አቅምም ነው።

የሰው ልጅ እንደ አንድ ማኅበረሰብ አሁን የደረሰበት የሥልጣኔም ሆነ የእድገት ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው በየዘመኑ በተፈጠሩ የለውጥ መነቃቃቶች እና መነቃቃቶቹ በፈጠሩት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ነው። በቀጣይም ዓለምን ለሰው ልጅ የተሻለች የመኖሪያ አካባቢ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የተለያዩ የለውጥ መሻቶች ከሚፈጥሩት ፍላጎት የሚመነጭ እንደሚሆን ይታመናል።

በእኛም ሀገር በተለያዩ ወቅቶች በተለያየ መንገድ የተገለጡ የለውጥ መነሳሳቶች /ህሳቤዎች ተስተውለዋል። እነዚህ መነሳሳቶች እንደ ማኅበረሰብ ሕዝባችንን ወደ አንድ ከፍ ያለ የታሪክ ምዕራፍ የማሻገር ማነቃቃት አቅም እንደነበራቸው የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ። ስለ መነቃቃቶቹም ትውልዶች ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይህም ሆኖ ግን እንደ ማኅበረሰብ የተፈጠሩ የለውጥ መሻቶችን ተፈጥሯዊ መሆናቸውን ካለመረዳት፤ ከዚያም ባለፈ የለውጥ መሻቶችን ተጨባጭ አድርጎ በተግባር ለመተርጎም የተሄደበት መንገድ በለውጥ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ተቃርኖዎችን መሻገር የሚያስችል ስክነት በመታጣቱ፣ አብዛኞቹ የለውጥ መነቃቃቶች የታሰበላቸውን ያህል ፍሬ ማፍራት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በተለይም ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የመጣንበት መንገድ ያስተናገዳቸውን ሀገራዊ የለውጥ መሻቶች ተጨባጭ ለማድረግ የተሄደባቸው መንገዶች አብዮታዊ የመሆናቸው እውነታ፤ ለማኅበረሰቡ የለውጥ መሻት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በማኅበረሰብ ውስጥ ተጨማሪ የተቃርኖ እሳቤዎችን በመፍጠር ስለለውጥ ያሉ አስተሳሰቦች አሉታዊ ትርጓም እንዲላበሱ አድርጓቸዋል።

ስለለውጥ የሚያቀነቅኑ ፤ ለለውጥ እሳቤዎች ራሳቸውን የሰጡ እና የሚተጉ ቡድኖች እና ግለሰቦች ወደ አደባባይ ሲመጡም በቀደመው የለውጥ ተሞክሮዎች ጥላ ውስጥ በማስቀመጥ ፤ አብዮታዊ ሆነው የሚገለጡበትን መንገድ የመጠበቅ አዝማሚያዎች በስፋት የሚስተዋሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

እንደ ሀገር ትውልዶች ሲቀባበሉት የመጡት ለሕዝባችን የለውጥ መሻት በመሠረታዊነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ድህነትን እና ኋላቀርነት ፤ ከዚህ የሚመነጭ ጠባቂነት የፈጠረውን ሀገራዊ ትርክት የመለወጥ ቁጭት ነው፤ ሀገርን እንደ ሀገር ወደቀደመው የከፍታ ርካብ መልሶ የማውጣት መሻት ነው ።

ይህ አይነቱ የማህበረሰብ መሻት ተቃርኖዎች በሚፈጥር አብዮታዊ የትግል መስመር የሚፈታ አይደለም። በተለይም እንደኛ ባሉ ብዝኃነት መለያቸው በሆነ ፤ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። የቀደሙት የአብዮታዊ የለውጥ ትርክቶቻችንም የሚያመላክቱት ይህንኑ እውነታ ነው።

በእኛ ሀገር ያለውን የለውጥ መሻትን ማስተናገድ የሚቻለው ከሁሉም በላይ ፤ የተለያዩ ፍላጎቶችን ማስተናገድ የሚያስችል ሀገራዊ የአስተሳሰብ መሠረት መገንባት ስንችል ነው። ለዚህ ደግሞ ከተለማመድነው አብዮታዊ አካሄድ ወጥተን ከፍ ያለ ማኅበረሰባዊ መረጋጋት /ስክነት ውስጥ መግባት እና ስክነት ወደሚፈጥረው አርቆ አሳቢነት መሸጋገር ይኖርብናል።

የለውጥ መሻት ተፈጥሯዊ እንደሆነ ፤ ለውጥም ለስኬታማነቱ እና ትርጉም ላለው ዘላቂ ተፈጥሯዊ ሂደቱ ስክነት ይፈልጋል። ስክነት ማኅበረሰባዊ የለውጥ መሻትን በአግባቡ ከመረዳት የሚመነጭ ፤ ራስን የለውጥ አልፋና ኦሜጋ አድርጎ ከማሰብ የሚታደግ ፤ ከዚያ ይልቅ ራስን እንደ አንድ የለውጥ ኃይል አድርጎ ማሰብ የሚያስችል ውስጣዊ አቅም ነው።

ማኅበረሰባዊ ስክነት ዛሬን ከትናንት በማስታረቅ ፤ ነገን በተሻለ ተስፋና ተስፋው በሚወልደው ማኅበራዊ ትጋት መጠበቅና መጨበጥ የሚያስችል ጉልበት ነው ። የለውጥ መሻቶችን ያለብዙ አላስፈላጊ ዋጋ እውን ማድረግ ፤ ትውልድ ተሻጋሪ ማኅበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶችን ለመፍጠር እና ለመተርጎም የተሻለ ዕድል የሚፈጥር ነው ።

በተለይም አሁን ላይ እንደ ሀገር ከትናንቶች እና ትናንቶቻችን እያስከፈሉን ካሉ ያልተገቡ ዋጋዎች ወጥተን ፤ የጀመርነው አዲስ የለውጥ መንገድ ውጤታማ እንዲሆን ፤ በለውጡ ያሰብነው የመለወጥ መሻታችን እውን እንዲሆን ከሁሉም በላይ ማህበራዊ ስክነት ያስፈልገናል።

ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ አሁናዊ እውነታዎችን ከነገ የለውጥ ተስፋው ጋር አጣጥሞ በስክነት መጓዝ ፤ ማህበረሰባዊ የለውጥ መነሳሳት ማኅበረሰባዊ ከዚያም በላይ ትውልዳዊ ግብ እንዳለው በመረዳትም ፣ ከገነገነ እኔነት ወጥቶ ለማኅበረሰባዊ ማንነቱ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ለጀመርነው ለውጥ ሁለንተናዊ ስኬትም ያለው መልካም አማራጭም ይኸው ነው!

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You