የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን የማሳደጉ ሥራ የመላው ሕዝባችንን የተቀናጀ ጥረት ይፈልጋል!

ለአንድ ሀገር የእድገት ጉዞ ስኬት ከሆኑት መካከል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም እንደሆነ ይታመናል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የማይፈልግ ሀገር የለም፡፡ አድገዋል የሚባሉት እንደ ቻይና ያሉት ሀገሮችም ጭምር ይህን የልማት አቅም በእጅጉ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ኢንቨስትመንት በተለይ ለድሃ እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገሮች ደግሞ ትልቅ አቅም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የእነዚህ ሀገሮች የልማት እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ይህ ኢንቨስትመንት ወሳኝ መሆኑም ይታመንበታል፡፡

እነዚህ ሀገሮች ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት እና አምራች ዜጋ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ሀገሮቹ የሚያንሳቸው ወይም የሌላቸው ካፒታል፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ደሃ ወይም በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገሮች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብትና አምራች ዜጋ ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ የሆነ የካፓታል እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡ በዚህ ላይ እውቀትና ቴክኖሎጂ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይህን ሁሉ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ይታመናል፡፡

ከዚህ በመነጨም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማፈላለግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የመወዳዳሪያ መድረክ እየሆነ መጥቷል። ሀገራት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ያለበት ሁኔታም በስፋት ይስተዋላል። ውድድሩም በብዙ መልኩ ጠንካራ ሆኖ መገኘትን እየጠየቀ ይገኛል።

ሀገራችን ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ሃይል በስፋት ወደ ልማት ለማስገባት ይህንኑ ዓለምአቀፋዊ እድል አሟጣ ለመጠቀም የሚያስችሉ ጥረቶችን ስታካሂድ ቆይታለች። ይህን ተከትሎ እየተገኘ ያለው ውጤትም ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ፤እንደ ሀገር ከዘርፉ ከሚጠብቀው፣ እንዲሁም ለመልማት ካላው ጽኑ ፍላጎጽ አኳያ ሲታይም ገና ብዙ መሰራት እንደሚኖርበት ይታወቃል።

በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር በልማት ድህነትን ለመሻገር የተጀመረው ሀገራዊ የልማት ንቅናቄ ስኬታማ እንዲሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም እንደሆነም ይታመናል ። ይህንን አቅም አሟጦ ለመጠቀም የሚደረገውም ጥረት የሁሉንም አካል ጥረት ይጠይቃል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በዚህ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ከፍተኛ ተወዳዳሪነት እየጠየቀ ባለበት አሁናዊ ሁኔታ ፣ የዕድሉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን በቂ ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርም ወሳኝ ይሆናል። ከዚህ አንጻር በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት እና እየተመዘገበ ያለው ውጤትም ተስፋ ሰጪ ነው።

ሀገሪቱ ከሀገራት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት ስትራቴጂክ ወደሆነ የልማት አጋርነት ከመለወጥ የሚጀምረው የመንግሥት ጥረት፤ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ለውጭ ዜጎች ዝግ የነበሩ እንደ ወጪና ገቢ ንግድ ያሉ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ ፣ የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለውጭ ባለሀብቶች ማስተዋወቅ ፣ ሀገር ውስጥ ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሀብቶች የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋትም የዚሁ ጥረቱ አካል ናቸው።

በዓመቱ ሦስት የቻይና ኢንዱስትሪዎችና ሁለት የህንድ ኩባንያዎች በሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሼዶችን በመውሰድ ሥራ የጀመሩበት ሁኔታም የዚህ ጥረት ማሳያዎች ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎቹ የሀገሪቱን የውጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንት በማሳደግ በኩል የጎላ ሚና ነበራቸው።

ከነዚህ ውጭም ሌሎች የቻይና ፣ የኔዘርላንድና የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየተሳተፉ ይገኛሉ ። ከአውሮፓ፣ አሜሪካና ኢሲያ የመጡት ትልልቅ ኩባንያዎችም እንዲሁ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሥራት ወስነው እየተንቀሳቀሱ ነው።

በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ ባለሀብቶች ጋር የተደረገው ውይይት እና በውይይቱ ማጠናቀቂያ የታየው ተስፋም ሆነ ፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር በሲንጋፖር እና በደቡብ ኮሪያ ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ከሀገራቱ ጋር በኢንቨስትመንት ዙሪያ የደረሱባቸው መግባባቶችም እንዲሁ የዚሁ የመንግሥት ጥረት ማሳያዎች ናቸው።

ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዕድገቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተቋቋሙ የሚገኙትና ብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትልቅ የሚባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እየጨመረ መሄድ እና መሰል አሁናዊ ልማቱ የፈጠራቸው ዕድሎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ፍሰት አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህም ሆኖ ግን ይህንን እድል በአግባቡ እንዳንጠቀምበት ተግዳሮት ሆነው የቆዩት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩትን የጸጥታ ችግር ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፣ የቢሮክራሲ ማነቆዎች … ወዘተ. ለመሻገር አሁንም የመንግሥትን ብቻ ሳይሆን የመላውን ሕዝብ የተቀናጀ ጥረት ይፈልጋል። ስለ ሰላም ዘብ መቆምን ፤ ጥቁር ገበያን አምርሮ መታገልን ፤የውጭ ባለሀብቶችን የልማታችን አጋር አድርጎ ተቀብሎ አብሮ መሥራትና መንከባከብን ይጠይቃል!

 አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You