ኢትዮጵያ ሁሉንም ባማከለ መልኩ ከሀገራት ጋር ግንኙነት ታደርጋለች፡፡ ለሕዝብና ለሀገር እስከጠቀመ ድረስ በገለልተኝነት መርህ ከአራቱም ማዕዘናት ጋር አብራ ትሠራለች፤ ወዳጅነት ትመሰርታለች፡፡ በዚህም ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ሀገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመስረት በሰላምና ልማት ዙሪያ አብራ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ብሪክስን በመቀላቀል ሰላምን ፣ ዕድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በመጣር ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ ብሪክስንም ስትቀላቀል እነዚህን ዓላማዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ነባራዊ የዓለም ሁኔታ ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሆኑ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም በየትኛውም ተቋም ለብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት የግድ ይላል፡፡ ብሪክስ ደግሞ የኢትዮጵያም ሆነ የሌሎች ሀገራት ምርጫ እየሆነ መጥቷል፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብ ይይዛሉ። ቀደም ብለው ብሪክስን የመሰረቱት ብራዚል፣ ሩስያ፣ ቻይና ህንድና ደቡብ አፍሪካ በጋራ ያላቸው ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ደግሞ የዓለምን 26 በመቶ የሚሸፍን ነው። ይህ ምጣኔ ሀብታቸውም በየጊዜው እየጨመረ በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ተጽዕኗቸው እያደገ ነው።
ይህን ግዙፍ ጎራ ለመቀላቀል በርካታ ሀገራት ጥያቄ እያቀረቡ የሚገኙ ቢሆንም የተሳካላቸው ግን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጥቂት ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ግብፅ እና አርጀንቲናንም ባለፈው ነሐሴ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው ስብሰባ አባልነታቸው ተቀባይነት አግኝቷል።የእነዚህ ሀገራት በቡድኑ መካተት ከወዲሁ የብሪክስን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከዓለም አቀፉ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 36 በመቶ አድርሶታል። ከዓለም አጠቃላይ ሕዝብም 47 በመቶውን እንዲይዝ አድርጎታል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድንን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከመስራቾቹ ቀጥሎ በሁለተኛ እረድፍ ላይ የቡድኑ ባለድርሻ ሆናለች፡፡ይህም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማሲና የምጣኔ ሀብታዊ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የዚህ ብሎክ አባል መሆኗ በርካታ ጠቀሜታዎች የሚያስገኙላት ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ቀዳሚው የኢኮኖሚ ትብብር ነው።በዚህ የኢኮኖሚ ትብብር ኢንቨስትመንትን እና ንግድን ከማበረታት ጋር ተያይዞ በተለይ በአባል ሀገራት ዙሪያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ሪሶርስ እና ገበያ አለ ተብሎ ስለሚታሰብ ብሪክስ አባል ሀገራት እርስ በእርሳቸው በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ እና የኢንቨስትመንት ሥራ ኢትዮጵያ ትልቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ትሆናለች ተብሎ ይታሰባል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ እንደመሆኑ መጠን የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ ድጋፍ ይሆናታል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ለሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ብድርና እና እርዳታ ከማግኘት አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ የብሪክስ ማኅበር የፈጠረው ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (New Development Bank) በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ ለመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ሀብት የማሰባሰብ ዓላማ ያለው ከመሆኑ አንጻር ኢትዮጵያም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን፣ ሰፋፊ የግብርና ሥራዎችን፣ የመንገድ መሠረተ ልማቶችንና ኢንዱስትሪዎችን የምትገነባ ሀገር በመሆኗ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህ ግብዓት የሚሆን ድጋፍ እና ብድር ከእነዚህ ሀገራት ይገኛል ተብሎ ይታሰባል። እንደ ቻይና እና ሩስያ ከመሳሰሉ ሀገራትም የብድር ተቀናሽና ስረዛ ለማግኘትም ዕድል ይሰጣል፡፡
ከምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው ጎን ለጎንም የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲዊ ተሰሚነት የሚጨምር ነው፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ የምትከተለውን ከሁሉም ወገን ጋር አብሮ የመሥራት አካሄድ ለመተግበርና ከምዕራቡም ከምሥራቁም ዓለም ጋር በወዳጅነት ለመዝለቅ የምትከተለውን ሚዛን የጠበቀ ግንኙነት ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችላት ነው፡፡
በሩሲያ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተወክላ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ስብሰባውም ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የኢኮኖሚ ትብብሯን ለማጠናከር የሚረዳት ነው፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ እያስመዘገበች ያለችውን የዘላቂ ልማት ግቦችንና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂዎችን ወደ መሬት አውርዶ የሕዝቡን ኑሮ ለመለወጥ ብሪክስን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ አጋሮች የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ በሕዝብ ቁጥር ብዛቷና እያስመዘገበችው ባለው ፈጣን እድገት የብሪክስ አቅም እንደምትሆን እምነት የተጣለባት ከመሆኑም ባሻገር ብሪክስ ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የልማት ሥራዎችም አዳዲስ ዕድሎችን የመፍጠር አቅም ያለው ነው!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም