ጋዜጠኝነት ከባድ ኃላፊነትን የተሸከመ ባለአራት ዐይና ሙያተኛ ይፈልጋል። አንድ ጋዜጠኛ ወይም ዘጋቢ ያገኘውን መረጃ እውነትነቱንና ፍትሃዊነቱን ደግሞ ደጋግሞ ማጣራትና መመርመር ይገባል። የሰማውን፣ ያየውንና ያነበበውን ሁሉ እንደ ትክክለኛ ዘገባ ከወሰደው በስተመጨረሻ የከፋ ስህተት ሊፈጥር ይችላል። ጋዜጠኝነት በሥነ ምግባር የሚገዛና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ብርቱ ሥራ ነው።
ውድ አንባቢያን ዛሬ ጋዜጠኝነትን ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም። በተሰማሩበት ሙያ ወይም ኃላፊነት ያለመታከት ለሀገርና ሕዝብ የሠሩ ባለውለታዎቻችን ታሪካቸው ቀርቦ በሚመሰገኑበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ ሥራዎቹን አንስተን የምናመሰግነው በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ጀማሪ የሆነውን ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማን ለማስታወስ ነው ።
ሰሎሞን ተሰማ የተወለደው አዲስ አበባ ውስጥ በ1926 ጥር ወር ላይ ነው። ከስፖርት ጋር ቁርኝቱን በሰፈር ውስጥ ጀመረ። ቀስ በቀስ የሰሎሞን የስፖርት ሙያ ሕልም ወደ ስካውት አባልነት ሲተላለፍ የደበዘዘ መሰለ። በሰውነቱ ውስጥ ሰሎሞን ተሰማ አዳፍኖት የነበረው ስፖርት እንደገና መቀስቀስ ሲጀምር በርካታ ትኲረትንና ብዙ ጆሮዎችን ይስብ ጀመር።
በዚህ ሂደት መሃል ግን አባቱን በሞት ተነጠቀ። ወደ ታላቅ የስፖርት ዓለም ሰውነት የመንደርደር ሕልሙ ለጊዜውም ቢሆን የራሱንና የቤተሰቡን ኃላፊነት ለመሸከም በሚደረግ ትግል ውስጥ እንደገና የተዳፈነ መሰለ። የክብር ዘበኛን ሰራዊት ተቀላቀለ። ሰሎሞን ተሰማ ለአምስት ዓመታት ያህል በክብር ዘበኛ ሰራዊት ውስጥ በሬድዮ ኦፕሬተርነት ሠራ። በመቀጠል ደግሞ ወደ ቴሌኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤት በመዛወር 7 ዓመታትን በዚያ አሳለፈ፡፡
የሕይወት ውጣ ውረድ ጉዳይ ሆኖ ሰሎሞን ተሰማ በተጠቀሱት መሥሪያ ቤቶች በኩል ይለፍ እንጂ ነፍሱና እርሱ ዘላለም ከሚወሳባቸው ሕያው ሥራዎች ጋር ገና አልተገናኙም ነበር። በወቅቱ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የፕሬስ ክፍል ሥራ ሲቀይር ግን ሰሎሞንና የሕይወት ጥሪው መቀራረብ ጀመሩ። ታታሪው ጋዜጠኛ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲ፣ ሕያው ያደረጉትን ሥራዎቹን ቀስ በቀስ ለማውጣት እንቅስቃሴውን ጀመረ። በተለይም ጋዜጦች የሰሎሞን ተሰማን ጽሑፎች ይዘው መውጣት የተለመደ ተግባራቸው እየሆነ መጣ።
በወቅቱ ብሥራተ ወንጌል የምሥራች ድምፅ ይባል የነበረው የሬድዮ ጣቢያም ለሰሎሞን ተሰማ በሳልና ማራኪ ስፖርታዊ ዘገባዎች የአየር ሰዓቱን ክፍት አደረገ፡፡
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ መሠረት የሆነው ሰሎሞን ተሰማ በዚህ ዐይነት ወደ መገናኛ ብዙኃን መድረክ ገባ። በአንድ ወይም በሁለት ቦታዎች ሳይሆን በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ዓይነቶች ላይ በንቁ ተሣትፎና በማይዘነጋ ታታሪነት ስለ ስፖርታዊ ክሥተቶችና ትዕይንቶች በማራኪ ድምፅ መዘገቡን ቀጠለ።
ስለ ስፖርት ባይተዋር የነበሩ በርካታ ጆሮዎችና ዐይኖች ለሰሎሞን ተሰማ ዘገባዎች ትኲረት መስጠት ጀመሩ። በልጅነት እድሜው በሕፃናት ፊት ጣፋጭ የስፖርት ዘገባዎችን ያሰማ የነበረው ያ የመንደሩ ትንሽ ሕልመኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደ ሚናፍቁት ትክክለኛ የሙያ ብቃት ተሸጋገረ፡፡
ሰሎሞን ተሰማ በበርካታ የመገናኛ ብዙኃን የሚፈለግና ዘገባዎቹም ለጆሮ የማይጠገቡ፣ ለንባብ የማይሰለቹ ቁልፍ ሰው ሆነ። በወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ በሚነበበው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የስፖርት ፋና አምዱ በቴሌቪዥን የስፖርት ዘገባዎቹና በሬድዮን ዝግጅቱ ስፖርትንና ሰሎሞንን በጥምረት መመልከት ግድ እየሆነ መጣ።
«የሰሎሞን ተሰማን የስፖርት ዓለም መሥዋዕትነት ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል» በማለት በአንድ ወቅት ወንድሞቹ አቶ ተፈራ ተሰማ እና በቀለ ተሰማ ተናግረዋል። «ሰሎሞን ሌት ተቀን መሥራትን የማይሰለች እስትንፋሱን ከስፖርት ጋር ያስተሳሰረ ታማኝ ባለሙያ ነበር» በማለት ይገልጹታል፡።
በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ባለ ሙያዎች በሚሠሩት የሚዲያ ዐይነት ጐልተው ሲወጡ ማየት የተለመደ ሊሆን ይችላል። የጋዜጠኛ ሰሎሞን ተሰማን ነገር ለየት የሚያደርገውና በርካታዎችን የሚያስገርመው ግን ልዩ ችሎታውና ታታሪነቱ ነበር። ሰሎሞን በቴሌቪዥን፣ ሰሎሞን በሬድዮ፣ ሰሎሞን በጋዜጣ፤ በአጠቃላይ ሰውየው በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ላይ የተዋጣለት ድንቅ ባለሙያ ነበር።
ሰሎሞን ተሰማ ፍጹም የተለያየ ባሕርይ ባላቸው ሦስት ሚዲያዎች ላይ በብቃትና በታታሪነት በሁለገብነት በመሥራት ይታወቃል። ይህንን ሁኔታ ከዛሬ ጋር ስናነጻጽረው የሰሎሞንን ግሩም ተሰጥዎ የሚያንጸባርቅ ይሆናል። የተፈጥሮ ክህሎቱ ድጋፍ ሰጪ መሣሪያዎችና እውቀት በሌለበት ጊዜ እንኳ ዘመኑን የቀደመ ሥራ እንዲሰራ ጠቅሞታልና። ሰሎሞን ተሰማ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ሙያ ላይ በአርኣያነት የሚጠቀስ፣ ስለ ስፖርት ለበርካቶች ጆሮም፣ ዐይንም የሆነ ብቸኛ ሰው ነበር ለማለት ያስደፍራል።
በአገራችን በአሁኑ ሰዓት አንጋፋ የሚባሉ የስፖርት ጋዜጠኞች ሁሉ መሠረታቸውና መነሻቸው ሰሎሞን ተሰማ ነው ሊባል ይችላል። ለበርካታ ዓመታት ከሰሎሞን ዐደራውን ተረክቦ በተወዳጅና በማራኪ ድምፅ የኢትዮጵያን ስፖርት የዘገበው አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ፣ “ጋሽ ሰሎሞን ድርጊቱ፣ ሁኔታው፣ እንቅስቃሴው ሁሉ ስፖርት ነበር። እሱ ለብዙዎች መነቃቃትን የመፍጠር ዐቅም የነበረው የማይዘነጋ፣ ከምንም ተነሥቶ ለዛ ያለውን ነገር ፈጥሮ የሚያሰማ ታላቅ ባለ ሙያና የሙያችን አባት ነው’ ሲል ይገልጸዋል፡፡
በቴሌቪዥን የስፖርት ፕሮግራም ሥርጭት የተጀመረው በጋዜጠኛ ሰሎሞን ተሰማ ነው። በወቅቱ በአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ ተሰሚነትና ውጤት የነበራት ኢትዮጵያ ለእግር ኳስ የነበራትን ንቁ ተሳትፎ በጥዑም ድምፁ የሚዘክርና የሚያሰማ፣ አስደሳቹን ነገር የበለጠ የሚያስፈነድቅ አድርጎ የሚያቀርብ፣ አስደንጋጩን ክሥተት ደግሞ ልብን ከክሥተቱ ጋር እንዲኮመሽሽ በሚያደርግ ሕያው ገለጻ ይደርስ የነበረው በሰሎሞን አንደበት ነበር።
አገራችን በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አስተናጋጅ በመሆን ብቸኛ የአፍሪካ ዋንጫ ድሏን አስመዝግባለች። ያንን ብቸኛ የአፍሪካ ዋንጫ ድል የማይዘነጋ ኅሊና ባለቤት የሆነ ስፖርት አፍቃሪ ሁሉ የድሉን ዜና በማራኪና ቁጭ ብድግ በሚያሰኝ ገለጻ አሳምሮ ያቀረበውን ኢትዮጵያዊ የስፖርት ዓለም ሰው ምንጊዜም አይዘነጋውም። ዛሬም ድረስ ከሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድል ጋር የሰሎሞን ተሰማ ሕያው ድምፅ አብሮ ይሰማል፡፡
አሁን በህይወት የሌለው ሌላው አንጋፋ የስፖርት ጋዜጠኛ ጐርፍነህ ይመር ከረፍቱ በፊት ስለ ሰሎሞን ተሰማ የሀገር ባለውለታነትና ታታሪነት ምስክርነቱን እንዲህ ሲል ሰጥቶ ነበር፤ «አስቸጋሪ በሆነው የሬድዮ ተንታኝነት በዘመኑ በብቃት የሠራ፤ ለአገሪቱ የስፖርት ጋዜጠኞችና ለዘመኑ የማይዘነጋ መሥዋዕትነትን የከፈለ» በማለት ሰሎሞን ተሰማን ገልጾታል፡፡
ታላቁ የስፖርት ጋዜጠኛ የዜማና ግጥም ደራሲ ሰሎሞን ተሰማ ስለ ስፖርተኞችና ስለ ስፖርት የሚያየውን ብቻ መዘገብንና ማስተላለፍን የሚመርጥ ጋዜጠኛ አልነበረም። ስፖርተኞች ከስፖርት ውጪ ያለ ሕይወታቸው ምን ይመስላል? እንዴት ይኖራሉ? ምን ይበላሉ? ምንስ ይጠጣሉ? የሚለውን ለማወቅ የሚተጋም «ውስጥ አዋቂ» ጋዜጠኛ ነበር፡፡
እንደ አሁኑ ስፖርተኞች በአንጻራዊ የተሻለ ክፍያ በማያገኙበት ወቅት ለሰሎሞን የሕዝብ ዕውቅናና የሙያ ስኬት ትልቅ ክፍያ እንደ ሆነ ለሚወደው ሕዝብ ማስረዳት ሥራው ነበር። በዚያን ወቅት አንድ ሆኖ ሳለ እንደ ብዙ ኢትዮጵያውያን ፈር ቀዳጅ ባለ ድሎች የብዙዎችን ገድል ለመተረክ ሰሎሞን ተሰማ ሰንፎ አያውቅም።
የማይረሱ ድሎች በማይረሱ ዘገባዎች፣ የማይዘነጋው የአትሌቶች ዓለም ክሥተት በማይሰለቸው የሰሎሞን ተሰማ ድምፅ ለዓመታት ተነግሯል። ለዚህ ድካምም ሆነ መሰልቸት ላልታየበት አስደናቂ ተግባሩ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ የስፖርት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ሕያው ምስክርነት የሰጡበት ተደጋጋሚ አጋጣሚ አለ፡፡
ለምሳሌ፦ ወደ ሜክሲኮ ሲቴ ኦሎምፒክ በትዝታ እንመለስ። በሮምና በቶኪዮ አበበ ቢቂላ ማራቶንንና ኢትዮጵያን፣ ማራቶንንና አፍሪካን በወርቅ ካስተሳሰረ በኋላ ሜክሲኮ ሲቲ ላይ ዐደራውን ለማሞ ወልዴ በመስጠት አቋርጦ ወጣ። ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ ሲቲ ኣደባባይ የኢትዮጵያንና የአበበን ዐደራ ተቀብሎ ሲሮጥ ግን ብቻውን አልነበረም። የድምፅ ማጉያ በመያዝ ማሞን የሚያበረታታ፣ ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደ ሮጠና ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደ ቀረው ለማሞ የሚናገር አንድ ሰው ነበር። ያ ሰው ጋዜጠኛ ሰሎሞን ተሰማ ነበር።
ማሞ ወልዴ ሜክሲኮ ሲቲ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማራቶን ድል እንዲውለበለብ ካደረገ በኋላ ለተገኘው አንጸባራቂ ድል የሰሎሞን ተሰማ ዕገዛ ከፍተኛ መሆኑንም፣ «ከጀርባዬ በመሆን እየተከተለ ያበረታታኝ ነበር። ሰሎሞን ተሰማ ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደሚቀረኝና እንዴት መጨረስ እንዳለብኝ በመምከር ለድሌ ወሳኙን ድርሻ ተወጥቷል፡፡» በማለት መስክሯል፡፡
የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ዓለም ተሳትፎ በ 1956 ዓ.ም ሜልቦርን ላይ ይጀመር እንጂ አገራችንን ለመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያዎች ያበቋት የአበበ ቢቂላ የሮም እና የቶኪዮ የማራቶን ድሎች ናቸው። አበበ ከማራቶን ድሉ በኋላ አዲስ አበባ ሲገባ ልክ በቅርቡ የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ እንደሚታየው ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት አቀባበል አድርጎለት ነበር። ያንን የአቀባበል ትዕይንት ሲያስተላልፍ የነበረው ጋዜጠኛ ሰሎሞን ተሰማ እንደ አበበ የባዶ እግር ሩጫ ድል ሁሉ የማይረሳ አሻራን በመተው ዐልፏል።
አበበ ቢቂላ ይጓዝበት የነበረውን መኪና፣ ሕዝቡ ስለ አበበ ያሳየውን የሞቀ አቀባበልና የአበበ ቢቂላን ስሜት ጋዜጠኛ ሰሎሞን የገለጸው ደግሞ ደጋግሞ ቢታይ እንዳይሰለች አድርጎ ነበር። ከዚህ የተነሣ፣ በርካቶችም «የመረጃ ፍሰት ባልነበረበት ሰዓት የስፖርት ጋዜጠኝነትን ጠንቅቆ በመረዳት ቀድሞ የተፈጠረ ሰው» ሲል ጋዜጠኛ ሰሎሞንን ያወድሱታል፡፡
ሰሎሞን ውስጠ ትኩስ የጋዜጠኛነት ተሰጥዎ ያለው ሰው ብቻ ሳይሆን የላቀ የምግባር ዕሴት የሚታይባቸውን የዘፈን ግጥሞች ለዘመኑ ምርጥ ድምፃውያን ያቀበለ ሰውም ነበር። ለምሳሌም፦ እንደ ተወደደች ላለፈችው ለብዙነሽ በቀለ «የእናት ውለታዋ»፣ «የሚያስለቅስ ፍቅር»፣ «የሰው ነገር በቃኝ»፣ ለታዋቂው ድምፃዊ ለጥላሁን ገሠሠ ደግሞ «ሞናሊዛዬ ነሽ»፣ «ለእውነት እሞታለሁ» እንዲሁም ለድምፃዊት ኂሩት በቀለ «ባህል እንዳትጠፋ» «እጮኛዬ» የተሰኙት የዘፈን ግጥሞች የዚሁ ተወዳጅ የስፖርት ጋዜጠኛ የብዕር ጠብታዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ከሁሉ መረሳት የሌለበትና ከእርሱ ቀጥተኛ ሙያ ጋር በጽኑ የሚቆራኘው የሜክሲኮ ኦሎምፒክ የወለደውና የወቅቱ የስፖርት ማኅበረሰብ የማይዘነጋው «ማራቶን ልዕልቷ» የተሰኘው የስፖርት ዜማው ነው።
ከዜማው ግጥም አራቱ ስንኝ የሚከተሉት ናቸው፦
ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ፣
አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ፣
ማራቶን ደንግጠሽ አቤን ብትቈጪ፣
ዕድሏ የኛው ነች የትም አታመልጪ።
እንደ በሳል የስፖርት ዘገባዎቹ ሁሉ የሰሎሞን ዜማና ግጥሞችም ዘመን አይሽሬ ናቸው። የሙዚቃ ግጥምና የዜማ ደራሲነቱን የሚያደንቀው አንጋፋው አቀንቃኝ ጥላሁን ገሠሠ በአንድ ወቅት የሰሎሞን ተሰማን ሕይወት አስመልክቶ በተሠራ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ «ሰሎሞን እንደ ስፖርት ጋዜጠኛ የማይረሳ፣ የሰው ልብ እንደ ፈለገ በቃላት የሚሰቅልና የሚያወርድ ሰው ነበር» በማለት ገልጾታል። ከበርካታ የአገራችን የሙዚቃ አፍቃሪዎች ኅሊና የማይጠፉት እነዚህ መልእክት ዐዘል ዜማዎች የሰሎሞን ተሰማን ሌላ የጥበብ ፈርጅ የሚመሰክሩ ሕያው ሥራዎች ናቸው፡፡
ሰሎሞን ተሰማ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ገና ብዙ መሥራት በሚችልበት ዕድሜው ነበር ። በህይወት በቆየባቸው 46 ዓመታት መሠረት ጣይ ሥራዎችን ሠርቶ ቀሪ ቅርስ ትቶ አልፏል።
ከምንም ነገር ላይ በመነሣት ለዘመናት የስፖርት ዓለም ጋዜጠኞች የሚሄዱበትን መንገድ ነድፏል። በማይዘነጋ ታታሪነትና መሥዋዕትነት በሦስት ዓይነት የመገናኛ ብዙኃን ላይ በርካታ ሰዎች የሚሠሩትን ሥራ ለብቻው ሠርቷል። ለኅሊናችን ጓደኛ፣ ለጆሮአችንም ጣፋጭ የሆኑ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ከትቦም አልፏል። ራሱን በአንድ ዓይነት ሥራ ብቻ ሳይገድብ በየሙያ መስኩ በትጋት ባከናወነው አኩሪ ተግባር ምሳሌነቱን አስመዝግቧል። እኛም የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት ፈርቀደጅ ሰለሞን ተሰማን ነፍስ ይማር እንላለን. ሰላም!
ይህንን ጽሁፍ ለማጠናከር በመረጃ ምንጭነት ደማቆቹ ጸሓያተ ሌሊት የተሰኘ መጽሃፍና ሌሎች ድረገጾችን ተጠቅመናል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም