የምን ዶክተር?

የደን ስነ ምህዳር ተመራማሪ እና ደራሲ የሆኑት አለማየሁ ዋሴ (ፒ. ኤች. ዲ) ባለፈው ሳምንት አንድ የፖድካስት ሚዲያ ላይ ቀርበው የተናገሩት ገጠመኝ የሀገራችንን ‹‹ዶክተሮች›› እንዳስታውስ አደረገኝ። እርሳቸውም በትዝብታቸው ‹‹እዚህ ሀገር ዶክተር መባልህን እንጂ የምን ዶክተር እንደሆንክ የሚጠይቅ የለም›› ብለዋል። ገጠመኛቸውን በአጭሩ እናስታውስ።

የሦስተኛ ዲግሪ (ፒ. ኤች. ዲ) ጥናታቸውን ሲሰሩ የመረጃ አተናተን የሚያሳይ መተግበሪያ አሰራሩን እንዲያጠኑት ይጠየቃሉ። በአውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባህል አንድ ሰው ምርምሩን ሲሰራ በዝርዝርና በጥልቀት ነው። እርሳቸው ደግሞ ዋናው መረጃውን መተንተኔ እንጂ መተግበሪያው እንዴትስ ቢሰራው ምን ያደርግልኛል ብለው ብዙም ትኩረት አልሰጡትም። እንዲያውም ሳይገባቸው ‹‹ገብቶኛል›› አሉ። አስተማሪያቸው እንዳልገባቸው ገብቶታል። ‹‹የገባው አልመሰለኝም›› ብሎ ለአማካሪያቸው ተናገረ። አማካሪያቸውም ያልገባው መስሎ ‹‹እስኪ አሳየኝ›› አላቸው። ነገሩ የማይቀር መሆኑን ሲያውቁ ትኩረት ሰጥተው እስከሚገባቸው ድረስ ተከታተሉት። ልክ ሲገባቸው ለአማካሪያቸው ሊያስረዱ ሲሄዱ ‹‹አውቀዋለሁ›› አላቸው። ‹‹አሳየኝ›› ብሎ የነበረው ምን ያህል ገብቶታል የሚለውን ለማወቅ ነበር ማለት ነው።

በዚሁ አጋጣሚ ከተናገሩት ሌላው የገረመኝ፤ የምርቃት ቀን ለአንድ ተማሪ አንድ ቀን ነው። ለምሳሌ፤ በአንድ የትምህርት ክፍል ውስጥ 60 የማስተርስ ወይም የፒ. ኤች. ዲ ተመራቂዎች ቢኖሩ በ60 ቀናት ውስጥ ነው የሚመረቁት። በአንድ ተማሪ የምርቃት ቀን አማካሪው ስለዚያ ተመራቂ ሲያብራራና ሲተነትን ነው የሚውለው። ተመራቂው የአካዳሚ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን ስብዕናው ሁሉ ሳይቀር ይጠናል። በተለይ ተማሪው የተሻለ ነው ብለው ካመኑ ብዙ ክትትልና ትኩረት ይደረግበታል። በአጭሩ በሚገባ ገንብቶ ሰው መሥራት ይችሉበታል። የአውሮፓውያንን የትምህርት ትኩረት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እና ሌሎች ምሁራንም ገልጸውት አንብቤያለሁ።

ይህን ይዘን ወደ ሀገራችን ‹‹ዶክተሮች›› እንምጣ። የኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአውሮፓውያኑ ጋር እያነፃፀርኩ አይደለም። ዳሩ ግን የሀገራችን ‹‹ዶክተሮች›› ቢያንስ ቢያንስ በምን ዘርፍ ላይ እንዳጠኑ እንኳን ለብዙዎች አይታወቅም። የሚታወቀው ምናልባትም በዙሪያቸው ላሉት ሰዎች ብቻ ነው። በአብዛኛው ማህበረሰብ ‹‹ዶክተር›› የሚለው ቃል የሚታወቀው ለሐኪሞች ነው። እንዲያውም የገጠሩ ማህበረሰብ ‹‹ዶክተር እገሌ›› ሲባል ሲሰማ ሐኪም የሚመስለው ብዙ ነው። በእንግሊዘኛ ምህፃረ ቃሉ ‹‹ፒ. ኤች. ዲ›› የሚባለው በአንድ ነገር ላይ መመራመርን (ፊሎሶፊ) ይገልጻል። እንደ ማዕረግ ሲቀመጥም በቅንፍ ውስጥ ከስማቸው ፊት ለፊት ነው። ለምሳሌ፤ አለማየሁ ዋሴ (ፒ.ኤች.ዲ) ተብሎ ነው። ወይም በሌላ አገላለጽ፤ አለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) ተብሎ ነው። በልማድ ግን ከስም በፊት በማስቀደም ‹‹ዶክተር እገሌ›› ይባላል። ከዚህም ይባስ ብሎ የክብር ዶክትሬትም ‹‹ዶክተር እገሌ›› የሚባልበት ሆኗል።

አቀማመጡና አገላለጹ ምንም ችግር አልነበረውም። ችግር የለውም ‹‹ዶክተር›› እንበላቸው። ችግሩ የሀገራችን ‹‹ዶክተሮች›› የምን ዶክተር እንደሆኑ የማይታወቅ መሆኑ ነው። ከሰሩት ምርምር ይልቅ የሚጠቀሙበት ማዕረጉን ነው። በአንድ ኃላፊነት ላይ የተቀመጠ ‹‹ዶክተር›› ምርምሩን በምን እንደሰራ አይታወቅም። ለሰዎች ክብደት የምንሰጠው በምርምሩ ሳይሆን ‹‹ዶክተር›› የሚል ማዕረግ ስላላቸው ነው። ‹‹ዶክተር›› መባሉን እንጂ የምን ዶክተር እንደሆነ፣ ምን ላይ እንደተመራመረ፣ ምርምሩ ምን ችግር እንደፈታ አይጠይቅም። በዚያ ‹‹ዶክተር›› በተባሉበት ምርምር የሆነ ችግር ሲፈቱበት ወይም ያገኙትን ግኝት ሲያስተዋውቁ አይሰማም። ማዕረጋቸው ከተጓደለ ግን ይደነፋሉ።

ምናልባት ከስንት አንድ ጊዜ (ለዚያውም በወሬ መሃል) ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ሦስተኛ ዲግሪዬን ስሰራ›› ሊሉ ይችላሉ። አብዛኞቹ ይህን የሚሉት አጋጣሚውን ለመናገር እንጂ ‹‹በዚህ ምርምሬ ባገኘሁት ግኝት›› ብለው ለመናገር አይደለም። ምርምራቸው የሚጠቀሰው እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ የአንዳንዶችም በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ለንባብ የበቃም አለ። የአብዛኞቹ ግን በምን ርዕስ እንደሰሩ ብቻ ሳይሆን በምን ዘርፍ ዶክተር እንደሆኑ ራሱ አይታወቅም። ያልታወቀበት ምክንያት ከምርምራቸው ይልቅ ማዕረጉን የበለጠ ትኩረት ስለሰጡት ነው።

ከመመረቃቸው በፊት ምርምሩ የሚደረግበት መንገድ ደግሞ ሌላ አሰልቺ ነገር አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ተማሪው እና አማካሪው የሚገናኙበት መንገድ የጌታ እና የባሪያ አይነት ግንኙነት ነው። ተማሪው አማካሪውን የሚያየው እንደ አማካሪ ሳይሆን የሆነ አስፈሪ ነገር አድርጎ ነው፤ ይህ የሚሆነው አማካሪዎች ከሚሰጡት አስፈሪ መልስ፣ ግልምጫ፣ ባስ ሲልም ስድብ በመነሳት ነው። ከምንም በላይ ደግሞ አማካሪ ተብየዎችን ማግኘት ሌላ የምርምር ሥራ ነው። በቀጠሩት ሰዓት ላይገኙ ይችላሉ፤ ሲጀመርም ላይቀጥሩ ይችላሉ። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ባለ ግንኙነት ችግር ፈቺ ምርምር ሊሰራ አይችልም። እዚህ ላይ የአንድ ጓደኛዬ ገጠመኝ መጥቀስ አለብኝ።

ጓደኛዬ የሁለተኛ ዲግሪውን (ማስተርስ) እየተማረ ነው። አማካሪ ተመደበለት። ከአማካሪው ጋር ከዚህ በፊት በአካል አይተዋወቁም። የተመደበለትን አማካሪ ስልክ አፈላልጎ ደወለ። ተማሪው ሲደውል አማካሪው ስድብ የተቀላቀለበት ቁጣ ተቆጣ። ቁጣው ‹‹ቢሮዬ ና እንጂ ለምን ትደውልልኛለህ!›› የሚል ነው። ተማሪው የደወለው ግን ቢሮውን ለመጠየቅ ጭምር እና የሚመችበትን ሰዓት ለማወቅ ነው። ይህ አማካሪ ተማሪው ሳይደውል ዘው ብሎ ቢሄድ ደግሞ ‹‹ቀጠሮ ሳልሰጥህ›› ብሎ መቆጣቱ አይቀርም ነበር። ሁልጊዜ ቢሮ እንደማይቀመጥም ያውቀዋል። በእንዲህ አይነት አማካሪ ምን አይነት ችግር ፈቺ ምርምር ነው የሚሰራው?

በደሞዛቸው ደስተኛ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ኑሮን ለማሸነፍ ተጨማሪ ሥራ የሚሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እልሃቸውን እና ቅሬታቸውን መግለጽ ያለባቸው የቀጠራቸው አካል ላይ እንጂ ተማሪው ላይ መሆን አልነበረበትም።

አንድ የሦስተኛ ዲግሪ (ፒ. ኤች. ዲ) ተማሪ ጓደኛዬ ከአማካሪው ጋር ሲደዋወል ያለውን መሽቆጥቆጥ ሳይ አዝናለሁ። ‹‹ለምን ደወልክልኝ?›› ይለኛል የሚል ከፍተኛ ፍርሃት አለው። አማካሪው በተደራቢነት በሌላ ኃላፊነት ላይ ያለ ስለሆነ የቀጠረበትን ቀን ሁሉ ይረሳዋል። መርሳቱን ለማስታወስ እንኳን ለመጠየቅ ያስፈራል ማለት ነው። በእንዲህ አይነት አማካሪ ምን አይነት ምርምር ይሰራ ይሆን? እንዲህ አይነት አማካሪዎች እንኳን ሰብዓዊነትን ሊቀርጹ ዋናውን የአካዳሚ ውጤት እንኳን ለማስጨረስ አይሆኑም ማለት ነው።

በጣም ብዙ የሀገራችን ‹‹ዶክተሮች›› የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከውጭ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ያገኙ አሉ። ዳሩ ግን እነዚያን የሰለጠኑ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ስም የሚጠቀሙት ለግል ክብር እንጂ የሰለጠኑ ሀገራትን የአሰራር ዘዴ አይጠቀሙትም። እዚያ ያዩትን አሰራር ከመጠቀም ይልቅ የዩኒቨርሲቲውን ስም ይጠቀሙበታል።

‹‹ዶክተሮቻችን›› የሰሩትን ምርምር ተግባር ላይ ያውሉትና የምን ዶክተር እንደሆኑ ይታወቅ!

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You