የትኛውም ትውልድ የራሱንም ሆነ የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ሊቀይር የሚችለው ትናንት ከፈጠራቸው ባርነቶች መውጣት የሚያስችል ሁለንተናዊ መነቃቃት መፍጠር ሲችል ነው። በተለይም ትናንቶች ላይ ለዘመናት ቆሞቀር ለሆነ ትውልድ የትኞቹም ከትናንት የመውጣት አማራጮች መሰረት የሚያደርጉት ይህንኑ እውነታ ነው።
የእያንዳንዱ ትውልድ ማንነት ከትናንት የሚቀዳ ነው። ትናንቶች ከቀንነታቸው ባለፈ ከሚያስተናግዷቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች አኳያ የትውልዶችን ማንነት በመቅረጽ ሂደት ውስጥ ትልቅ አቅም እንደሆኑ ይታመናል፤ በትውልድ ግንባታ ውስጥም ትልቅ ስፍራ ይሰጣቸዋል።
የሰው ልጅ እንደ አንድ አሳቢ ማኅበራዊ ፍጡር እና የብዙ ፍላጎቶች ባለቤት ነው፤ እነዚህን ፍላጎቶቹን አሟልቶ፤ ለራሱ የተሻለ ሕይወት ለመፍጠር ከሕላዌው ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል ። ነገን ከዛሬ የተለየ ለማድረግም ብዙ እያሰበ፤ የሃሳቡን ፍሬ ተጨባጭ ለማድረግም እየተጋ ይገኛል።
በዚህ የዘመናት የሕይወት ጉዞው ውስጥ አእምሯዊ ፣ መንፈሳዊ እና ባህላዊ እውቀቶቹ አሁን ለደረሰበት ሁለንተናዊ ዕድገት በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መንገድ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው። በቀጣይም ለሚያስበው የተሻለች ዓለም ግንባታ ስኬትም ሆነ ውድቀት ዋነኛ አቅምም ናቸው።
እስካሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ለአንድ ማኅበረሰብ ዕድገት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የዚያ ማኅበረሰብ ከትናንት የመውጣት መነቃቃት እንደሆነ የታመናል። ዛሬን በማይዋጅ ህሳቤ ከትናንቶች ጋር የተጋባ እና ለጋብቻው ታማኝ ለመሆን የሚጥር ትውልድ መቼም ቢሆን ነገዎቹን የተሻለ ሊያደርግ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር አይችልም።
ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ትውልድ እንደ ማኅበረሰብ የተሠራባቸውን ማኅበራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን፤ መሆን ከሚፈልገው መሻቱ አንጻር ቀጣይነት ባለው መንገድ በጠንካራ የህይወት ዲሲፕሊን መመርመር፤ የፍላጎት ለውጡን መሸከም በሚያስችል የለውጥ ሥርዓት ውስጥ መገኘታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
የገዘፈ ማንነት በመመስረት ሂደት ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ፣ እነሱን ተጨባጭ ለማድረግ የሚተገበሩ አስተምህሮዎች ፣ከሁሉም በላይ ከማኅበረሰቡ ሰብአዊ መሻቶች በተቃርኖ እንዳይቆሙ በዚህ ማኅበረሰቡን ያልተገባ ዋጋ እንዳያስከፍሉ መጠንቀቅ ተገቢ ነው።
በተለይም እንደኛ ባለ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያለው ፣ የብዙ ብሐየር፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባህል እና የተለያዩ ሃይማኖቶች በቀዳሚነት መገኛ የሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ለውጥ እና ከለውጥ ጋር የተያያዙ ዕውቀቶች /እሳቤዎች በብዙ ተግዳሮት መፈተናቸው የማይቀር ነው።
የለውጥ አስተሳሰቦችን ተቀብሎ ለመጓዝ የሚጥር የማኅበረሰብ ክፍል እንደሚኖር ሁሉ፤ ለውጥን ሊሸከም የማይችል ማንነት የገነባ፤ ለዚህም በብዙ ታማኝ የሚሆን የማህበረሰብ ክፍል ሊኖር እንደሚችል መገመት አይከብድም።ተጨባጭ ሀገራዊ እውነታው የሚያሳየውም ይህንኑ ነው።
በዘመናት ሀገራዊ ትርክታችን በመሥራት ማደግን ፣ በማደግ፣ መለወጥን እንደ ሰብአዊ መሻት አድርጎ የሚቀበል እንደነበር ሁሉ ፤ብህትናን እና ከብህትና የሚመነጨውን ሕይወት ለመንፈሳዊ ሽልማት እንደሚከፈል ዋጋ አድርጎ የተቀበለና በዚህም አጠቃላይ ለሆነው ማኅበረሰባዊ ሕይወት ትርጉም ለመስጠት የተሞከረበትም ጊዜ አለ።
የትኞቹም ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ የተቀበለው ዕውቀት በመሠረታዊነት ሰውን/ማኅበረሰቡን ታሳቢ ያደረገ፤ ለሰው ልጅ/ለማኅበረሰቡ የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር ዓላማ ያደረጉ ናቸው። ውጤታማነታቸውም የሚመዘነው በዚሁ ተጠባቂ ዓላማቸው ነው።
ይህም ሆኖ ግን በተለያዩ ምክንያቶች፤ በተለይም እውቀቶቹ ዘመኑን በሚዋጅ አዳጊ ዕውቀት ካለመታደሳቸው/ መቃኘታቸው ጋር በተያያዘ፤ የተለያየ ትውልድ በአንድም ይሁን በሌላ ዘመን የማይዋጅ እውቀቱ ተገዥ በመሆን በተመሳሳይ የሕይወት ምዕራፍ ውስጥ ለማለፍ የሚገደድበት ሁኔታ ይፈጠራል።
እነዚህ እውቀቶች በዘመናት መካከል ተለዋዋጭ የሆነውን የትውልድ መሻት ለማስተናገድ አቅም አልባ መሆናቸው ፤አንድም ትውልዱ በራሱ የሚተማመንበትን አቅም በማቀጨጭ ጠባቂ እንዲሆን ያደርገዋል። ከዚህም ባለፈ በነገዎቹ ላይ ተስፈኛ እንዳይሆን ይገዳደሩታል።
ይህ ችግር እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ እኛንም እየተፈታተነን የሚገኝ፤ የአብዛኞቹ ችግሮቻችን ምንጭ ነው። ከትናንት የከፍታ ታሪኮቻችን ያወረደን፤ እንዳንመለስም አቅም ያሳጣን ይኸው ዘመን ከማይዋጁ ዕውቀቶቻችን ጋር ያደርግናቸው ጋብቻዎች እና ለእነሱ ታማኝ መሆናችን የፈጠረብን ጫና ነው።
ከዚህ ጫና ወጥተን የምንፈልጋትን የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር ከሁሉም በፊት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች የተገዙበትን እውቀት መመርመር ፣ ለዚህ የሚሆን ድፍረት እና ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅብናል። ዕውቀቶቻችን ዛሬን የሚዋጁ ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ የተሟላ አቅም እንዳላቸው ማረጋገጥ ይኖርብናል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም