ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ሲፈጠሩ፣ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ በተከሰቱ ሁኔታዎች ወይም ሰፊ የፖለቲካ ሽግግሮች ውስጥ ባሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር የታለመ በሀገራዊ ባለቤትነት የተያዘ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ ያለው ሂደት ነው።
የተለያዩ ሀገራት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ሀገራዊ ችግሮችንና መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ያጋጠሙ አለመግባባቶችን አካታች በሆነ ሀገራዊ ውይይት መፍታት ችለዋል። በዚህም ዘላቂ ሰላም በማስፈን የተሳካ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ አምጥተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት እንዳለ ይታመናል። ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ተስፋ የተደረገበት ሀገራዊ ምክክሩ የተሻለ ሀገራዊ አንድነት ለመገንባት በሂደትም የመተማመን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ለማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸሩ ማኅበራዊ ዕሴቶችን ለማደስ የሚጠቅም ነው፡፡
የቆዩ አለመግባባቶችን ጨምሮ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት በመፍታት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለሚደረገው ጉዞ የውይይት ባሕልን ማዳበር እና ወቅታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል። በዚህ ረገድ የተሳካ ብሔራዊ ውይይት ማድረግ ሀገሪቱ ለምታደርገው የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ መደላደልን ከመፍጠር በዘለለ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ሚናው የጎላ እንደሆነ የሚታመን ነው።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ሙሉዓለም ኃይለማርያም እንደሚናገሩት፤ ሀገሪቱ በአብዛኛው አካባቢዎች የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውን በኃይል ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ በርካታ ቡድኖች አሉ። የእነዚህ አካለት ተግባር ደግሞ የዜጎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ ተፈጥሯዊ መብታቸውን በሚገታበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ይህንን ችግር ለመፍታት ሀገሪቱ የወሰደችው አማራጭ ብሔራዊ ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ ነው። አቶ ሙሉዓለም ምክክሩ ሁሉንም የሀገሪቱን ችግሮች ይፈታል የሚል እምነት ባይኖራቸውም መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይናገራሉ።
ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም አድሎና ማግለል አሳታፊ መሆን ስችል ነው የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፤ ጥያቄ አለን የሚሉ አካላትን ሁሉ በማሳተፍ የሚካሄድ ከሆነ ትላንትና የተፈጠሩና ለዛሬ ግጭቶቻችንና አለመግባባቶቻችን ምክንያት የሆኑ ዋልታረገጥ የሆኑ ሀሳቦችን የሚያስታርቅበት ዕድል ያለው ስለመሆኑ ይናገራሉ።
የነጠላ ትርክት የበላይነት እያገኘ ሀገራዊ የጋራ ትርክት መገንባት የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፤ ከዚህ አንፃር ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ ትርክት ያለት ሀገር በመፍጠር ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትርጉም ያለው በጎ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይገልጻሉ።
የትላንትና ችግሮቻችን ለዛሬ አለመግባባቶቻችን ምክንያት የሆኑት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ የጎደለን ነገር ስላለን ነው የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፤ ይህንን ስብራት ለመጠገን እውነተኛ የሆነ ምክክር ማድረግ ተገቢ ነው። ይህንን ማድረግ ከተቻለ የተረጋጋችና ፊቷን ወደ ልማትና ኢኮኖሚ የምታዞር ሀገር ከምክክሩ በኋላ ልናይ እንደምንችል ገልፀው፤ ነገር ግን ሀገራዊ ምክክሩን ሁሉንም ችግሮች እንደሚፈታ ቁልፍ አድርጎ መውሰድ ስህተት እንደሚሆን ተናግረዋል።
የዚህ አይነት የምክክር ሂደት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ ውጤታማ መሆን የቻለ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙሉዓለም፤ ለአብነት ለዓረብ አብዮት መፈንዳት ምክንያት በሆነችው የሰሜን አፍሪካ ሀገር ቱኒዚያ ሀገራዊ ምክክር ተደርጎ ሀገሪቱ በቀጣይ ለምታደርገው የሽግግር ሂደት ምቹ መደላድል የፈጠራ እንደነበር ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ለረዥም ግዜ በነጮች የበላይነት ወይም በአፓርታይድ የቅኝ ግዛት ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ተምሳሌታዊ ለሆነ ሀገራዊ ምክክር ጥሩ ምሳሌ ተደርጋ መወሰድ የምትችል ናት የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፤ ደቡብ አፍሪካውያን ሁለት ይቅርታና መርሳት የሚል መርህ ተከትለው የትላንትና በደሎቻቸውን ረስተው ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ተሻግረው የተረጋጋች ሀገር መገንባት መቻላቸው ለኢትዮጵያ አብነት መሆን የሚችል እንደሆነ ይገልጻሉ።
ምክክር ሁልጊዜም ሶስት እርከኖች እንዳሉት የሚናገሩት አቶ ሙሉዓለም፤ እነዚህም የዝግጅት፣ የሂደትና የትግበራ ምዕራፍ ተብለው የሚከፈሉ ናቸው። በእነዚህ በሶስቱም ምዕራፎች ላይ የምናደርጋቸው ነገሮች ወሳኝ ናቸው። በሀገራዊ ምክክር የተሳካላቸው ሀገራት እነዚህን ደረጃዎች በጥብቅ መርህ ተግባራዊ ማድረጋቸው በእጅጉ ጠቅሟቸዋል፤ በሌላ በኩል እንደ ሊቢያ፣ ሱዳንና የመን, ያሉ ሀገራት ችግሮቻቸውን በምክክር ለመፍታት ተቀምጠው ያልተሳካላቸው የምክክር ሂደቱ ምዕራፍ በተገቢው ሁኔታ ያልተመራ ብሎም አሳታፊነቱ ላይ ከፍተኛ ጉድለት የነበረበት በመሆኑ ከዚህ ልምድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
በብዙ ሀገራት ብሔራዊ ምክክር ስኬታማ መሆን ያልቻለው በአተገባበር ላይ በገጠማቸው ችግር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙሉዓለም፤ ተገዳዳሪ ወይም ፅንፍ የያዙ ሀሳቦችን ማስታረቅ ባለመቻላቸው ውይይቱ ተደናቅፎ ቀርቷል፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግሥት ልምድ በመውሰድ ሀገራዊ ምክክሩ ለመንግሥት ያጋደለ እንዲሆን በማሰብ ጣልቃ ባለመግባት፤ ገለልተኛ ሆኖ በምክክሩ የሚመጣውን የትኛውንም ውጤት ለመተግበር መዘጋጀት እንዳለበት ይናገራሉ።
እንደ አቶ ሙሉዓለም ገለፃ፤ በምክክር ኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አለን ወይም በኮሚሽኑ እምነት የለንም የሚሉ አካለት ወደ ምክክሩ ሳይገቡ ምክክሩ ምን ይዞ ይመጣል የሚለውን ሳይመለከቱ ራሳቸውን ማግለል ተገቢ እንዳልሆነና አትራፊ የሚያደርጋቸው እንደማይሆን ይናገራሉ።
ለይስሙላ ምክክር አደረግን ለማለት ሳይሆን እንደ ሀገር የሚያሻግር እውነተኛ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ መዘጋጀት ከሁሉም እንደሚጠበቅ የሚናገሩት አቶ ሙሉዓለም፤ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ውክልና ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል በውይይቱ ብንሳተፍም ውጤት አይኖረውም የሚሉ አካላትን በተቻለ መጠን በማሳመን ወደ ንግግር እንዲመጡ ለማድረግ የምክክር ኮሚሽኑ አሁን እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል እነዚህን አካላት ወደ ጠረዼዛ ዙሪያ እንዲመጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው መልሰው ለውይይት ዝግጁ እንዲሆኑና ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ በሚያበሉን ጉዳዮች ላይ ወደ መሃል መጥተው የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ መንግሥት፣ ሕዝብና የምክክር ኮሚሽኑ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ሙሉዓለም፤ ብሔራዊ ምክክሩን ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ውይይት ሳይሆን የወደፊት ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚወስን እንደመሆኑ በልዩ ትኩረት መመራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽንና አጋርነት ዘርፍ አስተባባሪና የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሀሳብ ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህን ችግሮችና የሀሳብ ልዩነትች ለመፍታት የሚካሄድበት መንገድ ደግሞ የኃይል አማራጭ በመሆኑ እንደ ሀገር ብዙ ነገር አጥተናል እያጣንም እንገኛለን ይላሉ።
ከዚህ እሽክርክሪት ለመውጣት እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በአጀንዳ መልክ በመለየት እነርሱ ላይ መመካከር ተመካክሮ ወደ መግባባት መድረስ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሀገሪቱ እንደ ሀገር አሁን ካለችበት ችግር ተላቃ ወደፊት መራመድ የምትችለው፤ ይህንን ለማድረግ ነው ብሔራዊ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሀገራዊ ምክክር እየተካሄ ያለው ይላሉ።
አቶ ጥበቡ እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ ለነበሩ አሁንም ላሉ፤ ካልተፈቱና ዘላቂ መፍትሔ ካልተገኘላቸው በቀር ወደፊትም በሀገሪቱ የሚቀጥሉ ችግሮችን ለመፍታት እስከአሁን ከተሞከሩ ሙከራዎች ለየት ያለ መንገድ መከተል ይጠይቃል ይላሉ።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ግዜያት በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል የሚሉት አቶ ጥበቡ፤ ነገር ግን እነዚህ ሙከራዎች በአንድ በኩል የአሳታፊነትና አካታችነት ችግር ስለነበረባቸው በሌላ በኩል ደግሞ በተወሰኑ ስልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት የሚፈለገውን ማምጣት የነበረባቸውን ውጤት ሳያመጡ እንደቀሩ ይናገራሉ።
አቶ ጥበቡ እንደሚናገሩት፤ አሁን ባለው ሂደት ግን አዲስ ውጤት ለማምጣት አዲስ መንገድ መከተል ተገቢ ስለሆነ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክር ሁሉን አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ የምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ እንደተቀመጠው በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ ውይይት ሁሉንም ባለድርሻ አካል የሚያሳትፍና የሚያካትት መሆን ያለበት በመሆኑ ከዚህ አኳያ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች የሚታዩባቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የሀሳብ መሪዎች በሂደቱ ተሳተፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ግዜ ተወስደው እየተሰሩ ናቸው በዚህም ውጤታማ ምክክር ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ጥበቡ ገለፃ፤ በሀገሪቱ ከወረዳ ጀምሮ ባለው እርከን የተለያዩ ወካይ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት በሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ አካሄድ እንደሀገር እስከአሁን ከመጣንባቸው መንገዶች የተለየ ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተቀምጦ እንዲነጋገርና መፍትሔ እንዲያመነጭ ማድረግ አንዱ የአሳታፊነትና የአካታችነት መገለጫ ነው ይላሉ።
በሌላ በኩል ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጥበቡ፤ በዚህም አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በሂደቱ እየተሳተፉ ነው። የተወሰኑ ፓርቲዎች ደግሞ የምክክር ሂደቱን ከውጭ ሆነው እየተከታተሉ ያሉ አሉ፤ ከዚህ አንፃር ምክክሩ ሁሉንም ፖለቲካዊ ህልውና ያላቸውን አካላት የሚያሳትፍ እንዲሆን እየተሰራ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
አቶ ጥበቡ እንደሚናገሩት፤ በሀገሪቱ ውስጥ አሉን የሚሉት አጀንዳ ተቀባይነት እንዲያገኝ የጦር መሳሪያ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላትን በምክክር ሂደቱ ለማካተት የምክክር ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት በመነሳት ጥረቶች እያደረገ ነው። ነገር ግን ኮሚሽኑ እነዚህን አካላት ከመንግሥት ጋር የመደራደር ተግባርና ኃላፊነት የተሰጠው አይደለም። ቢሆንም ሂደቱ አካታችና አሳታፊ እንዳይሆን እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች ሲኖሩ እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካለት ጋር በቅርበት መሥራት ከኮሚሽኑ ይጠበቃል ይህንኑ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ይናገራሉ።
የምክክር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት የሚሉት አቶ ጥበቡ፤ በሀገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አካለት ሁሉ ለብሔራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የየራሳቸው ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረው ይህንኑ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም