እንደሀገር ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን በማድረጉ ሂደት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል የዲጂታል ምህዳሩ ምቹ እንዲሆን በማድረግ ተደራሽ ለማስፋት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ትግበራ ውስጥ ዋንኛ ተዋናይ የሆነውን የግል ዘርፉን በተለያየ መልኩ በማሳተፍና በማበረታታት ወደፊት እንዲመጣ እየተደረገ ይገኛል። ባለፈው ወር የዚህ አንዱ አካል የሆነው ኤክስፖ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
ኤክስፖው የተካሄደው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዚየም ‹‹ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ››/STRIDE Ethiopia 2024 Expo)‹‹ሳይንስ በር ይከፍታል፤ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፤ ፈጠራ ወደፊት ያራምዳል›› በሚል መሪ ሀሳብ ከግንቦት 11 ጀምሮ እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ለ10 ተከታታይ ቀናት ነው።
በሳይንስ ሙዚየም የተካሄደው ኤክስፖ በአይነቱ ለየት ያለ የቴክኖሎጂ ድግስ የተሰናዳበት ነበር። በኤክስፖ የተለያዩ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎች ቀርበዋል፤ የሀገሪቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እምቅ አቅም ጎልቶ ወጥቶበታል።
በዘርፉ የተሰማሩ ሀገር በቀል የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽን እና ቴክኖሎጂ /የአይሲቲ /ተቋማት በቴክኖሎጂ የደረሱበት ርቀት እና ያላቸውን አቅም ያሳዩበት ከመሆኑ በላይ መጪውን ጊዜ ፍንትው አድርጎ ማሳየት ያስቻለ ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የዲጂታል ጉዞ ለማሳካት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ዲጂታል ኢትዮጵያን ከወዲሁ እውን ለማድረግ የራሱን ሚና ሊጫወት አንደሚችል የታመነበት ነው።
በመድረኩ ካነጋገርናቸው የሀገሪቱ የዘርፉ ተቋማት መካከል አንዱ ‹‹ዳን ኢነርጂ›› የተሰኘው ተቋም ነው። ዳን ኢነርጂ ከተመሰረተ ሰባት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ የድርጅቱ ዓላማ ሕይወትን ቀላል ማድረግ የሰው ልጆች አቅማቸውን እስከመጨረሻው አሟጠው እንዲጠቀሙ በማድረግ ራሳቸውንና አገር እንዲለውጡ ማስቻል ነው።
አቶ ነብዩ ምክር የዳን ኢነርጂ ፓርትነርሽ ሽፕ ማናጀር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ዳን ኢነርጂ የቴክኖሎጂ ተቋም ሲሆን ፣ የተለያዩ ፕሮግራሞችም አሉት። ከእነዚህ ውስጥ በዋናነቱ አምስት ዘርፎች ላይ ይሰራል። በምርምርና ልማት፣ ቢዝነስ አውት ሶርሲንግ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በስልጠና ላይ የሚሰራ ፋውንዴሽን የተሰኙ ፕሮግራሞች አሉት። ፋውንዴሽን በተሰኘው ፕሮግራሙ ከ10 ዓመት እስከ 18 ዓመት ያሉ ልጆችን ቅዳሜና እሁድ በማሰባሰብ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ኮርሶችን በነጻ እንዲማሩ ያደርጋል። ትምህርቱ በዋነኛነት ኮዲንግ የተሰኘ ኮርስን የያዘ ነው። በተጨማሪም በልጆቹ ፍላጎት የተመሰረቱ ስልጠናዎችን ይሰጣል።
እንደ ሀገር ቴክኖሎጂ በማምጣትና በመስራት ብዙ አይነት ቴክኖሎጂ ቢኖሩንም፣ ተጠቃሚ ከሌለ የትም ማድረስ አይቻልም ሲሉ ገልጸው፣ በቴክኖሎጂ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስና ለማደግ ወጣቱ ትውልድ ላይ መስራት አለብን ሲሉ ይገልጻሉ። ይህም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በማብዛት፣ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተሻለ ነገር የሚሰራ ትውልድ ማፍራት ያስችላል ብለዋል።
እሳቸው አንዳሉት፤ ድርጅቱ ዘንድሮ እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ አምስት ሺ ያህል ልጆች ስልጠና ሰጥቷል። በቀጣይም ድርጅቱ ስልጠናውን በማስፋት በክልል ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ልጆችን ለማስተማር አቅዶ እየሰራ ይገኛል። ከተመራቂ ተማሪዎች እና የቢዝነስ ስራ መነሻ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው /ስታርትአፖች/ን በማሰልጠን ብዙ ሥራዎችን እየሰራም ነው።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጀቱ አሁን የአይሲቲ አገልግሎቶች ለሦስት አገራት (ብሪታኒያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጃፓን) ለሚገኙ ድርጅቶች እየሰጠ ይገኛል። በምርምርና ልማት ዘርፍ ደግሞ በሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂዎችን አምርቶ ለአርሶ አደሩ እያቀረበ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉ የጸሀይ ሀይል ቴክኖሎጂዎች ‹‹ሶላር ሆም ሲስተም›› የተሰኘ አራት አምፑሎች /ሳይቋረጥ ለስምንት ሰዓት የሚያበራ/ ሶላር ሲስተም ነው። ይህ ቴክኖሎጂ/ ሲስተም/ በቀጥታ ለሁለት ሰዓት በጸሐይ ብርሃን ቻርጅ ስለሚደረግ ስልክን ጨምሮ ቻርጅ ማድረግ ያስችላል።
በተጨማሪም ድርጅቱ የርቀት መቆጣጠሪያ ቁሶች ‹‹ሪሞት ሞኒተሪንግ ዲቫይሶች››ንም ያመርታል። ይህም በኢትዮጵያ የትኛውም ቦታ ማሽነሪዎች እና መሰል ቴክሎጂዎችን የሚቆጣጠር የመገልገያ መሳሪያ/ ዲቫይስ/ ነው። ለምሳሌ ይህ ቁስ ጀነሬተር ላይ ከተገጠመ በኋላ ጀነሬተሩ ሲበላሽም ሆነ ነዳጅ ሲያስፈልገው አልያም አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ሲከሰቱ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ያሳውቃል።
ድርጅቱ ከዚህም ሌላ የአካባቢ መቆጣጠሪያ መገልገያ /ኢንቫይሮመንት ሞኒተሪንግ ዲቫይስ/ የተሰኘ መገልገያም እንደሚያመርት ይናገራሉ። መገልገያው የሰው ልጆች ሊያሸቷቸው የማይችሏቸው ጋዞችን እያሸተተ አደጋ እንዳይከሰት ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። እነዚህ ምርቶች ለረጅም ጊዜያት ከስምንት እስከ አስር ዓመታት ያህል ሳይቋርጡ ሊያገለግሉ የሚችሉ ናቸው። ድርጅቱ ወደፊት እነዚህ አይነት ምርቶች በሰፊው በማምረት ለአርሶ አደር እንዲደርሱ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ለአርሶ አደሩ በአንድ ጊዜ ክፍያ ከፍሎ መውሰድ ስለማይችል በረጅም ጊዜ ክፍያ እንደብድር እንዲከፈሉ የሚሰጡ መሆናቸው ይገልጻል።
አሁን ላይ ድርጅቱ ወደ አይሲቲ ፓርክ በመግባት ሥራዎች ለመስራት የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ብለዋል። እንዲህ አይነት ኤክስፖ ላይ መሳተፍ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ነብዩ ጠቅሰው፣ ኤክስፖው ድርጅቱ ያለውን የቴክኖሎጂ አቅም ከማሳየት በላይ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች የማያውቁና ያልተጠቀሙ ብዙ ሰዎችና ተቋማት አገልግሎቶቹ እንዲያውቁ እና እንዲረዱ ያስችላል ብለዋል። በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ምርቶችን ሀገር ውስጥ መስራት እንደሚቻል ለማሳየት አስችሎናል ይላሉ።
በሌላ በኩል የተለያዩ ሲስተሞችን ይዘው ከመጡ ከተሳታፊ ድርጅቶች ጋር ቢዝነስ ከቢዝነስ ጋር ተገናኝቶ ለመስራት የሚያስችል እድልን መክፈቱንም አስታውቀው፣ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ብለዋል። ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር የበለጠ ትኩረት አድርጎ የተለየ ነገር ለመስራት በእጅጉ እንደሚጠቅም ተናግረዋል።
ሌላው በኤክስፖው ላይ ያገኘነው ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ተቋም የዘረጋው ክላውድ የተሰኘው ድርጅት ነው። የዘረጋው ክላውድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ክላውድ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት መሆኑን የምትናገረው የድርጅቱ የገበያ ልማት/ ማርኬቲንግ/ ባለሙያ ናርዶስ አስጨናቂ እንደምትለው፤ ዘርጋው ክላውድ ከተመሠረተ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። አሁን በዋናነት የክላውድ (የመሰረተ ልማት፣ የሶፍትዌር እና የደህንነት) አገልግሎቶችን ይሰጣል፤ የብሮድባንድ ኢንተርኔትና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል።
ድርጅቱ የሚሰጠው አገልግሎት ለሁሉም ቢዝነስ አይነት የሚውል ሲሆን፣ አሁን ላይ አገልግሎቱን ከሚጠቀሙት መካከል ትልልቅ ድርጅቶች ባንኮች፣ ፊንቴኮች እና ማይክሮፋይናንስ ይገኙበታል። እንደየድርጅቱ ፍላጎት ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ አገልግሎቱን መጠቀም ይችላሉ ትላለች።
ድርጅቱ የመጀመሪያ የክላውድ አገልግሎት ሰጪ ሀገር በቀል ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በአገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ማላመድና መስጠት ከባድ እንደነበር ተናግራለች። አሁን ያለው እድገት ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሳ፣ አብዛኛዎቹ ድርጅቶች አገልግሎቱን ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ በዚህም ብዙ ተጠቃሚ ደንበኞች ማፍራት መቻሉን ተናግራለች።
ናርዶስ እንዳለችው፤ በእነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ ከ600 በላይ የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች የድርጅቱን አገልግሎት እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ለዚህም የኢትዮቴሌኮም እገዛ ቀላል የማይባል ነው። ኢትዮቴሌኮም ፖርታል ላይ አገልግሎቶቹ እንዲሰጡ ማድረጉ ትልቅ እገዛ አድርጎለታል።
ድርጅቱ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ጥናት በማድረግ በሀገር ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ ክፍተቶች መለየቱን ጠቅሳ፣ ይህን ለመሙላት የሚያስችል ሥራ እየሰራ መሆኑን ናርዶስ ትናግራለች፤ አሁን ላይ ጥራት ያለው አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እና በአጭር ጊዜ እየሰጠ ይገኛል ስትል ገልጻም፣ አገልግሎቱን የሚፈልጉ አካላት በጠየቁ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ አስታውቃለች።
ናርዶስ እንዳብራራችው፤ ዘርጋው ክላውድ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢዎች፣ ከአይሲቲ ፓርክ፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል። ከአይሲቲ ፓርክ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረትም አይሲቲ ፓርክ በመግባት የራሱን ዳታ ሴንተር ለመገንባት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሰራ ነው።
ድርጅቱ አዳዲስ ብዙ አገልግሎቶችንም እየሰራ ነው፤ የቢዝነስ ስራ መነሻ የፈጠራ ባለሙያዎች /ስታርትአፖች/ና ለተመራቂ ተማሪዎች የሚሆኑ ለየት ያሉ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል። ለተመራቂ ተማሪዎች ከሌሎች እህትማማች ድርጅቶች ጋር በጋራ ስልጠና ለመስጠት በዝግጅት ላይም ይገኛል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካም ታማኝ የክላውድ አገልግሎቶች አቅራቢ የመሆን ዓላማ እንዳለው ናርዶስ ጠቁማለች።
እንደ ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ አይነት መድረኮች በተለይ ለዘርጋው ክላውድ ድርጅት እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቅሳ፣ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በኤክስፖ ተሳታፊ የሆኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ /አይሲቲ/ ድርጅቶች በሙሉ የድርጅቱን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ስለሚችሉ ነው ብላለች። መድረኩ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ እድል እንደፈጠራላቸው ትናገራለች። ከጎብኚዎችም ጋር ግንኙነት በመፍጠር በርካታ ደንበኞች ለማፍራት መቻሉን ጠቅሳለች።
ዘርጋው ክላውድ አገልግሎት ወደ ሥራ በገባበት ጊዜ ሥራው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥመውት እንደነበር አስታውሳለች። ችግሮችን አልፎ፣ ብዙ ልምዶችን ያካበተ ድርጅት ነው የምትለው ናርዶስ፤ አሁን ላይ ያለው የዲጂታል ምህዳርም ሆነ ቢዝነሱ ጥሩ የሚባል መሆኑን አስታውቃለች። ምህዳሩ ሌሎች የክላውድ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች እንዲመጡ መልካም አጋጣሚን እየፈጠረ መሆኑን አመላክታለች። ቀደም ሲል በክላውድ አገልግሎት ላይ ኢትዮቴሎኮምና ዘርጋው ክላውድ ብቻ እንደነበሩ ጠቅሳ፤ አሁን ላይ ያለው ምቹ ሁኔታ ሌሎች እንዲመጡ አስችሏል ብላለች። በዚህ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ሁሉ ፈተናዎችን ተጋፍጠው በርትተው ሊሰሩ እንደሚገባም ትመክራለች።
የኤክስፖው ሌላኛው ተሳታፊ ‹‹ኢንፎናንስ ሶልሽን ፒኤልሲ›› የተሰኘ ድርጅት ነው። የድርጅቱ የሽያጭ ባለሙያ መቅደስ እሸቱ እንደምትለው፤ ድርጅቱ በአይሲቲ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመ ነው። ለማንኛውም አይነት ድርጅት በአይሲቲ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መፍትሔ ይዞ ቀርቧል። አሁን ላይ ሁሉም ነገር በሚባል ደረጃ ከኮምፒዩተርና ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ድርጅቱም የዳታ ሴንተር ፋሲሊቲ እና መሰል ሥራዎችን ይሰራል። ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ዘመናዊ ካሜራዎችን በማስመጣትም ለድርጅቶች ይቀርባል።
መቅደስ እንደምትለው፤ በአይሲቲ ዙሪያ ችግር የገጠመው አንድ ተቋም የገጠመውን ችግርና የሚፈልገውን አገልግሎት ካሳወቀ በሚፈልገው መጠን እና ልክ የሚፈልገው አገልግሎት እንዲሰጠው ይደረጋል። አሁን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባባር ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች (Smart Classrooms) እየሰራ ነው። ይህም በቦንጋ እና በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲም በመሰራት ላይ ይገኛል።
ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ተገኝተው መማር በማይችሉበት ጊዜ ትምህርቱን ኦንላይን መማር የሚያስችላቸው ነው። መምህሩም በክፍል ውስጥ መገኘት ካልቻለ ካለበት ቦታ ሆኖ ትምህርቱን መስጠት ያስችለዋል። ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች እንዳሉትም ተመላክቷል።
በተጨማሪም የአጭር መልእክት አገልግሎት /ኤስኤምስ(SMS)/ አገልግሎት ይሰጣል። በአጭር መልእክት አገልግሎቱ አንድ መልዕክት ለብዙ ደንበኞች አንድ ጊዜ መላክ የሚያስችል አገልግሎት እየሰጠ ነው። ኤስኤምስ አገልግሎት በርካታ ደንበኞች ያሏቸው ተቋማት ለደንበኞቻቸው መልዕክት ማስተላላለፍ ሲፈልጉ የሚጠቀሙበት አገልግሎት ነው። አሁን ይህን አገልግሎት አዳማ ከተማ አስተዳደር እና ቡና ኢንሹራንስ እየተጠቀሙበት ሲሆን፤ በቀጣይ ከንብ ኢንሹራንስ ጋር ለመስራት የሚያስችል ውል መፈረሙንም ትገልጻለች።
ድርጅቱ በቀጣይ ለአይሲቲው ዘርፍ መፍትሔ የሚሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የሚፈልጉት የቴክኖሎጂ ውጤት በሚመጥናቸው መልኩ አድርጎ ያቀርባል ያለችው መቅደስ፤ በቴክኖሎጂ ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረጉ ሂደት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብላለች።
‹‹ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ›› በአገር ውስጥ ያለው የቴክኖሎጂ አቅም የታየበት ነው። ድርጅቱን ብዙ ሰዎች እንዲያውቁትና ብዙ ደንበኞች ጋር እንዲያፈራ ያደረገ ነው። ከሌሎች የቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ብዙ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እንደረዳቸው መቅደስ ትናገራለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም