ሀገራችን ካላት ከፍተኛ የቀንድ እንስሳት ሀብት አንጻር በቆዳና ሌጦ ዘርፍ ከፍ ባለ ደረጃ ተጠቃሚ እንደምትሆን ይታመናል። ይህንን ሀገራዊ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ በየወቅቱ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም፣ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ግን አልተቻለም።
በአንድ ወቅት ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆነው ይህ ዘርፍ ፤ መፍትሄ አልባ ረጅም ዓመታትን አስቆጥሮ አሁን ይህ ሀብት ሀብት የማይመስልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ፤ እንደዋዛ በየቦታው እየተጣለ እና የጤና ጠንቅ እየሆነም ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ እርድ በሚካሄድባቸው በዓላት ወቅት ውድ ሀብት የሆነው ቆዳ እየተጣለ ያለበትን እውነታ መጥቀስ ይበቃል።
የቆዳው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እንዲሁም የሥራ እድል በመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው ቢታወቅም ፤ አሁን ላይ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት እየቻሉ አይደለም፤ አንዳንዶቹም መዘጋታቸው ይገለጻል፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት ኢንዱስትሪው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማበርከት ተስኖታል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ ኢትዮጵያ በዓለም በቆዳ ምርት ጥራት ከሚታወቁ ሀገራት በዋንኛነት ትጠቀሳለች። በተለይም በሀገሪቱ በስፋት የሚገኘው የደጋ ቆዳ በመባል የሚታወቀው የቆዳ አይነት በዓለም ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት እና ተወዳዳሪነት አለው።
ይህም ሆኖ ግን በሀገሪቱ ያለው የእንስሳት ጤና አገልግሎት ፤ የቆዳ አሰባሰብ እና የቆዳ ደህንነት አጠባበቅ በቆዳ ጥራት ላይ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ፤ ለቆዳ ኢንዱስትሪ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ግብአቶች 60 በመቶ ከውጭ የሚገቡ መሆናቸው ፤ ለዚህ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ ከሁሉም በላይ ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች የመጠቀም ፍላጎት ዝቅተኛ መሆን ለዘርፉ ዕድገት ፈተና ሆነዋል።
በቆዳ ልማት ለመሰማራት ዋና ዋና የሚባሉ መሠረተ ልማቶች አለመቻቸት፤ የሚመለከታቸው አካላት በዘርፉ ያሉ ባለሀብቶችን በመደገፍ ምርቱን የበለጠ ለዓለም ገበያ ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር አለመቻላቸው ሌሎች በዘርፉ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
መንግሥት በዘርፉ የሚታየውን ችግር ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ለመፍታት የዘርፉን እድገት ያፋጥናል በሚል ፤ ዘርፉን የሚመራ ኢንስቲትዩት እስከማቋቋም የደረሰበት አጋጣሚ እንደነበር ይታወሳል። አሁንም ቢሆን መድረኮችን ከማዘጋጀት እና በሚታወቁ የዘርፉ ችግሮች ዙሪያ ከመወያየት ያለፈ ተጨባጭ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ተግባር ሲከናወን እየታየም አይደለም።
ይህም በራሱ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሀብቶች እስከ ችግሮቻቸው ዓመታት እንዲያስቆጥሩ ከማድረግ ባለፈ ሀገራዊ ሀብቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲባክን አድርጎታል፤ ሀገር ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ በምትፈልግበት ባለንበት የልማት ወቅት ፤ዘርፉ ሊያመነጨው ለሚችለው ሀብት ባይተዋር ለመሆን የተገደድንበት እውነታ ተፈጥሯል።
አሁን ላይ ይህን ሀገራዊ ችግር ለመፍታት የሚያስፈልገው በችግሮቹ ዙሪያ ጉባዔ እየጠሩ ማውራት ሳይሆን፤ ችግሮቹ የሚፈቱበትን ተጨባጭ መፍትሄ ማፈላለግ ነው። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በሙሉ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱና ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት ሊፈጥሩ ይገባል።
በዘርፉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ፈጥነው ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ ማፈላለግ ፤ ከቆዳ ጥራት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እታች ወርዶ መሥራት የሚያስችል ሥርዓት ማበጀት፤ የኢንዱስትሪውንም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በጠንካራ ዲሲፕሊን መምራት የሚያስችል የአመራር ቁርጠኝነት መፍጠር ይገባል።
ከሁሉም በላይ ለኢንዱስትሪው ግብአት የሚሆኑ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችሉ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በስፋት በማቅረብ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች በብዛት በዘርፉ የሚሳተፉበትን ዕድል ማመቻቸትም ያስፈልጋል።
በተለይም የደጋ አካባቢ እንስሳት ቆዳን በጥራት እና በብዛት በዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚቻልበትን ስትራቴጂ ለብቻው በመንደፍ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ሀገር እና ሕዝብ የዚህ ትልቅ ሀብት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል መፍጠር እና ማስፋት ያስፈልጋል። ወቅቱ በሚታወቁ ችግሮች ዙሪያ ጉባዔ እየጠሩ የሚያወሩበት ሳይሆን ተጨባጭ መፍትሄ የሚፈለግበት እና ወደ ተግባር የሚገባበት ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም