የትምህርት ስብራቱን በማያዳግም ርምጃ መጠገን

“የትምህርት ስብራት” የጋራ ቋንቋ ከሆነ ቆየ። በተለይ ከለውጡ በኋላ “የትምህርት ስብራት” የሚለው “ብሶት የወለደው“ ኃይለ-ቃል አየር ለአየር በመናኘት የሚዲያው ሁሉ፣ የአጀንዳዎች ሁሉ፤ የማኅበረሰቡ ውይይቶች ሁሉ የበላይ ርዕሰ ጉዳይ በመሆን እነሆ እስካሁንም አለ።

ቀደም ሲል ተግባር ላይ ውሎ በነበረው “አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ“ ምክንያት በትምህርቱ ዘርፍ ያልደረሰ የትምህርት ስብራት የለም። ይህም ዛሬ ለውጥን ተከትሎ የመጣ ሳይሆን አጠቃላይ ሕዝቡ ቅሬታ ሲያቀርብበት የነበረ፤ እስከ “ዮዲት ጉዲት“ ድረስ የዘለቀ ወቀሳ ሲሰነዝርበት የቆየ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደ ነበር የሚታወስ ነው።

የዚህ ጽሑፍ መነሻ በቅርቡ (አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም) የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል (ዶ/ር) ከጋዜጣው ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ‹‹የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሁሉም አካላት ትኩረትና ርብርብ ያስፈልጋል›› በማለት የተናገሩት ሲሆን፤ ይህ የእሳቸው የቅርብ በመሆኑ ጠቀስነው እንጂ እስከዛሬ ድረስ ስለ “የትምህርት ስብራት?” ያልተባለ የለም። ያልተባለ አይኑር እንጂ በደፈናው ስለ መሰበርና መሰባበሩ ከመናገር ያለፈ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ · · · በማለት ቆጥሮ የተናገረ የለም። ወይም፣ ሀ፣ ለ፣ ሐ · · · በማለት ዘርዝሮ ያስቀመጠ አልተገኘም። በመሆኑም ጉዳዩ ከ”ሾላ በድፍን” ይወጣ ዘንድ ይህ ጽሑፍ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ከ1ኛ ደረጃው እንጀምር።

የትምህርት ፖሊሲው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ አንድ መምህር ያስተምር (″ሰልፍ ኮንቴይንድ″ ይባል የነበረው የማስተማር ሥነ-ዘዴ) ተብሎ የተወሰነ ጊዜ “ኧረ በሕግ“ ቢልም የሰማው አልነበረም። በመማር-ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ተማሪና አስተማሪው ቦታ ሲለዋወጡ “ኧረ ይሄ ነገር አያዋጣም“ ሲባል፣ በወቅቱ የነበረው መልስ “ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ“ ነበር። “ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ያለ ምንም አይነት ፈተና (ምዘና) ይለፉ“ የተባለ ጊዜ “እንዴ፣ እንዴት እንዴት ነው ነገሩ · · ·“ በማለት ያላጉረመረመ ሰው ካለ እሱ እዚህ አገር ያልነበረ ነው። ምኑ ቅጡ – ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት በትምህርት ላይ የደረሰው ስብራት፣ ቅጭትና አጠቃላይ ኪሳራ እዚህ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።

ስብራት፣ ቅጭትና ኪሳራው ከታችም አልፎ ወሳኝ የሆኑትን መምህራንን ሳይቀር የጎነተለ ሲሆን፤ በጽሕፈት ቤታቸው ተገኝተን ያነጋገርናቸው፣ በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ምሬሳ እንደሚሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ (በተለይ ለመምህራን) የክረምት ኮርሶች ሁሉ ሳይቀሩ በችግር የተተበተቡና በዚሁ በተበተባቸው ችግር ምክንያት ለውጡን ተከትሎ እንዲቋረጡ ተደርገዋል።

እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፣ በሀገራችን ከሚገኙት 800ሺህ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች (የመንግሥት) ከ94 በመቶ በላይ የሆኑት ተገቢው የትምህርት ደረጃ (ማስረጃ) ያላቸውና የሚሠሩበትን የሥራ ዘርፍ የሚመጥን ነው። ይሁን እንጂ ብቃትን ለማረጋገጥ በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም ሆነ የተገኘው የተማሪዎች የፈተና ውጤት (በተለይ ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት) የሚያሳየው መምህራን በሙያው የሚፈለገውን የትምህርት ደረጃና ማስረጃ ይያዙ እንጂ የአቅም ክፍተት ያለባቸው መሆኑ ነው።

የዴስክ ኃላፊዋ እንደነገሩን ከሆነ፣ በየዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በክረምት ኮርስ (ሰመር ፕሮግራም) ሲከታተሉ የነበሩ ሠልጣኝ መምህራን እንዲያቋርጡ የተደረጉት በመምህራን ልማት ስም ሲካሄድ የነበረው ፕሮግራም “የአመራር ክፍተት የታየበት፣ ወጥነት የሌለው፣ ግማሹ በሁለት ወር፣ ግማሹ በሁለት ዓመት፤ ያሰኘው ደግሞ ባሰኘው ጊዜ የሚያስመርቅበት፤ የተዘበራረቀና መምህራን ተመልሰው የትምህርት ጥራትን ሊያመጡ በሚችሉበት አይነት ዝግጅት አልነበረም እየተካሄደ የነበረው። በመሆኑም፣ ጥናት ተደርጎ በጥናቱ ግኝት መሠረት ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፤ በፕሮግራሙ 8ሺህ አካባቢ የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ) እና 34ሺህ አካባቢ ሁለተኛ ዲግሪ (ኤምኤ) መርሐ ግብሮችን የሚከታተሉ መምህራን ነበሩ። አካሄዱ የተሳሳተ ነገር ስላለው ተቋርጧል።“ ይህም ሌላው የትምህርት ዘርፉ ከወለምታም የዘለለ፣ ቅጭትና ስብራት ስለ መሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነውና ስብራቱን “የቱ ጋ?” በማለት ለሚጠይቁ ወገኖች መልስ ይሆናል።

የነበረው የተሳሳተ የትምህርት ፖሊሲ በትምህርቱ ሴክተር ያላደረሰው ስብራት የለም የሚሉ የትምህርቱ ዘርፍ ተቆርቋሪዎች 2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ አይችሉም፤ ከአጠቃላይ የማትሪክ ተፈታኞች 3 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ለአቅመ ከፍተኛ ትምህርት የደረሱት እና ለመሳሰሉት “የሚጠበቅ“ ከሚል መልስ በዘለለ ምንም ትኩረት ሳይሰጡ፤ ከፍተኛ ትኩረታቸውን የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ በመሸመት በየቢሮው የተሰገሰገውና ዜጋን በሚያተራምሰው፤ ዲግሪን እንደ አልባሌ ወረቀት በሚቸበችበው ላይ በማድረግ ያንን “አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ“ ሲወቅሱና ሲያወግዙ ይታዩና ይሰማሉ። ይህም ሌላው የነበረው የትምህርት ሥርዓት ስብራት መሆኑን ያሰምሩበታል። “ያለፈው ይበቃል” በሚል ዘይቤ ድርጊቱ መቸም መቸም እንዳይደገምም ይማፀናሉ።

የነበረውን የ12ኛ ክፍል ማትሪክ መውሰጃ ወደ 10ኛ ዝቅ በማድረግ ሁሉንም ነገር አብሮ ዝቅ ያደረገው የትምህርት ፖሊሲ፣ የነበረውን የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች አራት ዓመት ዝቅተኛ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ወደ ሦስት ዓመት በማውረድ ሁሉም ነገር አብሮ እንዲወርድ፤ የሁሉም ነገር አይንና ጆሮ እንዲጠፋ ያደረገው የትምህርት ፖሊሲ በአገርና ትውልድ ላይ ያላደረሰው ስብራት ብቻ ሳይሆን፤ ያልሰረቀው የትውልድ እድሜና ሥነልቦና፣ ያልቀረጠፈው የአገር ኢኮኖሚ፣ ያላባከነው ጊዜና ጉልበት አልነበረም። በመሆኑም፣ አሁን እየተሠሩ ባሉ የለውጥ ሥራዎች ውስጥ ሁሉ ይህ ሁሉ ብክነት ታሳቢ ሊደረግና (“ነቨር ነቨር አጌይን” እንደ ተባለው) ዳግም እንዳይደገም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ሳይቀሩ የክብር ዶክትሬት ማዕረግን በአካባቢ፣ በአምቻና ጋብቻ በመስጠታቸው ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር ከእንግዲህ እንዳይሰጥ ማገዱ (የአሰጣጥ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል) የዚሁ ውድቀታችን፣ የትምህርት ስብራታችን አንዱና ሌላው አስቂኝ ማሳያ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፋ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው መገኘታቸውም እንደዛው።

ከላይ እንደ ጠቀስናቸው፣ እንደ የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል (ዶ/ር) ሙያዊ አስተያየት ከሆነ የትምህርት ስብራት የተጀመረው የቀድሞውን የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በካልቾ ከመምታትና ብቁ መምህራንን ከማሠልጠን አኳያ ሲወጣ ከነበረው ተልዕኮና ኃላፊነት መንቀል የተጀመረ ጊዜ ነው።

ፕሬዚዳንቱ እንደ ተናገሩት ከሆነ በ1935 ዓ.ም የመጀመሪያው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ መደበኛ ትምህርት ማስተማር የጀመረውን ተቋም፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የትምህርት ዓይን ከፋች የሆነውን ተቋም፤ እንደነ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ከበደ ሚካኤልን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች የተማሩበት የመደበኛ ትምህርት ዓይን ከፋች የሆነውን የእውቀት ደብር፤ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ መምህራን ኮሌጅ ሆኖ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መምህራንን ለኢትዮጵያ ያበረከተ አንቱ ሊባል የሚገባውን ትልቅ ተቋም፤ አንጋፋ፣ ብዙዎችን ያፈራና በብዙኃኑ ሕዝብ ላይ ዐሻራውን ያሳረፈን ተቋም ወገቡን መምታት ሳያስፈልግ መመታቱ በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖውን ኣሳርፏል። ዶክተሩ ምክንያቱ ሲገልፁም “እንደስሙ ሳያድግ የቆየበት ምክንያት የነበሩት ሥርዓተ መንግሥታት ባሳረፉበት ጫና ነው። ሰውና ተቋምን ለይቶ ባለማየት በሰዎች ላይ ባላቸው ግላዊ ግጭትና ጥላቻ ተቋሙ ወደ ኋላ እንዲቀር ተደርጓል።“ ይህም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ደርሶ የነበረ አንዱ ስብራት ነውና አሁንም እየተሠሩ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ይህንን አይነቱን በተቋም ላይ ሳይቀር ያተኮሩ ስህተቶች እንዳይፈፅሙና ሀገርና ሕዝብን ዳግም ዋጋ እንዳያስከፍሉ ጥንቃቄ ያሻል።

“ለረጅም ዓመታት በትምህርት ዘርፉ አገልግለዋል። አሁንም በሀገሪቱ የመጀመሪያና ብቸኛ የሆነውን የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይመራሉ። በእርስዎ እይታ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ዋነኛ ችግር ምንድን ነው?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ:-

የኢትዮጵያ ትምህርት ዋንኛ ችግሮች ሁለት ጉዳዮች ናቸው። የመጀመሪያው ችግር ባለፉት ዓመታት ችግሮችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ ከመፍታት ይልቅ በጨበጣ ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት ነው። ችግሩን በጥናት ለይቶና መፍትሔዎችን አስቀምጦ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ችግርን በስብሰባ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ይስተዋል ነበር። ሁለተኛው ችግር ደግሞ ጥናት ተብለው የሚቀርቡ ጥናቶችም በረጂ ድርጅቶች ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸው ነው። ጥናቱ በርዳታ ላይ የተንጠለጠለ ስለሆነ የሆነ ሀገር የተሠራውን ጥናት አምጥተው የስም ለውጥ ብቻ በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠና አስመስለው ያቀርቡ ነበር። እነዚህ ጥናቶች በርካታ የሀገር ሀብት ቢፈስባቸውም መሠረታዊ ችግሩን የለዩ ባለመሆናቸው ሊፈቱት አልቻሉም።

ትምህርት ተሰብሮ ብልጽግና አይረጋገጥም፤ ትምህርት ተሰብሮ ልማት ሊለማ ይችላል ግን ያልተማሩ ሰዎች መጥተው ያፈርሱታል። ልማታችን ሰው ተኮር ካልሆነ ከባድ ነው። መሰል ችግሮችን ለማስቀረት በማሰብ ከተሠሩት ሥራዎች አንዱ በሀገራችን ምሑራን የተዘጋጀ ሀገር በቀል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ነው። በዚህም የእኛን ችግር ማዕከል ያደረገና ራዕያችንን የሰነቀ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅተናል።

በማለት መመለሳቸው አስተማሪነቱ እንዳለ ሆኖ፤ የአሁኑ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ ደግሞ አሁን ላይ በትምህርቱ ዘርፍ እየታየ ያለው ስብራት ለውጥ ከመምጣቱ በፊት በነበሩት “27 ዓመታት በትምህርቱ ላይ ሆን ተብሎ በተሠራ አሻጥር“ ምክንያት ነው። (“አሻጥር“ የሚለው “ሳቦታዥ“ የሚለውን እንግሊዝኛ ቃል የሚወክል ከመሆኑ አኳያ በቀላሉ ሊታይ የሚችል ጽንሰ ሀሳብ አይደለም የሚሉ ብዙዎች ሲሆኑ፤ ጉዳዩ የሚያወያይ፣ የሚያመራምር ወዘተ ስለ መሆኑ በስምምነት የሚያልፉ በርካቶች ናቸው።) ብርሃነመስቀል (ዶ/ር) መፍትሔ በማለት ያስቀመጡትና:-

ችግሩ ሰፊ ስለሆነ በቀላሉ ለመውጣት ሊከብደን ይችላል። ግን ያሉ ሀገራዊ አቅሞቻችንን አስተባብረን ከተጠቀምን ለውጥ የማናመጣበት ምክንያት አይኖርም። ችግሩ የመንግሥትን ትኩረትና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይፈልጋል። ለኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲም መንግሥት ሙሉ ትኩረት መስጠትና ሊሟሉ የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዲሟሉ ከማድረግ አንጻር እንዲያግዘን እንፈልጋለን። ዩኒቨርሲቲውም ዘር ላይ የሚስተዋለውን ችግር ከመቅረፍ አንጻር የበኩሉን ሚና ለመወጣት በቁርጠኝነት የምንሠራ ይሆናል። ሕዝቡ ደግሞ በየአካባቢው ልጆቹን ለማስተማር የሚሄዱለትን መምህራን ማክበርና ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በተመሳሳይ መልኩ፣ ከዚህ ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት፣ በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች “ትምህርት ማኅበራዊ ጉዳይ ነው። ባለቤቱም ማኅበረሰቡ ነው። በመሆኑም ለትምህርት ጥራት መጠበቅም ሆነ አለመጠበቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁሉም ኃላፊነት አለበት። በተለይ ባለ ድርሻ አካላት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ወላጆች ቀጥተኛ ተሳታፊዎች በመሆናቸው እየተከናወነ ካለው የትምህርት ሥርዓት ለውጡ ጎን ሊቆሙ ይገባል። በትምህርት ላይ የሚሠሩ ተቋማትም ከእኛ (ትምህርት ሚኒስቴር) ያልተናነሰ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ አብረን በጋራ ልንሠራ ይገባል” እንዳሉት ሁሉ፤ እኛም የእነዚህኑ ባለሙያዎች አስተያየት በማፅደቅ ዝግጅታችንን በዚሁ እንቋጫለን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You