በአረንጓዴ ዐሻራ ያስመዘገብነውን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ እናሸጋግር!

ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞገስ እና ተደማጭነት ካገኘችባቸው አጀንዳዎች አንዱ የአረንጓዴ አሻራ ነው። ይህ ሀገርን አረንጓዴ እናልብስ በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት በተፈጠረ ሀገራዊ መነቃቃት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የችግኝ ተከላ ዘመቻ የተራቆቱ መሬቶችን በደን ከመሸፈን ባለፈ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ ሊያጋጥማት የሚችለውን ፈተና ለመሻገር የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል።

በርግጥ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ የዛፍ ችግኞችን የመትከል ልማድ እንዳላቸው በየዘመኑ የነበሩ ነገስታቶችም ለችግኝ ተከላ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።ይህም በተወሰነ መልኩ የሀገሪቱን የተፈጥሮ አካባቢ መጠበቅ እንዳስቻለ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዘመናት ሂደት ውስጥ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የከተሞች መስፋፋት ፣ የሚታረስ መሬት መጨመር … ወዘተ የደኖች ምንጣሮ መብዛቱና እነሱን የመተካቱ ጥረት ዝቅተኛ መሆን ሀገሪቱን ከፍተኛ ለሆነ የደን መራቆት ዳርጓታል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ዓመታት ቆጥሮ ለሚመጣ የድርቅ አደጋ ተጋላጭ የሆነችበት ፣ ሰፊ የሚባል የተፈጥሮ አካባቢም ለአደጋ የተጋለጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው” የደን መራቆት ችግሩ ዓለምን እየተፈታተነ ካለው ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ ካርቦን ጋር ተዳምሮ ሀገሪቱን የከፋ የተፈጥሮ አደጋ ስጋት ውስጥ ሊከታት እንደሚችል፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጅት መፍጠር ካልቻለች አጠቃላይ በሆነው የሕዝቦቿ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ሊያሳድር የሚችለው አደጋ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይገመታል።

አሁን ላይ በግብርና ላይ የተመሰረተው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ጨምሮ በምግብ እህል አቅርቦት ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ እንደ ሀገር በጀመርነው ራሳችንን በምግብ እህል ለመቻል የጀመርነውን ሀገራዊ ንቅናቄ የሚፈታተን ፣ ከዚህም በላይ ድህነትን ታሪክ አድርገን ለመሻገር የጀመርነውን መራራ ትግል ትርጉም አልባ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል።

ይህንን ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስጋት ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ከ32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

በቀጣይ ሦስት ዓመታት ደግሞ 17 ነጥብ አምስት ቢሊዮን በመትከል 50 ቢሊዮን ችግኞችን በስምንት ዓመታት ውስጥ ለመትከል እቅድ ተይዟል። እስካሁን ለተተከሉት ችግኞች በተደረገው ክትትል እና እንክብካቤ የችግኞቹ የጽድቀት መጠን ከ90 በመቶ በላይ ደርሷል። ለዚህም መላው ሕዝብ ችግኝ ከመትከል ባለፈ እያዳበረ የመጣው የመንከባከብ ሥራ ትልቁን ስፍራ የያዘ ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮ ዓመት አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል። የችግኝ ቁጥር በሄክታር ሲሰላ ዘንድሮ ተከላ የሚደረግበት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚሆን ይገመታል።

የመላው ሕዝባችን የነቃ ተሳትፎ የታየባቸው በእነዚህ አምስት ዓመታት ሕዝባችን ከሁሉም በላይ የችግኝ ተከላ ለራሱም ሆነ ለመጪዎች ትውልዶች እጣ ፈንታ የቱን ያህል ወሳኝ አቅም እንደሆነ በአግባቡ መረዳት የቻለበት፣ ከዚህ በመነሳትም ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ የሚጠበቅበትን ለማድረግ በንቃት የተንቀሳቀሰበት ነው።

የችግኝ ተከላው በሂደት ለምግብነት የሚውሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን ታሳቢ እያደረገ መምጣቱ እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ለምናደርገው ሀገራዊ ንቅናቄ ስትራቴጅክ አቅም መሆን የቻለ ነው። እንደ ሀገር ያለብንን የተመጣጠነ የምግብ እህል አቅርቦት ችግር ለመፍታትም ሌላኛው አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ከዚህም ባለፈ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ብዛት ያለው የሰው ኃይል ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ባለው የሥራ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ እንደ ሀገር ያለብንን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረት ተጨባጭ አቅም የሆነበት ሁኔታም ተፈጥሯል። በዚህም ብዛት ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለስድስተኛ ጊዜ የምናካሂደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም ይህንን በዘርፉ እንደ ሀገር እያስመዘገብን ያለውን ትልቅ ስኬት በማስቀጠል ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሀገራዊ ተጠቃሚነታችንን ማጎልበት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ያገኘነውን ዕውቅናና ተደማጭነት በተሻለ መልኩ ማስቀጠል የሚያስችል ነው!

አዲስ ዘመን ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You