የትምህርት ሥርዓቱን ስብራት ለማከም!

ትምህርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ዋነኛ አቅም ነው። ከዚህ የተነሳም ሀገራት ለትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ ዘመኑን በእውቀት የሚዋጅ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። እንደ ሥራቸው ስኬትም ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ያሉበትን ከፍታ ለመቀናጀት ችለዋል ።

በዕድገት እና በሥልጣኔ አንቱ የተባሉ ሀገራት እና ሕዝቦች ፤ አሁን ለደረሱበት ደረጃ በዋንኛነት የሚጠቀሰው ለትምህርት /ለእውቀት ሽግገር የሰጡት ትኩረት ነው ። ነገዎቻቸውንም የተሻለ ለማድረግ የሚያደርጉት ሁለንተናዊ ጥረትም በትምህርት ላይ ካላቸው የጸና እምነት የሚነጭ ነው።

በእኛም ሀገር ከትምህርት ጋር በተያያዘ የነበረው አስተሳሰብ በየዘመኑ የተለያየ ገጽታ ቢኖረውም ፤ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትን ተከትሎ የተፈጠረው እሳቤ ግን ፤ ለትምህርት ትልቅ ትኩረት የሰጠ ፤ ለሀገርም ሆነ ለተሻለ ማኅበረሰብ ግንባታ ትምህርት ወሳኝ አቅም እንደሆነ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።

ለዚህም ሀገሪቱ ለዘመናዊ ትምህርት በሮቿን መክፈት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት እና መላው ሕዝብ የትምህርትን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ በነበሩ አማራጮች በሙሉ የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል ። በየዘመኑ የነበረ ትውልድ የተሻለ ትምህርት የሚያገኝበትን ዕድል ለመፍጠር የአቅሙን ያህል ተንቀሳቅሰዋል ።

ሕዝባችን ገና ከጅምሩ ልጆቹን ማስተማሩ ለራሱም ሆኑ ለሀገሩ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ብሩህ ነገዎች እንደማስተማመኛ አድርጎ በመውሰድ ፤ ተቸግሮና ተንገላቶም ቢሆን ልጆቹን ለማስተማር ብዙ ዋጋ ከፍሏል። በትምህርት ወስጥ አርቆ ያየውን ተስፋ ለመጨበጥ ዛሬዎቹን መስዋዕት አድርጎ አቅርቧል ።

ይህም ሆኖ ግን ሀገራዊ የትምህርት ሥርዓቱ በየወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ጥላ ያጠላበት በመሆኑ ፤ ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿ ለዘርፉ ለመክፈል የተገደዱትን ዋጋ ያህል ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዚህ ይልቅ በየዘመኑ የነበረው የትምህርት ሥርዓት በፈጠረው ግራ መጋባት ሀገሪቱ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደደችበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የትናንት ታሪካችን በተጨባጭ እንደሚያመለክተው ፤ እንደሀገር ብዙ ተስፋ የተጣለበት ትውልድ እውቀት ሊፈጥር የሚችለውን ስክነት አጥቶ ፤ የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን በሚጋጭ ጥራዝ ነጠቅነት ተወስዶ ፤ ለራሱም ሆነ ለሀገሩ ያልሆነበት ታሪካዊ ክስተት ተፈጥሯል ። የዚያ ጥራዝ ነጠቅነት እርሾም ዘመን ተሻግሮ አሁን ያለውን ትውልድ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።

ችግሩ/ስብራቱ ዛሬ ላይ አድጎ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሰፊ የተማረ ኃይል ባለበት ሁኔታ የተለየ ገጽታ ሊላበስ አልቻለም ፤ ይህም በማኅበረሰቡ ውስጥ ለትምህርት የነበረውን ከፍተኛ መነቃቃት አደብዝዞታል ፤ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘለት በሀገሪቱ ዛሬም ሆነ ነገዎች ላይ ይዞት ሊመጣ የሚችለው ፈተና በቀላሉ የሚሰላ አይሆንም።

ብዙ በመሥራት ራሱን እና ሀገርን መለወጥ የሚችለውን ትውልድ በቁሙ በጠባቂነት እና በጥራዝ ነጠቅነት እየጎዳ ያለው ሀገራዊ የትምህርት ሥርዓት አሁን ላይ ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተካከያ ሊደረግለት ይገባል፤ ይህንን ማድረግ ከተሳነንና ለዚህ የሚሆን ማኅበረሰባዊ መነቃቃት ካጣን እንደ ሀገር የምናስበው ብልጽግና ከምኞት ያለፈ ሊሆን አይችልም ።

በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ችግር/ስብራት ለማከም የምንችለው የምዘና ሥርዓትን በማዘመን ወይም ሥርዓተ ትምህርትን በማሻሻል ብቻ አይደለም ። ከዚህም ባለፈ በትምህርት ላይ የሚደረገውን ሪፎርም ከታች በመጀመር ፤ በማኅበረሰባችን ውስጥ ከትምህርት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን አሉታዊ አስተሳሰብ በአግባቡ በመግራት ጭምር ነው።

በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለው ችግር /ስብራት ለማከም ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ መፍትሄ የሚፈልግ ነው። በትውልድ ግንባታ ውስጥ ሰፊ አስተዋጽኦ ያላቸውን ማኅበራዊ ተቋማትን ጠንካራ ድጋፍ የሚሻ ፤ የቤተሰብንም ንቁ ተሳትፎ ፤ የትውልዱንም የእውቀት መሻት መነቃቃት የሚጠይቅ ነው!

አዲስ ዘመን  ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You