የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተግዳሮቶች – እንደ መልካም አጋጣሚ

ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስና በምጣኔ ሀብት ልቃ ለመውጣት በምታከናውናቸው ተግባሮች ውስጥ ለመሰረተ ልማትና መሰል ግንባታዎች ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች:: ለዚህም በየአመቱ ከምትይዘው ሀገራዊ በጀት 60 በመቶውን ለካፒታል በጀት ትመድባለች:: የቀጣዩ ልማት ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆናቸው የታመነባቸው የትምህርት፣ የጤና ፣የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ፣ የቴሌኮም፣ የኢንቨስትመንት እና የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች በስፋት የሚገነባበት ሀገር ናት::

የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪም እነዚህን መሰረተ ልማቶች በመገንባት ሂደት ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል:: ዘርፉ በሀገሪቱ በመሰረተ ልማት ዘርፍ ለተመዘገቡ ለውጦች ተጠቃሹም ነው:: ከግብርና ቀጥሎ ለዜጎች ከፍተኛ መጠን ያለው የስራ እድል በመፍጠርም ይታወቃል፤ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 23 በመቶውን የሚሸፍነውም በዚህ ኢንዱስትሪ የሚገኝ ነው::

በአንጻሩ ኢንዱስትሪው በውስብስብ ችግሮች የተተበተበ ስለመሆኑ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሁሌም ይነሳል:: ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ መሆኑን ተከትሎ የስነምግባር ጉድለትና ሙስና የተንሰራፋበት ፤ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር በስፋት የሚስተዋልበት፣ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጓተቱ ያለበት፣ በግዥና በክፍያ መጓተት በእጅጉ የሚፈተን ወዘተ በመባልም ተለይቷል::

ችግሮቹን ለመፍታትም የዘርፉ ተዋንያንም መንግሥትም የየበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ:: በዘርፉ ተግዳሮቶችና መውጫዎቻቸው ላይ ጥናቶች እየቀረቡ ውይይት ሲደርግባቸው ቆይተዋል:: አንዳንድ የአሰራር ማሻሻዎች ተደርገዋል፤ ከእነዚህም መካከል አዲሱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲና የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በአብነት ይጠቀሳሉ:: ይህም ሆኖ ግን ከችግሩ ውስብስብነት አኳያ በቀጣይም ብዙ ጥረት ማድረግን እንደሚጠይቅ እየተገለጸ ነው::

በቅርቡም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተማና መሰረተ ልማት እንዲሁም የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢንዱስትሪው ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ጥናቶችን በዘርፉ ባለሙያዎች አሰርቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የኢንዱስትሪው ተዋንያን ተወካዮች በተገኙበት በማቅረብ እንዲመከርባቸው አድርጓል:: በመድረኩ አራት ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ከጥናቶቹ መካከልም በኢንጂነር ዳዊት ኡርጌቾ ‹‹ የስራ ተቋራጮች፣ የአማካሪዎችና ግብአት አቅራቢዎች ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ›› በሚል ርእስ የቀረበው ጽሁፍ አንዱ ነው::

ኢንጂነር ዳዊት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሀይድሮሎጂና ወተር ሪሶርስ ከቻይና ያገኙ ናቸው:: የኢትዮጵያ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ኤንድ አርክቴክስ አሶሴሽንን በፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆኑ፤ የኤልዳ ኢንጂነሪግ ኮንሰልታንት መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተርም ናቸው:: በሙያው ከ30 አመት በላይ ተሞክሮ አላቸው::

ኢንጂነር ዳዊት ‹‹ኢንዱስትሪያችን በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ስለመሆኑ እናውቃለን፤ ከዚህ አኳያ የኢንዱስትሪው ተሳታፊዎች አካፋና ዶማውን ይዘን ፣ ግንባር ላይ ሆነን የዘርፉ ምልከታችን ምን ይመስላል፤ ከዚያ ባሻገር ያለውንስ በምን መንገድ እንጠቁም›› የሚለውን በአጭሩ ለማሳየት ብለው ጥናታቸውን አቅርበዋል::

የኢንዱስትሪው አሁናዊ ሁኔታ በሚገባ እንደተጠቆመ ጠቅሰው፣ እኛ በደረስንበት ቦታ የተመለከትነውም ልብ ሰባሪ፣ አንገት አስደፊ ሁኔታ ነው፤ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት፤ ከዚህ ቅርቃር ለመውጣት ከስህተቶቻችን ከተማርን መፍትሄውን ራሳችን እንፈጥራለን ብለን እናስባለን:: ስለዚህ በኢንዱስትሪው ላይ ተስፋ እንጂ ጨለምተኝነት የለንም ሲሉ አስገንዝበዋል::

ቻይናዎች ቀውስን በሁለት ከፍለው ይገልጹታል ያሉት ኢንጂነሩ፣ አንደኛውን ከአደጋ፣ ሁለተኛውን ደግሞ ከመልካም እድል አኳያ ብለው እንደሚመለከቱት ይገልጻሉ:: ቀውስ መልካም አጋጣሚ ፈጣሪ መሆኑን እንደሚረዱ ነው ያመለከቱት:: ቻይናውያን እኛ አሁን ካለንበት አስከፊ ሁኔታ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ኖረው ያውቃሉ:: ከዚያ ወጥተው ነው አሁን ለደረሱበት ደረጃ የበቁት ብለዋል::

እኛም ከስህተቶቻችን ከተማርን ከዚያ ደረጃ የማንደርስበት ሁኔታ አይኖርም ብለን እናምናለን ያሉት ኢንጂነሩ፣ እኛ ማነን ለሚለው የስራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ የግንባታ ግብአት አቅራቢዎች እና በስሮቻችን የሚተዳደሩ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ:: ከውጪም ባለቤቶች፣ አሰሪዎችና ተቆጣጣሪ አካላት አሉ ሲሉ አመልክተዋል::

ኢንጂነሩ ‹‹ሁሉም ሰው ይህን ኢንዱስትሪ የሚረዳው በጊዜ አላለቀም፤ ከተያዘለት በጀት በላይ ሆኗል፤ ጥራቱ አሁንም እየወደቀ ነው ከሚሉት አኳያ ነው፤ እነዚህ ሶስቱ የፕሮጀክት ማኔጅመነት አካላት ናቸው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የችግሩ መገለጫዎች ናቸው እንጂ የችግሩ ጠቋሚዎች ሆነው መታየት አለባቸው እንጂ የችግሩ ምንጮች አይደሉም፤ ለእነዚህ ችግሮች ቶሎ ደራሽ መፍትሄ እንፈጥራለን ብለን ማሰብ የለብንም:: መሰረታዊውን ችግር ፈልገን ተንትነን ልንደርስበት ይገባል ብለዋል::

በተደጋጋሚ እንደተጠቆመው፤ ዘርፉ ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው፤ የግዥ ስርአቱ ሊዘምንና ጊዜውን የዋጀ ሊሆን ይገባል:: ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቀው የሰው ሀይል ከ120 ሺ እስከ 150 ሺ ቢደርስም ብዙ ጊዜ የሙያ ክህሎት ክፍተት አለበት እንላለን:: ግን ደግሞ በኢንተርነሽፕ ጊዜ ፕሮግራሞችን አዘጋጅተን ምቹ ሁኔታ ፈጥረንለታል ወይ የሚለውንም በጋራ ማየት ይኖርብናል ሲሉ ያብራራሉ:: የዘርፉ ባለሙያዎችም ራስ መር በሆነ መንገድ እንዲመሩ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ይህንንም ከኬንያ እና ከሩዋንዳ ልንማር የምንችል ይመስለኛል ሲሉም ጠቁመዋል::

የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮቶች ከሆኑት መካከል የፕሮጀክቶች ደካማ አፈጻጸም የሚለው አንዱ መስተካከል ያለበት መሆኑን ሲሆን ፣ ሁለተኛው የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት መጨመር፣ ሶስተኛው የባለሙያ ብቃት ጉዳይ፣ አራተኛው ከውጭ የሚገቡ የግንባታ እቃዎች ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ መሆናቸውን ጠቁመዋል::

የዘርፉ ቀጥተኛ ባለድርሻዎች የምንባለው እኛ ኢንዱስትሪውን እንዴት ነው የምናየው? ትርፍ ማጋበሻ ሀርገን ወይስ ሀገር ማልሚያ? ሲሉም ጠይቀው፣ ይህን ግልጽ ማድረግ አለብን፤ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚመድበው በጀት የሀገር ሀብት መፍጠሪያ መሆኑን እንረዳለን፤ ስለዚህ ይህ ዘርፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት እንደሚገባ እናውቃለን ሲሉ ይገልጻሉ:: የጤና ተቋማትና የመሳሰሉት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በማለፍ ነው ህይወት የሚዘራባቸው:: ይህ ህይወት የተዘራበት ሀብት መልሶ ገቢ እንዲያመነጭ የሚደረግበት ነው:: ስለዚህ እይታችን ከዚያ የመነጨ ይሆናል ብለዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኢንዱስትሪው የስራ እድል በመፍጠርና ኢኮኖሚውን በማንቀሳቀስ ከፍተኛ ስፍራ እንዳለው ይታወቃል፤ የስራ ተቋራጮች ዝቅተኛ በሆነ የፕሮጀክት አስተዳደር ብስለት ደረጃ ላይ ይገኛሉ:: ከገንዘብና ተቋማዊ አቅም ውስንነት አኳያም እንዲሁ የተገደበ ኢንዱስትሪ ነው፤ ብዙ ጊዜ በክፍያ መዘግየት ክፍተቶች ሲፈጠሩ ድልድይ የሆነ የፋይናንስ አማራጭ ባለመኖሩ በቀላሉ ለአደጋና ለጉዳት ተጋላጭ ነው:: የስነ ምግባር ጉድለት በሁሉም የኢንዱስትሪው ተዋንያን ላይ ያለና ሊቀረፍ የሚገባው ነው::

ለሀገር በቀል ድርጅቶች ተወዳዳሪነትን የሚያጎለበት በቂ ጥበቃና ድጋፍ አለመኖር ይስተዋላል የሚል እይታም አለ፤ ይህ በምን ይገለጻል ከተባለም በሌሎች ሀገሮች ስራ ሲወጣ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች በተቋራጭ መረጣ መስፈርት /ኢቫልዌሽን ክራይቴሪያ/ ሰባት ወይም አስር በመቶ የማሸነፍ እድል እንዲኖራቸው ይደረጋል:: ይህ ግን በኢትዮጵያ የለም፤ ለውጭ ተቋራጮች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሲደረግ ለሀገር ውስጥ ተቋራጮች አይደረግም:: ለግብአት አቅርቦት የሚያስፈልጋቸውን 30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ አግኝተው መስራት ሲገባቸው የሚያገኙበት ሁኔታ የለም፤ ይህም ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያግዳቸዋል::

የሰው ሀይሉ ምርታማነት እንዲሁም የክህሎት ደረጃ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘትም ሌላው ችግር ነው:: ከአማካሪ ውስጣዊ እይታም አኳያ ዝቅተኛ የፕሮጀክት አስተዳደር ብስለት ሁሉም ዘንድ ያለ ችግር ነው:: ከእቃ አቅራቢዎች ውስጣዊ እይታ አኳያም እንዲሁ የዘርፉ ዋና ዋና ተዋናዮች እንደ ባለቤት አለመታየትና መገፋት ነገር ይታያል የሚባል ቅሬታም ይሰማል::

የአቅርቦት ሰንሰለቱ ዘላቂ እንዲሆን በሚል ለሚዘጋጅ እቅድ ዳታ ሲፈልግ በተገኘ መረጃ መሰረትም ስራዎች ከወጡና ውለታ ከተገባባቸው በበኋላ እንጂ በጨረታ እና በሀሳብ ደረጃ እያሉ እነዚህን አካላት የማቅረብ ሁኔታ አይታይም፤ በዚህ በኩል ትልቅ እንቅፋት እየተፈጠረ ነው የሚል ቅሬታ ይነሳል::

ላለፉት ጥቂት ዓመታት በኛ በኩል የዘርፉን ተዋናዮች ቀርቦ በማነጋገርና በማወያየት አዋጆች ፖሊሲዎችና የመሳሰሉት ሲወጡ በረቂቅ ሰነድ ደረጃ ንቁ ተሳትፎ እንድናደርግና አብረን እንድንሠራ እየተደረገ ያለውን ጥረት ሳናደንቅ አናልፍም ሲሉም ኢንጂነር ዳዊት ጠቅሰዋል::

የፋይናንስ ተቋማት አለመኖራቸው፤ ለኮንስትራክሽን እቃዎች አንድ ወጥ የሆነ ሀገር አቀፍ ስታንዳርድ አለመኖሩ፣ አንዳንዴም ጥራትን ያላሟሉ እቃዎች በግንባታ ስራ ውስጥ ሲካተቱ የሚስተዋልበት ሁኔታም ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የዋና ዋና የዘርፉ ተዋንያን ውጫዊ ምልከታ ከተቆጣጣሪና አስፈጻሚዎቹ አኳያ ሲታይ ተቋማዊ ውስንነት ይስተዋላል:: በግዥ ፣በሙያ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ወጥነት ያለውና በምርጥ ተሞክሮ ላይ የተመሰረተ ደንብና አሰራር አለመከተል፣ ምርጥ ተሞክሮን ለመቀበልና ጊዜውን የዋጀ አሰራርን ለመቀበል ዳተኛ መሆን፣ ዘርፉ የሚመራባቸው ወጥ የህግ ማእቀፎች፣ ስልቶች፣ መመሪያዎች፣ የአሰራር ደንቦችና ሂደቶች አለመኖር፣ የቁጥጥር ስራዎችን ለመተግበር ያለ የአቅም ውስንነት ይታያሉ::

አሰሪና ባለቤቶችን በሚመለከት የፕሮጀክት ማስተዳደር ደረጃ፣ የስነ ምግባር ጉድለቱም በሁሉም ዘንድ እንደሚስተዋል፣ ደካማ የፋይናንስ አቅምና የክፍያ መዘግየት ፣ ጣልቃ ገብነት እንደሚታይም ጠቁመዋል:: በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በኩል ወሰን የማስከበር ስራው ከአቅም በላይ ሆኖ እንደሚታይም ጠቅሰው፣ በመንገድ በኩል አንዳንዴም ከግንባታ ክፍያው በላይ የወሰን ማስከበር ከፍያው ከፍተኛ እየሆነ ያለበት ሁኔታም ወጪውን እየተፈታተነው ያለበት ሁኔታ በትኩረት ሊታይ ይገባዋል ሲሉ አስገንዝበዋል::

ወደ ስኬት ለመሄድስ ምን ማድረግ ይገባል ሲሉም ጠይቀው፣ ችግር ላይ ቆም ከመቆዘም ይልቅ ከችግራችን በመማር ወደፊት ለመሻገር መስራት ያዋጣናል ሲሉም ነው ያስታወቁት::

አሁን ያለው ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸም እንዴት ሊቀረፍ ይችላል? ሲሉም ጠይቀው፣ ይህ ችግር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ ለሌሎች ወገኖች አሳልፈን የምንሰጠውም አይደለም:: በጋራ በመሆን በአስቸኳይ መፍትሄ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል:: ሁለተኛ የኢንዱስትውን ተወዳዳሪነት በሀገር ውስጥና በቀጣናው የማሳደግ ጉዳይ መሆኑን አመልክተው፣ ይሄ በአዲሱ የዘርፉ ፖሊሲ ላይ መቀመጡን ተናግረዋል:: እንዴት እናሳካዋለን የሚለው በተወሰነ ደረጃ ሲታይም ሙያዊ ብቃትን ማሳደግ ይገባል የሚለው አንዱ መፍትሄ መሆኑን አመላክተዋል::

የትኛውንም አፈጻጸም ሂደት ለመተግበር የመጀመሪያው ስራ መሆን ያለበት የችግሩን ምንጭ መረዳት እንጂ ጊዜ ደራሽ መፍትሄ ይዞ ጣልቃ መግባት አይደለም ሲሉም አስገንዝበው፤ ከዚህ አይነቱ አሰራር ተቆጥበን ስራችንን መስራት ይኖርብናል ሲሉም መክረዋል::

የግዥ ሂደቱን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ሂደቱ አንዳንዴ ስራውን ከምንከውንበት የበለጠ ጊዜ ሲወስድ እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ይህም ሊፈተሸ የሚገባው የጊዜ ሂደት አለ ማለት ነው ብለዋል:: አፈጻጸም የባለድርሻ አካላት ድምር ውጤት ነው ያሉት ኢንጂነር ዳዊት፤ አፈጻጸማችን ቢወድቅ ሊመጣ የሚችለውን መረዳት ያስፈልገናል፤ ስለዚህ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ብስለት ደረጃችንን ለማሻሻል በትኩረት ልንሰራ ይገባል:: ይህን በሚመለከት የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በጀመረው ስራ ላይ በጋራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል::

የችግሮች መፍቻው መንገድ በእኔ እይታ እስከ አሁን ያለን አቀራረብ ሁለንተናዊና በስርአት የሚመራ / ሲስተሚክ / አካሄድን የተከተለ አይደለም ሲሉም ጠቅሰው፣ ብዙ ጊዜ ከባህል ጋር ተያይዞ ይሁን ከአስተዳደግ የጦሱን ዶሮ ፍለጋ ላይ ነው የምናተኩረው ሲሉ ያስገነዝባሉ:: ማነው ጥፋተኛው እንላለን እንጂ ከዚህ ጥፋት ምን እንማራለን ብለን አንሰራም፤ ከዚህ አካሄድ ካልወጣን መፍትሄ አናገኝም ብለዋል::

በአቬዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ አንድ የተለመደ ነገር አለ ያሉት ኢንጂነሩ፣ እያንዳንዱ የአውሮፕላን አደጋ የሚቀጥለውን የአውሮፕላን ጉዞ ጤናማ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታይ አስታውቀው፣ ከችግር የመማርን አስፈላጊነት አመልክተዋል::

ስኬትም ክሸፈትም ያለባቸው ብዙ ፕሮጀክቶችን ሰርተናል፤ ላለፉት ሰላሳ አመታት የዳበረ እውቀት አግኝተናል:: እነዚህን ፕሮጀክቶች በሚገባ አጥንተን ወደ መፍትሄ ፍለጋ ከሄድን መፍትሄው እጃችን ውስጥ ነው፤ ከስኬታችን ከክሽፈታችን መማር ለችግሮቻችን ዋናው መፍትሄ ነው፤ ስለዚህ በችግሮች ስረ መሰረት ላይ ትንታኔ መስራት ይኖርብናል ብለዋል::

የግንባታ ግብአቶችን በሚመለከት በፖሊሲው የገቢ ምርት መተካት በግልጽ ተቀምጧል:: ይህንንም ‹‹የቲንክታንክ ቡድኑ›› የሚያየው ጉዳይ ይሆናል ሲሉም ጠቅሰዋል:: ኢንጂነሩ ሲዛር ፔሊ የሚባለው የማሌዢያው ፕትሮናስ ህንጻ አርክቴክት ‹‹ኮንስትራክሽን በጨለምተኝነት የመቆዘም ሳይሆን የብሩህ ተስፋ ጉዳይ ነው፤ የወደፊቱን በልበ ሙሉነት የመጋፈጥ ጉዳይ ነው›› ሲል የገለጸውን ጠቅሰው፣ ዘርፉ በችግሮች የተተበተበ ቢሆንም ተስፋም አብሮት እንዳለና የችግሮችን ስር መሰረት በመለየት ለመፍታት መረባረብ እንደሚገባም አስገነዝበዋል::

ከመድረኩ በባለሙያዎችና ተሳታፊዎች ከተሰጡት አስተያዮች መካከልም ኢንጂነሩ ሀሳብ አጠናክረዋል:: ዋናው ነገር የችግሮች መንስኤ መፈለግ ስራ ላይ የቆየነው አሰራር /ሜቶዶሎጂ/ ላይ ጥናትና ምርምር መታከል እንዳለበት ተጠቁሟል:: እስካሁኑ ዘዴ በአስተዳደራዊ መንገድ፣ በማማከር ፣ በልምድ ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ መንገድ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ጠቅሰው፣ ይህ መንገድ የሚፈለገውን ያህል ችግር እንዳልፈታ ተጠቁሟል::በዚህ አሰራር /ሜቶዶሎጂ/ ላይ ምርምርና ጥናት ማማከል እንደሚገባም ተመልክቷል::

ኃይሉ ሣህለድንግል

 አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You