ባለፉት አምስት ዓመታት እንደሀገር ውጤታማ ከሆንባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ነው። በዘርፉ ያስመዘገብናቸው ስኬቶች ሀገርን ከፍ ካለ ስጋት መታደግ የሚያስችል አቅም የፈጠሩ፤ ለጀመርነው ልማት ውጤታማነት ስትራቴጂክ ጉልበት የሆኑ ናቸው።
በገለልተኝነት የሀገር እና የሕ ዝብ ጥ ቅሞችን መሠ ረት ያደረ ገው የሀገሪ ቱ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ፣ ም ሥራቅ እና ምዕራብን ፣ ሰሜን እና ደቡብን ሳይለይ ፣ በሰላም እና በወንድማማችነት ፣ በመከባበር እና በወዳጅነት ፣ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ፣ ብሔራዊ ክብር እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ ነው ።
በፉክክር እና በትብብር መካከል ሚዛን በመጠበቅ፣ ተቃርኖዎችን በማስታረቅ የሚጓዘው ብሔራዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ ክብርን ያስቀደመ፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ ጎረቤት ሀገራትን ያስቀደመ የውጭ ግንኙነት፣ ቀጣናዊ ትብብርና የኢኮኖሚ ውህደት ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ነው።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖር ግንኙነት በመነጋገርና በመተባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን፤ የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ እጣ ፈንታ የተሳሰረ በመሆኑና የጋራ ጥቅማችን መሠረት ያደረገ መተጋገዝና ትብብር መመስረት እንደሚገባ፤ብሔራዊ ጥቅም በአንድ ወገን ሊበየን የማይችል እና ወጥና የማይለወጥ እንዳልሆነ ከግንዛቤ በማስገባት የሀገሪቷን እሴቶች ተከትሎ በትብብርና በንግግር ጥቅምን ማስከበር እንደሚገባ ያምናል።
ይህን የውጪ ዲፕሎማሲያዊ ህሳቤ መሠረት ያደረገው የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ፤ሀገሪቱ ከውጪ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶቿ ስትራቴጂክ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ተጨባጭ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም ሀገሪቱ ከዘርፉ በሁለንተናዊ መልኩ የተሻለ ተጠቃሚ የሆነችበትን እድል ፈጥሯል።
በለውጡ ማግስት የተጀመረው በቀጣናው ሰላም እና እርቅን ታሳቢ ያደረገው የመንግሥት የዲፕሎማሲ ጥረት በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችልበትን የተሻለ አማራጭ መፍጠር የቻለ እንደነበር፤ ጥረቱ ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማት ባለቤት ሆነው የተመረጡበትን አጋጣሚ መፍጠሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
የለውጡ አመራር ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ በተለያዩ የአረብ ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን ከነበሩበት ፈታኝ ሁኔታ በማላቀቅ ወደ ውድ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። ይህም የዜጎች ክብር የብሔራዊ ክብራችን ዓይነተኛ መገለጫ እንደሆነ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
ከዚህም ባለፈ በለውጡ ማግስት ሀገሪቱ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው ዘርፍ ያጋጠማትን ፈተና ለመሻገርም ሆነ ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አቅም በማጎልበት የተከናወኑ ተግባራት፤ በሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው።
በተለይም ለውጡን ለመቀልበስና ኢትዮጵያን የሚለውጡ ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ከውስጥም ከውጪም የተቀናጀ ሴራ በስፋት በሚጠነጠንበት ወቅት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ ጫናዎችን በመቋቋም ሀገርን በመታደግ ሂደት ውስጥ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተገኘው ስኬት የነበረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ። በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ እልህ አስጨራሽ ፈተናዎችን መሻገር ያስቻለ ፣ ሀገርን እና ሕዝብን ከአደጋ ከመታደግ ባለፈ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት መፍጠር ያስቻሉ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተከናውነዋል።
የዓባይ ግድብን ጨምሮ የሕዝባችንን የመልማት ፍትሐዊ ጥያቄዎች ላይ የተነሱ ያልተገቡ ጫናዎችን ተቋቁሞ፤ የግድቡን ግንባታም ሆነ የሕዝባችንን የመልማት ጥያቄ ፍትሐዊነት ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በማስረዳት የተሻለ ተሰሚነት ለማግኘት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ዘርፉ ያበረከተው አስተዋጽኦ መተኪያ የሌለው ነው።
ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ የአጋርነት እድሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የብሪክስ አባል ሀገራት ኅብረት አባል እንድትሆን በማስቻል ፣ ከኅብረቱ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት እና የተገኘው ውጤትም ዲፕሎማሲያችን የቱን ያህል ውጤታማ እንደነበር ያመላከተ ነው።
ከዚህም ባለፈ በነዚህ አምስት ዓመታት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በማኅበራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጠንካራ ትብብር በመፍጠር፤ እንደ ሀገር የጀመርነውን ልማት ትርጉም ያለው ተጨባጭ ፍሬ እንዲያፈራ አስችሏል፤ በቀጣይም የመልማት ተስፋችንን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ከፍ ያለ ስትራቴጂክ አቅም እንደሆነም ማየት ተችሏል ።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ ኮሪያ እና በሲንጋፖር ያደረጉት ጉብኝት እና ጉብኝታቸውን ተከትሎ ከሀገራቱ ጋር የተደረሰበት ስምምነት የዚህ ውጤታማ የሆነው የሀገራችን የውጪ ዲፕሎማሲ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ስኬቱ የኢኮኖሚ አጋርነትን በማስፋት ሀገራዊ የልማት ግቦቻችንን ተጨባጭ ለማድረግ ትልቅ አቅም የሚሆንም ነው።
ፍላጎቶች በበዙበት ባለንበት ዓለም አቀፍ ይሁንታ፤ መንግሥት የሀገር እና የሕዝብ ጥቅምን ታሳቢ ባደረገ መንገድ እየተጓዘበት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድ፤በቀጣይ እንደሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ታሪካዊ ጉዞ የልማት አጋሮችን ለማስፋት ከዚህም ጎን ለጎን ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች የነበራትን ተደማጭነት ማሳደግ የሚያስችል ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም