የኢትዮጵያን የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ለማሻሻል ዕቅድ ተይዟል

አዲስ አበባ፦ የሀገሪቱን የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ለማሻሻል እና አዲስ “የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ፍኖተ ካርታ” ለማዘጋጀት ማቀዱን ፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን (ዶ/ር)የ2024 የዓለም ሕዝብ ሪፖርት በኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ ይፋ ሲሆን በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሀገሪቱን የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ለማሻሻል እና አዲስ “የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ፍኖተ ካርታ” ለማዘጋጀት አቅዷል። ይህንንም እውን ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችውን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚመጥን ፖሊሲ እና ተቋማዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አምኗል ያሉት ስዩም መኮንን (ዶ/ር)፤ ሚኒስቴሩ የሕዝብ ቁጥርን እንደ ልማት ማዕከል በመቁጠር ለሕዝብ እና ለልማት ጉዳዮች በቂ ትኩረት ሰጥቷል። ይህም የአስር ዓመት የልማት እቅድ አካል ነው ብለዋል።

መንግሥት የሀገሪቱን የሥነ-ሕዝብ ለውጥ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ልማት አንቀሳቃሽ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ያሉት ስዩም መኮንን (ዶ/ር)፤ ይህም ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት የምታደርገውን የሥነ- ሕዝብ ሽግግር በአግባቡ እንድትጠቀም ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሥነ ሕዝብ ፖሊሲን ለማሻሻል እና የሥነ-ሕዝብ አወቃቀር ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት የዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ስዩም መኮንን (ዶ/ር)፤ አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር እና ልማትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የሕዝብ ቁጥር ዕድገትም ሴቶችና ወጣቶችን ለማብቃት ከሚደረገው ጥረት ጋር የሚመጣጠን አይደለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማጎልበትና ሴቶችን ለማብቃት በፖሊሲና በፕሮግራም ጣልቃገብነት ተጨባጭ ዕርምጃዎችን በመውሰዷ የሴቶችን መብት በማስከበር ረገድ ተጨባጭ መሻሻሎች መገኘቱንና ሙሉ አቅማቸው ላይ እንዲደርሱ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ይህም በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ በፆታ ላይ የተመሠረተ የጥቃት መጠን በመቀነስ፣ የሴቶችን መብት ሲጥሱ የቆዩ ጎጂ ድርጊቶችን በማስቀረት እንዲሁም ሴቶች እና ልጃገረዶች አቅማቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲሟሉ በማድረግ የመጣ ውጤት ነው ያሉት ሙና አህመድ፤ እነዚህ ተስፋ ሰጪ እመርታዎችን እኤአ ከ2024 የዓለም ሕዝብ ጋር በማዋሃድ ስልታዊ እቅድ ለማውጣት እንደሚሞከር ገልጸዋል።

በመድረኩ የዘረኝነት፣ የፆታ ስሜት እና ሌሎች የመድልዎ ዓይነቶች የሚያሳድሩት ተጽዕኖዎች፣ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተገናኘ በተለይም በግጭት ቀጣናዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ሞትን መቀነስ የሚቻልባቸው መንገዶች፣ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ተነስቷል።

በመድረኩ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ሥነ ሕዝብ ፈንድ ኃላፊዎች እና ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

Recommended For You