ስለ ሰላም የሚደረግ የትኛውም ንግግር ሀገርን ለማሻገር የሚያስችል መነቃቃት ነው !!

እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችል የትኛውም አይነት የሰላም ንግግርና ውይይት እውቅና ሊሰጠው የሚገባ እና የሚበረታታ ነው። ለረጅም ዘመናት ብዙ ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን ከመጣንበት የግጭት አዙሪት ለመውጣትም አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ። የጀመርነውን ሀገራዊ ልማት በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ወሳኝ አቅምም ነው።

በርግጥ ብዝሃነት መለያዋ በሆነው፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሰፊ የግጭት ማስወገጃ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ የዳበሩ እሴቶች ባለቤት በሆኑበት ሁኔታ፤ በግጭት አዙሪት ውስጥ ሆነን ያልተገቡ ብዙ ዋጋዎች የመክፈላችን እውነታ በብዙ መንገድ ተጠየቃዊ አይደለም።

አብዛኛው ሕዝባችን ሀይማኖተኛ በሆነበት፣ በሀይማኖት አስተምህሮዎች ወስጥ ሰላም ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶት በሚሰበክበት ሀገር ፣ ትውልዱ በሰላም እጦት ያለመውን መሆን ሳይችል ቀርቶ እስከ ተስፋቸው የሚያልፍበት እውነታ መኖሩ ለአዕምሮ የሚከብድ ነው።

የብዙ መቶ ሺ ዓመታት ሀገረ- መንግስት ታሪክ ባለቤት የሆነ ሕዝብ፤ በየዘመኑ በሚፈጠሩ የሰላም እጦቶች፤ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረው የሀገረ መንግስት ትርክቶቹ የግጭት እና የጦርነት መሆናቸው፤ ዛሬም ከትናንት መማር አቅቶት በተመሳሳይ የግጭት እና የጦርነት የታሪክ ምእራፍ ውስጥ መገኘቱ የታሪክ ሂደትን እና አስተምህሮን የሚመጥን አይደለም።

በተለይም የብዙ ታሪኮች ባለቤት የሆነ ሕዝብ፤ ከትናንት ታሪኮቹ ቆም ብሎ መማር አቅቶት፤ በትናንቶች ውስጥ ሲዳክር ፤ በዚህም ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ሲገደድ ከማየት የከፋ ነገር አይኖርም፤ የክብደቱን ያህል ችግሩን ቆም ብሎ ለማየት አለመሞከርም ለችግሩ የበለጠ አቅም ከመስጠት ያለፈ ፋይዳ የለውም።

እኛ ኢትዮጵያውያን ስለሰላም ዕለት ተዕለት የመሰበካችንን ያህል፤ ሰላማችንን ጠብቀን በማስቀጠል ሂደት ወስጥ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለን ሕዝቦች ነን። ከሰላም ጋር በተያያዘ የከፈልነውም ሆነ እየከፈልን ያለነው ያልተገባን ዋጋ ያህል ስለሰላማችን ዘብ መቆም የሚያስችል ማኅበረሰባዊ መነቃቃት ውስጥ አይደለንም።

እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብና ሀገር ሰላምን ለትውልዶች ከመስበክ ጀምሮ፤ ለሰላም ዋጋ ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ የሆነ ትውልድ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ያለብን ክፍተት በየዘመኑ ስለሰላም ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል። በዚህም እንደ ሀገር የብዙ ስብራቶች ቁስለኝ አድርጎናል።

አደባባዮቻችን ስለሰላም በብዙ እየተዘመረባቸው፤ የዝማሬያችንን ያህል ሀገራዊ ሰላም መፍጠር ሳንችል ቀርተን በግጭቶች እና በጦርነቶች ምክንያት የድህነት እና የኋላ ቀርነት ማሳያ ሆነናል። ከትልቅ የስልጣኔ ማማ ወርደን ጠባቂነትን መሻገር ያልቻለ ሀገራዊ ገጽታ ተላብሰናል።

በ21ኛው ክፍለዘመን ላይ ቆመን በፉከራና በቀረርቶ የገዛ ሰላማችንን እየተገዳደርን ፤ በእኔነት እና በማን አለብኝነት የትውልዶችን ራስ የመሆን መሻት እየተፈታተንን፤ ዘመንን በማይዋጅ የአስተሳሰብ ልምሻ መራመድ አቅቶን በእንፉቅቅ ለመሄድ የተገደድንበት የታሪክ ምእራፍ ውስጥ ተገኝተናል።

ከዚህ የትናንት ጥላ ከሸፈነው የዛሬ ሕይወታችን ለመውጣት፤ በየትኛውም አጋጣሚ ስለ ሰላም ከልባችን ልናስብ ፤ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ በየዘመኑ ትውልዶች የከፈሉትን ያልተገባ ዋጋ ቆም ብለን ልናጤን ይገባል። በቀጣይም እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም መፍጠር የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ካልቻልን ልንከፍል የምን ችለውንም የከፋ ዋጋ መገመት ተገቢ ነው።

ከዚህ ተጨባጭ ከሆነው ከትናንት እየተሻገረ የትውልዶችን ዛሬ እና ነገዎች እያበላሸ ያለውን ሀገራዊ የሰላም እጦት ለዘለቄታው ለማስቆም የሚያስችል የትኛውም ዓይነት የሰላም ንግግር ሀገርን ከዘመናት ርግማን የመታደግ ያህል የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ፤ ሀገርን እንደ ሀገር ለማሻገር የሚያስችል መነቃቃት ነው!

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You