አዲስ አበባን ለነዋሪዎቹዋ የተመቸች ፣ ለዘመናዊ አኗኗር የተሻለች ፣ ለኢትዮጵያ ከዚያም ባለፈ ለአፍሪካ የኩራት ምንጭ የምትሆንበትን እድል ለመፍጠር የተጀመረው ከተማዋን የማደስ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን እየተሠራ ይገኛል። በእያንዳንዷ ቀን የሚታየው ለውጥም በርግጥም አዲስ አበባ ሥሟን በሚመጥን ደረጃ እየታደሰች ፣ እየተዋበች ስለመሆኑ በተጨባጭ አመላካች ነው።
ከተቆረቆረች ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው አዲስ አበባ፤ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ ባጋጠሟት የተለያዩ ፈተናዎች የዕድሜዋን ያህል ልታድግ ፣ለነዋሪዎችዋ ፍላጎት የተመቸች ልትሆን አልቻለችም ። የሀገሪቱ ርዕሰ ከተማ፤ የአፍሪካውያን መዲና ከመሆኗ አኳያም የነበረችበት የከተሜነት ደረጃ የሚመጥናት ሳይሆን ብዙ ዓመታትን አስቆጥራለች።
ከተማዋ ልታመነጭ የምትችለውን ሀብት በአግባቡ መሰብሰብ እና ለከተማዋ ልማት ማዋል አለመቻል፣ለከተማዋ እድገት ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራት ፣ የአመራር እና የአመራር ቁርጠኝነት ክፍተት … ወዘተ ለከተማዋ አሁናዊ ኋላ ቀር ገጽታ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በከተማዋ ዘመናዊ ሕይወትን ለመምራት የሚያስችሉ የተሟሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አለመኖር ፣ በነዋሪዎቿ ላይ ዘመናዊ የከተሜነት ስነልቦና መፍጠር አለመቻል ፣ ዘመኑን የሚዋጅ የከተማ አስተዳደር አለመገንባት ከሁሉም በላይ ከተማዋን በባለቤትነት መንፈስ የሚመራ የፖለቲካ አመራር ክፍተት ከተማዋ የዕድሜዋን ያህል እንዳታድግ አድርጓት ቆይቷል ።
በየወቅቱ የሚደረጉ የከተማዋን የማልማት ሥራዎችም ቢሆኑ መጪ ጊዜያትን ታሳቢ ያደረጉ ፣ ከተማዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ የዲፕሎማሲ ከተማዎች አንዷ መሆኗን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ፤እንዲሁም የከተማዋን እና የነዋሪዎቿን ፍላጎቶች ታሳቢ ያደረጉ አለመሆናቸው ፣ ለከተማዋ አሁናዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጠቃሽ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።
በከተማ በዝቅተኛ ደረጃ የሚሰበሰበው ሀብትም ቢሆን አግባብ ባለው መንገድ ለልማት የሚውልበት ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት አለመኖሩ ፣ የከተማዋ ሀብት በአንድም ይሁን በሌላ ለተበላሸ አሠራር እና ለብክነት የተዳረገ መሆኑ ለከተማዋ ዕድገት ማነቆ ሆነው ቆይተዋል።
እነዚህን የተጠራቀሙ የከተማዋን ችግሮች በመፍታት፤ከተማዋ በአዲስ የለውጥ እና የልማት ጎዳና ውስጥ መጓዝ እንድትጀምር የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምር ግዙፍ የቤት ሥራዎችን ወስዶ እየሠራ ይገኛል። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጪ እየሆነ ነው።
በአንድ በኩል ከተማዋ ልታመነጭ የምትችለውን ሀብት በአግባቡ ለመሰብሰብ ሰፊ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፤ ለዚህም የከተማዋን ገቢ የማመንጨት አቅም የሚያጎለብቱ በዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የተደገፉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በዚህም የከተማዋ ገቢ በየዓመቱ ከፍ ባለ ደረጃ እያደገ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከከተማ የሚሰበሰበውን ሀብት ለከተማዋ ዕድገት ለማዋል የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በከተማዋ አስተዳደር እና በፌዴራል መንግሥት በኩል በቅንጅት እየተካሄዱ ነው። ከነዚህም አሁን ላይ በዋነኛነት የሚጠቀሰው ከተማዋን የማደስ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው ።
ከተጀመረ ጥቂት ወራት ያስቆጠረው ይህ ፕሮጀክት ከተጀመረ ማግስት ጀምሮ ከፍተኛ በሆነ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ውስጥ ቢያልፍም “እውነት እና ጉም እያደር ይጠራል” እንደሚባለው፤አሁን ላይ የብዙ ውሽታሞችን አፍ ያዘጋ ፣ ብዙዎችን በአግራሞት እጃቸውን በአፋቸው ያስጫነ ፣ የሚታይ እና የሚጨበጥ ፍሬ እያፈራ ይገኛል። በአጠቃላይ የብዙዎችንም ቀልብ ስቦ ትልቅ ሀገራዊ የልማት አጀንዳ ሆኗል።
ፕሮጀክቱ እየተመራበት ያለው መንገድ ፤በርግጥም ሀገሪቱ ለልማት ቁርጠኛ አመራር ካገኘች፤በለውጡ ዋዜማ እንደ ሀገር ተስፋ ያደረግነው በልማት የመበልጸግ ተስፋችን ከተስፋ በላይ ሊጨበጥ የሚችል እውነት ስለመሆኑ አመላካች ነው። ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመርነው ትግልም በብዙ መልኩ ተስፋ ሰጪ እንደሆነም ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ከተማዋን በማደስም ሆነ በኮሪደር ልማቱ ፕሮጀክቱ ዜጎች ተጎጂ እንዳይሆኑ በመንግሥት በኩል የተወሰደው ጥንቃቄ ፤ልማቱን በራሱ በጠንካራ የሥራ ዲሲፕሊን ለመምራት በከፍተኛ አመራሩ በኩል የታየው ቁርጠኝነት ፣ የከተማዋ ነዋሪም በፕሮጀክቱ ዙሪያ በስፋት ለተካሄደው የጥፋት ፕሮፓጋንንዳ ጆሮውን ሳይሰጥ ለፕሮጀክቱ ስኬት እያሳየ ያለው ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው ።
ፕሮጀክቱ ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ለዘመናት የቆየውን ደካማ የሥራ ባህል በመቀየር ፤አዲስ ዘመኑን የሚዋጅ የሥራ ባህል በመፍጠር ሂደት ውስጥ ትልቅ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በፕሮጀክቱ የሚሳተፉ ዜጎችም ፕሮጀክቱ በጥራት እና በፍጥነት ተጠናቆ ለማየት ያላቸው ጉጉት፣ ከዚህ ጉጉታቸው የሚመነጨው የሥራ ተነሳሽነታቸው እንደ ሀገር የአዲስ የሥራ ባህል ጅማሬ ተደርጎ የሚወሰድም ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም