የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዋናነት ሰው ወዶ እና ፈቅዶ የራሱን ገንዘብ፣ ጊዜ እና ጉልበት ለሌላ ሕይወት ላለው አካል መስጠት ማለት መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ መምህር ዶክተር ታዬ ንጉሴ በበኩላቸው፤ አንድ ሰው ያለውን ዕውቀት፣ ክህሎት እና ማንኛውም ሃብት ለሌሎች ማለትም ለሰው ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሕይወት ላላቸው እንስሳትም ሆነ ዕፅዋት ደህንነት እንዲጠበቅ የራሱን ድርሻ መወጣት መቻል ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ::
በጎ ፈቃደኝነት አንፃራዊ ቃል ነው:: ለቤተሰብ የሚሰጥ አገልግሎት ጥሩ ቢሆንም፤ እውነተኛ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከአንድ ሰው ጠባብ ክበብ ውጪ ማገልገልን የያዘ ነው:: ከራሳቸው ከባቢ ወጥተው የሚያገለግሉ ሰዎች አስተሳሰባቸው አድጓል ማለት ይቻላል:: የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ከራስ ጋር በዘር፣ በዝምድና ወይም በሃይማኖት የሚገናኙትን ለይቶ ማገዝ ሳይሆን፤ ማንኛውንም ሕይወት ያለውን ሰው ማገልገል በጎ ፈቃደኝነት ነው::
እንደ ዶ/ር ታዬ ገለፃ፤ በጎ ፈቃደኝነት ከላይ ወደ ታች እና ከታች ወደ ላይ የሚባል አካሔድ አለው:: ከታች ወደ ላይ ቢመጣ መልካም ነው:: ሕዝቡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል ኖሮት መንግስት ያንን ቢያበረታታ እና ቢያጠናክር ምርጥ ነው:: ሕዝቡ የራሱ ባሕል ካለው ከመንግስት ጫና እና ግፊት ሳይኖር በራሱ ወስዶት የሚሔድበት ሁኔታ ይኖራል:: እነኚህ ዓይነት ነገሮች ከላይ የሚጫኑ ሳይሆኑ ከኅብረተሰቡ ባሕል የሚመነጩ ናቸው:: ሁሉም ሰው በጎ ፈቃደኛ ነው ማለት አይቻልም:: የበጎ ፈቃደኝነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አሉ:: ይህንን ዝንባሌ የሚወስነው የስብዕናቸው ከፍታ ነው:: ስብዕና ማለት ደግሞ የሰውየው የስነልቦና አመለካከት ለበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ዝንባሌ አለው ወይስ የለውም የሚለውን ይወስናል:: በሌላ በኩል ከባቢያዊ ሁኔታዎች አሉ:: አንዳንድ ባሕሎች ለበጎ ፍቃደኝነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ናቸው ይላሉ::
እንደ ዶ/ር ታዬ ገለፃ፤ ባሕሎች መንፈሳዊ፣ ሃይማኖታዊ እየተባሉ የሚከፋፈሉ ናቸው:: ከባሕል በተጨማሪ እውነተኛ ትምህርትም ሰውን በሳል እና ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዝንባሌ እንዲኖረው ያደርጋል:: ስለዚህ የበጎ ፈቃደኝነት ዋናው መሠረት ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ማሰብ መቻላቸው ነው:: ማለትም ግለኝነት ወይም ስለራስ ከማሰብ እና ከማውጠንጠን በላይ ለሌሎች መጨነቅ ነው:: ይህ ወደ ፍልስፍና ይወስዳል:: እነ ሶቅራጥስ፣ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች እና ቅዱሳን ስለሰው ማንነት የሚገልጹት ነገር አለ:: ራስህን እወቅ ይላሉ:: ሰው የስጋ እና የአጥንት ክምችት የሆነ ስግብግብ ፍጡር መሆኑን ይገልፃሉ:: ነገር ግን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲታሰብ ሰው የስጋ እና የአጥንት ክምችት የሆነ ስግብግብ ፍጡር ከመሆን በላይ መሆኑ ሲታሰብ፤ ግለኝነትን እየተቀረፈ ይሄዳል::
ነገር ግን ትምህርት ሁሉ ይህን ያደርጋል ማለት አይደለም:: አንዳንድ ትምህርቶች እንዲያውም ራስ ወዳድ ያደርጋሉ:: ነገር ግን ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች እንዲያስቡ የሚያደርጉ ጉዳዮች መካተት አለባቸው:: እውነተኛው የምንመኘው ትምህርት ሰዎች ከራሳቸው በላይ ለሌሎች እንዲያስቡ ተደርጎ የተቀረፀ ከሆነ ነው:: ለምሳሌ ሲቪክ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌላው እንዲተርፉ የሚገፋፋ ነው::
እንደ ዶ/ር ታዬ ገለፃ፤ ነገር ግን ከትምህርት ባሻገር ዋናው ሰዎች በግላቸው ራሳቸውን ሲያሳድጉ እና ሲያበለፅጉ እንዲሁም ዓዕምሯቸውን ሲያሰፉ በተጨማሪ ከፍ ወዳለ አመለካከት ሲያድጉ ከጥቃቅን ነገሮች ይልቅ ትልልቅ ነገሮችን ማሰብ ይጀምራሉ፤ ወደ በጎ ፍቃደኝነት ሊያዘነብሉ ይችላሉ:: ስለዚህ እነኚህ ነገሮች በጎ ፈቃደኞችን ይፈጥራሉ የሚል እሳቤ አለ::
ዶ/ር ታዬ ከባህል አንፃር ሲያስረዱ፤ ባሕል የአንዱ አገር ከሌላው አገር፣ የአንዱ ማኅበረሰብ ከሌላው ማኅበረሰብ ይለያል:: ባሕሎች ደግሞ በሁለት ይከፈላሉ:: ቡድናዊ እና ማኅበረሰባዊ የሚባሉ አሉ:: ቡድናዊ በተለይ የማኅበረሰብ ትሥሥር ላይ ትኩረት የሚሰጡ ባሕሎች ለበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች ይፈጥራሉ:: ሶሻል ካፒታል የተባለ ፅንሰ ሃሳብ አለ:: ቀመር (ፎርሙላ) አለው:: በእዚህ ቀመር በእዛ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለው የስልጣኔ ባሕል (የሲቪክ ካልቸር) የበጎ ፈቃድ ዝንባሌ ጎልቶ እንደሚወጣ ያሳያል:: ይሔ ደግሞ ከመንግስት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ጋር ሲደጋገፍ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል:: በማለት የራሳቸውን ተሞክሮ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ::
ለትምህርት በሄዱባት ጃፓን እንደተመለከቱት በዩኒቨርሲቲው በመቶ የሚቆጠሩ ክለቦች አሉ:: በትምህርት መጀመሪያ ቀን ተማሪዎች በሌሎች ተማሪዎች ማደሪያቸው ድረስ በመሄድ ለሊቱን ሙሉ እያንኳኩ ተማሪዎችን ይመለምላሉ:: ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በእረፍት ሰዓት ጊቢው በጣም ደስ ይላል:: ምክንያቱም ክለቦች ትርዒት ያሳያሉ:: የአካባቢ ጥበቃው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ እየሠሩ ያሉትን ያሳያሉ:: ሰዓሊዎች ስዕላቸውን ያስጎበኛሉ:: እንዲህ ያለ ነገር ሕይወትን ሙሉ እንደሚደርግ ያስረዳሉ::
በተቃራኒው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሲያብራሩ፤ አገር ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ረፍት ሲኖር፤ ሰው የሆነ ቦታ ቁጭ ብሎ ከመቆዘም ውጪ ምንም ሲያደርግ አይታይም:: የአካዳሚክ ተቋማቱም በሌላው ዓለም እንደተለመደው የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ይህንን አያበረታቱም:: እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ለበጎ ፈቃደኝነት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ::
በተጨማሪ ዶ/ር ታዬ እንደሚያስረዱት፤ ባሕል ብቻ ሳይሆን የመንግስት ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችም ለእዚህ አገልግሎት ምቹ ሁኔታን መፍጠር አለባቸው:: የሲቪክ ባሕል ማለት የሰለጠነ ባህል ማለት ነው:: ይህ ትርጉሙ ለሌሎች መቆርቆር እና ለሌሎች ማሰብ ሌሎችን መርዳት ማለት ነው:: ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በዘመኒቷ ኢትዮጵያ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጅማሬዎች አሉ:: ብዙም በጥናት የዳበረ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ባይሆንም ለምሳሌ በቀዳማይ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በጣም በተደራጀ መልኩም ባይሆን የማኅበረሰብ አገልግሎት በሚል፤ ተማሪዎች በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎችን ፊደል የማስቆጠር ሥራ ይሠሩ ነበር:: እንዲሁም የስካውት ቡድን ነበር::
ለስካውት ቡድን አባላት የዓዕምሮ የአካል እና የሥነልቦና ሥልጠና ይሰጣቸዋል:: እንደ ወታደር ጫካ ገብተው ይሰለጥናሉ:: ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሔዱ ለገበሬው አረም በማረም፣ አነስተኛ የመንገድ ሥራ ይሠራ ነበር:: እዛ ውስጥ የነበሩት በትምህርት የላቁ እና አስተሳሰባቸውም ከፍ ያሉ ነበር:: በኋላም ወደ ፖለቲካው ዓለም የመጡት ብዙዎቹ እነርሱ ናቸው:: ኢህአፓም ሆነ ሌላ ወደ ፖለቲካው የተጠጉ ልጆች መነሻቸው በንጉስ ቀዳማይ ኃይለስላሴ ዘመን የስካውት አባል ነበሩ:: እነዚያ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ለመሆን ራሳቸውን ያዘጋጁ ነበሩ:: ነገር ግን ተጠናክረው አልቀጠሉም:: ደርግ አቋረጣቸው::
በሌላ በኩል የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ በተጠናከረ መልኩ በደርግ ዘመን በአዋጅ መልክ የዕድገት በሕብረት ዘመቻ እና መሠረተ ትምህርት ተካሂዷል:: ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት ቤት ተዘግቶ ወደ ገጠሪቷ ኢትዮጵያ በማምራት ሕብረተሰቡን የማደራጀት እና የማሥተማር ሥራ ይሠራ ነበር:: እነኚህ ተማሪዎች ደግሞ ከአካባቢያቸው ወጥተው ይዘምቱ ነበር:: የአዲስ አበባው ሐረር፣ የትግራዩ ሸዋ እየተባለ በጣም የተራራቀ ቦታ ይዘምቱ ነበር:: ያ ዘመቻ የራሱን በጎ አሻራ ጥሎ አልፏል በማለት ካስገኘው ጥቅም መካከል ለምሳሌ ሰዎች ከአካባቢያቸው ወጥተው የሌሎችን ክልሎች እንዲያውቁ ማድረግ ተጠቃሽ ነው ይላሉ:: በሌላ በኩል አሁንም ያሉት ገበሬ ማኅበራት እና ቀበሌዎች የመስተዳድር መዋቅሮች የተመሠረቱት ዕድገት በሕብረት በተማሩ ሰዎች መሆኑን ያስረዳሉ::
በደርግ ጊዜ የነበረው የብሔራዊ ዘመቻም በኋላ በግዳጅ ተጫነ እንጂ በውትድርና ሰዎች በአካል ብቻ ሳይሆን በዓዕምሮም እንዲሰለጥኑ የሚያደርግ ነው:: በኋላ ጦርነት ሆኖ በግዳጅ ተጫነ እንጂ በፈቃድ ሲሆን፤ ውትድርናም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው:: በእስራዔል እና በአሜሪካ ሀገራዊ የውትድርና ሥልጠና ማንነትን፣ ዘመናዊ አስተሳሰብን ከራስ በላይ ለሌሎች መሆንን የሚያሳድጉበት መሆኑን ያስረዳሉ:: ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ይሠለጥናሉ፤ በተጨማሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ:: ይህ ኤርትራም አለ:: ሰዎች ከራሳቸው እና ከቅርብ አካባቢያቸው በላይ ለአገራቸው እንዲያስቡ የሚያደርግ መሆኑን ዶ/ር ታዬ ያብራራሉ::
አሁን ከበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር ተያይዞ በመንግስት በኩል እየተሠሩ ያሉ ጥሩ ጅምሮች አሉ:: ነገር ግን የተቀናጀ ወጥነት እና ቀጣይነት ያለው ስለመሆኑ እንደሚጠራጠሩ ይናገራሉ:: በበጎ ፈቃደኝነት የተወሰኑ ቤቶችን መገንባት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን ያነቃነቀ ከታች ወደ ላይ የሚሔድ ሥራ መሠራት እንዳለበት ይጠቁማሉ:: ያንንም ቢሆን በትምህርት ቤት በማስተማር እና በመማር ብቻ ሳይሆን በማንበብ በቤተሰብ ደረጃ ጀምሮ የበጎ ፈቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረጉ ጥሩ ነው ይላሉ::
የቤት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ከበጎ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ሥራዎች አረንጓዴ ልማትን ጨምሮ መንግስት በተቀናጀ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ቢሄድበት ጥሩ መሆኑን በማስታወስ፤ የአንድ ሰሞን ወይም የተወሰኑ ሰዎች ጉዳይ ብቻ ሊሆን አይገባም የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ::
የበጎ ፈቃድ ባሕልን ለማስፋት ዶ/ር ታዬ እንደገለፁት፤ የግለሰቦች የዓዕምሮ ብልፅግና ወሳኝ ነው:: ሰዎች በዕለት ተዕለት በተራ ሕይወት መርካት የለባቸውም:: ለማደግ እና ሌሎችን ለማገልገል ከተራ ሕይወት ከፍ ማለት አለባቸው:: ራሳቸውን በዓዕምሮ ለማበልፀግ፣ ራሳቸውን ለማሳደግ መቁረጥ እና መወሰን ይኖርባቸዋል:: ፍላጎት መምጣት ያለበት ከውስጥ ነው:: ከውስጥ እንዲመጣ የሚረዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ:: መፅሐፍ ሊያነቃቃ ይችላል:: አሁን ቴክኖሎጂውም ስለሚያግዝ የሚያነቃቁ እና ፍላጎቶችን የሚያመጡ የሚያበለፅጉ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው::
መንግስትም በጎ ፈቃደኝነት እንዲሰፋ፤ ከፍተኛውን ሚና መጫወት አለበት:: ካሪኩለምን ከማስተካከል ጀምሮ ሰዎች እንዲነሳሱ እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ሁኔታዎች ማመቻቸት አለባቸው:: ከላይ ፖሊሲ ማውጣት እና የማይፈፀም ስትራቴጂ መንደፍ ዋጋ የለውም:: ዋናው ጉዳይ ማኅበረሰቡ ላይ መሥራት፤ ዕድሎችን መጠቀም መሆኑን በመጥቀስ፤ መንግስት ፍትሃዊ፣ አቃፊ እና ዲሞክራሲያዊ ከሆነ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው አስተዳደር በመሄድ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠታቸው አይቀርም:: ይህ ሲሆን ያሉ ማኅበራዊ እሴቶችን ማለትም ከዕድር ጋር የሚቀራራቡ እቁብ እና ሌሎች ማኅበራትን በመጠቀም የበጎ አገልግሎትን ማስፋት ይገባል ይላሉ::
በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ የወጣቶች ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓብይ ሀይለ መለኮት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጥቅምን አስመልክቶ እንደሚያስረዱት፤ አገልግሎት ተቀባዩ በእርሱ ሆነ በመንግስትም ሊከወን ያልቻለው አስፈላጊ የገንዘብ፣ የባለሞያም ሆነ የጉልበት ጥቅም ያገኛል:: የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች በተለይ ወጣቶች ስብዕናቸውን ይገነባሉ:: ሥራን፣ ታዛዥነትን እና አገልጋይነትን ይለማመዳሉ:: የቡድን ሥራን ይለምዳሉ:: አንዱ ዕውቀት ይዞ ሲመጣ፤ ሌላው ጉልበት አንዱ ገንዘብ ሲያዋጣ እና አንዱ የሌላውን ችግር ሲፈታ የሚገኘው ልምድ ትልቅ ነው:: ከአካባቢያቸው ወጣ ብለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጡ የሌሎችን ባሕል ማወቅን ጨምሮ ብዙ ልምዶችን ያገኛሉ::
አቶ ዓብይ የህክምና ባለሞያዎችን እንደምሳሌ በማንሳት፤ የሕክምና ባለሞያዎች በዘርፉ ላይ በፈቃደኝነት አገልግሎት ሲሰጡ ሰፊ ልምድ እንደሚያገኙ ያስረዳሉ:: ሌሎች ባለሞያዎችም በሞያ ደረጃም የሚገኘው ልምድ ቀላል አለመሆኑን ያመለክታሉ::
የኢትዮጵያ መንግስትም ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቁርጠኝነት ማሳየቱን ያመለክታሉ:: መንግስት ተቋማዊ እስከሚሆን ከመስራት ጀምሮ ኅብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባሕሉ እንዲያደርገው እየጣረ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ:: የመንግስት ተነሳሽነት ብቻ ሳይሆን፤ በሒደት ሕብረተሰቡም ሙሉ ለሙሉ ሊቀበለው ይገባል ይላሉ:: የተሰጠውን ወይም የተሠራውን የበጎ አገልግሎት ሥራ መቀበል እና መንከባከብ ከሕብረተሰቡ እንደሚጠበቅ በማስታወስ፤ ሥራው ለአገር ሰላምም ሆነ ለኢኮኖሚ ግንባታም የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ:: አሁን የቤት ግንባታን ጨምሮ እየተሠሩ ያሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በጣም ጥሩ መሆናቸውን በማስታወስ፤ ነገር ግን ከዚህም በላይ ሥርዓት ተበጅቶሎት ሊቀጥል ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ::
አቶ ዓብይ እንደ ዶ/ር ታዬ ሁሉ ማኅበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባሕሉ ማድረግ አለበት ይላሉ:: በሌሎች አገሮች ከአገር ወደ አገር ሔዶ የሕክምና አገልግሎት መስጠትም ሆነ ሌሎች ሞያዊ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ በኢትዮጵያም እንዲለመድ የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት አለበት ይላሉ:: ለበጎ ፈቃደኞች ዕውቅና መስጠት እና ለወጣቶችም የሥራ ዕድል በተሻለ መልኩ መስጠት ይገባል ይላሉ::
መንግስት ወርዶ ሕብረተሰቡን ለማሳተፍ ከታች ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግስት ድረስ መዋቅር ተቀርጾ፤ በጀት ተይዞ ሠራተኛ ተቀጥሮ እየተሠራ መሆኑን በማመልከት፤ በተለይ በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ መትከልም ሆነ የቤት ግንባታ እንዲሁም ደም ልገሳ እና የክረምት ማጠናከሪያ ሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከማኅበረሰቡም የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2016 ዓ.ም