ከችግሮቻችን የምንወጣበት ተጨባጭ አማራጭ!

እኛ ኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤቶች ነን። በነዚህ ዘመናትም እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ ብዙ አሉታዊ እና አወንታዊ ክስተቶችን አሳልፈናል። ከፍ ካለ ሥልጣኔ ጀምሮ ልብን የሚሰብሩ የግጭት እና የጦርነት ፤ የረሀብ እና የጉስቁልና ታሪኮችን ለማለፍ ተገድደናል።

በአንድ ወቅት የአክሱም ሐውልቶችን ፤ የላሊበላ ቤተመቅደስን …ወዘተ መገንባት የቻልነውን ያህል ፤ ይህንን ድንቅ የሰው ልጅ የአዕምሮ እሳቤ እና የእጅ ጥበብ ባለመደማመጥ መርገምት ማስቀጠል አቅቶን የትናንት ገናናነታችን ነበር በሚል የታሪክ ትርክት ዘመን እንዲያስቆጥር አድርገናል ።

ሁሉን አጥፍቶ / አፍርሶ በአዲስ በመተካት ላይ የተመሰረተው ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳታችን ፤ ተተኪ ትውልዶች ትናንታቸውን በተጨባጭ አውቀው ፤ ትናንትን መሠረት ያደረገ ጅማሪ እንዳይኖራቸው ተግዳሮት ሆኖባቸዋል ፤ ስለ ትናንት በቂ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው በማድረግ ዛሬያቸው በብዙ ግራ መጋባት እንዲፈተን አድርጎታል ።

ከዚህም ባለፈ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች የታሪክ ክፍተት በፈጠራቸው የተዛቡ ትርክቶች ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆነዋል። ይህም አጠቃላይ በሆነው የትውልድ ቅብብሎሽ የሚጠበቀውን እንደ ሀገር የመለወጥ ፣ የማደግ እና ከትናንት የተሻለ ማኅበረሰብ እና ሀገር የመገንባት መሻት እውን ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ ስም የተሰጣቸው ጦርነቶች እና አብዮቶች ተካኂደዋል። እነዚህ ጦርነቶች እና አብዮቶች እንደ ሀገር የጠበቅናቸውን እና ተስፋ ያደርግናቸውን ማኅበረሰባዊ መሻታችንን ተጨባጭ ሊያደርጉልን አልቻሉም ። ለአንዳንድ ችግሮቻችን መፍትሄ ይዘው የመጡ ቢመስልም ከዚህ በተቃራኒው ሄደው ለተጨማሪ ሀገራዊ ፈተናዎችን ዳርገውናል።

እንደ ሀገር ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የሆነውን ብናነሳ እንኳን “ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም፣ በጸና መንፈስ ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳት የተጀመረው አብዮት ፣ የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለንና እንደሀገር ምን እንዳሳጣን የአደባባይ ሚስጥር ነው ። አብዮቱ በማኅበረሰባችን ውስጥ ጥሎት ያለፈው ጠበሳም የቱን ያህል ከባድ እንደነበር ሁሌም የሚታወስ ነው።

ይህንን ሀገራዊ እውነታ በመቀልበስ በሚል በየመንደሩ የተጀመሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከፍ ወዳለ የፖለቲካ ፍላጎቶች አድገው ፣ ብዙ ጠብመንጃ ያነገቡ ቡድኖችን በመፍጠር ወደ ለየለት የርስ በርስ ጦርነት ከቶናል። በዚህም ያሳለፍናቸው አስርት ዓመታት የቅርብ ትዝታዎቻችን ናቸው። እንደ ሀገር በሕዝባችን ውስጥ የፈጠሩትም የልብ ስብራት ቀላል አይደለም ።

አብዮቶቹም ሆኑ ጦርነቶቹ ፣ የአሸናፊ እና ተሸናፊ ትርክቶችን መሠረት ያደረገ የኃይል አስተሳሰብን የተደገፉ መሆናቸው ፣ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ሆነ የጋራ ማኅበራዊ ፍላጎታችንን ተጨባጭ ለማድረግ አላገዙንም ። ከዚያ ይልቅ የእብሪት መንፈስን በመፍጠር ባልተገቡ የፖለቲካ ሴራዎች እንድንፈተን አድርገውናል ።

በአንድ በኩል በኃይል አሸናፊነቱን ያጸናው ቡድን አሸናፊነቱን ለማስቀጠል የኃይል እና የሴራ ፖለቲካን ዋንኛ አማራጭ አድርጎ መውሰዱ ፣ በሌላ በኩል ይህ የአሸናፈው የኃይል እና የሴራ እንቅስቃሴ እንደሀገር የሚፈጥረው ማኅበራዊ አለመረጋጋት በራሱ ሀገር ወደ ስክነት እና መረጋጋት እንዳትመጣ አድርጓታል።

ይህ በመሠረታዊነት ፍላጎቶችን በኃይል እና በሴራ በሌሎች ላይ በመጫን የመጣንበት ርቀት እንደሀገር የድህነት እና ኋላቀርነት ማሳያ የሆነች ኢትዮጵያን ፈጥሯል ። እውነታውን ተረድተን ፈጥነን መንቀሳቀስ ካልቻልን ችግሩ ድንገትም በብዙ መስዋዕትነት ዛሬ ላይ የደረሰችውን ሀገራችንን ሊያሳጣን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።

ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ ያለን አማራጭ በልዩነቶቻችን /በፍላጎቶቻችን ዙሪያ በሰከነ መንፈስ ፣ በተረጋጋ አእምሮ ፣ የሀገር እና የትውልድ ኃላፊነት በሚሰማው ማንነት ቁጭ ብለን መነጋገርና መወያያት ይኖርብናል ፤ ከዚህ ቀደም ዓይናችንን ከፍተን ለማየት ያልቻልነውን ይህን አማራጭ ፈጥኖ መጠቀም ፣ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርም ይጠበቅብናል ። ለዚህ ደግሞ ከፊታችን ያለው ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ዕድል ፣ በዕድል ውስጥ ያለ ተስፋችን ነው ።

ይህ ከችግሮቻችን የሚያወጣን ተጨባጭ አማራጭ ሁላችንንንም ስለ ሀገራችን እና ስለ ሀገራዊ ተስፋችን ሁላችንንም በእኩል አሸናፊም/ ተሸናፊ የሚያደርገን ነው። ከዚህ ባለፈም እንደ ሀገር ተፈጥሮ ለማየት ለምንመኘው አዲስ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ትልቅ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ፣ ለቀጣይ ትውልዶችም የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር መሠረት የሚሆን ነው።

ለዚህ ነው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ሰሞኑን ፣ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ ጦርነትና አብዮት የተሟላ መፍትሔ የማያመጡት አሸናፊ እና ተሸናፊ ስለሚያስከትሉ ነው። ቢዘገይም የተሸነፈው ለማሸነፍ ይታገላል። ያሸነፈውም ድሉን ለመጠበቅ ይዋጋል። ምክክር ግን ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል። ከተሸነፍንም ሁላችንም ለሀገራችን ብለን እንሸነፍ”

“ጦርነትን ኖረንበታል። የተወሰኑ ችግሮቻችንን ፈትተንበታል። አብዮትን ደጋግመነዋል። የተወሰኑ ችግሮችን ፈትተንበታል ፤ በሁለቱም ያልተፈቱትን ችግሮች ለመፍታት የቀረን መንገድ ምክክር ነው ማለታቸው። ለምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም ዜጋ በሃላፊነት እንዲንቀሳቀስ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው!

አዲስ ዘመን ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You