አቶ ደስታ አንፎሬ ተወልደው ያደጉት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከንባታ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ የወይራራማ ቀበሌ ነው። የአርሶ አደር ልጅ ቢሆኑም እርሳቸው ግን በቋሚነት የሚተዳደሩት በንግድ ሥራ ነው። ቡና እና መሰል ሰብሎችን ከገበሬው ተረክበው ወደ ውጭ ሀገር በመላክና በመሸጥ ብዙ ሀብት ማፍራት ችለዋል።
አባታቸውን ሊጠይቁ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው በመጡ ቁጥር የአባታቸውም ሆነ የአካባቢው የእርሻ መሬት በተፈጥሮ ሀብት መመናመን ምክንያት የመጎዳቱ ጉዳይ ያንገበግባቸዋል። በተለይ ደግሞ እንደወረርሽኝ አካባቢውን የወረረው ባህር ዛፍ መሬቱ ሌላ ሰብል ጨርሶ እንዳያበቅል ማድረጉ፤ ይህን ተከትሎም አርሶ አደሩ የሚሸጠው ቀርቶ ለራሱ የእለት ጉርስ የምትሆን እህል ማግኘት አለመቻሉ ሁልጊዜም ይቆጫቸው ነበር።
ትውልድ አካባቢያቸው ደርሰው በተመለሱ ቁጥር ‹‹ይህንን አካባቢ እንዴት ነው ወደ ቀድሞ ልምላሜውና ምርታማነቱ መመለስ የሚችለው?›› ሲሉም ራሳቸውን ሲጠይቁም ኖረዋል። ‹‹አርሶ አደሩ ወርቅ የሆነ መሬት ይዞ መራብም ሆነ የሰው እጅ መጠበቅ የለበትም›› የሚል አቋም ይዘው በቅድሚያ ባህር ዛፉን የማስወገድ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመኑ።
ይህ ግን እንዳሰቡት ቀላል አልሆነላቸውም፤ ይህን ሃሳባቸውን የሱሙ ሁሉ የተቃውሞ ጅራፋቸውን አወረዱባቸው። ሃሳባቸውን አብዛኛው የአካባቢው ሰው የሚተዳደረው ከባህር ዛፉ የሚገኘውን አጣና በመሸጥ በመሆኑ የገቢ ምንጫቸውን ለማድረቅ የመጣ ክፉ ሃሳብም አድርገው ቆጠሩባቸው። ተቃውሞው የወላጅ አባታቸውና የባለቤታቸው ጭምር ሆነባቸው።
አቶ ደስታ ‹‹ይህንን ሃሳብ ሳማክራቸው መጀመሪያ ያገለለኝ አባቴ ነው፤ ባለቤቴም እንዲህ ዓይነት ሥራ ውስጥ እንዳልገባ ተማጽናኝ ነበር›› ይላሉ። እሳቸው ግን ይህ ሁሉ ተቋውሞ አልበገራቸውም፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ በመሆን የራሳቸውን አንድ ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬት ማልማት አለብኝ በሚል ቆርጠው ተነሱ። ከፍተኛ በጀት መድበው ለእርሻ የማይመቸውንና ጉብታ የበዛበትን መሬታቸው ላይ ለዓመታት በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የነበረውን ባህር ዛፍ በመመንጠር ሥራቸውን ጀመሩ።
ከ500 ሺ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ባህር ዛፉን አሰመነጠሩ፣ ጉቶው እንዲነቀልም አደረጉ። በአግባቡ በባለሙያ እየታገዙ የሚሰሩ 15 ቋሚ እና ከ30 በላይ በጊዜያዊነት የሚሰሩ ሠራተኞችን በመቅጠር በባህር ዛፍ ምክንያት ንጥረ ነገሩን ሁሉ አጥቶ የተጎዳው መሬት መልሶ እንዲያገግም የማድረግ ሥራ እንዲከናወን አስደረጉ።
መሬቱ ከታከመ በኋላ ዘመናዊ የተፋሰስ ልማትና እርከን ሥራዎችን በማካሄድ ፤ የላቀ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸው እንደ ሙዝ፣ ሽንኩርት፤ ቃሪያ፣ ኩከምበርና መሰል አትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎችን ማልማት ውስጥ ገቡ። በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ድጋፍ አንድ ሺ የሙዝ ችግኝ በነፃ አግኝተው ተከሉ። አቶ ደስታ የሙዝ ዝርያው በሰባት ወራት ውስጥ የሚደርስ መሆኑን ጠቅሰው፣ ውጤቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ አገኛለሁ የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ይገልፃሉ።
‹‹የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ወደቀድሞው ገፅታው ከመመለስ ባለፈ ለህብረተሰቡ የአትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት ለማሳደግ ያስችላል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ሥራው ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻለ መሆኑ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።
አቶ ደስታ መሬቱን ሁሉ ወሮ ያለው ባህር ዛፍ ቢጠፋ ሰው ከድህነት ይወጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ የእሳቸውን ተሞክሮ ያዩ አርሶ አደሮች ባህር ዛፉን ወደ መመንጠርና መሬታቸውን የማልማት ሥራ መግባት መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።
አቶ ደስታ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራቸውን የማስፋፋት እቅድ አላቸው። በተለይም በቀሪው አንድ ነጥብ ስምንት ሄክታር መሬታቸውና በማሳቸው አቅራቢያ ያለው የባህር ዛፍ አሁን የተከሉትንም አትክልት የመጉዳት አቅም ያለው እንዳለው በማመን ዛፉን መንጥሮ አካባቢውን በሙሉ በፍራፍሬና ሌሎች አካባቢውም ሆነ ለሀገር ፋይዳ ያላቸውን ሰብሎች በማልማት ልማቱን ለማጠናከር መፈለጋቸውን አጫውተውናል።
ለዚህ መሳካት ግን የዞኑ አስተዳደር እገዛ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዛፉን ከመነጠሩ በኋላ የፓፓያና አቮካዶ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ያመለክታሉ። ለዚህም የክልሉ መስተዳደር የተሻሻሉና ምርታማ የአቮካዶና ፓፓያ ዝርያዎችን ለመስጠት ቃል እንደገባላቸው ጠቁመዋል።
አቶ ደስታ ለዚህ እቅዳቸው መሳካት በተለይ የክልሉ መንግሥት የተለመደው ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተዋል። ‹‹በተለይ የውሃ ፓምፕና የመሬት አቅርቦት ቢያመቻቹልኝ ላሰብኩት ሥራ መሳካት የበለጠ ወሳኝ ነው›› ይላሉ።
‹‹የእኔ ዋና አላማ ከዚህ ማሳ ትርፍ ማግኘት ሳይሆን የምግብ ሰብሎችን በስፋት በማልማት የአካባቢው ህብረተሰብ ያለበትን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ማሻሻልም ነው›› የሚሉት አቶ ደስታ፤ ወደ ፊት ግን እንደሮዝመሪ ያሉ ተክሎችን በማልማት ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት አቅደው እያሰሩ ስለመሆኑንም ነው የተናገሩት። መሬት የሚያገኙም ከሆነ የእንስሳት እርባታ ለመጀመር ማቀዳቸውን ጠቅሰው፣ ይህንንም ከመኖ ልማት ሥራው ጎን ለጎን ለመሥራት ማሰባቸውን ይናገራሉ። በዚህም ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
አቶ ደስታ እስካሁን በማሳቸው ላይ ባህር ዛፍ ተክለው በችግር ውስጥ ያሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች የእሳቸውን ተሞክሮ እንዲወስዱ መክረዋል። በባህር ዛፉ ምትክም ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን እንዲያለሙና በሀገር የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ሥራ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
‹‹ባህር ዛፍ መሬት ያደርቃል፤ ከተተከለ ከሰባት ዓመት በኋላ ከባህር ዛፉ የሚገኘውም ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ይህን ባህር ዛፍ በማስወገድ ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን ለማምረት መረባረብ ይገባዋል›› በማለት ይናገራሉ። በተለይም በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ በማምረት ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኙ እንደ ሽንኩርትና መሰል ሰብሎችን ቢያመርቱ አዋጭ እንደሆነም መክረዋል።
አቶ አንፎሬ ወተንጎ የአቶ ደስታ ወላጅ አባት ናቸው። እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ከ40 ዓመታት በፊት በባህር ዛፍ በተሸፈነው መሬት ላይ ሰፊ የቡና እና የእንሰት እርሻ ነበር፤ በወቅቱ ከማሳቸውም ሆነ ከጎተራቸው እህል ጠፍቶ አያውቅም ነበር ። እያደር ግን መላው የአካባቢው አርሶ አደር እንሰት ነቅሎ ባህር ዛፍ ተከለ። በባህር ዛፍ የሚገኘው ገቢ ዓመታትን ጠብቆ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ለምግብ የሚውሉ እህሎች በሙሉ ከሌላ አካባቢ በውድ የሚገዙ በመሆኑ መላው የአካባቢው ነዋሪ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ተጋለጠ።
መሬቱ ለረጅም ዓመታት በባህር ዛፉ የተጎዳ እንደነበር አስታውሰው፣ ልጃቸው ባህር ዛፉን መንጥሮ ሰብል ለማልማት ሲነሳ ገንዘቡን ማበከን አይገባውም የሚል እምነት እንደነበራቸው ይገልፃሉ። ባህር ዛፉ ለመመነጠር ብቻ ከ100 ሺ ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ሲመለከቱ ደግሞ ልጃቸው የቱንም ያህል ቢለፋ ወጪውን የሚተካ ምርት አያገኝም የሚል ጥርጣሬ እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ይሁንና ልጃቸው በእንቢታው ፀንቶ መሬቱን እንደ ቀድሞ ለም የማድረግና የተለያዩ ፍራፍሬዎችን የማልማት ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ሲመለከቱ ቀስ በቀስ ጥርጣሬያቸው መቀነሱን ይናገራሉ። ‹‹ አሁን መሬቱ ፍሬ ላይሰጥ ይችላል የሚለው ስጋቴ ተወግዷል፤ እንዳውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን በማየቴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተስፋ አጭሮብኛል፤ የልጄም ልፋት ከንቱ ባለመቅረቱ ተደስቻለሁ›› ሲሉ ይናገራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ የልጃቸውን ሃሳብ በመጋራት የአቅማቸውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። ሌሎችም የአካባቢው አርሶ አደሮች ወደዚህ ልማት እንዲገቡ ምክር እየሰጡ ይገኛሉ። ‹‹በዙሪያችን ያሉ አርሶ አደሮች የልጄን ማሳ ካዩ በኋላ እነሱም መሬታቸውን ከባህር ዛፍ ለማፅዳትና ለማልማት ተነሳስተዋል፤ በየእለቱ እዚህ እየመጡ ተሞክሮ ይወስዳሉ›› በማለት ያስረዳሉ።
‹‹ባህር ዛፍ ወደቀያችን ከመጣ በኋላ ድህነት ወደ እያንዳንዳችን ጎጆ ሰተት ብሎ ገባ›› የሚሉት አቶ አንፎሬ፤ በዓመት ሁለት ሶስት ጊዜ ያመርት የነበረው አርሶ አደር ባህር ዛፉ ከተተከለ በኋላ ስንፍናን ወርሶ ቤቱ ቁጭ ማለቱን ይገልፃሉ። አንዳንዱ ረሃቡ የፀናበት አርሶ አደር ወደ ልመናና ስርቆት የገባበት ሁኔታም እንደነበረም ያስታውሳሉ። ‹‹ሰባት ዓመት ጠብቆ ባህር ዛፉን ሲሸጥም አብዛኛው ሰው ጨፍሮ ይጨርሰዋል እንጂ በሕይወቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ አላመጣበትም›› ሲሉ ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ልጃቸው አቶ ደስታ በአካባቢው ላይ በሰሩት የፍራፍሬና አትክልት ልማት ማህበረሰቡ ከብር በላይ ለምግብነት የሚውል ሰብል ማምረት አዋጭ እንደሆነ መገንዘብ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የከንባታ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተክሌ ሃብቴ በበኩላቸው፤ ባህር ዛፍ ማሳን የማድረቅ፣ ለምነትን የማሟጠጥ ባህሪ እንዳለው ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በዚህም ረገድ በአካባቢው ያለው መሬት በአብዛኛው በሚባል ደረጃ የባህር ዛፍ አሉታዊ ተፅዕኖ የደረሰበትና ለምነቱን ያጣ ነው። ይህንንም በመረዳት የወረዳው አስተዳደር በባህር ዛፍ ማስወገድ ሥራ ከምግብ ዋስትና አኳያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። አርሶ አደሩ ባህር ዛፉን እየነቀለ የምግብ ዋስትናውን የሚያሻሽልበት ሥራ እንዲሰራ በመስኖ፣ በበልግና በመኸር ወቅት የተለያዩ ተሞክሮችን እንዲወስድ ተደርጓል።
በዚህ ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አቶ ደስታን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች ለምግብነት የሚውሉም ሆነ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ይገልፃሉ። ‹‹ በወረዳችን ባህር ዛፍ ነቅሎ ከአንድ ሄክታር በላይ ቡና ፣ ሙዝ፣ ፓፓያና ሌሎች ሰብሎች በማጣመር ማልማት የቻለ አርሶ አደር አለ›› ሲሉም አስታውቀዋል።
በወረዳው የተገኙ ምርጥ ተሞክሮችን በመቀመር አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን የሚያረጋግጥለትን ሰብሎች እንዲያመርት ቅስቀሳ እየተደረገ ስለመሆኑንም ያስረዳሉ። የንቅናቄ መድረኮችንም በማዘጋጀት ባህር ዛፉን የማስወገዱን ሥራ የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር ተጣምረው እየሰሩ መሆኑንም ያብራራሉ።
‹‹ከዚህ ቀደምም ቢሆን ባህር ዛፍ ውሃ የማድረቅ ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ ከምንጭ ዙሪያ ይነቀል የሚል አዋጅ ወጥቶ ነበር፤ በእድርም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ ክዋኔዎች ላይ በተደጋጋሚ ይነገር ነበር። ይሁንና በቁርጠኝነት ባህር ዛፉን በማስወገድ ረገድ ክፍተት ነበር›› ሲሉ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን እንደ ክልል የተሰጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ በወረዳው በተሰራው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የአመለካከት ለውጥ እየመጣ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ እንደ አቶ ደስታ ያሉ ግለሰቦች የራሳቸውን ማሳ ማሳያ አድርገው ባከናወኑት የልማት ሥራ በርካታ አርሶ አደሮች ባህር ዛፍን በሌሎች ሰብሎች ለመተካት ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳዩ መሆናቸው ገልጸዋል። ይህን መሰረት በማድረግም የክልሉም ሆነ የዞኑ አመራር ለአርሶ አደሩ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የሙዝና የሌሎች ሰብሎችን ችግኞች በነፃ ከማቅረብ ጀምሮ የቴክኖሎጂና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ እገዛ እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ። ጽሕፈት ቤቱ በቀጣይም ሁሉም አርሶ አደር የምግብ ዋስትናውን የሚያረጋግጥለትን ሰብሎች እንዲያለማ ለማድረግ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመናበብና በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም