በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም ነፍስ እየዘራ ያለውየሥነጽሑፍ እንቅስቃሴ

እንደሚታወቀው ትምህርት አጠቃላይ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የትምህርት ዓይነትም ሆነ የጥናት መስክ በዚሁ በ“ትምህርት” ስር ይካተታል። በመሆኑም፣ ስለእያንዳንዱ የትምህርት አካል ሲወሳና ሲነሳ ስለ ትምህርት ማውሳት ማለት መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ይሆናል።

የአብዮቱ ቀዳሚ አዋላጅ ነው የተባለለት የተማሪዎች ንቅናቄ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑ ተደጋግሞ የተመሰከረለት፤ “ከቬትናም ጦርነት ወዲህ የታየ ትልቁ የተማሪዎች ንቅናቄ” ተብሎ የተፃፈለት፤ በውጭም በሀገር ውስጥም የነበሩ ተማሪዎችን አንድ በማድረግ በአንድ ያሰለፈ፤ በአንድ ዓላማ በአንድ ላይ መቆም መገለጫው፤ አጠቃላይ ራእዩና ግቡ ሶሻሊዝም (ሥር-ነቀላዊነቱ እንዳለ ሆኖ) የነበረ ንቅናቄ፤ በእነ ታጠቅ፣ ቻሌንጅ፣ ትግላችን እና የመሳሰሉት መጽሔቶች የመከራከሪያ መድረኩ የነበሩት ንቅናቄ፣ “The Student movement started as a care­ful challenge of authority through poetry, stage plays and the paper News and Views (published between 1959–66)“ (የተማሪዎች ንቅናቄ የተጀመረው የነበረውን ሥርዓት በመቃወም ሲሆን፣ ይህም ይገለፅ የነበረው ተማሪዎች ሲያቀርቧቸው በነበሩ ግጥሞች፤ መድረክ ላይ በሚያቀርቧቸው ትያትሮች፤ በየጋዜጦች ላይ በሚወጡ መጣጥፎች እና አተያዮች (በተለይም እአአ ከ1959–66 ባለው ጊዜ ውስጥ ይታተሙ በነበሩት)) ተብሎ በታሪክ ውስጥ ሁነኛ ስፍራን ያገኘ ንቅናቄ (“En­cyclopedia Aethiopica” ይመለከቷል)፤ “በተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት ጥያቄው የብሔሮች መብቶች ይታወቁ እንጂ ከኢትዮጵያ የመለያየትን ሃሳብ ለማጉላትና ኢትዮጵያን ለመበተን አልነበረም” (የ“ለውጥ ናፋቂ ሕይወቴ” መጽሐፍ ደራሲና በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ማኅበር ጸሐፊ የነበሩት አበራ የማነ አብ) ሲሉ ለንባብ ያበቁለት ንቅናቄ የመታገያ መሳሪያው የነበረችው ኪነጥበብ ስትሆን፣ በተለይም ሥነ ጽሑፍ የማይተካውን ሚና ተጫውቷል።

የታሪክ ተመራማሪዎችን ጨምሮ፤ ብዙዎች እንደሚስማሙበትና በበርካታ ሰነዶችም ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሊባል የሚችል ጫና አሳድሯል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች አሠርት ያህል በቆየው የፖለቲካ ትግላቸው ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ሁለቱና መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉት የመሬትና የብሔረሰብ ጥያቄ ናቸው። በየካቲት 1958 ‹‹መሬት ለአራሹ›› የሚል መፈክር በማንገብ አደባባይ ወጡ። ያ ጥያቄም ሲንከባለል ቆይቶ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በ1967ቱ ሥር ነቀል የመሬት አዋጅ የመጨረሻ ምላሹን አገኘ። በጥቅምት 1962 ዓ.ም. ዋለልኝ መኮንን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔረሰብን ጥያቄ በማንሳት ትልቁን ቦንብ አፈነዳ። ያኔ የተጫረው ሃሳብም ከአሠርት ዓመታት የብሔረሰባዊ ትጥቅ ትግል በኋላ ኢሕአዴግ በ1983 የፖለቲካ ሥልጣንን ሲጨብጥ መጀመሪያ በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር፣ ቀጥሎም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አማካይነት ሕጋዊ መሠረት ከማግኘትም አልፎ “እስከ መገንጠል”ም ዘለቀ።

ይህንን እዚህ መጥቀስ ያስፈለገው ተወደደም ተጠላ የታሪካችን አካል በመሆኑና በሀገራችን ታሪክም ሆነ በታሪክ ጥናት ውስጥ ሁነኛ ስፍራን ይዞ በመገኘቱ ምክንያት፤ እንዲሁም ይህ ግዙፍ የሀገራችን ታሪክ ይሰራባቸው በነበሩት በእነዚያ ጊዜያት ውስጥ ሥነ ጽሑፍ ሁነኛው መሄጃ ስለነበረ ነው።

እዚህ ላይ ይህ ሁሉ “ታሪክን የኋሊት” ለምን አስፈለገ? የሚል ገራገር ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል። ቢነሳም ተገቢ ነውና ምክንያቱን እንደሚከተለው ማስረዳት ይቻላል።

በመግቢያችን ላይ ለመነካካት እንደሞከርነው ሥነ ጽሑፍ አንዱ፣ ምናልባትም ጥልቁና በሰብዓዊነት (ሂዩማኒቲስ) ስር የሚፈረጅ የትምህርት አካል ነው። በመሆኑም እንደ አንድ የትምህርት አካልነቱ የተለየ ነገር አለው ተብሎ ልዩ ትኩረትን ላያገኝ ይችል ይሆናል።

ሥነ ጽሑፍን ከሌሎች የትምህርት ዓይነቶች (ወይም፣ የጥናት መስኮች) የሚለዩት በርካታ መሠረታዊያን ያሉ ሲሆን፣ አቅምና ፍላጎቱ፤ ሰብዓዊ ስሜቱና ሁለንተናዊነቱ በብዙዎች ዘንድ መኖር መቻሉና ከትምህርት ዓይነትነት (ከጥናት መስክነት) በዘለለ የሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉ ጥልቅ ስሜት መግለጫነቱ ከሁሉም ይለየዋል። ይህ በበኩሉ ሥነ ጽሑፍን የሁሉም ያደርገዋል ማለት ነው።

ይህንን ስንል የሥነ ጽሑፍ አድናቂ ለመሆንና ስሜትን በሥነ ጽሑፍ ለመግለፅ የግድ ሥነ ጽሑፍን በጥናት መስክነት ማጥናት፤ ወይም፣ በሥነ ጽሑፍ ከፍተኛ ዲግሪን መጨበጥ አይጠበቅም። ማንበብና መጻፍ በራሱ በቂ ነው። ያ ማለት በዘርፉ ጠለቅ ብሎ መሄድ አያስፈልግም ማለት አይደለም፤ ያ ማለት ሌላ ስለሆነ እንጂ።

ዓለማችን እንደምታሳየን ታላላቅ ሰዎች በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ብቻ አይደለም ውጤታማ ሲሆኑ የሚታዩት። ባላጠኑት መስክም እውቅ ሥራዎችን ሰርተው ማየት የተለመደ ነው። በመሆኑም ነው በ1960ዎቹ የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የእንቅስቃሴውን አራማጆች በሙሉ ማለት እስኪቻል ድረስ፣ ያለ ምንም የጥናት መስክ ልዩነት በሥነ ጽሑፍና በሥነ ጽሑፍ ውድድሮች ዙሪያ አሰባስቦ የነበረው።

ዮሐንስ አድማሱ፣ መስፍን ወልደማሪያም፣ ኢብሳ ጉተማ፣ አበበ ወርቄ፣ ተገኝ የተሻወርቅ፣ ታምሩ ፈይሳ፣ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው)፣ ጸጋዬ ገ/መድህን (ደብተራው)፣ ይልማ ከበደ፣ መላኩ ተገኝ – – – – በወቅቱ በሥነ ጽሑፍና ውድድሩ ዘርፍ የተሰማሩ፤ የተለያዩ የጥናት መስክ ምሁራን ነበሩ። (ለተሟላ ግንዛቤ በ1993 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የወርቅ ኢዮቤልዮውን (50ኛ ዓመት) ሲያከብር “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” በሚል ርእስ ያሳተመውን፤ ከ1951 እስከ 1960 ዓ.ም ለውድድር ከቀረቡት ግጥሞች ከፊል ያህሉን ብቻ የያዘውን፤ የወቅቱ ተማሪዎችን የግጥም ስብስብ ጣፋጭ መጽሐፍ ማንበብ ጠቃሚና ይሆናል።)

የመጽሐፉን ርእስ በተመለከተም∶-

ግጥሞቹ በዚህ ስም የተጠቃለሉት በየዓመቱ ግንቦት ወይም ሰኔ በሚከበረው የኮሌጅ (ከ1954 በኋላ “ዩኒቨርስቲ”) ቀን ስለቀረቡ ነው። ከኮሌጅ ምሥረታ ጀምሮ የግጥም ክበብ እንደነበረና ቅዳሜ ቅዳሜ ገጣምያን ስንኞቻቸውን በት/ቤቱ ምግብ አዳራሽ ያቀርቡ እንደነበረ ይነገራል። ት/ቤቱ ውስጥ በሚደረገውም የግጥም ውድድር ላይ የሚቀርቡት ግጥሞች እየተሻሻሉ ስለመጡ ለኮሌጅ ቀን ዝግጅት ለማቅረብ ታሰበ። በዚህም መሠረት በ1951 ዓ.ም ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት የወጡት ገጣሚዎች የኮሌጅ ቀን ግጥሞቻቸውን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ሌሎች ባለሥልጣናት በተገኙበት እንዲያነቡ ተደረገ። ንጉሡም በግጥሞቹ፣ በተለይም ተገኘ የተሻወርቅ ባቀረበው “ሰው እንቆቅልሽ ነው” [በተሰኘ ግጥም] ስለተደሰቱ በትምህርት ሚኒስቴር ግጥሞቹ እንዲባዙ አዘዙ።

ከዛን ጊዜ ጀምሮ የግጥም ንባብ ከኮሌጅ ቀን ዝግጅት ጋር ተጣመረ። ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም ሶስቱ አሸናፊ ግጥሞች ከተነበቡ በኋላ ለታዳሚው አምስት አምስት ሳንቲም ይሸጡ ጀመር። የቅዳሜ ግንቦት 12 1959 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቀን ፕሮግራም እንደሚያሳየውም ሶስቱ አሸናፊ ግጥሞች የሚነበቡት ከሰዓት በኋላ ነበር። የተለያዩ የስፖርትና የመዝናኛ ትርኢቶች ከቀረቡ በኋላ ሶስተኛ የወጣው ግጥም ይነበባል። ከዛም የተለያዩ የተማሪ ማሕበሮች ዓመታዊ ዘገባ ያቀርቡና ሁለተኛው ግጥም ይቀርባል። የቀኑ ዝግጅት የሚጠናቀቀው አሸናፊው ግጥም ተነቦ ሽልማቶችም ከተሰጡ በኋላ ነበር።

በማለት ኅሩይ አብዱ የተባሉ ጸሐፊ ማስፈራቸው ይታወሳል።

የተማሪዎቹን ግጥሞች ተፅእኖ ፈጣሪነት በተመለከተም∶-

ሕዝቡ በታምሩ ፈይሳ ድፍረት በመገረም ቶሎ ግጥሙን ለመግዛት ይጣደፍ ጀመር። ቀን አምስት ሳንቲም ሲሸጥ የነበረው ግጥም ማታ ሊገኝ ስላልቻለ በአንዳንድ ቡና ቤቶች እስከ አምስት ብር እንደተሸጠ ይነገራል።

የግጥሙ ዝና ከአዲስ አበባ አልፎ ከተለያዩ ክፍለ ሀገሮች ግጥሙ እንዲላክላቸው በደብዳቤ የሚጠይቁ ብዙ ነበሩ። በማለት አስፍረዋል።

ከላይ የጠቀስናቸው የወቅቱ የማህበሩ ጸሐፊ እኔ “የማውቀው ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ነው ” እንዳሉት ሁሉ በወቅቱ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ የሚቀነቀንበት፤ የሕዝብ መጨቆን ይወገድ ዘንድ ደም አፋሳሽ ትግል የተካሄደበት፤ የማህበረሰቡን ንቃተ-ህሊና ከፍ ለማድረግ ቀን ከሌት የተለፋበት ወዘተ ወቅት እንደ ነበር የተሳተፉትም ሆኑ የታሪክ ጸሐፍት በአንድ ድምፅ የሚመሰክሩት ነው። ጸሐፊው “የመሬት ለአራሹ አዋጅ ፍትሐዊና ሕዝባዊ ስለሆነ ማንኛውም ተራማጅ ወገን ሊደግፈው የሚገባ ነው የሚል ቁርጠኛ አቋም ነበረን” እንዳሉት በተለይ የ“መሬት ላራሹ” ጉዳይ ከዛሬውም ጊዜ በላይ ትኩረትን ያገኘበት ወቅትና እንቅስቃሴ ነበር። “በኋላ ላይ ትግሉ ‘ተጠለፈ’ እንጂ ባይጠለፍ ኖሮ ኢትዮጵያ ከዛ በኋላ ለመጡት መከራዎች ሁሉ አትጋለጥም ነበር” የሚሉ ወገኖች ሲናገሩ (ሲናደዱ) እንደሚሰማው የተማሪዎቹስ እንቅስቃሴ ወደር-አቻም የነበረው አልነበረም።

እንቅስቃሴው “በተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት ጥያቄው የብሔሮች መብቶች ይታወቁ እንጂ ከኢትዮጵያ የመለያየትን ሃሳብ ለማጉላትና ኢትዮጵያን ለመበተን አልነበረም” እንደተባለለት ሁሉ በከፍተኛም ሆነ በየትኛውም የትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የሥነ ጽሑፍ ውድድሮች ሀገራዊ አንድነትን ከማፅናት፤ ህብረ ብሔራዊነትን ከማስረፅ፤ የግፍ አገዛዝን ከማጋለጥ ወዘተ አኳያ የሚኖራቸው ፋይዳ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለምና በአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም እንዲያንሰራራ መደረጉ ይበል የሚያሰኝ ነው። እስከዚህ ድረስ ወደኋላ፤ የሥነ ጽሑፋችን ወርቃማ ዘመን መነሻ ድረስ ሄደን ታሪክን ልንጠቅስና ወደ አሁኑ እንደረደር ዘንድ ያነሳሳን አቢይ ጉዳይ የሰሞኑ ዜና ሲሆን እሱም “ሠመራ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የሥነ-ጽሑፍ ውድድር ማካሔድ ሊጀመር ነው፡፡” የሚለው የዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ድረ-ገጽ ዜና ነው።

“ዩኒቨርሲቲው ‘ፈኒ ዶጊሳ’ የተሰኘ ዓመታዊ የሥነ ጽሑፍ ውድድር በአማርኛ እና በአፋር ቋንቋዎች ማካሔድ ሊጀምር መሆኑን አሳውቋል፡፡“የሚለው ይኸው ዜና ፕሮግራሙ በሁለት ዘርፎች፣ ማለትም በግጥም እና መነባንብ የሚከናወነውኑ ውድድሮች እንደሚካሄድ፤ ፕሮግራሞቹም በተቋሙ የባሕል እና ሀገር በቀል ጥናቶች ማዕከል እንደሚያዘጋጁ ዶ/ር ሬዶ በተባሉ የማእከሉ ኃላፊ አማካኝነት ተገልጿል፡፡ በውድድሩም የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ፤ እንዲሁም የአፋር ክልል ነዋሪዎች መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጿል። ፍላጎቱ ላላቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና የአካባቢው ህብረተሰብ የምዝገባ ጊዜው ከግንቦት 23-25/2016 ዓ.ም እንደነበር ሰፍሯል።

ተቋሙ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሠራተኞች በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በአካል በመቅረብ መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን፤ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ያሉ ተወዳዳሪዎችም በስልክ ዘርፍና ቦታ፣ የሚወዳደሩበትን ዘርፍና ይዘት በማካተት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፤ ወይም በቴሌግራም በመላክ መመዝገብ የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል።

ባጠቃይ፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለኪነጥበብ ክፍት መሆን እንዳለባቸው (የየዩኒቨርሲቲዎችን የባህል ማዕከላትንም ከዚሁ አኳያ ማየት ይገባል) ከላይ ከተመለከትነው፤ ከራሳችንም ባለፈ የዓለም ተሞክሮ ያስረዳል። በትምህርትና ስልጣኔ ከገፉት ሀገራትም ሆነ ሌሎች የምንማረው ይህንኑ ነው። ሠመራ ዩኒቨርሲቲም ወደዚሁ ተግባር መምጣቱ ሊያስመሰግነው የሚገባ ሲሆን ከተማሪዎች ሁለንተናዊ ሰብእና ግንባታ፤ ሃሳብን የመግለፅ መብት፣ የተግባቦት ክሂሎታቸውን ከማዳበር፣ ከባሕል ልውውጥ ወዘተ አኳያ ሌሎችም የሠመራን ፈለግ ሊከተሉ ይገባል እያልን፤ ሊቁ እጓለ ዮሐንስ∶-

እሊህ [እኚህ ለማለት ነው] ውድድሮች [የኦሎምፒኮች ውድድሮች መሆናቸውን ገልጸዋል] የሰው አካል የቱን ያህል ለመንፈስ ብርታት፤ ለበላይነት ስሜት፤ ለፈቃድ ጉልበት የሚታዘዝ መሆኑን ለማስረዳት ዋኖቹ ዘዴዎች ነበሩ። በዚህ መልካቸው እስከ ዘመናችን ድረስ ዘልቀዋል። ወደ ሁለተኛው ዓይነት እንሂድ። ይህም በሥነ ጽሑፍ የሚገለፀው የመንፈስ ውድድር ነው። የሰው መንፈስ የቱን ያህል ፈጣሪና ወላድ (Creative, Productive) መሆኑን ለማወቅ የሚቻለው በውድድር ነው።

“ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደሳት” አለ ደራሲ። የሰውን መንፈስ እንደ እሳት የሚያጋግለው የሚያሟሙቀው ውድድር ነው። ውድድር ከሌለ ቆሞ መቅረት ይመጣል። መንፈስ ወደ ብቸኝነት፤ ወደ ብሕትውና ከተመለሰ በራሱ ክበብ ውስጥ ተወስኖ ይቀራል። መካን ይሆናል። ምንም ሊያስገኝ አይችልም። እርስ በርሱ የሚፋጭ ብረት እንኳን ስለት ያስገኛል። በዚህ ሃሳብ በመመራት የቀድሞ ዘመን ግሪኮች ውድድርን በመንፈስም ረገድ በመቀጠላቸው በመላው ዓለም ሥልጣኔ ውስጥ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው የሥነ ጽሑፍ ድርሰቶች ወይም በተለይ ስማቸው ትራጀዲዎችና ኮመዲዎችን አስገኝተዋል። (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 123) ሲሉ ባሰፈሩት ሃሳብ እናጠቃልላለን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You