በግብርናው ዘርፍ የታየው መነቃቃት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው ትግል ስኬት ዋነኛ አቅም ነው!

እንደ ሀገር ከፍተኛ የሚታረስ መሬት ፣ ተስማሚ አየርና ሰፊ የሰው ኃይል ቢኖረንም ለግብርናው ዘርፉ ተገቢው ትኩረት መስጠት ባለመቻላችን ፣ በምግብ እህል እጥረት ምክንያት በየወቅቱ የተለያዩ ፈተናዎችን አስተናግደናል ። ብሔራዊ ክብራችንን በሚነኩ የረሀብ አደጋዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደድንባቸውን ታሪካዊ ክስተቶችንም አልፈናል።

በአንድ በኩል በየወቅቱ የነበሩ ሀገራዊ የመሬት ፖሊሲዎች ፣ በሌላ በኩል ለግብርናው ዘርፍ የተሠጠው አነስተኛ ትኩረት፣ ከቋንቋ ባለፈ ዘመኑን በሚዋጅ ስትራቴጂ አለመቃኘቱ ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ትልቅ አቅም ተጨባጭ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል ።

ከዚህ የተነሳም 80 ከመቶ የሚበልጠው የሀገሪቱ አምራች ኃይል /አርሶ አደር በተሳተፈበት የግብርናው ዘርፍ ፣ በቂ ምርት ማምረት ሳይቻል በመቅረቱ ፣ በዘርፉ የተሰማራው ኃይል ሳይቀር ለከፋ የምግብ እህል እጥረት ተጋላጭ የሚሆንበት ሁኔታ የተለመደ ሆኗል።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በየአስር ዓመቱ ከሚከሰተው የድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለከፋ የረሀብ አደጋ የሚጋለጡበት ሁኔታ ፈጥሯል። ይህም የግብርናው ዘርፍ ካለበት ኋላቀርነት ጋር ተዳምሮ እንደ ሀገር የዕለት የምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ጠባቂነትን ፈጥሯል ።

ይህንን ዘመናት ያስቆጠረ ሀገራዊ ችግር ለመፍታት የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ ሰፊ ጥረቶችን እያደረገ ነው ። ሀገራዊ የመሬት ፖሊሲውን ከማሻሻል ጀምሮ አዳዲስ የእርሻ መሬቶችን ወደ ሥራ ማስገባት፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂክ የቴክኖሎጂ አቅሞችን በማስፋት ላይ ይገኛል።

ለዚህም በስንዴ ልማት እንደሀገር ያስመዘገብነው የደመቀ ስኬት ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ነው። በሌማት ትሩፋትም ሆነ በከተማ ግብርና እየተመዘገበ ያለው ውጤት በዘርፉ ያሉንን አቅሞች አቀናጅተን ወደ ሥራ መግባት ከቻልን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በምግብ እህል ራሳችንን የመቻል ህልማችን ተጨባጭ እንደሚሆን ያመላከተ ነው።

በተለይም መንግሥት የግብርናው ዘርፍ ዘመኑን በሚዋጅ ቴክኖሎጂ እንዲበለጽግ እያደረገ ያለው ሰፊ ጥረት ፤ዘርፉ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ፤ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ፤ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ድርሻ እንዲኖረው የተሻለ ዕድል ሊፈጥርለት የሚችል ነው ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችንም ህይወት ትርጉም ባለው መንገድ መለወጥ የሚያስችል ነው።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት መንግሥት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ ፤ ሁለት ሚሊዮን 532 ሺህ 454 የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች እና 852 ሺህ 683 ለቅድመ ምርት የሚያገለግሉ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ወደ ሀገር እንዲገቡ አድርጓል።

ሁለት ሚሊዮን 210 ሺህ 327 ዘመናዊ የእህል ማከማቻዎች ፣ ሦስት ሺህ 675 ትራክተሮች ፣ 652 ሺህ 92 የመርጫ መሳሪያዎች ፣ 196 ሺህ 916 የውሃ ፓምፖች ፣ 217 ሺህ 58 መውቂያዎች ወደ ሀገር ገብተዋል ። የተለያዩ ኮምባይነሮች ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያዎች ፣ ማበጠሪያ እና መፈልፈያዎች በብዛት ተገዝተዋል።

ማሽነሪዎችን ከማስገባት ጎን ለጎን የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ዘጠኝ ማዕከላትን በማቋቋም የማጠናከር ሥራ ተከናውኗል፤ በተጨማሪም በተቋቋሙት የአገልግሎት ማዕከላት ለሚያገለግሉ 78 ባለሙያዎች የአራት ዙር ስልጠና ተሰጥቷል። ይህም መንግስት ዘርፉን ለማዘመን ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ ያመላከተ ነው።

ይህ የመንግሥት ቁርጠኝነት ከግብርናው ዘርፍ ባለፈ ፤ እንደ ሀገር ወደ ኢንደስትሪ ለምናደርገው ሽግግር ትልቅ ጉልበት ፤ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻልም ሆነ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እንደ ትውልድ ለጀመርነው እልህ አስጨራሽ ትግል ስኬት ዋነኛ አቅም እንደሚሆን ይታመናል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You