ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ሶስት ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ በ1948 የእንግሊዟ ለንደን ከተማ ታላቁን ኦሊምፒክ አዘጋጀች። በጦርነቱ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ስፖርት ለማነቃቃት ኦሊምፒኩ ምቹ አጋጣሚ ቢሆንም አዲስና ምርጥ ስፖርተኛን ከተቀረው ዓለም የሚያስተዋውቅ መድረክ መሆኑ በይበልጥ አጓጊ አድርጎት ነበር። የስፖርት ቤተሰቡ በእርግጥም የናፈቀውን የአትሌቶች የብቃት ልክ ለመመልከት ቻለ፤ ይሁንና አቀባበሉ ሁለት መልክ ነበረው። የኦሊምፒኩ ወደር የለሽ ተወዳዳሪ 4 የወርቅ ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ተመልካቹን ‹‹አጃኢብ›› ቢያሰኝም፤ የዚህ ብቃት ባለቤት ሴት አትሌት መሆኗ ግን ለብዙዎች ሊዋጥላቸው ያልቻለ ጉዳይ ነበር።
የሴት ስፖርተኞች ተሳትፎ በሚወዳደሩባቸው ስፖርቶች እንዲሁም በቁጥራቸው እግድ ተጥሎበት እያዘገመ በነበረበት በዚያ ዘመን ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ይህቺ ሴት የሁለት ልጆች እናት ነበረች። ነገር ግን አስገራሚው ብቃቷ ‹‹በራሪዋ እመቤት›› የሚል ሙገሳ አሰጥቷታል። ችሎታዋን በግልጽ እየተመለከቱ ነገር ግን መቀበል ያልፈለጉ የጾታ እኩልነት ደፍጣጮች አትሌቷን ቢቃወሙም፤ እሷ ግን የሴቶችን አቅምና የጥንካሬ ልክ ሚዛን ላይ ያወጣች የስፖርቱ ዓለም ጀግና ናት። ኦሊምፒክ በእኩል የስፖርት ዓይነት እኩል ተሳትፎን ለማስተናገድ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ቢፈጅበትም ይቺን አይነት ብርቱ ግን ታሪክ ሲያወሳት ይኖራል።
የኦሊምፒክ ጀግናዋ አትሌት ፍራንሲኔ ኮይን ትባላለች። የሆላንድ ተወላጅ ናት። አትሌቷ እ.ኤ.አ በ1935 የስፖርቱን ዓለም ብትቀላቀልም የነበራት ተሰጥኦና ችሎታ በቀጣዩ ዓመት በርሊን ላይ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ሊያሳትፋት የሚችል ነበር። ነገር ግን ከኦሊምፒኩ መካሄድ አስቀድሞ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመነሳቱ ህልሟ ሊሳካ አልቻለም። በዚህ መካከልም የስፖርት ዘጋቢና የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ከሆነ ሰው ጋር ትዳር በመመስረት የሁለት ልጆች እናት ለመሆን በቃች። ይህንን ተከትሎም የአትሌቲክስ ህይወቷ አብቅቶ እንደብዙዎቹ ሴቶች በቤት እመቤትነት ተወስና ትቀራለች የሚለው የብዙዎች እምነት ነበር። ወቅቱ ሴቶች ከወንዶች እኩል መሆናቸው የማይታመን እንደመሆኑ ባለቤቷም ጭምር የዚሁ እምነት አራማጅ ነበር። ከኮይን ጋር ከተዋወቁ በኋላ ግን ይህ አመለካከት ተቀርፎ ይካሄዱ በነበሩ የሃገር ውስጥ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች እንድትሳተፍ ከማድረግ ባለፈ ከወሊድ ጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ልምምድ ስትመለስ በማገዝ አብሮነቱን ማስመስከር ችሏል።
ለንደን ኦሊምፒክ ላይ ሀገሯን ወክላ ለመሳተፍ ዝግጅት በማድረግ ላይ ሳለችም በርካቶች ‹‹ቤት ሆነሽ ልጆችሽን አሳድጊ›› በማለት ተስፋ ሊያስቆርጧት ሞክረዋል። ከዚያም ባለፈ የ30 ዓመቷ አትሌት ‹‹ውጤታማ ለመሆን እጅግ ያረጀች›› በማለት የመገናኛ ብዙሃን ጭምር ዘመቻ ከፍተውባት ነበር። ብርቱዋ አትሌት ግን ይህንን ለመሰለው ትችት በቀላሉ እጅ የማትሰጥ በመሆኗ ከቡድኑ ጋር የኦሊምፒክ መንደርን ተቀላቀለች። ወደ መም ስትወጣም ከቀንደኛ ተቺዎቿ መካከል አንዱ የሆነውንና ከተመልካቹ መካከል የተቀመጠውን ሰው ‹‹ምን እንደማደርግ አሳይሃለሁ›› በማለት በራስ መተማመኗን አንጸባርቃም ነበር።
በእርግጥም ቃሏን በተግባር አውላ በችሎታዋ ተቺዎቿን ዝም ማሰኘት ችላለች። ኮይን የመጀመሪያ ውድድሯ 100 ሜትር ሲሆን በአሳማኝ ብቃት ግማሽ ፍጻሜ በመድረስ በዝናባማ የአየር ሁኔታ በተደረገው የፍጻሜ ውድድርም አሸናፊ ለመሆን ቻለች። ይህም አትሌቷን የመጀመሪያዋ የኦሊምፒክ ሜዳሊያን ያጠለቀች ኔዘርላንዳዊት አድርጓታል። በዚህ ብቻ ሳታበቃም በ200 ሜትር፣ 80 ሜትር መሰናክል፤ እንዲሁም 4 በ400 ሜትር ሪሌ በድምሩ 4 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማስቆጠር ቻለች። አምስተርዳም ስትገባም ከህዝብ እስከ ቤተመንግስት ብሄራዊ የጀግና አቀባበል ሲደረግላት በርካታ ስጦታዎችም ተዥጎደጎዱላት።
ሞራል የሚነኩ ዘገባዎችን ሲያስተላልፉ የቆዩ የመገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው በትችቱ ምትክ ‹‹በራሪዋ እመቤት፣ በራሪዋ ኔዘርላንዳዊት፣ …›› በሚል ማንቆለጳጰስ ጀመሩ። ታሪካዊቷ ኮይን ከዚያ በኋላ በተደረጉ የኦሊምፒክ መድረኮች ላይ ባትታይም በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ግን በተለመደ ውጤታማነቷ ዘልቃ የአትሌትነት ህይወቷን አብቅታለች። ነገር ግን የኔዘርላንድ አትሌቲክስ ቡድንን በመምራት፤ እንዲሁም አሁንም ድረስ በስሟ የሚጠራ ዓመታዊ ውድድርን በመመስረት የምትወደውን ስፖርት ስታገለግል ቆይታለች።
በርካታ ሽልማቶችና ክብሮች የተበረከቱላት አትሌቷ በዓለም አትሌቲክስ ‹‹የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ሴት አትሌት›› በሚልም ሰይሟታል። ኮይን እ.ኤ.አ በ2004 ከዚህ ዓለም ብታርፍም ኔዘርላንዳዊያን የተለያዩ ስፍራዎች ላይ ሃውልት በማቆም፤ እንዲሁም ልምምድ ትሰራባቸው የነበሩ ስፍራዎችንና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛዎችን በስሟ በመሰየም ጀግኒታቸውን ያከብራሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም