የሰላም እጦት ሊያስከፍል ስለሚችለው ያልተገባ ዋጋ ከኛ ከኢትዮጵያውያን በላይ ሊመሰክር የሚችል አለ ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ በዘመናት ውስጥ ዋጋ ያልከፈለ ትውልድ የለም ብሎ ለመናገር በሚያስደፍር የታሪክ ትርክት ውስጥ ያለን ሕዝቦች ነን። ይህ እንደ ጥላ የሚከተለን ችግር ዛሬም ያለውን ትውልድ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።
ለዘመናት ላለንበት ድህነት እና ኋላቀርነት ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ይህ ሀገራዊ የሰላም እጦት ፤ በቀደመው ዘመን ከነበርንበት ከፍያለ የስልጣኔ ማማ አውርዶናል፤ በየዘመኑ ወደዚያ ማማ ለመመለስ የምናደርገውን ሀገራዊ ጥረት እና መነሳሳት ትርጉም ያለው ውጤት እንዳይኖረው በማድረግ በተስፋ ቁዘማ ውስጥ እንድንኖር አስገድዶናል።
የሰላም እጦት ችግራችንን በአግባቡ ለመረዳት ፈቃድ ማጣታችን፣ በችግሮች ዙሪያ በግልጽ የመነጋጋር ባህል ማዳበር አለመቻላችን ፣ ከሁሉም በላይ የተለያዩ ፍላጎቶችን አጣጥሞ ማስኬድ የሚያስችል ማህበረሰባዊ የፖለቲካ ባህል አለማዳበራችን በብዙ ስለ ሰላም እየዘመርን ፣ በብዙ የሰላም እጦት ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደድን ሕዝቦች ሆነናል።
ተመሳሳይ ነገር እየተነጋገርን ለመደማመጥ ፈቃደኝነት ከማጣታችን የተነሳ የአንድ ዘመን የረጅም ዘመናት ቅዥት በሚመስል የታሪክ ትርክት እንዲቋጭ ሆኗል።“ቀይ” እና “ነጭ” በሚል የሽብር ትርክት ለሀገር ነገዎች በብዙ ተስፋ የተነቃቃ ትውልድ ትርጉም አልባ ለሆነ መስዋዕትነት ተዳርጓል።
እያንዳንዱ የለውጥ መነቃቃት በአሮጌ /ዘመኑን በማይዋጅ የመናናቅ እና ኃይል አምላኪ የፖለቲካ ባህላችን እየተጠለፈ ፣ ሀገር እንደሀገር በለውጥ ማግስት በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትዳክር ፣ በዚህም ዜጎች የለውጥ ተስፋቸውን ብቻ ሳይሆን ሁለንተናቸውን ባልተገባ መልኩ መስዋእት እንዲያደርጉ የተገደዱበት ሁኔታ በስፋት ተስተውሏል።
በቅርቡ በብዙ መስዋዕትነት ፣ በብዙ እልልታና ሆይታ ፣ በብዙ ተስፋ የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄ ብዙ ርቀት ሳይጓዝ በተመሳሳይ ፈተና ውስጥ መወደቁ ፣ በዚህም እንደሀገር መላው ሕዝባችን ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል እንደተገደደ ፣ የአደባባይ ምስጢር ነው።
በለውጡ ማግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት የተጀመሩ መነቃቃቶች ፣ እንደ አቅመቢስነት መገለጫ ታይተው በይዋጣልን ፉከራ የተጀመሩ ግጭቶች እንደሀገር ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል። ሀገርን በዘመናት ባልታየ የግጭት አዙሪት ውስጥ በመክተት ሕዝባችንን ከለውጥ ተስፋው ጋር አጋጭተውታል።
ይህ እንደ ሀገር ከትናንት የጥፋት ታሪኮቻችን ቆም ብለን ለመማር የሚያስችል ማህበረሰባዊ ማንነት መፍጠር ካለመቻላችን የመነጨ ችግራችን ዛሬ ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ እየፈተነን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ድንገትም ዛሬ ላይ እውነታውን በአግባቡ ለመገንዘብ የሚያስችል ፈቃደኝነት ካጣን ነገዎቻችንን ተስፋ አልባ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይታመናል።
ብዙ ፍላጎቶች እና ፍላጎቶች የወለዷቸው ጽንፈኛ አመለካከቶች ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ስጋት እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶቹና ጽንፈኛ አመለካከቶች ሊያስከፍሉ የሚችለውን ያልተገባ ዋጋ ለመከላከ፣ ከሁሉም በላይ ዜጎች በችግሮቻቸው ዙሪያ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለው የሚነጋገሩበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ ነው።
ለዚህ ደግሞ አሁን ከጀመርነው ብሄራዊ ምክክር የተሻለ ዕድል ሊኖር አይችልም ፤ ይችላል ብሎ ማሰብ አንድም የችግሮቻችንን መሠረታዊ ምክንያት በአግባቡ ካለመረዳት ፣ ከዚያም በላይ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለውን መንገድ ካለማጤን የሚመነጭ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው ትልቅ ስህተት ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም