የኮንስትራክሽን ኢግዚቢሽኑን ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ትብብር

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው ይታመናል። በሀገሪቱ በመንገድ፣ በጤናና ትምህርት፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በመስኖ መሠረተ ልማት፣ በአየር ማረፊያ፣ ወዘተ… መሠረተ ልማቶች ግንባታዎች ለታዩ ለውጦችም ተጠቃሹ ይሄው ዘርፍ ነው።

የሕዝቡን እንግልት የሚቀንሱ፣ ኢኮኖሚውን የሚያሳድጉ መሠረተ ልማቶችን፣ መኖሪያ ቤቶችን፣ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ወዘተ የመገንባት አጀንዳ ሲነሳ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አብሮ ይነሳል። ሀገሪቱ በቀጣይ ልትደርስበት የምትፈልገው የመሠረተ ልማት አቅም ሲታሰብም እንዲሁ ዘርፉ ይጠቀሳል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ይህ ኢንዱስትሪ ከሀገሪቱ የካፒታል በጀት 60 በመቶውን የሚያንቀሳቅስ፣ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከ23 በመቶ በላዩን የሚይዝ፣ ከግብርናው ቀጥሎ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ይታወቃል።

በሀገር በቀል ኢኮኖሚው ማሻሻያው የአስር ዓመቱ መሪ እቅድም በዘርፉ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ታቅደው እየተሰሩ ናቸው። ከእነዚህ መካከልም በመንገድና በቤቶች ልማት የተያዙትን እቅዶች በአብነት መጥቀስ ይቻላል። የሀገሪቱን የመንገድ ሽፋን ከ166 ሺ ወደ 246 ሺ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፤ ከ400ሺ በላይ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል።

ይህ ኢንዱስትሪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ኮቪድ ወረርሽኝ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትና ያንን ተከትሎ በሀገሪቱ ላይ ከተፈጠሩ አንዳንድ ጫናዎች እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ኢንዱስትሪው ተቀዛቅዞ ቆይቷል።

ፊቱንም ቢሆን በግንባታና ባለሙያ ጥራት ጉድለት፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንትና በሥነ ምግባር ችግሮች፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ተወዳዳሪ አለመሆን፣ ከግዥና ክፍያ ወዘተ ጋር በተያያዙ ችግሮች ይፈተን በነበረው በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ እነዚህ ፈተናዎች የወለዷቸው ችግሮች ሲደማመሩ ኢንዱስትሪውን በአያሌ ተግዳሮቶች የተተበተበ አድርገውታል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደማምረው ህልውናው አደጋ ውስጥ የወደቀ እስከ መባል አድርሰውታል።

ችግሮቹን በመገንዘብ ዘርፉን ለመታደግ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉም ቆይተዋል፤ እየተደረጉም ይገኛሉ። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የኢንዱስትሪውን ችግሮች ለመፍታት ከተከናወኑ ተግባሮች መካከል የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑ፣ አዲስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ መዘጋጀቱ ይጠቀሳሉ። የዘርፉን የልህቀት ማእከል ለመገንባትም እየተሰራ ነው።

የዘርፉ ችግሮች በኢንዱስትሪው ተዋንያን ተለይተዋል፤ መንግሥትም የኢንዱስትሪውን ችግሮች በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍታት እንደሚያስፈልግ በማመን ይህንኑ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት፣ ከተማ ልማትና መሠረት ልማት ቋሚ ኮሚቴ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን መልካም እድሎች፣ ችግሮችና መፍትሔያቸውን ያመላከቱ ጥናቶችን በዘርፉ ባለሙያዎች አሰርቶ በቅርቡ ያካሄደው አንድ መድረክም ለዚህ ማሳያ ነው።

የዘርፉ ምሁራን፣ የኢንዱስትሪው ባለድርሻዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተሳተፉበት በዚህ መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፤ የዘርፉ ችግሮች ተለይተዋል፤ ችግሮቹን በጋራ መፍታት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።

በመድረኩ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ችግሮቹን የግሉ ዘርፍ ወደ መንግሥት፣ መንግሥትም ወደ ግሉ ዘርፍ ሳይገፋ በጋራ እየመከሩ መፍታት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ነባር ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ እንዲሁም አዳዲስ የግንባታ ሞዴሎችን ማምጣት ላይ መሰራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ከተነሱት ችግሮች መካከል ኢንዱስትሪው የሚከተለው ኋላቀር አሰራር አንዱ ነው። ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ መስራት ያለበት መሆኑ ተጠቁሞ፣ ቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ መስራት ካልተቻለ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል እንደማይቻልም ተመልክቷል።

ቴክኖሎጂን ለመታጠቅ ብዙ የሚያስፈልጉ ነገሮች ቢኖሩም፣ የውጭ ምንዛሬ ወሳኙ ነው። ዘመኑ ያፈራቸውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ማሽነሪዎችንና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በርግጥም የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል።

ከዚህ ውጭ ደግሞ በዘርፉ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሱ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሰሩ ከሚገኙ የውጭና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ልምድና ተሞክሮ መቅስምም ያስፈልጋል። ኢንዱስትሪውን አስመልክቶ ከሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ሀገር አቀፍ ኢግዚቢሽንና ባዛሮችም ልምድና ተሞክሮ መቅስም፣ ትስስር መፍጠር ሌሎች የዘርፉን ችግሮች መሻገሪያ መንገዶችና እድሎችን መጠቀሚያ መሳሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

የዘርፉን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ለማዋል በተለይ የዘርፉ ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽኖች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። በሀገራችን የሚካሄዱ ኢግዚቢሽኖች በርካታ ድንበር ዘለል የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች፣ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ ወዘተ የሚገኙባቸው እንደመሆናቸው የኛ ተቋራጮች ራሳቸውን እንዲመለከቱ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ በሽርክና እንዲሰሩም ፋይዳቸው የጎላ ይሆናል።

እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ኩባንያዎችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ይታመናል። ለእዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን መድረኮች፣ የልምድ ልውውጦች፣ ወዘተ ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ‹‹ኢትዮጵያን እንገንባ›› በሚል መሪ ሃሳብ ከትናንት በስቲያ በሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢግዚቢሽን /ቢግ ፋ5 ኮንትራት ኢትዮጵያ/ ለእዚህ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ በመንግሥትም በዘርፉ አካላትም ታምኖበታል።

ኢግዚቢሽኑን የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንዳስገነዘቡትም፤ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚከናወኑ ኢንቨስትመንቶች በፍጥነት በማደግ ላይ ያለውን የከተሞችን እድገት ለመምራት እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገቱን ለመደገፍ ያስፈልጋሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ መንግሥት በ10 ዓመቱ ብሔራዊ የልማት እቅድ መሠረት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚፈጸሙ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ተግባራት አቅዶ እየሰራ ነው። የመንገድ ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የባቡር፣ የመኖሪያ እና የከተማ ልማት ግንባታ፣ የኃይል አቅርቦት እና መገልገያዎች ግንባታ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ምስረታ፣ የአቅም ግንባታ እና የክህሎት ልማት፣ የቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን ልማት፣ የመንግሥት እና የግል ትብብር ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቁልፍ መሠረተ ልማቶቿን ለመገንባት በተመጣጣኝ ወጪ መኖሪያ ቤቶችን ለዜጎች ለማቅረብ እንዲሁም የተሻሉ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ዘላቂ ተባባሪ ወዳጆችን እንደምትፈልግም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽን የመጪው ዘመን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መልክን እያስያዙ ያሉ የዘርፉ መሪዎች፣ አምራቾች፣ የሃሳብ አመንጪዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኢግዚቢሽኑ አዳዲስ ትብብሮችን የሚፈጥርና የሁለትዮሽ ጠቀሜታን የሚያጎለበት እንዲሁም በዘርፉ ዘላቂ ወዳጆችን መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

የቢግ አምስት ኮንስትራክት ኢግዚቢሽን ከሚካሄድባቸው ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እና ኬንያ መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህ በራሱ ትልቅ እምርታ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህም ሀገሪቱ የሚመጣውን ከመቀበል ባሻገር ብዙ የምትሰጠው እንዳላት ያመላክታል።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የምታደረጋቸው ጥረቶች የዚህ ዓይነት ትላልቅ ኢግዚቢሽኖችን በላቀ ሁኔታ ለማስተናገድ የምትችልበትን አቅም እየፈጠረላት ነው። ኢግዚቢሽኖቹ ለተጀመረው የቱሪዝም ልማትም መንገድ ከፋች ናቸው ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህ መድረክም ከባለፈው ዓመት በበለጠ ከ8300 በላይ ባለድርሻዎች መካፈላቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኢግዚቢሽኑ ንግድ ድርጅቶችን ከባለሀብቶች ጋር በማገናኘት በመሠረተ ልማት፣ በከተማ ልማት እና በሪል እስቴት ልማት ላይ ለታቀዱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ምቹ መድረክ ይፈጥራል። በፍጥነት እያደገ ያለውን የኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ የገበያ ክፍተት ለመሙላት በርካታ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ግንዛቤ ኖሯቸው በዘርፉ በስፋት እንዲሳተፉ ያስችላል።

ለሀገር ውስጥ አቅራቢዎች አማካሪዎች እና ሥራ ተቋራጮች ልምድ የመቅሰሚያ እድል ከመፍጠሩ በዘለለ የንግድ ትስስር የሚፈጠርባቸው መድረኮች ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ሲሉም ጠቅሰው፣ መድረኩ ከግንባታ ማዘመን እስከ አገልግሎት ያለውን ሂደት በማሳደግ ስማርት ሲቲን ለመገንባት የሚያስችል ልምድ እና እውቀት የሚገኘበት መሆኑንም አመላክተዋል።

የዓለም አቀፉ ዲኤምጂ ኢቨንትስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ቤን ግሪንሽ በበኩላቸው ኢግዚቢሽኑ በኢትዮጵያ መካሄዱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ዕድገት እንደሚያፋጥነው ገልጸዋል። ከፍተኛ የንግድ ትስስርን፣ ኢንቨስትመንትን፣ ቱሪዝምን እና የገበያ ዕድልን ይዞ እንደመጣ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢግዚቢሽኑ በውጭ ሀገራት አምራቾችም ሆነ በሀገር ውስጥ የግብዓት አምራችና አቅራቢዎች መካከል መልካም የግንኙነት መደላድል በመፍጠር የኢትዮጵያን ዘላቂ የልማትና ኢንቨስትመንት ዕድገት ያፋጥናል። በአጠቃላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ከግንባታ አገልግሎት እስከ ስማርት ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች ይሳተፉበታል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፤ ሀገራችን ቀጣይነት ያለው እድገት እና ብልጽግናን እውን ማድረግ እንድትችል የሀገራዊ የኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪ ልማት ስኬት ድርሻ የጎላ ነው።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በርካታ ባለድርሻዎችን የሚያሳትፍና ሰፊ ሀብት የሚጠይቅ የኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢንዱስትሪውም በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እና እድሎችንም በአግባቡ ለመጠቀም የሁሉንም ተዋንያን ቅንጅት እና የጋራ ርብርብን ይጠይቃል ብለዋል።

ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ካደጉ ሀገራት ጋር ጭምር በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ሚኒስትሯ፣ ኢግዚቢሽኑ በሌሎች ሀገራት ያለውን የቴክኖሎጂ አቅምና ልምድ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የተሻለ ሥራ ለማከናወን እንደሚረዳ ገልጸዋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት፣ የዘርፉን ዋነኛ ተዋንያኖች እርስ በእርስ ለማስተዋወቅና አብሮ የመሥራት ባሕልን ለማዳበር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት፤ ከኢግዚቢሽኑ ጎን ለጎን የኮንስትራክሽን ዘርፉን በዕውቀት በምርምርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ የሚያስችሉ አውደ ጥናቶች ይካሄዳሉ። የኮንስትራክሽን ግብዓት አማራጮችን ለማግኘት፣ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ ኩባንያዎችን ከኢትዮጵያዊያን ኩባንያዎች ጋር በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀት ሽግግር፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ለማስተሳሰርም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።

ኢግዚቢሽኑ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን እድገት ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ የብልጽግና ጉዞአችንን ስኬት ለማስመዝገብ የሚያስችለን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉትን የፋይናንስ፣ የግብዓትና፣ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ እና የክህሎት ተግዳሮቶችን በመለየት የውጭ ባለሀብቶችንና የሀገር ውስጥ የግብዓት አምራቾችን በከፍተኛ ደረጃ በማስተሳሰር ሀገራችንን ወደላቀ ደረጃ ማሽጋገር እንደሚያስችል አመላክተዋል።

የኮንስትራክሸን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ተከታታይነት ያለው ሙያዊ ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች እውቀታቸውን እንዲያሰፉ ኢግዚቢሽኑ ትልቅ የልምድ ማዕከል እንደሚሆን ይታመናል ብለዋል።

ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ ባለፈው ዓመት በተዘጋጀው ተመሳሳይ መድረክ ከ28 ሀገራት በላይ ተሳትፈዋል፤ ከ153 በላይ የኤግዚቢሽን አቅራቢ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን እንዲሁም አገልግሎታቸውን ማቅረብ ችለዋል። ከ20 በላይ ይዘታቸው የተረጋገጠላቸው የፓናል ጽሑፎች በከፍተኛ ባለሙያዎች፣ በዘርፉ ተመራማሪዎች ቀርበዋል። ከ10 ሺዎች በላይም ኤግዚቢሽኑን የመጎብኘት እድል አግኝተዋል። ከ10 ሚሊየን በላይ ዜጎችም መረጃዎች ተደራሽ የተደረጉበት ነው።

በዚህ ዘንድሮ እየተካሄደ በሚገኘው ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ኢግዚቢሽንም ከ150 የዓለም ሀገራት የመጡ የኤግዚቢሽን አቅራቢዎች ይሳተፉበታል፤ ከእነዚሀም መካከል ከ40 በላይ የሚሆኑት የሀገር በቀል ኩባንያዎች ናቸው።

በኢግዚቢሽኑ ላይ ለበርካታ ዓመታት በምርምር ዘርፍ በተለይ በምህንድስና፣ በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በመሠረተ- ልማትና ሕንፃ ግንባታ ላይ ያተኮሩ፣ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ የፓናል ውይይቶች፣ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ባላቸው ምሁራን እንደሚቀርቡ፣ በተለያዩ ሀገራት የሚመረቱ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እንደሚጎበኙ መርሃ-ግብሩን አስመልክቶ በወጡ መረጃዎች ተመላክቷል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You