ኢትዮጵያን ያለ ቀይባህር ፤ ቀይባህርንም ያለኢትዮጵያ ማሰብ ከባድ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ያሳለፈቻቸው መነሳቶችም ሆነ መውደቅ በቀጥታ ከቀይ ባህር ጋር ይያያዛል። ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የበላይነት ይዛ በቆየችባቸው ዘመናት ገናና እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና ቆይታለች። በአንጻሩ ከቀይባህር አካባቢ ከተገለለች በኋላ አቅሟ የደበዘዘ፣ ኢኮኖሚዋ የተዳከመ እና ሰላም የራቃት ሀገር ለመሆን በቅታለች።
ኢትዮጵያን ከቀይባህር የማራቁ ስልት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ነው። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የአረብ እና የቀጣናው ሀገሮች ኢትዮጵያን ከነጭራሹ ከአካባቢው ገሸሽ የሚያደርጉ ስምምነቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የቀይ ባህር ጥምረት (Red sea Alliaince) ወይም ደግሞ የጂቡቲ የሥነ ምግባር ደንብ (Code of conduct) እና የቀይ ባህር ደህንነት ተለዋዋጭነት መድረክ (Red sea security dynamics forum)ን የመሳሰሉ ኢትዮጵያን ያገለሉ ስምምነቶች ተመስርተዋል።
በተለይም ኢትዮጵያንና እስራኤልን ያገለለ የቀይ ባህር ደህንነት ተለዋዋጭነት መድረክ (Red sea security dynamics forum) ተመስርቷል። ይህ መድረክ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላትን ትስስር የካደና ከነጭራሹም የዘነጋ ነው። ይህ እና ሌሎች ከላይ የተፈረሙት ስምምነቶች ኢትዮጵያውያን በቀይ ባህር ላይ ያላቸውን መብቶች በአንድነት ለማስከበር እስካልተነሱ ድረስ ሀገሪቱን ከቀይ ባህር የማራቁ ጉዳይ የበለጠ እየተጠናከረ እንደሚሄድ አመላካች ነው ።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑ 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው። ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት በዓለም ላይ ከሚታወቁት ሀገራት አንዷ ስትሆን አፈጣጠሯም ከውሃ ጋር የተያያዘ ነው። የዓባይ ወንዝ መነሻና በቀይባህር ዳርቻ መገኘቷ የዚሁ አመክንዮ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የባህር በር ከሌላቸው 44 ሀገራት አንዷ ነች። በአፍሪካም ካሉት 16 የባህር በር ከሌላቸው ሀገራትም ተርታ ትሰለፋለች። ሆኖም ኢትዮጵያ ከእነዚሁ ሀገራት የሚለዩዋት በርካታ ነገሮች አሉ። አንደኛው የሕዝብ ቁጥሯ ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል። በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል።
ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባህር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር ደግሞ የለም። ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በባህር በር የተከበበች ሀገር መሆኗ ነው። በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባህር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር በአፈጣጠሯ ለቀይ ባህር የቀረበ ነው። በሦስተኛ ደረጃ በታሪክም በቀይ ባህር ላይ ለዘመናት የበላይ ሆና መቆየቷን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ያሏት ሀገር ናት።
ስለዚህም ኢትዮጵያ በግፍ ከይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጪ ባለቤትነቷን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባህር እንድትወገድ የተደረገበት አካሄድ ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው ብዙ ምሁራን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅ የተደረገው 1900፤ 1902 እና 1908 ከቅኝ ገዥዎች በተደረጉ ውሎች አማካኝነት ነው። እነዚህ ውሎች ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት መመስረቻ ቻርተር ሕጋዊነታቸውን አጥተዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያ የባህር በርም ሆነ ወደብ እንዳታገኝ የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም።
ይህን የተረዳው መንግሥትም ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ቀይባህር እንድታዞር አድርጓል። የባህር በር ጥያቄን ዋነኛ ብሔራዊ አጀንዳ እንዲሆን በመሥራትም ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ወደብ እና ባህር አልባ በመሆኗ እያስከተሉባት ያሉ ጉዳቶች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቁጭት እንዲነሳ አድርጎታል።
በተለይም ወደብ አልባ ሆና በዘለቀችባቸው ያለፉት 33 ዓመታት በኢኮኖሚም ሆነ በድሀነት ዘርፍ በርካታ ጉዳቶችን አስተናግዳለች። በየዓመቱ ለወደብ ከምታወጣው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በተጨማሪ የሉአላዊነት አደጋ ባጋጠማት ወቅት እንኳን ራሷን ለመከላከል የሚያስችሏትን ስትራቴጂክ የሆኑ መሳሪያዎችን በምስጢር ለማስገባት ስትፈልግ የግድ የወደብ አከራዩን ሀገር መልካም ፍቃድ ማግኘት ይጠበቅባታል።
ስለዚህም ኢትዮጵያ ለዘመናት ሉአላዊና ነጻ ሀገር መሆኗ የታወጀ ቢሆንም በባህር በርና በወደብ አልባነቷ ምክንያት ለዘመናት ይዛ የቆየችው ነጻነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ስለዚህም የባህር በር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጥያቄም ጭምር መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተረድቷል።
ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነትም የኢትዮጵያን ተስፋ ያለመለመ እና ኢትዮጵያን ወደ ታሪካዊ የቀይባህር አካባቢ እንድትመለስ ጥርጊያ መንገድ የከፈተ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሙሉ ልብ የደገፈው ነው። ስምምነቱም ኢትዮጵያ በቀጣይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባህር በር እና የወደብ አማራጮችን እንድታሰፋ በር የከፈተ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም