‹‹ታዝማ›› – በልብ ቀዶ ሕክምና ፈር ቀዳጁ ማዕከል

የልብ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነታቸው እጅግ አደገኛ ከሆኑ በሽታዎች መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ሕክምናው እጅግ የሰለጠኑ ባለሙያዎችንና ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ መሆኑ ደግሞ የበሽታውን አሳሳቢነት የበለጠ አስጊና የከፋ ያደርገዋል። በሽታው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የሚያስከትለው ችግር ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የሚያሰኝ ነው።

በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰት ሞት በእጅጉ ጨምሯል። ከእነዚህ በገዳይነታቸው እጅግ አደገኛ ከሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ ደግሞ ይሄው የልብ በሽታ ነው። ችግሩ እንዲህ የተንሰራፋና ስር የሰደደ ሆኖ ሳለ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የልብ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን የልብ ታማሚዎች ሕክምናውን በፍጥነትና በጥራት የሚያገኙበት የልብ ሕክምና ተቋም አልነበረም።

ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ሀገር ወዳዱ የልብ ሐኪም ዶክተር ፍቅሩ ማሩ፣ ከሌሎች ግለሰቦችና ተቋማት ጋር በመተባበር ከልብ ቀዶ ጥገና ውጭ ያሉ የልብ ሕክምናዎችን የሚሰጥ ‹‹አዲስ የልብ ሕክምና ሆስፒታል›› (Addis Cardiac Hospital) የተባለ ተቋም አቋቁመው ወገናቸውን ማገልገል ጀመሩ። ሆስፒታሉ በሚሰጣቸው የልብ ሕክምናዎች (የልብ ምርመራ፣ የልብ ሕመምተኛ ክትትል፣ የልብ ባትሪዎችን የመትከል፣ የጠበቡ የልብ የደም ስሮችን ማስፋት…) የበርካታ ዜጎችን ስቃይ በማስቀረት ሕይወታቸውን መታደግ ቢችልም፣ ከልብ ሕክምና ባሻገር የልብ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ተግባር ሊያከናወን የሚችል የሕክምና ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ነበር።

በዚህም መሠረት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከ‹‹አዲስ የልብ ሕክምና ሆስፒታል›› ጋር በመተባበር ያቋቋሙት ‹‹ታዝማ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል›› (TAZMA Medical and Surgical Specialized Center) በ2004 ዓ.ም የልብ ቀዶ ሕክምና እንዲጀምር አደረጉ።

የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ዓለማየሁ እንደሚገልፁት፣ የማዕከሉ መቋቋም ዋና ዓላማ የልብ ቀዶ ሕክምናን በሀገር ውስጥ በመስጠት በበሽታው የሚሞቱ ዜጎችን ሕይወት መታደግና ለሕክምናው ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረገውን ጉዞ በማስቀረት ታካሚዎችን ከእንግልት ማዳን ነው። ይሁን እንጂ ማዕከሉ ሥራውን ሲጀምር የልብ ቀዶ ሕክምና ሙያን የተማሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ስላልነበሩ፣ የልብ ቀዶ ሕክምናው ከስዊድን በሚመጡ ባለሙያዎች ይሰጥ ነበር። እነዚህ ባለሙያዎች በየዓመቱ ለሶስትና ለአራት ጊዜያት ያህል ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የልብ ቀዶ ሕክምናዎችን ሰጥተዋል።

ይህ አገልግሎት የልብ ቀዶ ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እፎይታን የፈጠረ ቢሆንም፣ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ፣ በልብ ቀዶ ሕክምና የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችን ማፍራት እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነበር። ከስዊድን በመምጣት የልብ ቀዶ ሕክምና ያከናውኑ የነበሩ ባለሙያዎች ከልብ ቀዶ ሕክምናው ባሻገር ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በዘርፉ ብቁ እንዲሆኑ የእውቀትና ልምድ ሽግግር ተግባር አከናውነዋል።

የልብ ቀዶ ሕክምናውን በውጭ ባለሙያዎች የማከናወኑ ተግባር የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ እስከተከሰተበት ወቅት ድረስ ቀጥሎ ነበር። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የልብ ቀዶ ሕክምናው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መከናወን ጀመረ።

ይህ ወቅት ከኢትዮጵያ የሕክምና ታሪክ ወሳኝ ምዕራፎች መካል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። እጅግ ውስብስብ የሆነውንና በኢትዮጵያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይደረጋል ተብሎ ያልተገመተውን የሕክምና ዓይነት በብቃት ማከናወን ለዜጎች ተስፋ፣ ለሀገርም ኩራት ነው። በወቅቱ የሕክምና ባለሙያዎቹ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ጥቂት ቢሆንም የልብ ቀዶ ሕክምናን በውጭ ሀገራት ተምረው የመጡ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ነበሩ። እነዚህ ባለሙያዎች እውቀታቸውን ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እያጋሩ ያከናወኗቸው የልብ ቀዶ ሕክምናዎች ለታካሚዎች፣ ለተቋሙና ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ተግባራት ነበሩ።

‹‹ታዝማ›› የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ሁሉንም የሕክምና ዓይነቶች በጥራት የሚሰጥ ተቋም ቢሆንም፣ በልብ ቀዶ ሕክምና ዘርፍ የሚሰጣቸው ሕክምናዎችና ያስመዘገባቸው ስኬቶች፣ ተቋሙን በሀገሪቱ በዘርፉ ፈር ቀዳጅና ብቸኛ እንደሚያደርጉት ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አስቻለው ይገልፃሉ።

‹‹ታዝማ ኢትዮጵያ ውስጥ ይከናወናሉ ተብለው የማይገመቱ ውስብስብ የልብ ቀዶ ሕክምናዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በስኬት አከናውኗል። የልብ ቀዶ ሕክምና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ብቻ እንዲከናወን ያደረገ የመጀመሪያው ተቋምም ነው። እነዚህ ሕክምናዎች ኢትዮጵያን በዘርፉ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ፈር ቀዳጅ እንድትሆን በማስቻል ሀገር አኩርተዋል፤ ሕይወት ታድገዋል። ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከጅቡቲ የመጡ ዜጎችም ወደ ማዕከሉ በመምጣት እነዚህን የሕክምና አገልግሎቶች አግኝተዋል› ሲሉ አብራርተዋል።

‹‹ታዝማ›› ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በስኬት ካከናወናቸው የልብ ቀዶ ሕክምናዎች መካከል ልብና ሳምባ ሥራቸውን አቁመው ከልብ ወደ ሰውነት የሚወስደውን ትልቁን የደም ቱቦ የመቀየር (Bentall Procedure)፣ ትልቁን የልብ የደም ቧንቧ በድጋሚ የመቀየር (Redo Bentall)፣ ልብና ሳምባን ተክቶ ከሚሰራው ማሽን ውጭ ልብ መደበኛ ሥራውን እየሰራ የሚከናወን የልብ የደም ስር ቅያሬ (Off-Pump Coronary Artery Bypass Surgery – CABG)፣ ‹‹ፐልመሞነሪ ኢንዳይርቴሬክቶሚ›› (Pulmonary Endarterectomy) እና ‹‹አርተሪዎ ቬንቲኩላር ሴፕታል ዲፌክት ሪፔይር›› (Arterioventricular Septal Defect Repair) ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሕክምናዎች በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካም ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወኑ ውስብስብ የልብ ቀዶ ሕክምናዎች ናቸው።

አካላዊ መቀራረብና መነካካት እጅግ አስፈሪና እንደ ተዓምር በሚቆጠርበት በዚያ የኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ‹‹ታዝማ›› አገልግሎቱን እንዳላቋረጠ የሚያስታውሱት አቶ አስቻለው፣ ማዕከሉ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅትም ሕይወት የመታደግ ተግባሩን በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት ሲያከናውን እንደነበር ይገልፃሉ።

‹‹ታዝማ›› የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል የልብ ቀዶ ሕክምና ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በውጭ ባለሙያዎች ከ500 በላይ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ደግሞ ከአንድ ሺ 200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል። በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ካገኙ ዜጎች መካከል 440 የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው።

ከልብ ቀዶ ሕክምና በተጨማሪ በሌሎች የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ዘርፎች በሰጣቸው ሕክምናዎች ደግሞ ከ132ሺ በላይ ለሚሆኑ ታካሚዎች አገልግሎት ሰጥቷል። ‹‹ታዝማ›› የልብ ቀዶ ሕክምናዎች በሀገር ውስጥ እንዲሰጡ በማድረጉ ዜጎች ወደ ውጭ ሀገራት ተጉዘው ለሕክምና ሊያወጡት የነበረውን ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።

‹‹ታዝማ›› በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ በማከናወን ጥራት ያለው ሕክምና በመስጠት እና በዘርፉ የሰለጠነ ሰው ኃይል እንዲኖር በመትጋት ሀገራዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በዓመት ከ400 በላይ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ያደርጋል። የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ቁጥር ለማብዛትና አቅማቸውን ለማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን ከሌሎች የሕክምናና የትምህርት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርሞም እየሰራ ይገኛል።

ማዕከሉ ከሕክምና ሥራው ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል፤ እያከናወነም ይገኛል። በዚህ ረገድ በትምህርትና በጤና መስኮች ያደረጋቸው ድጋፎች ተጠቃሽ ናቸው። ለዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል፣ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ልዩ ልዩ የሕክምና ቁሳቁስን እንዲሁም አቅም ለሌላቸው ወገኖች ለሚደረጉ የምገባ መርሃ ግብሮችና ለአገልግሎት መስጫ ተቋማት የገንዘብ ድጋፎችን አድርጓል። በተለይም ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የልብ ቀዶ ሕክምና እንዲጀምር በከፍተኛ ወጪ የተገዛውን ልብና ሳምባን ተክቶ የሚሰራውን ማሽን (Cardiopulmonary Bypass Machine) ማበርከቱ ጎልቶ ሊጠቀስ የሚችል የ‹‹ታዝማ›› በጎ ተግባር ነው። ከዚህ በተጨማሪም መማር እየፈለጉ አቅም ላጠራቸው ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስን አበርክቷል። ማዕከሉ በሀገራዊ ጥሪዎች ላይም ንቁ ተሳታፊ ነው።

አቶ አስቻለው ‹‹ማዕከሉ ከልብ ቀዶ ሕክምና በተጨማሪ ሌሎች ሕክምናዎችንም ይሰጣል። ሁሉም ዓይነት የውስጥ ደዌ ሕክምናዎች (የስኳር፣ የጨጓራ፣ የነርቭ እና ሌሎች ቀዶ ጥገናዎች) በሰብ ስፔሻሊስቶች ይሰጣሉ።›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የልብ ቀዶ ሕክምናው ግን በልዩ ሁኔታ የሚሰጥ አገልግሎት ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ጥራት ያለው ሕክምና በመስጠት፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በማፍራት እና ለውጭ ሕክምና ሊወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ስኬታማ ነው። ሕሙማን ወደ ውጭ ሀገራት ሳይሄዱ በራሳቸው ቋንቋ እየተግባቡ፣ በቤተሰባቸው መሐል ሆነው፣ በራሳቸው ወገን ሲታከሙ ለታካሚዎች፣ ለተቋሙና ለሀገር ትልቅ ትርጉም አለው።

‹‹ታዝማ›› በተሰማራባቸው የሕክምና መስኮች፣ በተለይም በልብ ቀዶ ሕክምና ዘርፍ፣ በርካታ ስኬቶችን ሲያስመዘግብ ሁሉም መንገድ አልጋ በአልጋ ሆኖለት አይደለም። ማዕከሉ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ተስፋ መሆን የቻለው ለሚያጋጥሙት ችግሮች ሳይበገር በፅናት በመጓዙ ነው።

የአላቂ እቃዎች እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም የቦታ ችግር የማዕከሉ የሥራ መሰናክሎች እንደሆኑ አቶ አስቻለው ይናገራሉ። ‹‹የልብ ቀዶ ሕክምና ለማከናወን በግብዓትነት የሚያገለግሉ እቃዎች በአስመጭዎች ዘንድ ስለማይታወቁና ዋጋቸውም ውድ ስለሆነ እቃዎቹን ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል። እነዚህን እቃዎች በበቂ ሁኔታ ማግኘት ከተቻለ ማዕከሉ አሁን ከሚሰራው የበለጠ ሥራ በመሥራት ብዙ ወገኖችን መርዳት ይቻላል›› ይላሉ።

መንግሥት ለ‹‹ታዝማ›› የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ፣ የመንግሥት ድጋፍ ለማዕከሉ ሥራዎች ጉልበት እንደሆኑለት የሚጠቁሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹መንግሥት ለማዕከሉ ሥራዎች ድጋፍ ያደርጋል። የልብ ቀዶ ሕክምናው የሚከናወነውም መንግሥት እነዚህ ግብዓቶች በልዩ ፈቃድ እንዲገቡ በመፍቀዱ ነው። የልብ በሽታ በዓለም ላይ ተላላፊ ካልሆኑና በገዳይነታቸው በዋናነት ከሚጠቀሱት በሽታዎች መካከል አንዱ ነው። መንግሥትም ይህን ሁኔታ በመገንዘብ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር ተጨማሪ ትኩረት መስጠትና ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል›› በማለት ያስገነዝባሉ።

‹‹ታዝማ›› የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ላከናወናቸው ሀገር የሚያኮሩ የሕክምና ተግባራትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከተለያዩ አካላት ምስጋና ተችሮታል፤ እውቅናዎችንም አግኝቷል። ከእነዚህም መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ ለማዕከሉ መስራች ለዶክተር ፍቅሩ ማሩ የሰጡት እውቅናና ምስጋና በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ2014 ዓ.ም ‹‹ሕክምና ትጉህነትን፣ ርኅራኄንና ሥነ-ምግባርን ብሎም ከራስ ይልቅ ሌሎችን ማስቀደምን የሚሻ ሞያ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀብቷን አፍስሳ የምታፈራቸው የሕክምና ባለሞያዎች በቅንነት ሲያገለግሏት ማየት ተስፋን ይሰጣል። እርስዎም የሕክምና ተግባርዎን ሲከውኑ ዕውቀትዎን ሳይቆጥቡ፣ ያለመታከት ላበረከቱት አስተዋፅዖ እና ስለሰጡት ትኅትና የተመላበት አገልግሎት ከልብ የሆነ ምስጋናዬ ይድረስዎ!›› በማለት ለዶክተር ፍቅሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ማዕከሉ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል፣ ከተለያዩ የጤና ዘርፍ የሙያ ማኅበራት፣ ከአአቢሲንያ የጥራት ሽልማት፣ ከክፍለ ከተሞች፣ ከትምህርት ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ምስጋናና እውቅና ተሰጥቶታል።

በልብ ቀዶ ሕክምና በአርዓያነትና በስኬታማነቱ የሚጠቀሰው ‹‹ታዝማ›› የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ተልሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነና ጥራቱን የጠበቀ ሕክምና መስጠት የሚችል ተቋም ለመሆን እየተጋ ይገኛል። ‹‹ማዕከሉ ሁሉም ሰው ለልብ ቀዶ ሕክምና ከሀገር ውጭ እንዳይወጣና እንዳይጉላላ የማድረግ እቅድ አለው። መንግሥትን በመጠየቅና በራሳችን በምናደርጋቸው ጥረቶች ሰፊ ቦታ በማግኘት አሁን ካለው የበለጠ ቁጥር ያለውን ታካሚ ተደራሽ ለመሆንም እየሰራ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቂ ባለሙያዎችን በማፍራት የልብ ንቅለ ተከላ ማድረግ የሚችልና የምርምር ሥራዎችን የሚያከናውን ተቋም እስከ መገንባት የዘለቀ የረጅም ጊዜ እቅድም አለው›› በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አስቻለው ዓለማየሁ ስለ ‹‹ታዝማ›› የወደፊት እቅዶችም ገልጸዋል።

 

አንተነህ ቸሬ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You