
አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ የሚገኙ ከ70 በመቶ በላይ ተቋማት ከትምባሆ ጭስ ነፃ መሆን ችለዋል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ትምባሆ ማጨስ ቀንና በመዲናዋ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ያለውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ አስመልክቶ ባለስልጣኑ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከትምባሆ ነፃ አካባቢን ለመፍጠር በተለያየ መልኩ በከተማዋ የንቅናቄና የቁጥጥር ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ ተቋማት ከትምባሆ ነጻ የሆነ አካባቢ ከመፍጠር አኳያ ለሕግ ተገዥነታቸው ከ40 በመቶ በታች የነበረ ሲሆን፤ አሁን ወደ 70 በመቶ ማደግ ችሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጇ እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ በመዲናዋ ከትምባሆ የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር የፊት ለፊት የውይይት መድረኮች ከተለያዩ አካላት እስከ ብሎክ አደረጃጀት በማድረግ፤ በርካታ የአደባባይ ግንዛቤ ፈጠራዎችንና የፓናል ውይይቶችን በማድረግ የንቅናቄ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ከንቅናቄው ባለፈ በቀንና በማታ ፕሮግራሞች በትምህርት ቤቶች፣ በወጣት ማዕከላት፣በምግብ ቤቶች፣ በመዝናኛ ቦታዎችና በተለያዩ ተቋማት የቁጥጥር ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
እስካሁን በተሠሩ ሥራዎች ትምህርት ቤቶች ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው የትምባሆ ጎጂነትን በተመለከተ የነበራቸው ግንዛቤ እያደገ መሆኑን ጠቁመው፤ የተለያዩ ድርጅቶችን ከትምባሆ ጭስ ነፃ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡
የትምባሆ ምርቶች በዜጎች በተለይም በሕፃናት ላይ እያደረሱ ያለው ተጽዕኖ በተመለከተ በመዲናዋ ሰፊ ጥናት አለመሠራቱን ወይዘሮ ሙሉ እመቤት አንስተው፤ የከተማዎች መስፋፋት፣ የቁጥጥር ሥራው በቀንና በማታ ወጥ አለመሆን በአፈጻጸም ሂደቱ እንደተግዳሮት የሚነሳ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
ባለስልጣኑ ዓለም አቀፍ የፀረ ትምባሆ ቀንን አስመልክቶ በከተማዋ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የንቅናቄ ሥራዎችን እየሠራ በመሆኑ የተለያዩ አካላት መሥሪያ ቤቱ ከትምባሆ ነጻ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የሚያደርገውን ተግባር በመደገፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የመድኃኒት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በትምባሆ ምክንያት በዓለም በየዓመቱ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸው ያልፋል፡፡
በትምባሆ ውስጥ ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ኬሚካሎች መኖራቸውን አመላክተው፤ ከነዚህ ኬሚካሎች 70 የሚሆኑት በቀጥታ ካንሰርን እንደሚያመጡ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ችግሩን በመረዳት በትምባሆ ምርት ላይ ቁጥጥር ማድረግ በኅብረተሰብ ጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን ስምምነት ከፈረሙ ሀገራት አንዷ ነች ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ትምባሆን በተመለከተ ጠንካራ መመሪያ ቢኖርም ከትግበራው አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ የገለጹት አቶ ስዩም፤ በኢትዮጵያ ከትምባሆ ጋር ተያይዞ ያለውን የጤና ችግር በዝርዝር ለማወቅና ችግሩን ለመቅረፍ እየተከናወነ ያለው ጥናት በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም